የሥም ቅጥያ ነገር!?

0
739

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

ባለትዳር ነሽ?
ባልናገር እመርጣለሁ።
ለምን?
ለወሳኝ ኩነት መዝጋቢ ካስፈለገ እንጂ ለሌላው የእኔ የትዳር ሁኔታ ምን ይሠራለታል?
/ሳቅ/ እንዲሁ ነው…ምን ችግር አለ ብትነግሪኝ?
ሊወዳጀኝ የፈለገ ጥያቄ አቅራቢ መጥቶ ነው?
አይደለም…በቃ እንዲሁ ለማወቅ ነው
የእኔ የትዳር ሁኔታ ለጠቅላላ እውቀት ግብዓት ይሆናል?
ታፍሪበታለሽ ማለት ነው! ወይስ ሌላ ጉዳይ አለ?
ሌላ ጉዳይ ማለት?
እሱን ተይው! ግን የአገር ጉዳይ አስመሰልሽውኮ!
ሆይ! ለምን አልተነገረኝም ባይ ነው እነጂ የአገር ጉዳይ ያደረገው
የዘንድሮ ሴቶች! ደግሞ እንዲህ ጀመራችሁ?
/ከጥቂት ደቂቃዎች ክርክር በኋላ/
እሺ! በቃ ወይዘሪት ነኝ…አላገባሁም
ውይ! ለምን? ምነው?
እስቲ እንደው ምክንያቴን እንኳ ለራሴ እንድይዘው ይፈቀድልኝ
እስከአሁን ምን ነካሽ ብዬ ነዋ! ወንድ ጠፍቶ ነው ወይስ ጸባይ የለሽም?
/ሌላ ምልልስ/
እንዲህ ያለ ምልልስ የሰለቻቸው ብዙ ሰዎች አውቃለሁ፤ ወንዶችም ሴቶችም። አይሰለችም? ነገሩ ደግሞ በሴቶች ሲሆን ይገናል። እንዴት ቢሉ በመደበኛ መንገድ ራሷን እንድታስተዋውቅ የተጠየቀች ሴት ከስሟ በፊት የምታኖረው ቅጥያ የትዳሯን ሁኔታ ይገልጻልና ነው፤ ወይዘሪት አልያም ወይዘሮ። ግን አለመናገር አይቻልም ወይ?
አንድ ሰው አንዲትን ሴት ለግሉ ተመኝቶና ሊወዳጃት ፈልጎ ካልሆነ በቀር፤ የትዳሯ ሁኔታ ምን ይሠራለታል? የአንዲት ባለሥልጣን ሴት ሥራዋ እንጂ የትዳሯ ሁኔታ ለቀሪው ሕዝብ ምኑ ነው? አንዳንዱ በእርግጥ በመክፈቻ ንግግሮች ላይ እንደተለመዱት «ክብርት…እና ክቡር…ወይም ክቡራንና ክቡራት» የተሰኙ ቅጥያዎች፤ ወይዘሮና ወይዘሪት ካላሉ ዜማው ስለማይመጣላቸው ነው እንጂ ቅጥያ የማኖሩን ምክንያት አያውቁትም።
ምክንያታቸውን አለማወቃቸው በምን ይታወቃል? ሦስተኛ ዲግሪ የያዙና ዶክተር ተብለው የሚጠሩ፤ የህክምና ባለሙያዎች፤ መሃንዲሶች፤ ጋዜጠኞች፣ ሙዚቀኞች…ወዘተ ለሥማቸው ቅጥያ ሙያቸው እንጂ ወይዘሮና ወይዘሪት አይደለም። «ለምን ወይዘሮ አልያም ወይዘሪት አትይም?» ብለው የሚጠይቁቱ እነዚህን ሰዎች ለምን አትነግሩንም አይሉም፤ አላሉምም። እንግዲህ ሴቶች ሁሉ በእነዚህ ሙያዎች ላይ መዝመት ነው!
ወይዘሮነታቸው ደምቆ እንዲጠራ የሚፈልጉ እንዳሉ ሁሉ ወይዘሪት መሆናቸው እንዲጠቀስ የሚያሳስቡም አሉ። «ወይዘሮ ወይዘሪትም መባል አልፈልግም» የምትል ሴት ይህ ምርጫዋ ነው። ለሕጋዊ አሠራር ያመች ዘንድ ማወቅ ላለባቸው ተቋማት ካሳወቀች አይበቃም? እንደሰው ተስማመተን ልናልፋቸው በምንችላቸው ጉዳዮች ሁሉ ላይ «የሕግ ያለህ!» እንድንል ከሆንንማ የምንዘልቀው አይሆንም።

መቅደስ /ቹቹ/
mekdichu1@gmail.com

ቅጽ 1 ቁጥር 8 ታኅሣሥ 27 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here