በጉራ ፈርዳ ወረዳ አጥፊዎችን ለመቆጣጠር መልክዓ ምድሩ ፈተና መሆኑ ተገለጸ

0
549

በቤንች ሸኮ ዞን ጉራ ፈርዳ ወረዳ የታጠቁ አጥፊዎቸን በቁጥጥር ሥር ለማዋል የአካባቢ መልክዓ ምድር ስፋት ለመደበቅ እና ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ ምቹ ቀጠና በመሆኑ አጥፊዎችን ለመያዝ ፈተና አንደሆነበት የደቡብ ክልል የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

በደቡብ ክልል ቤንች ሸኮ ዞን በጉራ ፈርዳ ወረዳ ካሳለፍነው ጥቅምት 18/2013 ጀምሮ ግጭት በመቀስቀሱ እስካሁን ድረስ ከ60 በላይ ዜጎች ሕይወታቸው እንዳለፈ እና ከአምስት ሺሕ በላይ ዜጎች ከመኖሪያ ቀያቸው እንደተፈናቀሉ ይታወሳል።

በአካባቢው ሰፋቱ እጅግ የበዛ ጫካ በመኖሩ ጥቃት ፈጻሚው የታጠቀ ኃይል በየጊዜው እየተዘዋወረ ትክክለኛ አድራሻውን ለማግኘት እና እርምጃ ለመውስድ አስቸጋሪ ከመሆኑም በላይ አሁንም ድረስ ጨለማን ተገን በማድረግ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ንብረት እየዘረፈ ጫካ እየገባ መሆኑን የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ መልካም አስተዳደር ክላስተር አስተባባሪ እና የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አለማየሁ ባውዲ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ለታጠቀው ቡድን እንቅስቃሴ ምቾትን የፈጠረው የጫካ ቀጠና ስፋቱ እስከ ሱዳን ድንበር ድረስ የሚዘልቅ በመሆኑ የታጠቀው ቡድን በየእለቱ አድራሻውን እየቀየረ ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ሆኖ መቀጠሉን የጠቆሙት ኃላፊው “የታጠቀው ቡድን እንደቀድሞው በወታደር ብቻ አሳድዶ የሚያዝ አይደለም” ሲሉ ገልጸዋል።

ኃላፊው ለአዲስ ማለዳ እንዳስረዱት በአካባቢው ጥቃት የሚፈጽመው የታጠቀ ኃይል ሕዝብ ለሕዝብ በማጋጨት ለግል ፍላጎት የሚሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል። ለግል ፍላጎት ጫካ የገባውን የታጠቀ ቡድን የሚደግፉ የአካባቢው ማኅበረሰብ አካል መኖራቸው ደግሞ ችግሩን በአጭር ጊዜ እልባት ለመስጠት ሌላው እንቅፋት መሆኑንም ኃላፊው ጨምረው ገልጸዋል።

ጫካ ገብቶ ጥቃት በማድረስ ላይ የሚገኘው የታጠቀ ቡድን በአካባቢው ተጨማሪ አደረጃጀት ይፈቀድልን በሚል ሽፋን የሕዝቡን መብት ለማስከበር ነው የሸሸሁት የሚል የተዛባ አመለካከት እና በተለያየ ጊዜ በወንጀል ድርጊት ላይ የተሳተፈ ቡድን የተፈጠረውን አጋጣሚ ተጠቅሞ ጫካ ገብቶ የተቀላቀለ መሆኑን አለማየሁ ለአዲስ ማለዳ በሰጡት ማብራሪያ ጠቁመዋል።

አለማየሁ አክለውም በተለያዩ ጊዜያት የመንግሥትን እና የግለሰብን ንብረት በመዝረፍ ሀብት በማካበት በወንጀል የተሳተፈ ቡድን እና የሕዝብን መብት ለማስከበር በሚል ጫካ ገብቶ የሚገኘው ቡድን በተፈጠረው ችግር የተፈናቀሉ ዜጎችን ንብረት ጨለማን ተገን በማድረግ ለመዝረፍ እየሞከረ መሆኑን ተናግረዋል።

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚቻለው የአካባቢው ማኅበረሰብ ጨለማን ተገን አድርገው እቤት ድረስ እየገባ በልቶ እና ጠጥቶ ዘርፎ የሚሄደውን የታጠቀ ቡድን በአንድ አቋም ማጋለጥ እና ጥቆማ መስጠት ሲቻል ብቻ ነው፤ ያሉት አለማየሁ ይህ ካልሆነ ችግሩን በአጭር ጊዜ ለመፍታት አዳጋች መሆኑን ጠቁመዋል።

የመከላከያ ኃይል በአካባቢው የሚገኘውን የክልሉን የጸጥታ ኃይል ለማገዝ መግባቱን ያስታወሱት አለማየሁ አሁን ላይ በአገሪቱ በተፈጠረው ወቅታዊ ሁኔታ ከአካባቢው መውጣቱን ተናግረዋል። በአካባቢው ተሰማርቶ የነበረው መከላከያ በመልቀቁ የሕዝቡን ደህንነት ለመጠበቅ የክልሉ ልዩ ኃይል ተሰማርቶ እየጠበቀ መሆኑን አመላክተዋል።

በሌላ በኩል ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት አሁን በተፈጠረው ችግር በማኅበረሰቡ ውስጥ ኹለት አይነት አመለካከት መፈጠሩን አለማየሁ ገልጸዋል። አንደኛው በነባር የአካባቢው ነዋሪዎች በኩል “እኛ ሳንጠቀም ከኋላችን የመጡ ሰፋሪዎች ሀብት አካብተዋል” በሚል አመለካከት ጫካ የገባውን ቡድን የሚደግፉ መሆናቸው ተመላክቷል።

ኹለተኛው ከነባሮቹ በተቃራኒ የሆነው በተለያየ ጊዜ ከሌላ አካባቢ በመምጣት ሐብት ንብረት ያፈራ የማኅበረሰብ ክፍል ሐብቴና መብቴን በኃይል ተደራጅቼ አስከብራለሁ የሚል መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል።

በዚህም ጫካ የገባውን የታጠቀ ቡድን የሚደግፉ የማኅበረሰብ ክፍል በመኖራቸው የታጠቀውን ቡድን መውጫ መግቢያ እያወቁ እና ጨለማን ተገን አድርገው አብልተው እየሽኙ የታጠቀውን ቡድን መቆጣጠር እነዳይቻል ፈተና መሆናቸውን ገልጸዋል።

በክልሉ ከተፈጠረው ችግር ጋር በቀጥታ በመሳተፍ የተጠረጠሩ አመራሮችን ጨምሮ 93 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ማዋላቸውን አለማየሁ ገልጸዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 106 ኅዳር 5 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here