ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ መበራከት

0
1403

በኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት ቁጥራቸው የበዛ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያዎች ሲያዙ እና አዘዋዋሪዎችም በቁጥጥር ሥር ሲውሉ ቆይተዋል። ይሁን እንጂ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበዛ ለመጣው ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ደግሞ የሕግ አካላት ከኅብረተሰቡ ጋር በመሆን ቁጥጥር ሲያደርጉ ይስተዋላሉ።
ይህ ጉዳይ ደግሞ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ በቅርብ ቀናት የሕገ ወጥ የጦር መሣሪያዎች በቁጥጥር ሥር መዋል እና ባስ ሲልም በተለያዩ ስፍራዎች ፈንድተው ጉዳት አድርሰዋል። የፌደራል መንግሥት በቅርቡ የሕግ ማስከበር ተልዕኮውን ከጀመረባቸው ቀናት ወዲህ ደግሞ በአዲስ አበባ በርካታ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያዎች በአዲስ አበባ ተይዘዋል። አዲስ ማለዳ በዚህ ሳምንት ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውርን በተመለከተ እና በአዲስ አበባ ደግሞ በቁጥጥር ሥር የዋሉትን የቅርብ ሳምንታት ቁጥሮችን ለመዳሰስ ሞክራለች።

ኢትዮጵያ ከጥንተ ታሪክ መረዳት እንደሚቻለው በህዝቦቿ ዘንድ የጦር መሣሪያ በግለሰብ ደረጃ መያዝ፤ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ መጠቀም የተለመደ ተግባር መሆኑን ካለፉ ሁኔታዎች መገንዘብ አዳጋች አይደለም። ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ በግለሰቦች እጅ በብዛት መኖሩ ኢትዮጵያን በቅርብ ጊዜት ብቻ ለበርካታ የንጹሐን ሕይወት መጥፋት የግብዓትነት ሚናውን በከፍተኛ ሁኔታ መጫወቱን ለመረዳት ይቻላል።

ሕግ ወጥ የጦር መሣሪያ በተለይም በአርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ የገጠሩ ማኅበረሰብ ዘንድ በእጅጉ ተከማችቶ እንደሚገኝ በግልጽ የሚያሳብቁ ሁኔታዎች የሚታዩት በአንድ አካባቢ ግጭቶች ሲፈጠሩ ሁሉም ከየጓዳው አውጥቶ ሲታኮስ ነው። ኢትዮጵያ ለዘመናት ተቀዳጅቷት የነበረው ሕግ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር በእጅጉ ጎልቶ የሚታየው በአንድ አካባቢ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች ሲፈጠሩ መሆኑን ለመታዘብ የሰሞኑን የሕግ ማስከበር ሥራ የተባለው የሕወሓና የፌደራል መንግስት ግጭት እንደ ዋና ማሳያነት ማንሳት ይቻላል። የሰሞኑን ግጭት ተከትሎ በመላው አገሪቱ በየዕለቱ የሕገ ወጥ ጦር መሣሪያ ዝውውር በቁጥጥር ሥር መዋል በየዕለቱ እና በየሰዓታት ልዩነት መታየት ችሏል። ይሁን እንጅ ከዚህ በፊትም ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ በገፍ ሲንሽራሽር እንደነበር ያኋላ ታሪኮችን ተመልሰን ማስታወስ በቂ ነው።

ከሰሞኑ የሕግ ማስከበር ጋር በተያያዘ በክልል ከተሞች እና በአዲስ አበባ ከተማ ከወትሮው በተለየ መልኩ በርከረት ያሉ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያዎች ከግለሰብ እስከ መሥሪያ ቤት ድረስ ተገኝተዋል።

ሕገ የማስከበር ሥራ የተጀመረው ባሳፍነው ጥቅምት 24/2013 መሆኑ የሚታወስ ነው። ታዲያ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የቁጥጥር ሥራዎች በእጅጉ ተጠናክረው በመቀጠላቸው በአዲስ አበባ ባለፉት 14 ቀናት በተካሄደ “ዘመቻ ከፅንፈኛው ህወሃት እና ኦነግ ሸኔ” ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ 287 ሰዎች ከተለያዩ የጦር መሣሪያዎች ጋር በቁጥጥር ስር ማዋሉን የኢትዮጵያ የፌዴራል ፓሊስ ባሳለፍነው ኅዳር 9/2013 ለሚዲያዎች ባሰራጨው መግለጫ አስታውቋል።

ኮሚሽኑ እነዳስታወቀው በአጠቃላይ በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች “ፅንፈኛው ህወሃት እና ከኦነግ ሸኔ” ጋር ግንኙነት አላቸው ብሎ የጠረጠራቸውን 287 ሰዎች በቁጥጥር ስር አውሎ ምርምራ እየተካሄደባቸው መሆኑን ጠቁሟል። በከተማዋ በተደረገ ብርበራ፣ ፍተሻ፣ ከኅብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ፣ በፖሊስ አሰሳ እና ከግለሰቦቹ እና ከተጠረጠሩ ተቋማት አንድ ሺሕ 32 የተለያዩ ጠመንጃዎች፣ 131 የተለያዩ ሽጉጦች እና 46 ሺሕ 39 ጥይቶች በ14 ቀናት ቁጥጥር መያዙን ኮሚሽኑ አብራርቷል። በተጨማሪም 14 ቦምቦች፣ አንድ ፈንጂ፣ አምስት ጂ ፒ ኤስ፣ ስምንት የጦር ሜዳ መነፀር፣ አምስት ካቴና፣ 55 የክላሽ መጋዘን እና እጀታ እና አንድ ሺሕ 339 የተለያዩ የመገናኛ መሣሪያዎች መያዛቸውን ኮሚሽኑ ባስራጨው መግለጫ አመላክቷል።

ከሕግ ወጥ የጦር መሣሪያዎች በተጨማሪ የተለያዩ የሠራዊት አልባሳት፣ ፓስፖርቶች፣ የውጭ አገር የሥራ ፍቃድ ሰነዶች፣ በርካታ ገንዘብ ያዙ የባንክ ደብተሮች፣ በሽጉጥ ላይ የሚገጠም የድምፅ ማፈኛ፣ የተለያዩ ኮምፒዩተሮች እና ፀረ ታንክ መሣሪያ በቁጥጥር ሥራው መያዙ ተጠቁሟል።

አንዳንድ ድርጅቶችም በሕግ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውወውር እና ክምችት ተግባር እንደተገኘባቸው ተገል ቷል። በዚህም አንድንድ ድርጅቶች ከተቋቋሙበት ዓላማ ውጭ ለአገር እና ለሕዝብ ስጋት የሆነ ተግባር ላይ መሰማራታቸው እንደተደረሰበት ነው ኮሚሽኑ የገለፀው።

ኮሚሽኑ ሕግ ወጥ የጦር መሣሪያ አገኘሁባቸው ካላቸው መስሪያ ቤቶች መካከል ሱር ኮንስትራክሽን በተባለው ድርጅት ላይ በተደረገ ሕጋዊ ብርበራና ፍተሻ ለተለያዩ ዘመቻዎች የተዘጋጁ ተሽከርካሪዎች፣ የፀሀይ ሀይል ማመንጫ፣ ተንቀሳቃሽ እና ቋሚ ወታደራዊ ሬዲዮ መገናኛዎች በህንፃው ምድር ቤት ተሸሽጎ እንዳለ መያዙን የፌዴራል ፓሊስ ኮሚሽን በመግለጫ ላይ አስታውቋል።
ሌላኛው ሕግ ወጥ ነው የተባለ የጦር መሣሪያ ተገኘበት የተባለው ወጋገን ባንክ ነው። ፖሊስ በባንኩ ዋና በሥሪያ ቤት በርከት ያ የጦር መሣሪያ አገኘሁ ቢልም ባንኩ በበኩሉ የተገኙብኝ የጦር መሣሪያዎች በሕጋዊ ሰነድ አስፈቅጀ የገዛኋቸው ናቸው ብሏል።

አዲስ አበባ ውስጥ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ በአዘዋዋሪዎች፣ በድርጅቶችና በጥቃት አድራሾች እጅ ተገኘ ከመባሉ በላይ ከዚህ ከደም ከተለመደው በተለየ ሁኔታ በየቦታው ተጥለው የሚገኙ ፈንጅ የጦር መሣሪያዎች ተበራከጅተዋል።

ኀዳር 2/2013 ከጠዋቱ ኹለት ሰዓት አካባቢ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሰባት ልዩ ቦታው አድዋ ድልድይ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ በአንድ ግለሰብ ላይ ቀላል ጉዳት እንደደረሰ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ማስታወቁ የሚታወስ ነው። በተጨማሪም ኅዳር 5/2013 በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሰባት ልዩ ቦታው በተለምዶ 02 ወይም ካፒቴን ደምሴ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ህፃናት በሚጫወቱበት ሜዳ ላይ በተጣለ የእጅ ቦንብ በአንድ የ13 ዓመት ህፃን ላይ ከፍተኛ እንዲሁም በአራቱ ላይ ቀላል የኣካል ጉዳት ማድረሱን የክፍለ ከተማው አስታውቋል።

አምስቱ ህፃናት ወድቆ ያገኙትን ቦንብ መጫወቻ መስሏቸው እኔ ልወሰድ እኔ ልውስድ በማላት ሲጓተቱ ቦንቡ የ13 ዓመት ታዳጊ በሆነው እጅ ላይ መፈንዳቱን ኃላፊው ገልፀው በታዳጊው ግራ እጅ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሲደርስ የተቀሩት አራቱ ህፃናት ቀላል ጉዳት እንደደረሰባቸው አስረድተዋል።
ሕግ የማስከበር ሥራ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በአንዳንድ ክልሎች የተያዙ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያዎችን ብንመለከት ጥቅምት 28 /2013 በደቡብ ክልል በተለያዩ ዞኖች በሕገወጥ ሲዘዋወር የነበረ የጦር መሣሪያ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቆ ነበር።፡ በኹለት ቀናት ብቻ በደቡብ ኦሞ፣ ካፋ፣ ኮንሶና ሸካ ዞኖች በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ 25 ክላሽንኮቭ ጠመንጃ፣ አራት ሽጉጦችና 11 ተተኳሽ ጥይቶች ተይዘዋል።

በጋምቤላ ክልል ዲማ ወረዳ በሕገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ 5 ክላሽንኮቭ የጦር መሣሪያ እና አንድ ኤፍ አንድ የእጅ ቦንብ ከስድስት ተጠርጣሪ ጋር መያዙን ፖሊስ ማስታወቁ የሚታወስ ነው። የጦር መሣሪያው በያዝነው ኅዳር ወር የመጀመሪያ ሳምንት ከደቡብ ሱዳን ድንበር ወደ ዲማ ወረዳ በማስገባት ሊሸጥ ሲል ነው በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ተጠቁሞ አልፏል።

በአሮሚያ ክልልም እንዲሁ በርካታ ሕግ ወጥ የጦር በሣሪያዎች ተይዘዋል። እነደ ማሳያነት ጅማን ብናይ፣ በጅማ በሰባት ቀናት ውስጥ በርካታ ቁጥራቸው ያልጠገለጸ የጦር መሣሪያዎች መያዛቸውን የኦሮሚ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል። በክልሉ ከኦነግ ሽኔ ታጣቂ ቡድን ጋር በርካታ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ መያዙን የክለሉ ፖሊስ ሰሞኑን ማስታወቁ የሚታወስ ነው።

በነዚህ ወር ባልሞሉ ቀናት ውስጥ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ በርካታ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያዎች በጥፋት ኃይሎች በተባሉ አካላትና ድርጅቶች መገኘታቸውና ሕዝብ በሚበዛባቸው አደባባዮች ተጥለው የሚገኙ ፈንጅ የጦር መሣሪያዎች አንደምታቸው ምን ይሆን?

በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ሰሞኑን በእጅጉ የተጋነነው ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ በተመረጡ የክልል ከተሞችና በአዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ ጥቃት ለማድረስ የተዘጋጁ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ማርቆስ ፋንታ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል። ኮማንደሩ አክለውም አሁን ላይ በፌደራል መንግሥትና ሕገ ወጥ ከተባለው ህወሃት ጋር በተገባው ግጭት ምክንያት ባልታሰቡ ቦታዎች ጥቃት ለማድረስ የታለሙ የጦር መሣሪያዎች ናቸው ይላሉ።

እንደ ኮማንደሩ ገለጻ በቁጥጥር ሥር እየዋሉ የሚገኙ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያዎች አስቀድመው ጥቃት ለማድረስ ሥልጠና በወሰዱ ግለሰቦች መሆኑ በተገኙ ግኝቶች ማረጋገጥ እንደተቻለ ያነሳሉ። አስቀድመው ሥልጠና በመውስድ ጥቃት ለማድረስ ታጥቀው በተለያየ መንገድ አዲስ አበባ ከተማ በመግባት ሕዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ጥቃት ለመፈጸም በሚዘጋጁበት ጊዜ በኅብረተሰቡ ጥቆማ የተያዙ መሆኑም የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አስታውቋል።

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሕገ ወጥ መንገድ በግለሰቦች እጅ የተገኙ የጦር መሣሪያዎች በፍጹም ከመከላከያ ኃይል ውጭ በማንኛውም ግለሰብ እጅ ሊገኙ የማይችሉ መሣሪያዎች መያዛቸውን የጠቆሙት ኮማንደር ፋሲካ በከፍተኛ ዝግጅት ሕዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች፣ ሕዝብ በብዛት ተከማችቶ በሚኖርባቸው ኮንዶሚንየምና በባለሥልጣናት መሥሪያ ቤት ላይ ጥቃቱን ለመሰንዘር የተዘጋጁ መሣሪያዎች እንደነበሩ አንስተዋል።

በሌላ በኩል በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ቦታዎች ተጥለው ጉዳት ያደረሱ እና በኅብረተሰቡ ጥቆማ ጉዳት ሳያደርሱ የተያዙት በሕዝብ እና በባለሥልጣናት ላይ አጥቂዎች ሊደርሱት ያቀዱት ጥፋት ምቹ ሁኔታዎችን በማጣታቸው መሆኑን ኮማንደሩ ይገልጻሉ። በዚህም ሕዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ላይ ከቆሻሻ ጋር አስመስሎ መጣል አማራጭ የጥቃት ስልት አድርገው በመውሰዳቸው እንደሆነ አብራርተዋል።

ጠቅላይ አቃቢ ሕግ በበኩሉ እነዚህ ተጥለው የተገኙ የጦር መሣሪያዎች በኅብረተሰቡ ጥቆማ መሰረት እየተደረሰባቸው በመሆኑ ከተጠያቂነት ለማምለጥ የተጣሉ ጭምር መሆናቸውን ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል። የጠቅላይ አቃቢ ሕግ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አወል ሱልጣን ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት ከሆነ የትግራይ ክልል መንግሥት ሕገ መንግሥቱን በመጣስ እያደረገ ባለው ተግባር መንግሥት ሕግ የማስከበር ሥራ በመጀመሩ በርካታ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያዎች ለጥቃት መፈጸሚያ ሲዘጋጁ ከነ ተጠርጣሪዎቻቸው መያዛቸውን ጠቁመዋል። የተያዙት የጦር መሣሪያዎች ከዚህ ከደም የመከላከያ አባል የነበሩና እስካሁንም በመከላከያ ኃይል ውስጥ የነበሩ አባላት በቤታቸው ፍቃድ የሌላቸው ከኹለት በላይ ጦር መሣሪያዎች ተገኝተዋል ብለዋል።

አወል እንደሚሉት ከሆነ በዚህ ጉዳይ ላይ ተጠርጥረው ቤታቸው የተፈተሸ ግለሰቦች በቤታቸው በግለሰብ ደረጃ ሊገኝ የማይችል የጦረፍ መሣሪያ እና ከኹለት በላይ ሽጉጥና ክላሾች ተገኝተዋል ብለዋል። እነዚህ የጦር መሣሪያዎች በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ምንም በሌለበት ሰላማዊ ሁኔታ መገኘታቸው እና ካላቸው የአገልግሎት ተግባር አንጻር ለጦርነት የተዘጋጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በሕገ ወጥ መንገድ በግለሰቦች እጅ የተገኙት የጦር መሣሪያዎች ከመያዛቸው በዘለለ የጥቃት ዝግጅቶችን ከመደገፍ ጋር በቀጥታ የተገናኘ መሆኑን አወል ያስረዳሉ። በመቶዎች የሚቆጠሩ የጦር መሣሪያዎች በሕገ ወጥ መንገድ በግለሰብ እጅ ገብተው ፍተሻዎች ሲጠናከሩ ለሰወር ተብሎ ተጥለው በገኘታቸውን የጠቆሙት አወል በኅብረተሰቡ ጥቆማ ማስርጃ በማሰባሰብ ግለሰቦቹ ተጠያቂ እንደሚሆኑ ጠቁመዋል።

በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ እየተገኙ ያሉ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያዎችና አዘዋዋሪዎቻቸው ያላቸውን አንደምታ ለጦርነት በሚባል ደረጃ የተደራጁ እንደነበሩ አወል ገልጸዋል። የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ በበኩላቸው አዲስ አበባ ላይ ያለው የጦር መሣሪያ ወድቆ መገኘት እና ለጥፋት በተዘጋጁ ግለሰቦች ስር አሁንም እንደሚኖር ጠቁመዋል። ኃላፊው አንደጠቆሙት ከሆነ አዲስ አበባ ላይ አሁንም ሰሞኑን ከታዩት ዘንባሌዎች ሙሉ በሙሉ ነጻ የሆነ እንዳልሆነ በመጥቀስ ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሻ አመላክተዋል።

አሁንም ድረስ በአዲስ አበባ ችግር ለመፍተር እየተሠራ መሆኑም ያመላከቱት ኮማንደር ፋሲካ ኅብረተሰቡ የከተማዋ ሰላም ለማስጠበቅና ከጥቃት ለመዳን በትኩረት አካባቢውን ከጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር መጠበቅ አንደሚገባወው አሳስበዋል።

የሕገ ወጥ የጦር መሣሪያዎቹ ባለቤቶችን የሕግ ተጠያቂነት በተመለከተ አስካሁን በተለያዩ ከተሞች ጥቃት ለመፈጸም በዝግጅት ላይ እንዳለኩ ከነ ጦር መሣሪያቸው የተያዙና ወደፊትም የሚያዙ አካላት ላይ በጦር መሣሪያ አስተዳደር አዋጅ መሰረት ተጠያቂ እንሚሆኑ አወል ገልጸዋል። ተጠያቂነቱ ከሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር የዘለለ እንሚሆን የገለጹት አወል ተገቢ የሆኑ ማስረጃዎችን በማሰባሰብ በጸረ ሽብር እና ወንጀል ነክ አዋጆች እነደሚታይ ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ባሳለፍነው 2012 “የጦር መሣሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ” በሚል በአዋጅ ቁጥር 1177/2012 አጽድቃ ተግባራዊ በማድረግ ላይ ትገኛለች። አዋጁ የጦር መሣሪያን በተመለከተ ራሱን የቻለ ሕግ ሆኖ በመውጣቱና የፈቃድ አሰጣጥ እንዲሁም አስተዳደር ጉዳዮችን ከተቋማዊ ተግባር እና ኃላፊነቶች ጋር በዝርዝር ያካተተ ነው። አዋጁ በቀዳሚነት የጦር መሣሪያ ቁጥጥር የአገርንና የሕዝብን ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ እንዲሁም የዜጎችንና የሕዝቦችን መብትና ደህንነት ለማስከበር አስፈላጊ መሆኑን በአጽንኦት ያስገነዝባል።

አዲሱ ሕግ የተከለከሉ ተግባራትን በዝርዝር አስቀምጧል። በዚሁ መሰረት ማንኛውም ሰው የፀና ፈቃድ ሳይኖረው የጦር መሣሪያ፣ በጦር መሣሪያው ላይ ሊገጠም የሚችል ማንኛውንም ዓይነት መነፅር ወይም የጦር መሣሪያ ሲተኮስ ድምጽ ለማስወገድ የሚያገለግል መሣሪያ ወደ አገር ማስገባት፣ ማስወጣት፣ መያዝ፣ ማስቀመጥ፣ ማከማቸት፣ መገልገል፣ ማሳየት፣ መደለል፣ መሸጥ፣ መግዛት፣ ማስተላለፍ፣ ማዘዋወር፣ ማጓጓዝ፣ ማምረት፣ ማሰልጠን፣ መጠገን ወይም ማስወገድ እነደማይችል ተደንግጓል።

ይህ ድርጊት በአንድ የጦር መሣሪያ ከተፈጸመ ከአንድ እስከ ሦስት ዓመት ቀላል እስራት እና ከአምስት እስከ አስር ሺሕ ብር እንደሚያስቀጣ አዋጁ ደንግጓል። ኹለት እና ከዚያ በላይ በሆኑ የጦር መሣሪያዎች ከተፈጸመ ደግሞ ከስምንት እስከ ሃያ(20) ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራትና ከአንድ መቶ እስከ ኹለት መቶ ሺሕ ብር ያስቀጣል ይላል።

ቅጽ 2 ቁጥር 107 ኅዳር 12 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here