“ጆ ባይደንና ካማላ ሀሪስ እንኳን ደስ አላችሁ!”

0
1091

አሜሪካ ያለዴሞክራሲ ዴሞክራሲም ያለ አሜሪካ አገር ያላቸው አይመስልም። ሰሞኑን በምድረ አሜሪካ በተደረገው የፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዴሞክራሲን ጥግ አሳዩን ይላል አብርሐም ጸሐዬ።ዴሞክራሲ በአገረ አሜሪካ ለላይኛው እና ለታችኛው መደብ አባላት ተብሎ የማቸረቸርባት ሁሉም በሕግ እና በሕግ ብቻ የሚዳኝባት አገር ብሎ ያሞካሸበትን ጽሑፍ ጋበዝናችሁ

“ዲሞክራትን ወክዬ የምርጫ ዘመቻ አድርጌያለሁ፤ ሳሸንፍ ደግሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ነኝ” ጆ ባይደን
“አሜሪካ የይቻላል ምድር ነት” ካማላ ሀሪስ
ዎል ስትሪት ጆርናል በዲጂታል የንግድ ዘርፍ ውስጥ ያሉ የአሜሪካ ኩባንያ አስተዳዳሪዎች ስለአዲሶቹ የዋይት ሃውስ ሰዎች ምን አሉ የሚል ዘገባ ሰርቷል። እንደአሜሪካ ባሉ አገራት በአንድ አገር የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ባለሃብቶች ሚና አላቸው። በገንዘብ ከመርዳት አንስቶ የምርጫ ቅስቀሳው ላይ እስከመሳተፍ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። እንደኛ አገር ተሸሽጎ መደገፍ፣ ተደብቆ መርዳት፣ ስም ቀይሮ መጻፍ የሚባል ነገር የለም። ነጻነት በገፍ አለ። እኛ የመጣንበት የሺህ ዘመናት የአግላይ ፖለቲካ በአግባቡ እየተተገበረ በመሆኑ ጎመን በጤናው እንደቀጠሐ ነው። ከአትላንቲክ ማዶ እከሌ ዴሞክራት ነው፤ እከሊት የሪፐብሊካን ደጋፊ ናት መባባል የሕይወታቸው አንድ አካል ነው። አረ እኔ ፖለቲካ አልወድም ወይም የማንም ደጋፊ አይደለሁም የሚባል የዘፈን ቅኝት ያለው እዚህ እኛ ቤት ነው። ፖለቲካውንም እህሉንም በሆድ ነው። ተጽእኖ ከሚያሳድረው ፖለቲካ ይልቅ የየትኛው የእግር ኳስ ክለብ ደጋፊ እንደሆንን መናገር የኛ ነጻነት ነው። በሱ በኩል አስታኮ ትቶ የማይተወውን የፖለቲካ ስሜት የሚወጣው እልፍ ነው። ስሜትን ማፈን ተፈጥሯዊ አይደለምና ራሱን የሚገልጥበት መድረክና ጊዜ እያገኘ ይፈነዳል። ምንም ማድረግ አይቻልም የሚባለውን ዘመነኛ አባባል አስታውሰን እንለፈው።

“ኑ የዓለማችንን መሪ እንምረጥ”
ዶናልድ ጆን ትራምፕ የነጩ ቤተ መንግስት የአራት ዓመታት ቆይታ ያበቃላቸው ይመስላል። ባለቢጫው ጸጉር አልታደሉ፤ ከ28 ዓመታት በኋላ አራት ዓመታት ብቻ ቆይተው የተሰናበቱ መሆናቸው ነው። የዘንድሮ ምርጫ ሁልጊዜም አሜሪካውያን እንደሚሉት “ኑ የዓለማችንን መሪ እንምረጥ” ብለው መርጠዋል። አገር አንድ የምትለይበት ልዩ ምልክት ይኖራታል። ያ ምልክት የውጭ አካል ወይም ዜጎቿ የሚሰጧት መለያዋ ነው። አሜሪካ ምን አለሽ ስትባል ‘ዴሞክራሲዬ’ ትላለች። የፈረንሳይ ዜጎችም እንዲህ የሚሉት ነገር አላቸው፤ የነርሱ ዴሞክራሲ አይደለም። “ለአሜሪካ ዴሞክራሲዋ ለኛ ደግሞ ቮልቴር አለልን!”። ይላሉ። ጸሐፊያቸውን የሀገራቸው ትልቁ ስዕል አድርገው ያስቀምጡታል። ሩሲያም መሪያቸው ቭላድሚር ፑቲንን “ንጉሥ ሆይ ሺህ ዓመት ይንገሱ! እርስዎ የታላቋ ሩሲያ ኃያል ገዢ በመሆንዎ ዓለም ሁሉ ወደኛ ያያል” ይሏቸዋል። የአንድ አገር ህዝቦች በዓለም መድረክ የተተዉ ሲመስላቸው አለሁ ለማለት ይፍጨረጨራሉ። ያላቸውን አውጥተው ያሳያሉ። ፑቲን ባይመጡ የእነቶልስቶይና የዲየስቶቭስኪን ሥራዎች እየተነተኑ እኛ እኮ የዓለም ስነጽሑፍ ዓርማዎች ነን እያሉ ይቆዩ ይሆናል ነገር ግን ከማንም የሚገዳደር መሪ አግኝተዋልና ሰውየውን ከፍ አድርገው ይዘምራሉ። አንዲት አገርን ወደዓለም መድረክ ያመጣ ህዝብ ወይም መሪ በታሪክ ዘመኑ ይወደሳል። ለዚህም ነው አሜሪካኖቹ ዴሞክራሲያችን የዓለም ምሳሌያችን ነው ብለው የሚመጻደቁት። አዎ ለራሳቸው ተጠቅመውበታል! ዴሞክራሲያቸው ባለኹለት ሰይፋቸው ነው። ለውስጥ አስተዳደራቸው ተገን ነው፤ ዓለምን ደሞ የሚቀጡበት ልምጭ አድርገው አሻጥር ይሰሩበታል።

ታላቋ አገር ያላት የዴሞክራሲ ጥራት አጠያያቂ ቢሆንም እንኳን የዴሞክራሲ ፈጣሪ ከሆኑት ግሪኮቹ በላይ እሷ የወለደችው አስመስላ ትከውነዋለች። መገናኛ ብዙሃኖቿም የጥሩ ድርሰት ጸሐፊ ናቸው። ጥፋት ሲፈጠር መሪዎቹን ወይም ተቋማትን ይኮንናሉ። መልካም የመሠላቸው ነገር ሲከሰት ደግሞ “የአሜሪካ ዴሞክራሲ እኮ እንዲህ ያለ ቅዱስ ነው” ይላሉ። “አሜሪካ ማለት ጥቁሩን ባራክ ኦባማ ያስመረጠች የሁሉም ቤት ናት፤ ዘርና ቀለም ይለያሉ አትበሉን” ይላሉ። በፕሮፓጋንዳ የነጮቹን የበላይነት ይከልሉበታል፤ አንዲት የሚፈጥሩትን ጥሩ ክስተት ደግሞ አግዝፈውና አድምቀው በመሳል ያደናግራሉ። አሁንም እየሆነ ያለው ያ ነው። ዓለም ምንጊዜም ሸፍጠኛ ነች! “ዋናው ግን ጥቅም ነው” ይላል የካፒታል መርህ። የአሁኒቷ ዓለም ቀለሟ ካፒታሊስት ነው – አለቀ! ምንም ሆነ ምን ጥቅምን እያስጠበቁ መሄድ ነው። ፍትህና እኩልነትን በኋላ ላይ ጠይቅ። ይኸው ነው!

አሜሪካኖቹ ካፒታሊስት መሪ መርጠው ዓለምን ግዛ ብለው ይሾሙታል። ቻይናን በዓይነ ቁራኛ እንዲጠብቅ፤ ሰሜን ኮሪያን እንዲገስጽ፣ አውሮፓን እንዲከታተል፣ የእንግሊዝና የእ ሥራኤልን አብሮነትን እንዲጠብቅ፤ አፍሪካን በረጅም ገመዱ እንዲያስር ወዘተ ተልዕኮዎች ይሰጡታል።

አሜሪካና ዴሞክራሲዋ
ካማላ ሃሪስ ዝርያቸው ከወደህንድ ይመዘዛል። ጆ ባይደን ምክትላቸው አድርገው በመምረጥ ወደስልጣኑ እንዲመጡ መንገድ አመቻቹላቸው። የመጀመርያዋ ጥቁር ሴት ምክትል ፕሬዝደንት ለመባል ጉዟቸውን እንዳጠናቀቁ እሙን ወደመሆን መረጋገጡ ሲቃረብ ህንዳውያን ጨርቃቸውን ጣሉ። ሀገሪቷ በርችት ደምቃ ነበር፤ አሁንም ትኩሳቱ አልበረደም። ሃሪስም “ሁሉም ይቻላል” ሲሉ የአሜሪካንን ምርጫ አሞካሽተዋል። መገናኛ ብዙኃኑም ተቀባበሉት። ሃሪስ ሴትም ጥቁርም ናቸው። እንደኦባማ ሳቂታ ናቸው። ያው ጥቁሮች ይስቃሉ! “አሜሪካ የሚኖር ማንኛውም ሰው ይህንን ሲያይ እኔም አገር እመራለሁ የሚልባት ምድር ነች” ብለዋል ሴትዬዪቱ፤ የታላቋን አገር ዴሞክራሲ መመስከራቸው ነው። እንዴት አይመስክሩ?! ከአ ሥራ ኹለት ዓመታት በፊት አባታቸው ከወደኬንያ እንደሆነ የሚታውቀው ባራክ ሁሴን ኦባማ በወቅቱ ፕሬዝደንት ሆነው ሲመረጡ ኬንያውያን በተመሣሣይ መልኩ ቦርቀው ነበር። እኛም ሳንቀር ቲሸርት ለብሰንላቸዋል።

ጥቁር ናቸውና እንደአቅሚቲ ቀለመኛ መሆናችን ነበር እንግዲህ። ከአሜሪካ ዴሞክራሲዎች አንዱ መገለጫ በእርግጥም ዜጎች የመረጡትን ሰው መሪ ማድረግ መቻላቸው ነው። ይመርጣሉ፤ ወደየቤታቸው ተመልሰው በቀጥታ ስርጭት ውጤቱን ይቆጥራሉ። አሸናፊውን ለማወቅ ቀናት ይበቃቸዋል። እንዲህ ነው! በእርግጥ ያሁኑ ምርጫ በኮቪድ ምክንያት የምርጫ አሰጣጡ ላይ የአካሄድ ለውጥ በመከሰቱ እንጂ እንደዚህም አይዘገይም ነበር። ኮቪድ አላገዳቸውም፤ ሞት አላስተዋቸውም። እንደውም እኛ አሜሪካውያን በማንኛውም ጊዜ የማንበገር ታላቅ ህዝብ ነን እያሉበት ነው። ሕጋቸው ሕግ ሆኖ በማይነቀል ሚስማር ተመቷል። ለምን ቆጠራው ዘገየ ብለው ሰልፍ እስከማድረግ ደርሰዋል።

መጠየቅ ይቻላል! መሠለፍ ይቻላል። ዴሞክራሲው ለራሳቸው በደንብ ይሠራል። በዴሞክራሲያቸው ተማምነው ‘Count Every Vote’ እያንዳንዱ ድምጽ ይቆጠር እያሉ የምርጫ አስተዳደሩን በገሃድ ጠይቀዋል። ትራምፕም ቆጠራውን እጠራጠራለሁ እያሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል። ዶናልድ ትራምፕ ፕሬዝደንት ሆነው የኢራኑን የጦር አበጋዝ እንደመግደል በአገራቸው ላይ የምርጫውን ቀን ማስቀየር ወይም ተጭበርብሯልና ይሰረዝ ብሎ ለመወሰን አይቀላቸውም። የህዳሴ ግድባችንን በሚሳኤል አደባዩት ብሎ እንደመናገር አይፈቀድላቸውም። ፕሬዝዳንቱ እንደማንኛው ዜጋና ቅሬታ አቅራቢ መክሰስ ይችሉ ይሆናል እንጂ ሌላ ገደብ ያለፈ ውሳኔ አይፈቀድላቸውም። ምክንያቱም የመጣ ሁሉ እንዳይፈነጭ እግር ከወርች የሚያስር ሕግ አለ። የአሜሪካ አባቶች ገና ድሮ የመጪው ሰው ዓመል ስለገባቸው በሰው የሚመራ ሳይሆን በሲስተም የሚተዳደር አገር መስርተዋል። የማይነቃነቅ ሕግ መንግስት ቀርጸዋል። ማንም ሆነ ማን ገደብ አለው። ለሁሉም የሥልጣን ዓይነት ልኩ ተቀምጦለታል። ውልፍት የለም – አከተመ!

አሜሪካውያን
ብልጥ ናቸው። ቤታቸውን በዴሞክራሲ እየመሩ ውጭ ባላቸው ግንኙነት ግን በጥቅማ ጥቅማቸው ልክ ይወዳጃሉ። ዴሞክራሲ ኖረ አልኖረ ምጣኔ ሃብታቸውና የፖለቲካ መስመራቸው ካልተነካ አያገባቸውም። እነርሱ እንዲህ ናቸው፤ የውስጣቸው ጥንካሬ ዓለም ላይ አንግሷቸዋል። ኢፍትሃዊ ዓለምን በዴሞክራሲያቸው ጭምብል ፈጥረዋል። አምባገነኖችን ያሞካሻሉ፤ ዋናው ነገር ከትዕዛዛቸው አይውጣ። የትም አገር ላይ ዱካቸው አለ። እንኳን አፍሪካ ስልጡኖቹ አውሮፓውያንም እንደጉድ የሚፈሯት አገር ናት። ቻይናን ግን አዞባታል መሠለኝ፤ የዓለም ታሪክ እንደሚነግረን ለውጥ ተፈጥሯዊ እስከሆነ ድረስ በቻይና ትተካ ይሆናል። ያም ሆነ ይህ አሜሪካ አሜሪካ ናት። ከዜጎቿ አልፋ የሌሎች አገራት ሰዎችም አቃፊ ምድር ናት። ለዓለም ዜጎች በተለይ እንደኛ ላሉት የትንሳኤ ምድራችን እንደሆነች ቀጥላለች። ሄሎ ማማ ይሏታል።

ፕሬዜደንት ጆ ባይደንን እና ምክትላቸው ካማላ ሀሪስ እንኳን ደስ አለዎ!
“ዲሞክራትን ወክዬ የምርጫ ዘመቻ አድርጌያለሁ፤ ሳሸንፍ ደግሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ነኝ” ጆ ባይደን ይህንን የተናገሩበት ቋንቋ ደስ ይላል። ነጩ ቤት ስገቡ የመረጣቸውን ብቻ ሳይሆን ያልመረጣቸውንም ለማገልገል ቃል የገቡበት አገላለጽ ነው። መሆንም ያለበት ይህ ነው። መሪ ሲኮን ከነበሩበት ጠባብ ዓለም መውጣት ነው።

ከዚህ በላይ ባለው ጽሑፍ ለማተት እንደሞከርነው ከተራው ሕዝብ አንስቶ እስከላይኛው መደብ ያሉት አሜሪካኖች የአገራቸውን ጉልህ እንቅስቃሴ ይከታተላሉ። ዴሞክራሲያቸውን ያሞካሻሉ። ባለሃብቶችና ታዋቂ ሰዎች ፖለቲካቸውን በአንክሮ ይቃኛሉ። ምርጫው ወደባይደን እንዳደላ ሲያውቁ በየገጻቸው መልዕክት አስተላልፈዋል። አንዳንዴ ይህቺ አገር ታስቀናለች። ማንም በነጻነት ያሰበውን የሚናገርባት ምድር ናትና! እስኪ ዎልስትሪት ከዲጂታል ነጋዴዎቹ ያሰባሰበውን መልዕክት እንስማ፦

ጄሚ ዳይመን
ጄፒሞርጋን ቼዝ የተባለ የኒው ዮርክ ትልቁ የኢንቨስትመንትና የፋይናንስ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው። እንደሁልጊዜ እንደአሜሪካዊነታችን ድምጽ የሰጡ መራጮችን በማክበር ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እንዲኖር መደገፍ አለብን። እኛ የታላቅ አገር ህዝቦች ነን ልዩነትን የምናከብር በማንኛውም የፖለቲካ ልዩነት የጋራ የሚያደርገንን ይዘን የተለየችውን አሜሪካችንን እንደዚህ እናጠንክር በማለት ጽፏል።

ጄፍ ቤዞስ
ቁጥር አንዱ የዓለማችን ባለጸጋ፣ የአማዞን መ ሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ነው። አሜሪካውያን አሁንም በአንድነት፣ በአብሮነትና በመልካም ምግባር ሆነው የዴሞክራሲያቸውን ጥንካሬ ሪከርድ ባስመዘገበ የመራጮች ቁጥር አረጋግጠዋል። እንኳን ደስ አላችሁ ሲል ስሜቱን ገልጿል።

ቢልጌትስ
በባለጸጋነት ከአንደኝነቱ ሸርተት ቢሉም ከጄፍ ቤዞስ በላይ የሚታወቁ ናቸው። የማይክሮ ሶፍቱ መ ሥራቹ ሰው ኮቪድን አስመልክቶ የዶናልድ ትራምፕን አካሄድ በመተቸች ይታወቃሉ።

እሳቸውም ምርጫውን አስመልክቶ ተናግረዋል። አስመራጮችና የዘመቻው አስተባባሪዎች ያለድካም ስለሠራችሁ እናመሠግናለን። አሜሪካ በአስቸጋሪ ጊዜ የመምረጫ አካሄዱን መላ በመፈለግ ጭምር ስለሠራችሁ እንደውም የበለጠ ቁጥር ያለው ሕዝብ ወጥቶ መሪውን እንዲመርጥ አድርጋችኋል። በችግር ጊዜም አሜሪካ ብርቱ መሆኗን ያሳየችበት ድንቅ ጊዜ ነው ብለዋል።

ብራድ ስሚዝ
የማይክሮሶፍት ዋና የሕግ ሰውና በፕሬዝደንት እርከን ላይ ያለ ነው። ረጅሙና ውጥረት የበዛበት ምርጫ ተካሂዷል። አሜሪካውያን በየጊዜ ዓይናቸው ከስክሪን ላይ ሳይላቀቅ ቆይቷል። ምንም ቢከሰት በራሳችን የምንተማመን መሆናችንን ያሳየንበት ታላቅ ጊዜ ነበር ሲል ገልጿል።

ሼሪል ሳንድበርግ
በፌስ ቡክ የሥራ ስምሪት ክፍል ዋና መሪ ነው። የካማላ ሀሪስ በአሜሪካ ምድር ሥልጣን ላይ መሆኗን አይተናል። አሜሪካ የልዩ ልዩ ሕዝቦች ምቹ መኖሪያ መሆኗል አረጋግጣለች። የትኛዎቹም ወጣቶች ቴሌቪዥን ሲያዩ ይህችን አገር እኔም ልመራ እችላለሁ እንዲሉ የሚያስችል አስተሳሰብ እንዲኖራቸው ያደረገ ታላቅ ክስተት ነው ብሏል።

ዳን ሸልማን
ዓለም አቀፍ የኢንተርኔት ወይም ኦን ላይን ገንዘብ አስተላላፊ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ነው። አሜሪካ ለካማል ሃሪስም ቦታ ያላት በታሪክ ውስጥ ከህንድ ዝርያ የተመዘዘ ጥቁር መሪ በምክትል ደረጃ ማስቀመጧ የሚደንቅ ነው። በተለይም በመካከለኛና አነስተኛ ቢዝነስ ውስጥ ከዚህ የዲጂታል ዘመን ጋር በማያያዝ ጆ ባይደንና ሃሪስ በጥምረት እንደሚሰሩ ተስፋ አለኝ ሲል መልዕክቱን አስተላልፏል።

ቻክ ሮቢንስ
የሲስኮ ሲስተምስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው። እኛ እንደሲስኮ ነገን ከናንተ ጋር አብረን ሆነን እንገነባታለን፤ ሁሉን በሚያቅፍ ማንነት እንቆማለን። በተባበረ ክንድ ከኮቪድ ነጻ የሆነ የኢኮኖሚ ግንባታ በማድረግ ጠንክረን በጋራ እንሰራለን ሲሉ ትዊት አድርገዋል።
ሲስኮ ከአዲሱ አስተዳደርና ኮንግረስ ጋር በዲጂታል መሠረተ ልማት የማዘመን ዘርፍ ላይ በመሠማራት በትምህርት ቤቶች፣ በሆስፒታሎችና በመንግሥት ኤጀንሲዎች ላይ አብረን እንሰራለን። ዲጂታሉ ባልተስፋፋበትና በሳይበር ሰኩዩሪቲ ላይ መጠነ ሰፊ ሥራዎችን በመሥራት የዲጂታል ሥራዎች ድልድይ በመሆን እንሰራለን በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ለዓለም ህዝብ ሁሉ ሰላም ይሁን!
አብርሐም ጸሐዬ (Gmail: geraramc@gmail.com)

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here