‘ሚዲያ’ መር ዴሞክራሲ

0
462

ብዙኃን መገናኛዎች የፖለቲካ ፓርቲ ወይም ወገን ለይተው ከሚተዳደሩበት፥ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ አስተዋፅዖ ወደ ሚያደርጉበት ‘ብዙኃን መገናኛ መር ዴሞክራሲ’ መሸጋገር አስፈላጊነት ቤተልሔም ነጋሽ ይህንን መጣጥፍ አቅርበዋል።

 

 

በግሌ ባደረግኩት ግምገማ፥ የአገራችን ብዙኃን መገናኛ ሚዛናዊነት የሚጎድለው፣ ወደ አንድ ጎን ያደላ፣ ከብዙኃን መገናኛነት ይልቅ ለፖለቲካ ፓርቲነት የቀረበ ነው፡፡ ከሁለት ዐሥርት ዓመታት በፊት ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ሲታወጅ ‘ከፖርኖግራፊ’ እስከ የመንግሥት ተቃዋሚና ጠንካራ እንዲሁም ግልብና ጭፍን ተቺ ጋዜጦችና መጽሔቶች እንደ አሸን ፈልተው እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ ይሁንና የተሻለ ሚዛናዊ ለመሆን የሚሞክሩ፣ በመረጃ ምንጭነትም ይሁን ዕውቀት በማካፈል እና ማኅበራዊ ሕፀፆችን ነቅሶ በማውጣት ሚናቸውን ለመወጣት የሚሞክሩ በጥቂቱም ቢሆን እንደ ነበሩ መጥቀስ አስፈላጊ ነው፡፡
በአገራችን የምርጫ እና በከፊል የዴሞክራሲ ሒደት ማቆጥቆጥ ምሳሌ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችለው ምርጫ 97 መጥቶ የጋዜጦችን ሕልውና አደጋ ላይ እስኪጥል አማራጭ ሊባል የሚችል ሚዲያ ነበረን፡፡ በተለይ በምርጫው ዋዜማ ከዚያ ሁሉም ተቋረጠ፡፡ ብዙ የሚዲያ ተቋማት በሕግም አለሕግም ተከሰሱ፣ ተዘጉ፣ ኪሳራ ውስጥ ገቡ፡፡ በነበረው ተቋማዊ፣ ቀጥታና ተዘዋዋሪ ተፅዕኖ እስርና እንግልት ብቅ ብላ የነበረችው የብዙኃን መገናኛ ጀንበር ጠለቀች፡፡
በመካከል በዳያስፖራም ይሁን ሁሉም በሚባል መልኩ እስኪታገዱ ድረስ በድረ ገጾች እየታገዙ ዜና እና ትንታኔ ጽሑፎችን ለማጋራት እንደ አማራጭ ብዙኃን መገናኛ ሲመጣ የለመደው ስልት ነው ሊባል ቢችልም፥ ተመልካች ፍለጋ ወይም የራስን የፖለቲካ አቋም ከጭፍን ድጋፍና ፕሮፓጋንዳ ልሳንነት እስከ የተቃውሞ ፖለቲካ በይፋና በተከታታይ ማቅረብ ከሚዲያ ይልቅ ወደ ፖለቲካ ፓርቲ ጎራ ቃል አቀባይነት ያደላል፡፡
ብዙኃን መገናኛ በዲሞክራሲዊ ግንባታ ቁልፍና የማይተካ ሚና ቢኖረውም፥ በአገራችን ሚዲያ ዕድገቱ እንዲቀጭጭ ሆኖ ሚናውን በአግባቡ ለመወጣት ሳይችል ቀርቷል፡፡ የብዙኃን መገናኛ ከባቢውም ሚና ለመወጣት ቀርቶ በኅትመት ለመቆየትም የሚስችል ባለመሆኑ በተለያዩ ምክንያቶች በተለይ ነጻ የሚባል ገለልተኛ፣ በሕዝብ የሚታመን ብዙኃን መገናኛ ማግኘት ሕልም ሆኖ ቆይቷል፡፡
ብዙኃን መገናኛ የዲሞክራሲ ሒደትን ከማገዝ አንፃር ሊወጣ ከሚችላቸው ኃላፊነቶች ጥቂቶቹም ብዙኃን መገናኛ ከሕዝብ ጎን የቆመ እንደመሆኑ፣ ሥልጣን ላይ የወጡ ፖለቲከኞችና ፓርቲዎቻቸው በፖሊሲ ደረጃ ካወጧቸው ጉዳዮች አንስቶ፥ እንፈታዋለን ብለው በተናገሩትና በሕዝብ ዘንድ ተመራጭ እንዲሆኑ ካደረጋቸው የሕዝብ አጀንዳና አንገብጋቢ ጉዳዮች አፈፃፀም ላይ እንዲሠሩ በማስታወስ፣ ካልሠሩም ተጠያቂ እንደሚሆኑ ማስታወስ አንዱ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በተለይ በምርጫ ወቅት ኅብረተሰቡ ይወክሉኛል የሚለውን እንዲመርጥና በዲሞክራሲው ሒደት የድርሻውን እንዲወጣ በንቃት እንዲሳተፍ ማስተማር ነው፡፡
በአገራችን ባለን የብዙኃን መገናኛዎች ታሪክ ግን፣ ከላይ የተጠቀሰው የምርጫ 97 ምሳሌ እንዳለ ሆኖ፥ በተለያዩ ምክንያቶች ሚዲያው ያን ያህል ፖለቲካው ላይ ተፅዕኖ አሳድሮ በብዙኃን መገናኛዎች የሚመራ ነው ለመባል ደረጃ አልደረሰም፡፡ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ሲታይ ግን ዲሞክራሲ መገናኛ ብዙኃን መር ከሆነ ቆየ፡፡ በዴሞክራሲያዊ ሒደቱ አሁን ላለበት ደረጃ መድረስ ብዙኃን መገናኛዎች ትልቅ ሚና ነበራቸው፡፡ እንዲያውም እንደ ‘ላንስ ቤኔትና ሮበርት ኢንትማን’ ዓይነት የፖለቲካ ተግባቦት ጎምቱ ባለሙያዎች እምነት ያለ ብዙኃን መገናኛዎች ዴሞክራሲና ፖለቲካ አሁን ባለበት ሁኔታ ሊገኙ አይችልም ነበር፡፡ እናም በአውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር ካለፉት ሁለት ዐሥርታት ወዲህ ያለው ዲሞክራሲ ሚዲያ-መር (Mediated Democracy) ሆኗል፡፡ በተለይ ባደጉት አገራት ይህ ዘርፍ የፖለቲካ ተግባቦት ‘ዲሲፕሊን’ አንድ የጥናትና ምርምር ዘርፍ ከሆነ ቆይቷል፡፡
በዓለም ዐቀፉ የሚዲያ ታሪክ በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የሚዲያው ለሙያው ተገዢ የመሆንና ሥነ ምግባሩን አክብሮ መሥራቱን መተው፣ ከዜናና መረጃ ጥራት ይልቅ የተሻለ አንባቢ ለመግዛት በሚል ለስሜት ቀስቃሽ ወሬና የዝነኞች ወሬ ነጋሪ ወደ መሆን በተሻገረ ቁጥር የሚዲያና የዴሞክራሲ ቁርኝትም ይላላል፡፡ በተጨማሪም የበይነመረብ መፈጠር፣ የዜና አገልግሎት ተቋማት መቀነስ፣ የጋዜጦች መመናመን፣ መገናኛ ብዙኃኑ ለዴሞክራሲ ግንባታ አጋርና መሣሪያ እንዳይሆን እያደረጉ ከሚገኙ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ፡፡ በአጭሩ ብዙኃን መገናኛው ለፖለቲካ ወገንተኝነት ተሸጦ የፖለቲከኞች መሣሪያ ሆኗል፡፡
ለምሳሌ ‘ፒው ሪሰርች ሴንተር’ የተባለው የአሜሪካ በምርጫና በመራጮች ጉዳይ ጥናት በማካሔድ የሚታወቅ ተቋም እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2013 ያቀረበው ትንታኔ እንደሚያስረዳው ከምርጫ ጋር በተያያዘ ሪፖርት ያደርጉ የነበሩ ጋዜጠኞች የምርመራ ጋዜጠኝነት በማከናወን ፈንታ በዋነኛነት ፖለቲከኞችና ደጋፊዎቻቸው የሚያቀርቧቸው ሐሳቦችና ገለጻዎች ላይ ብቻ በመመርኮዝ ዘገባ የሚሠሩ እንደ ‘ሜጋ ፎን’ የእነሱን ድምፅ ተቀብለው የሚያስተጋቡ ብቻ ነበሩ፡፡
ብዙኃን መገናኛ የፖለቲካ አቋም ደጋፊ ሲሆን መዘዙ ብዙ ነው፡፡ እንደ ምዕራባውያኑ ጋዜጦችና ቴሌቪዥን ጣቢያዎች በግልጽ አቋማችን ይህ ነው እገሌ የተባለውን ዕጩ እንደግፋለን ማለት ባልተለመደበት እንደ አገራችን ያለ ታዳጊ ብዙኃን መገናኛ እና ዴሞክራሲ አቋምን እንደ ዜና እና የግል አስተያየት መሆኑን ሳይገልጹ እንደ እውነታ ማቅረብ፣ ታሪኮችን ከፈለጉበት አንፃር በማሳየት ሁሉንም ጎን ወይም የሁሉንም ወገን ሐሳብ ባለማካተት እንዲሁም ጥቂቶችን ሐሳብ የብዙኃኑ በማስመሰል ማቅረብ በዚህም ሕዝብን ወዳ አልተፈለገ አቅጣጫ መምራት፣ በትክክለኛ መረጃና እውነታ ላይ ያልተቀሠረተ ውሳኔ እንዳያሳልፉ በማድረግ የዴሞክራሲ ሒደቱ እንዲዛባና ኢፍትሐዊ እንዲሆን ማድረግ አንዱ ነው፡፡
ይህንን ሐሳብ የሚያጠቃልልልኝን የሱዚ ቃሲምን ንግግር በጥቂቱ ላቅርብና ወደ ማጠቃለያዬ ልሒድ፦
“አብዛኛውን ጊዜ የሚየታየውን ቀርበን መርምረን ከመረዳት ይልቅ፥ የምናየው ማየት የምንፈልገውን ብቻ ነው፡፡ አንዳንድ ስህተቶችን የምንቀበለው ስህተቶቹ የአብዛኛው ሰው ሐሳብ እንደሆኑ ተደርው ስለሚቀርቡ ነው፡፡ እውነታው ግን ስህተቶቹ ታዋቂነት ያገኙት በብዙኃን መገናኛ በድምቀትና ተደጋግመው ስለቀረቡልን ነው፡፡ የብዙኃን መገናኛዎቹ ጉልበት ደግሞ ሐሰተኛ መረጃዎችን እንደ እውነት አድርጎ ያሳየናል፡፡”
ወደ አገራችን ወቅታዊ የብዙኃን መገናኛ ከባቢ ስንመለስ፥ ባለፉት 8 ወራት የተፈጠረውን ለውጥ ተከትሎ ለብዙኃን መገናኛዎች አዲስ ፀሐይ የወጣ ይመስላል፡፡ አቁመው የነበሩ ሕትመቶች ዳግም ተመልሰዋል፡፡ እንደ አዲስ ማለዳ ያሉ አዳዲስ ጋዜጦችም ገበያውን ተቀላቅለዋል፡፡ አዲስ ለመጡትም ሆነ ለሚመጡት በተለይ በፖለቲካና ዴሞክራሲ ግንባታ አስተዋፅዖ እንዲያደርጉ ምን መደረግ አለበት የሚለው ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ምሁራን ዩኒቨርሲቲዎች፣ የብዙኃን መገናኛዎች ባለሙያዎችና ሌሎችም የብዙኃን መገናኛውን አካሔድ እየመረመሩና እየተቹ ይህን ሚናውን እንዲወጣ ሊያግዙት ይገባል፡፡
ጋዜጠኝነት እንደ አንድ ሙያ ዳብሮና በልፅጎ፣ እንደ ‘ፕሬስ ካውንስል’ እና በአግባቡ የተደራጁ፣ ለሙያው የቆሙ የሙያ ማኅበራት ወዘተ. ያሉ ራስን በራስ የመቆጣጠርያ ተቋማት ተጠናክረው ሊወጡ ይገባል፡፡ ከሁሉም በላይ ብዙኃን መገናኛው ኃላፊነት እንደሚሰማው ተቋም በሚቻለው አቅም ነጻና ገልለተኛ ሆኖ ሚዛናዊ ዘገባ ማቅረብ ሁሌም ሊቆምለት የሚገባው ዓላማ መሀኑን መገንዘብ ይገባዋል፡፡ ብዙኃን መገናኛ የሚያቋቁሙ አካላትም ዘርፉን እንደ ንግድ ብቻ ሳይሆን የጋዜጠኝነት መርሖና መሠረታዊ መመሪያዎችን በመገንዘብ ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡ በሚቀጥለው ምርጫ ለብዙኃን መገናኛዎች የተሻለ አስተዋፅዖ ጅምር እንዲሆን በመመኘት አበቃሁ፡፡

ቅጽ 1 ቁጥር 8 ታኅሣሥ 27 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here