ቤቶች ኮርፖሬሽን ማስተካከያውን የማይቀበሉት ላይ ቁልፍ እሰከመንጠቅ የሚደርስ እርምጃ እወስዳለው አለ

0
639

የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን አዲስ ባወጣው የኪራይ ቤቶች ዋጋ ማስተካከያ አተገባበር የማይቀበሉ ነጋዴዎች ላይ ቁልፍ እሰከመንጠቅ የሚደርስ እርምጃ እንደሚወስድ ገለጸ። ባሳለፍነው ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 25 ከነጋዴዎች ጋር ባደረገው ውይይት ከመግባባት ላይ ሳይደርስ የቀረው ኮርፖሬሽኑ አዲስ ያወጣውን አተገባበር ተቀብለው ክፍያ በማይፈጽሙት ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቀዋል።
ከዚህ ቀደም እሰከ ጥር 2011 ድረስ ክፍያ የተቀመጠው የጊዜ ገደብ ለአንድ ወር መራዘሙንም ያስታወቀው ኮርፖሬሽኑ፤ አዲስ የተተመነው አተገባበርም እያንዳንዱ ነጋዴ በሦስት ዓመታት ክፍያውን እንዲያጠናቅቅ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
በአዲሱ አተገባበር መሠረት ማንኛውም ነጋዴ በመጀመሪያው ዓመት የአዲሱን ክፍያ 35 በመቶ እንዲከፍል፤ በሁለተኛው ዓመት በተመሳሳይ 35 በመቶ እንዲከፈል ተወስኗል። ቀሪው 30 በመቶ ደግሞ በሦስተኛው ዓመት ላይ እንዲከፈል ተወስኗል።
በወጣው መሥፈርት መሠረት ክፍያ በማይፈጽሙ ነጋዴዎች ላይ ማን ይወስናል ብላ አዲስ ማለዳ ለኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ረሻድ ከማል ላቀረበችው ጥያቄ “ክፍያ በማይፈጽሙ ነጋዴዎችን ቁልፍ እስከመንጠቅ የሚደርስ እርምጃ እንወስዳለን” በማለት ምላሻቸውን ሰጥቷል። “እኛ ሕጋዊነትን ተመርኩዘን ነው እየሠራን የምንገኘው ላለፉት 40 ዓመታት ኮርፖሬሽኑ ማግኘት ከሚገባው ባነሰ መልኩ ነበር ገቢ የሚሰበስበው” በማለት ኮርፖሬሽኑ በቀጣይም ግልጽ ጨረታ በማውጣት የንግድ ሱቆችን የማስረከብ ሥራ እንደሚሠራ ረሻድ ጨምረው ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ኮርፖሬሽኑ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች የንግድ ሱቆችን በመገንባት ላይ ነው ያሉት ዋና ሥራ አሥፈጻሚው በሚሰበሰበው ገቢም ሌሎች ግንባታዎችን ለማካሄድ እንደታሰበ አስታወቀዋል። በዚህ ሁኔታ ላይ መተባበር የማይችል ነጋዴ ካለ በራሳችን እርምጃዎችን ለመውሰድ እንገደዳለን ሲሉ ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ ባለፈው ሐሙስ የተሰበሰቡት ነጋዴዎች ኮርፖሬሽኑ ባስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች አልተስማሙም። ነጋዴዎቹ በቀጣይ ችግሮቻቸው የማይፈታ ከሆነ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትና ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር ቅሬታቸውን ለማቅረብ ደብዳቤ ማስገባታቸውንም ገልጸዋል።
አለማየሁ ፈቃዱ የተባሉ በጊዜያውነት የተዋቀረው የኪራይ ቤቶች ነጋዴዎች ማኅበር ኮሚቴ ዋና ሰብሳቢ እንደገለፁት፤ መንግሥት ያደረገው የአተገባበር ለውጥ እንጂ የዋጋ ማስተካከያ አላደረገም ብለዋል። አክለውም ያለምንም ጥናት የተተገበረን ዋጋ ማስተካከያን የአተገባበር ሁኔታ መቀየር ምንም ለውጥ አያመጣም ብለዋል። በተጨማሪም የኮርፖሬሽኑን እርምጃ እንደማይቀበሉት ገልፀዋል።
ከእርሳቸው በተጨማሪ፤ በተለያዩ አካባቢዎች የኮርፖሬሽኑን የንግድ ሱቆች የተከራዩ ነጋዴዎችም ከባለፉት ሳምንታት ጀምሮ በጭማሪው ቅሬታቸውን በተደጋጋሚ እያሰሙ ይገኛሉ። ከመጠን ባለፈ ጭማሪ ተደርጎብናል ከሚሉት ነጋዴዎች ውስጥ አንዱ የሆኑት ግርማ አሰፋ ጭማሪው አያስከፋንም ነገር ግን ድንገተኛና ያልተማከርንበት ነው ብለዋል።
ከዚህ ቀደም ስከፍል ከነበረው ሶስት እጥፍ ያህል በመጨመሩ ቀጥሬ የማሰራቸውን ሰራተኞች ለመበተን ተገድጃለው የሚሉት ሌላው ነጋዴ መሰፍን ጥላሁን ጭማሪው ሌላ የፖለቲካ አውድ እንዲኖረው የሚፈልግ አካል ያደረገው ነው ይላሉ። ጭማሪውን በሚመለከት ከኮርፖሬሽኑ ሃላፊዎች ጋር የምናደርጋቸው ውይይቶችም ፍሬ አልባ ናቸው ብለዋል።
በፊት ከሚከፍሉት ከ 2000 በመቶ በላይ በመጨመር 509 ብር በካሬ እንዲከፍሉ የተጠየቁት ደረጀ በላይ በበኩላቸው፤ ኮርፖሬሽኑ አንዲህ አይነት የተመን ማስተካከያ ማድረጉ ሸማቾችን የበለጠ ተጎጂ ሊያደርጋቸው እንደሚችል ያስጠነቅቃሉ።
የዋጋ ተመኑ ላይ ቅናሽ ለማድረግ የተለያዩ አማራጮችን አይተናል የሚሉት የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ ረሻድ ከማል በበኩላቸው፤ በተለይም የዋጋው ጭማሪ በዝቶባችዋል ብለን የምናስባቸው ሱቆች፣ የዘርፍ ለውጥ ያደረጉ፣ አትራፊ ያልሆኑ የበጎ አድራጎት ማህበራት፣ የሃይማኖት ተቋማትና መሰል በኮርፖሬሽኑ የሚተዳደሩ ሱቆችን ከግምት ያስገባ ነው ብለዋል።
ይሁን እንጂ፤ በአንዳንድ አካባቢዎች ለትርፍ ያልተቋቋሙ ተቋማት ላይ ከፍተኛ ጭማሪ መደረጉን አዲስ ማለዳ መገንዘብ ችላለች። ለአብነትም ያህል፤ ፒያሳ አራዳ ሕንጻ የሚገኝ ዕድር ለትርፍ ያልተቋቋመ ቢሆንም፤ የሚከፍለው ኪራይ ከ 554 ብር አካባቢ ወደ 19642 ብር እንዲያድግ ተደርጓል።
የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በስሩ 6635 የሚሆኑ የንግድ ሱቆችን በአዲስ አበባ የሚያስተዳድሩ ሲሆን በከተማዋ ኮርፖሬሽኑ የሚያስተዳድራቸው ትላልቅ ሆቴሎችና የንግድ ማዕከላት ይገኛሉ። አብዛኞቹ ሱቆችም የኢጣሊያን መንግስት ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት የተሰሩ ናቸው።

ቅጽ 1 ቁጥር 8 ታኅሣሥ 27 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here