“እግዚኦ!” – የክህደት እና የጭካኔ ጥግ

0
807

ያለፈው ማክሰኞ፣ ኅዳር 1 ለኢትዮጵያውያን እንደ ከዚህ ቀደሞቹ ማክሰኞዎች ሆኖ አላለፈም፤ ፍጹም የተለየ ቀን ሆኖ እንጂ!
ሕወሓት በትግራይ የሚገኘውን የሰሜን ዕዝ ላይ ድንገተኛ ስልታዊ ጥቃት መፈጸምን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መከላከያ ሠራዊት እርምጃ እንዲወስድ ከማዘዝ ባሻገር በጡረታ ለተገለሉ ከፍተኛ የጦር መኮንኖችን ጥሪ አድርገዋል። ይህንንም ተከትሎ ሌተናል ጀነራል ባጫ ደበሌ ጥሪ ከተደረገላቸውና ሠራዊቱን በፍጥነት ከተቀላቀሉት መካከል አንዱ ናቸው።

ሌተናል ጀነራል ባጫ ሥራቸውን የጀመሩት በቀጥታ ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ በመብረር ማክሰኛ፣ ጥቅምት 24 በሠራዊቱ ላይ የደረሰውን አሰቃቂ ጥቃት በአካል ሄደው የታዘቡትን በተመለከተ ለመገናኛ ብዙኀን ሰቅጣጩ ድርጊት በተፈጸመ በሳምንቱ ማክሰኞ፣ ኅዳር 1 በሰጡት መግለጫ ላይ ይፋ አድርገዋል። ሕወሓት በሠራዊቱ አባላት ላይ በፈጸመው ዘግናኝ ድንገቴ ጥቃት ቁጭትና ሐዘን እንዲሁም እልህ እየተናነቃቸው አድማጭ ወተመልካች በምናብ ምስሉን እንዲያይ በሚያደርገው ስዕላዊ አገላለጻቸው መላ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ሐዘን ውስጥ ከትተዋል፤ እንባ አራጫተዋል። ብዙዎችንም ለብስጭትና ቁጭት ዳርገዋል።

ጀነራሉ በገለጻቸው የሕወሓት አመራር ሴራ ሲጎኖግኑ ረዘም ያለ ጊዜ እንደወሰደ እንዲሁም በሠራዊቱ ውስጥ የሚገኙ አባላቱንም በሴራው ተዋናይ ማድረጉን ገልጸዋል። የሰሜን ዕዝ ሠራዊት አባላት ቢያንስ በትንሹ ለ21 ዓመታት እንደሚተዋወቁ፣ አብረው በቀበሮ ጉድጓድ እንደመሸጉ፣ በጦርነት ፍልሚያ ጎን ለጎን ሆነው ጀግንነት እንደፈጸሙ፣ አንዱ ለሌላው የሕይወት መስዕዋት የከፈሉ መሆኑ እና ከምንም በላይ ደግሞ ለኢትዮጵያዊነትና ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት መከበር አብረው ዘብ የቆሙ አጋሮች ናቸው ያሉት ጀነራል ባጫ፥ ሆድ እንዴት ቢጨክን ነው እነዚህ አባላት በአጋሮቻቸው ጀርባ ደባ ጎንጉነው ክህደት ሊፈጽሙ የቻሉት የሚለው ግን እስካሁን በሁሉም ያልተፈታ እንቆቅልሽ ሆኗል።

በሴራው ጥቃት ላይ ማዕከል የሚገኙ ከፍተኛ የመከላከያ መኮንኖች ጭምር እንደተሳተፉበትና የሠራዊቱን አጠቃላይ የግንኙነት መስመር እንዲቋረጥ በማድረግ መጀመሩም ታውቋል። ጥቃት የሚፈጸምበት ጊዜ የተጠና መሆኑን የሚያሳያው ደግሞ የሠራዊቱ ቀለብ እና ደሞዝ መጥለፍን ያካተተ መሆኑ ነው።

“የሠራዊቱ አባላት ምንም ባልተዘጋጁበትና ትጥቅ ፈትተው በተቀመጡበት፥ ከአጋሮቻቸው እና ከሕወሓት ሚሊሻ ድንገተኛ ጥቃት ከሌሊቱ አራት ሰዐት ጀምሮ ተሰነዘረባቸው። አባላቱን ከመግደል ባሻገር ሬሳቸውን ልብስ በመግፈፍ ራቁታቸው በማድረግ እያጨበጨቡ ጨፍረዋል። . . . ያፈኗቸውን [ደግሞ] የደንብ ልብሳቸውን አስወልቀው ራቁታቸውን ወደ ኤርትራ እንዲሄዱ አድርገዋል።” ሲሉ ጀነራል ባጫ ቁጭት በተቀላቀለበት ሲቃ ገልጸዋል። የሚገርመው ግን ሠራዊቱ በጠላትነት የተዋጋቸው የኤርትራ ሠራዊት አባላት ልብሳቸውን አውልቀው እርቃናቸውን መሸፈናቸው፥ ወገን ከሚባሉት አካል ከደረሰባቸው ጋር በማነጻጸር የድርጊቶቹን ወለፈንዲነት ያሳያል።

የጀነራል ባጫ መግለጫ በመደበኛውም ሆነ በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኀን በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደቫይረስ በከፍተኛ ፍጥነት ተሠራጭቷል። ብዙዎችን ለቁጭት እና እልህ በመዳረግ መንግሥት ቀይ መስመር ታልፏል በማለት ሕወሓት ላይ የወሰደው ሕግን የማስከበር እርምጃ ካልዘገየ በስተቀር ተገቢና ወቅታዊ መሆኑ በመደገፍ በማንኛውም መልኩ ከመከላከያ ሠራዊት ጋር መሆናቸውን አረጋግጠዋል። ዜጎች በሞራል፣ በገንዘብ፣ በስንቅ አቅርቦት፣ በደም ልገሳ እንዲሁም ሰልፍ በማካሄድ የመከላከያ ሠራዊት አጋር መሆናቸውን በተግባር አሳይተዋል።

አንዳንዶች በሕወሓት እና በፌደራል መንግሥቱ መካከል ያለውን ልዩነት ወደ ኀይል እርምጃ ማደጉን በመንቀፍ፥ ልዩነቶን ለመፍታት “ጦርነት መፍትሄ አይሆንም፣ የፖለቲካ መፍትሄ ይፈለግ” በሚሉ እንዲሁም በእንግሊዝኛ “We want peace, no war” እና “Say no to war” በማለት በማኅበራዊ ገፆቻቸው ላይ ቅስቀሳ መሰል ዘመቻ አካሂደዋል።

ይሁንና አንዳንዶቹ እነዚህ የጦርነቱ ተቃዋሚዎች ብዙም ሳይቆዩ በሰሜን ዕዝ አባላት ላይ የደረሰውን ጭካኔ የተሞላበት ክህደት ወለድ ጥቃት መጋለጥ ተከትሎ የቀደመ አቋማቸን ይዘው ለመቀጠል ሞራል እንዳጡ አስታውቀዋል። በመከላከያ ሠራዊቱ ላይ የተፈጸመውን የከሃዲ ጥቃት ከጠነሰሰው፣ ካቀናበረውና ከመራው ሕወሓት ጋር ምንም ዓይንት ውይይትም ሆነ ድርድር ሊደረግ አይገባም ሲሉ ድምጻቸውን በቁጭትና ንዴት ከፍ አድርገው አሰምተዋል።

አንዱ ዘግናኝ ድርጊት ታልፎ ሠራዊቱ ከመከላከል ወደ ማጥቃት እርምጃ ሲሸጋገር ማይካድራ በምትባል ትንሽ ከተማ ላይ በአማራ ተወላጆች ላይ የተፈጸመው ዘግናኝ እልቂት ተሰማ። ብዙዎችን አንገት አስደፍቷል፤ አሳዝኗልም። ሕወሓት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከኢትዮጵያ ምድር መጥፋት እንዳለበት ለብዙዎች ተጨማሪ ምክንያት ሆኗል። ነገ ደግሞ ምን ዓይነት ዘግናኝ ድርጊት እንሰማ ይሆን የሚለው ስጋት ግን የብዙዎች እንደሆነ ዛሬ ላይ ተደርሷል።
ቸር ያሰማን!

ቅጽ 2 ቁጥር 106 ኅዳር 5 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here