ጊዜያዊ ተልዕኮ ወይስ የተራዘመ ጦርነት?

0
778

በሕወሓት ቡድን እና በፌደራሉ መንግሥት በኩል የተፈጠረው አለመረጋጋት ሲሰፋ እና ውጥረቱም ሲበረታ ቆይቶ ወደ ጦር መማዘዝ ወይም ደግሞ በፌደራል መንግሥቱም እንደተባለው ሕግን የማስከበር ተልዕኮ ተገብቷል። ይህ ጉዳይ ታዲያ ሲጀመር በብዙዎች ዘንድ እንደታሰበው በአጭር ቀናት ሳይቋጭ ቀርቶ አንድ ሳምንትን ተሻግሯል። በሰሜን ዕዝ ላይ በተፈጸመው ጥቃት ተከትሎ የተጀመረው የወታደራዊ እርምጃ ታዲያ እንደተባለው ጊዜያዊ ሕግን የማስከበር ተልዕኮ ወይስ ደግሞ አንድ ፤ ኹለት እያለ አንድ ሳምንትን ተሸግሮ ወደ ኹለተኛ ሳምንቱ እያዘገመ መምጣቱ የተራዘመ ጦርነት ሊሆንስ ይችል ይሆን? የሚሉ ጥያቄዎችን በማንሳት ለመዳሰስ ተሞክሯል።በዚህም መሰረት የአዲስ ማለዳው ኤርሚያስ ሙሉጌታ በጉዳዩ ላይ ሙሑራንን በማነጋገር እንዲሁም የተጻፉ ጽሑፎችንም በማገላበጥ የሐተታ ዘማለዳ ጉዳይ አድርጎታል።

የጦርነት ድምጽ ተሰማ ከተባለ የሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በድምጹ የሚደነቁር እና ለሰማይ አሞራዎች መሰብሰቢያ እና የሕብረ ብሔራዊው ጦር ደም ለመጨቅየትም የሚቀድመው ያለ አካባቢ ካለ ቢያንስ በዚህ ትውልድ ውስጥ ለማግኘት የሚከብድ ይመስላል። ለምን የሰሜን አሞራ የዜጎች ስጋ እንደሚናፍቀው እና ሰሜን መልከዓ ምድርስ በወገን ደም ለመረስረስ ለምን ተፈረደበት የሚለው ጥያቄም ታሪክም ሆነ ሳይንስ እስካሁን ያልፈቱት ጉዳይም ነው።

ከአሰልችው እና የብዙኃኑን ሕይወት ከቀጠፈው የ17ቱ ዓመታት የትግል ጉዞ በኋላ እፎይ የማያ ጊዜ ሳይኖረው ነበር ለ20 ዓመታት ሰላምም የለም ጦርነትም የለም (no peace no war) በሚል በቅጡ ባለየ ሁኔታ ቀጠናው ሲወጠር ብረት ለበስ የተደራጀ እንዲያውም እንደሚባለው ከሌላው በተለየ የተጠናከረ ነው የተባለለት የኢትዮጵያ ጦርም የአንድ ወጣትን ዕድሜ በድንበር ላይ ከትሞ ነበር። ታዲያ ይህ ዓመታትን በዚሁ አካባቢ ድንበርን እና ሕዝብን፣ ወገንን ሲጠብቅ የኖረው ብቻ ሳይሆን ከመኖር እና ከመላመድም ባሻገር (መዋለድንም የጀመረ እንደሆነ ለአዲስ ማለዳ ሀሳባቸውን የሰጡ አልታጡ) ጦር ጥቃት እንደደረሰበት ተነገረ። ጥቅምት 23 ለ24/2013 አጥቢያ ሌሊት ከወትሮው በተለየ መልኩ ምናልባትም ከሰኔ 15/2011 ጥቃቱ ወዲህ ባልታየ ሁኔታ በሌሊት ነበር በብሔራዊው የቴሌቪዥን ጣቢያ ብቅ በማለት ዘግናኝ ተባለውን ጥቃት ያበሰሩት እና ይህንንም ተከትሎ መንግስት የጻፋ እርምጃ እንዲሁም ሕገ መንግሥቱን የማስከበር እንቅስቃሴ መጀመሩን የተናገሩት።
ይህ ከባድ ጉዳይ ከተፈጠረበት ሽራፊ ሰኮንዶች ጀምሮ ታዲያ በርካታ መረጃዎች ከፌደራል መንግሥቱ እና ከትግራይ ክልልም (እንደ ክልልም ባይሆን) ይወጣ ነበር።

በዚህ መሀል ታዲያ በማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ የሚሰሙት ውዥንብሮች ከልክም አልፈው ነበር። ከዋና ዋና የመረጃ እና የመገናኛ ብዙኃን ከሚሰራጩ መረጃዎች በእጅጉ በሚበልጥ ደረጃ በፍጥነት እየደረሱ ያሉት ጉዳዮች በስፋት ነበሩ። ይሁን እንጂ ይህን እና የተከፋፈሉ ማለትም በየደረጃው ያሉ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች በተለያየ ጊዜ መግለጫዎችን ሲሰጡ እና መረጃዎችን ሲያወጡ መታዘብም ተችለሏል። ይህ ጉዳይ ታዲያ በመንግሥት ደረጃ የታወቀ ይመስለኛል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገጉን ተከትሎ አንድ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ የሚሰጥ አካልም ተቋቁሞ መረጃዎችን በፍጥነት ለማድረስም እየሞከረ ታይቷል ነገር ግን አሁንም ለየብቻ የሚደረገው መረጃ አሰጣጥ አልቆመም።

ለዛሬ አዲስ ማለዳ ለማንሳት የተሞከረው ግን ሳምንትን የተሻገረው ጦር መማዘዝ እና የአለመረጋጋት ጉዞ ቀጣይነትን መሰረት ያደረገ ነው። ጉዳዩ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) በመጀመሪያው ቀን እንዳሉት ሳይፈለግ የተገባ ጦርነት እንደሆነ እና ጦርነቱ ሕግን ከማስከበር ባለፈ አጥፊዎችን ለሕግ የማቅረብ የማይቀለበስ እና ማይቋረጥ ተግባር መሆኑን አስረግጠው ተናግረው የአገር መከላከያ ሰራዊትም አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ እንደታዘዘም ይፋ አድርገዋል።

ይህ ጉዳይ ግን ከቀናት በኋላ በጠቅላይ ሚንስትሩ በኩል የሚሰጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የተጠቃሰውን ጦርነት እና ሕግ ማስከበር እንቅስቃሴ በታቀደው መልኩ እየተከናወነ እንደሆነ እና ቶሎ አጠናቆ ወደ ተጀመረው ልማት እና ብልጽግና ጉዞ የመመለስ መርሃ ግብር እንደተያዘ በይፋ ሲናገሩም ተስተውለዋል። ይህን ጉዳይ ደግሞ የሚያጠናክሩት እና በመረጃ መስጠቱ መርሃ ግብርን በመምራት ወደ መገናኛ ብዙኃን ብቅ ያሉት በኮሙኒኬሽኑ ዘርፍ ልምድ ያላቸው እና በአምባሳደርነት አገልግለው ወደ ዋና ቢሮ በመጠራት የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ዲኤታ በመሆን እያገለገሉ ያሉት አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ያጠናክሩታል። ከእንግሊዘኛው ካፒታል ጋዜጣ ጋር ቆይታ ያደረጉት ሬድዋን አሁን ያለው ጉዳይ የአጭር ጊዜ ተልዕኮ እንደሆነ እና አጥፊዎችን ለሕግ በማቅረብ የሚደመደም እንጂ ብዙም ዕድሜ የሌለው ክስተት እንደሆነ ለማስቀመጥ ሞክረዋል።

በመንግሥት በኩል የሚነገሩት ተደጋጋሚ እና የአጭር ጊዜ ነው የሚባለውን ጉዳይ ታዲያ አዲስ ማለዳ ከተ፤ያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች እና ከሰላም እና ደኅንነት ባለሙያዎች ጋር ባደረገችው ቆይታ ጉዳዩን በጥቀት ለመዳሰስ ቆይታለች። አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ኹለት የተለያዩ ሐሳቦችን ለማንጸባረቅ ችለዋል። በቅርቡ የተፈጠረው የጦር መማዘዝ እና ከፍተኛ የሆነ የወታደራዊ እርምጃ በእርግጥም በቅርቡ እንደማይጠናቀቅ እና ወደ ተራዘመ ጦርነት የሚገባበት ጉዳይ ወይም አዝማሚያ ሊኖር ይችላል የሚል ሐሳብ ያላቸው ሲሆን ሌሎች ለአዲስ ማለዳ ሐሳባቸውን የሰነዘሩ ሰዎች ደግሞ እንደሚሉት የለም ይህ ጉዳይ በአጭሩ የሚፈታ እንደሆነ እና መንግሥትም እንዳለው ለሕግ የሚቀርቡ ሰዎችን በአስቸኳይ በማቅረብ ወደ ነበረበት ጉዳይ የመመለስ እና ሁሉም ሰላም እንደሚሆን ሐሳባቸውን ያስቀምጣሉ። አያይዘውም መንግስት እንደሚለው ይህ ጉዳይ ጦርነት ሳይሆን ሕግን የማስከበር አጭር ተልእኮ እንደሆነ እና ግስጋሴውም በተጠበቀው እና በታሰበው ልክ እንደሚካሔድ እና እየተካሔደም እንደሆነ ይናገራሉ።

በቀድሞው ጦር ረጅም ጊዜ ያገለገሉት እና ከኤርትራ እስከ መላው የትግራይ ክልል በውትድርና ዘመናቸው ያካለሉት የዕድሜ ባለጸጋው ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደተናገሩት የመንግሥትን ትዕግስት በማድነቅ ይጀምራሉ። ነገር ግን በመንግሥት ትዕግስት ውስጥ አጥፊው ቡድን ለጦርነት ሲዘጋጅ እና ሰፊ እንቅስቃሴ ሲያደርግ በመቆየቱ በአጭር እንኳን ቢቋጭ ለፌደራል መንግሥቱ ቀላል ጦርነት እንደማገጥመው ያብራራሉ። ነገር ግን እንደ አስተያየት ሰጪው ከሆነ ከነበራቸው የዝግጅት ጊዜ እና ከመልክዓ ምድሩ አኳያ እንዲሁም መንግሥት ንጹሐን እንዳይጎዱ በሚል በሚያደርገው ጥንቃቄ ምክንያት ጦርነቱ በአጭር ይቋጫል የሚል እምነት እንደሌላቸው ያስቀምጣሉ። እንደተባለው አጥፊዎችን ወደ ሕግ የማቅረብ ተልዕኮው በተሳካ ሁኔታ ይደመደማል የሚል እምነት ቢኖራቸውም የአጭር ጊዜ ግን ለመሆኑ አሁንም ጥርጣሬ አላቸው። ይህን ጉዳይ ቢመለከት ግን ሐሙስ ሕዳር 3/2013 ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻቸው እንዳሰፈሩት የአጥፊውን ቡድን እየፈጸመው ያለውን ጥፋት እና የፌደራል መንግሥትን ግስጋሴ በአጭር ጊዜ እንደሚቋጭ አንደምታ ያለው ጽሑፍ እንዲህ አስነብበዋል።

‹‹ለስግብግቡ ጁንታ ግፍ እስትንፋሱ፣ ጭካኔ ነፍሱ ነው። ጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችን ሽራሮን ሲቆጣጠር፣ እጅና እግራቸውን የፊጥኝ ታሥረው የተረሸኑ የመከላከያ አባላትን አግኝቷል። ጭካኔው ልብ ሰባሪ ነበር። ዓላማው ኢትዮጵያን መስበር ነው። አላወቁም ከአልማዝ የጠነከረች መሆኗን። ዓላማው ሠራዊታችንንና ሕዝቡን አስቆጥቶ ለበቀል ርምጃ ማነሣሣት ነው። አላወቁም ልበ ሰፊ ሕዝብና ሠራዊት እንዳለን።

በየቦታው ስንደርስ ከዚህ የከፋ ጭካኔና ግፍ ሊገጥመን ይችላል። ይህ ግን ለዚህ ጁንታ የመጨረሻው ነው። ጥንቃቄያችን ‘ሙት ይዞን እንዳይሞት’ ነው። መፍጠን አለብን፤ የተረፉትን ለመታደግና ግፍ የተፈጸመባቸውንም ለዓለም ለማጋለጥ። የምዕራቡን የትግራይ ክልል ቀጣና ነጻ ወጥቷል። በዚያ ቀጣና ሠራዊቱ ሰብአዊ ርዳታና አገልግሎት እየሰጠ ነው። ነጻ ባወጣቸው አካባቢዎች ሕዝቡን እየመገበ፣ እያከመና እየተንከባከበ ነው›› የሚል ነው። የጠቅላይ ሚንስትሩን ሐሳብም የሚጠናክረው የኢፌዲሪ መከላከያ ሰራዊት ኢታማዦር ሹም ጀነራል ብርሀኑ ጁላ አጥፊው ቡድን ፈጽሟቸዋል ያላቸውን ሕገ ወጥ ተግባራት በገለጹበት መግለጫቸው ፍጻሜው እየተፋጠነ ያለውን ግዳጅ በሚመለከት ‹‹ሰራዊቱ በአሁኑ ወቅት ከሁመራ 60 ኪሎሜትር ወደ ምስራቅ ኢድሪስ በሚባል ቦታ ላይ የጥፋት ቡድኑን እየደመሰሰ እንደሚገኝ ያመለከቱት ጀኔራል ብርሃኑ፤ “ሰራዊታችን በተፈፀመበት ኢሰብዓዊ ድርጊት በመበሳጨቱ በከፍተኛ ወኔ፣ ጀግንነትና ተነሳሽነትም ሁሉንም ነገር ወደነበረበት ለመመለስና ከሃዲውን ቡድን በህግ ፊት ቀርቦ እንዲቀጣ ለማድረግ እየሰራ ነው” ብለዋል።

ሰራዊቱ የትግራይን ህዝብና የትግራይን የፀጥታ ሃይል ጭምር ነፃ ለማውጣት ግስጋሴውን ወደ ሽሬ ማድረጉን ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ ጠቁመዋል።
“ህገወጡ ጁንታ ህዝቡና የፀጥታ ሀይሉን እንደ ምሽግ ስለተጠቀመ፣ ህዝቡንና የፀጥታ ሀይሉን ከዚሁ ወንጀለኛ ቡድን በመነጠልና እሱኑ ኢላማ ያደረገ እንቅስቃሴ እየተካሄደም ይገኛል” ያሉት ጀኔራል ብርሃኑ፤ ህግ የማስከበሩን ስራ ባጠረ ጊዜ ለማጠናቀቅ ሁለንተናዊ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ አመልክተዋል።
የመከላከያ ሰራዊት ጁንታውን ለህግ ለማቅረብ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ህዝቡ እንዳይጎዳ ተገቢውን ጥንቃቄ እያደረገ እንደሆነ ጠቁመዋል።

የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት የሰሜን ዕዝ ለጦርነት ባልተዘጋጀበት ሁኔታ ላይ እያለ በህወሃት የጥፋት ቡድን ልዩ ሃይል አማካኝነት ጥቃት የተፈጸመበት መሆኑ የሚታወስ ሲሆን ይህንኑ ተከትሎ መንግስት ህግ የማስከበርና የህልውና ዘመቻ እያካሄደ ይገኛል››። ሲሉም ይህ ጽሑፍ እስከተጠናቀረበት ድረስ ያለውን መረጃ አስታውቀዋል።

ተመሳሳይ ድምዳሜ ላይ የሚደርሱ ግን ደግሞ የጦርነቱ ወይም ሕግ የማስከበሩ እንቅስቃሴ ረጅም ጊዜያትን የሚወስድ እንደሆነ ከወዲሁ ግምታቸውን የሚያስቀምጡ አስተያየት ሰጪዎችም ደግሞ ምክንያታቸውን ያስቀምጣሉ። ሲጀመር በአጭር ጊዜያት ምናልባትም በቀናት የሚያልቅ የሚመስል እና ፌደራል መንግሥት ካለው ጠንካራ አቋም የተነሳ አንድ ሳምንትን መሻገር ብቻ ሳይሆን ሳምንት መድፈኑን እንኳን ስንመለከት ይሄ ጉዳይ በጣም ጠንካራ ነው የሚል ሀሳብ እንዲያድርብን ሆነናል የሚል ምላሽ እና አስተያየት ሲሰጡም ተደምጠዋል።

በሌላ ጎራ ደግሞ ዓለም አቀፉ ግጭት ተንታኝ ቡድን የሆነው (international crisis group) እንደሚገልጸው የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐብይ አሕመድ ወደ በይፋ ሕግ የማስከበር እንቅስቃሴውን ካስታወቁ በኋላ ኢትዮጵያ ወደ እርስ በርስ ጦርነት የሚወስዳትን መንገድ እየተከተለች ነው ሲልም ትንታኔውን አስቀምጧል። በተለይም ደግሞ የግችት ተንታኙን ቡድን መሰረት አድርጎ የዘሆርን የተሰኘ የፖድካስት አዘጋጁ አለን ባዝዎል በመግቢያው ላይ እንደሚተርከው ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ወታደራዊ እርምጃ በሕወሓት ላይ እንዲወሰድ ካዘዙ በኋላ አብዛኛው ሰው ሲፈራው የነበረው የእርስ በርስ ጦርነት ጅማሬ እንደሆነ አድርጎ ያስቀምጣል። በዚሁ መርሃ ግብር ላይ የክራይሲስ ግሩፑ ተንታኝ እንግሊዛዊው ዊሊያም ዴቪድሰን እንደገለጸው ለቁርሾው እና ለአለመግባባቱ እንደመነሻ የሚነሳውን የክልላዊ ምርጫው ከሕገ መንግሥት ውጪ መደረጉን እና በአገር አቀፍ ደረጃ የተራዘመውን ምርጫ ትግራይ ውስጥ መካሔዱ እንዲሁም ይህን ተከትሎም መንግስት ኢ-ሕገ መንግስታዊ ነው ማለቱ የመካረሩን ጉዳይ እንዳባባሰው በመግለጽ ይጀምራሉ።

ነገሮች እየባሱ መምጣታቸውን እና እንደሚባባሱም ዊሊያም በውይይቱ ወቅት ጠቁሟል። አሁን ለተደረሰበት ከባድ ግጭት በእርግጠኝነት ምን አይነት ምክንያት እንደመራው በእርግጥም የሚታወቅ እና ይህ ነው ሊባል የሚችል ጉዳይ እንደሌለ ዊሊያም ይናገራል። ነገር ግን እንደ ምክንያት ሊሆን ይችላል በሚልም በቅርቡ የአገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን ዕዝ ዋና አዛዥ ሆነው የተሾሙትን እንደማይቀበሉ የሕወሓት ቡድን መናገሩን እና ምክትላቸውንም በክልሉ ልዩ ኃይል እንዲመለሱ መደረጋቸው (ይታወሳል) የወታደራዊ ጣልቃገብነቱ ጫፍ ላይ እንደደረሰ ማሳያ እና ግጭቱም አይቀሬ መሆኑን ማሳያ እንደሆነ ግምቱን ያስቀምጣል።

ነገር ግን በተቃራኒው ዊሊያም ዴቪድሰን ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደተናገሩት በሰሜናዊው ክፍል የሚገኘው ግጭት እና ቢበዛ ሳምንታት ወይም ወር ድረስ ሊራዘም እንደሚችል ትንበያቸውን ያስቀምጣሉ። ሕወሓት ሚሊሻዎችን እና የክልሉን ልዩ ኃይላት ሊያሰልፉ ከመቻላቸው ጋር ተዳምሮ ወደ በፍጥነት ወደ ፍጻሜ የመቃረቡን ሒደት ሊያስተጓጉለው ቢችል እንጂ በቅርቡ ግን ፍጻሜ እንደሚያገኝ ተናግረዋል። በተለይም ደግሞ በዚህ ክስተት ላይ መንግሥት ጉዳዩን ሕግን የማስከበር ተልዕኮ ከሆነ እንደዛው ተብሎ ሊጠራ እንደሚገባውም ሀሳባቸውን ሰንዝረዋል።

በዚህ ጉዳይ ላይ በርካታ የሰላም እና ደኅንነት ተንታኞች በተለይም ደግሞ በቀጠናው ላይ ሊያመጣ የሚችለውን መጻኢ ተጽእኖም በማስቀመጥ ከወዲሁ የውጭ ጣልቃ ገብነት እንዲኖር እንደሚያስፈልግ ቢያስቀምጡም በሌላ ወገን ደግሞ የኢትዮጵያ አገር መከላከያ ሰራዊት በቅርቡ ነገሮችን የመቆጣጠር አቋም ላይ በመሆኑ ጉዳዩ በአገር ውስጥ እንዲፈታም ሀሳባቸውን ይሰነዝራሉ። በእርግጥም በቀጠናው ላይ ኢትዮጵያ ያላትን ተቀባይነት እና ተሰሚነት ኹለቱም ጎራዎች ማስቀመጥ ችለዋል። ይህን በሚመለከትም በኢትዮጵ የቻይና አምባሳደር ከቀናት በፊት ከውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዲኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ጋር ባደረጉት ቆይታም የአገር ውስጥ ችግር መሆኑን ጠቅሰው ኢትዮጵያ ያለምንም የውጭ ጣልቃ ገብነት ችግሩን በራሷ አቅም መፍታት እንደምትችል አስታውቀዋል።

የሰላም እና ደኅንነት ተንታኞች እንደሚናገሩት ዘላቂ ጦርነት ሊባል የሚችለው ተቀራራቢ ወታደራዊ አቋም ላይ የሚገኙ አካላት መካከል የሚደረጉ ውጊያዎች ወይም ጦርነቶች እንጂ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ እየተካሔደ ያለው ጉዳይ ወይም መንግሥት እንደሚለው ሕግ የማስከበሩ ተልዕኮ በቅርቡ ይጠናቀቃል ሲሉም ያስረግጣሉ። በሌላ እይታም የሚናገሩት ተንታኞች የተራዘመው ጦርነት እንዲሆን አካላት አቅማቸውን የሚያጎለብቱበት እና ተደራጅተው አጸፋዊ ምላሽ የሚሰጡበት ስፍራ እና ከተቀናቃኛቸውም እፎይታን ሊያገኙ የሚገባበት አጋጣሚ ቢኖር እንደሆነ ይናገራሉ። ነገር ግን ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ይራዘማል ማለት ወይም ደግሞ ተራዝሞ ከፍተኛ ውድመት እና ትልቅ ኪሳራ በአገር ላይም ሆነ በሕዝብ ላይ ያደርሳል ሚል ዕምነት እንደሌላቸው ያስገነዝባሉ።

ከዚህ በተቃራኒው አንድ ሳምንትን በተሻገረው ጦርነት 10 ሽሕ የሚሆኑ ሰዎቸች ከቀያቸው ተፈናቅለው ድንበር በመሻገር ወደ ጎረቤት አገር ሱዳን መሰደዳቸውን ሬውተርስ ዘግቧል። ይህ በአጭር ጊዜ ውስጥ በተፈጠረው ውጥረት የተፈጠረ ዳፋ እንደሆነ ያስቀምጣል። ይህንንም ተከትሎ በሱዳን የሚገኘው የሰብዓዊ እርዳታ አድራሽ ቁጥሩ ከጠበቁት በላይ እንደሆነባቸው እና ይህም ደግሞ እርዳታውን በተገቢው ሁኔታ ለማዳረስ ችግር እንደሚሆንባቸው ጠቁሟል። ይሁን እንጂ አሁንም ቁጥሩ ሊጨምር እንደሚችል እና ሱዳን 200 ሽሕ የሚሆኑ ኢትዪጵያዊያን ስደተኞችን በቀጣይ ቀናት እንደምትጠብቅም ሬውተርስ በዘገባው ለማስቀመጥ ሞክሯል።
ይህንንም ተከትሎ ምክረ ሀሳባቸውን የሚስቀምጡ ምሁራን መንግሥት ሕግን የማስከበር ግዳጅ ባለው የዚህ እንቅስቃሴ በያዘው ፍጥነት እንዲቀጥል እና የአለመረጋጋቱን ዕድሜም በያዘው መርሃ ግብር እንዲያሳጥርም ጠቁመዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 106 ኅዳር 5 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here