የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለቀረበለት ረቂቅ አዋጅ ምላሽ አልሰጠም

0
687

ጉዳዩን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአካል ቀርበው ወይም በጽሑፍ እንዲያስረዱ ተጠይቋል

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ቤት የዱር እንሰሳት ልማት፣ ጥበቃና አጠቃቀም አዋጅ ለማሻሻል ለቀረበለት ረቂቅ ምላሽ አለመስጠቱን የኢትዮጵያ የዱር እንሰሳትና ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን የዱር እንሰሳት ልማት፣ ጥበቃና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 541/1999ን ለማሻሻል ረቂቅ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ካቀረበ ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ ቢሆነውም እስካሁን ድረስ ምላሽ አለመሰጠቱን የባለሥልጣኑ የሕግ ጉዳይ ዳይሬክተር ምትኩ ገ/ሚካኤል ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ዳይሬክተሩ ለአዲስ ማለዳ እንዳስረዱት ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ አዋጅ ቁጥር 541/1999ን ለማሻሻል ያዘጋጀውን ረቂቅ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት 32 ቅጅ አንዲያቀርብ ተጠይቆ ቅጅውን ማስተላለፉን አስታውሰዋል። ዳይሬክተሩ አክለውም የኢትዮጵያ ዱር እንሰሳት ልማት እና ጥበቃ ባለሥልጣን ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ያቀረበው የማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ላይ የተሰጠው ምላሽ ባለመኖሩ፣ ባለፈው የካቲት 24/2012 ለጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የረቂቁን ቅጅ እንደሰጠ በተላለፈለት መልዕክት መሰረት ቅጅውን ያስተላለፈ ቢሆንም ምላሽ አለማግኘቱን መግለጹን አዲስ ማለዳ ለማወቅ ችላለች።

ባለሥልጣኑ ለጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ያቀረበው የጽሑፍ ደብዳቤ ሥልጣን እና ኃላፊነቱን በተገቢው ለመከወን አስፈላጊ ነው የተባለው ረቂቅ ማሻሻያ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ እንዲጸድቅለት መሆኑም ተመላክቷል። ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ የካቲት 24/2012 በጽሑፍ ደብዳቤ ለቀረበለት ጥያቄ አስካሁን ምላሽ አለመስጠቱን ለማወቅ ተችሏል።

ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ አዋጅ ቁጥር 541/1999ኝን ለማሻሻል ያዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ባለሥልጣኑ ከተሰጠው ሥልጣን እና ኃላፊነት አንጻር መስራት የሚጠበቅበትን ሥራ ለመስራት የቀድሞው አዋጅ እንቅፋት ስለሆነበት መሆኑ ተመላክቷል። የባለሥልጣኑ የሕግ ጉዳይ ዳይሬክተር ምትኩ እንደሚሉት አሁን ባለሥልጣኑ የሚጠቀምበት የዱር እንሰሳት ልማት፣ ጥበቃና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 541/1999 ዋና ዓላማ እና የትርጉም ችግር ስላለበት ባለሥልጣኑን የሚገባውን ያክል እየሰራ እንዳልሆነ የሚሳዩ ጥያቄዎች እያስነሳበት ነው ብለዋል።

ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የ2013 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ለኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና፣ አርበቶ አደር እና አካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያሳለፍነው ረቡዕ ኅዳር 9/2013 አቅርቧል። ባለስልጣኑ አፈጻጸሙን ባቀረበበት ጊዜ ቋሚ ኮሚቴው ችግሩን ተረድቶ ረቂቅ ማሻሸያ አዋጁ እንዲጸድቅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ግፊት እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል።

የረቂቅ አዋጁ መዘግየት ባለስልጣኑ አልፈጸማቸውም ለተባሉት ክፍተቶች የአዋጁ ክፍተት እንዳስቸገረው ለቋሚ ኮሚቴው ባስረዳበት ጊዜ የቋሚ ኮሚቴ አባላትም የባለሥልጣኑን ሐሳብ በመጋራት ረቂቁ ታይቶ ክፍተቶቹ እንዲታረሙ አሳስበዋል። ቋሚ ኮሚቴው በሚከታተላቸው መስሪያ ቤቶች በኩል ለሚኒስትሮች ምክርት ቤት የሚቀርቡ ረቂቅ አዋጆች መዘግየት እና ምላሽ ማጣት በተደጋጋሚ እየታየ መሆኑን በማንሳት ጠቅላይ ሚኒስቴሩ በጉዳዩ ላይ በአካል ተገኝተው ወይም በጽሑፍ ጉዳዩን ያስረዱ ሲሉ ተደምጠዋል።

በረቂቅ ደረጃ ከተዘጋጀ አንድ ዓመት ከግማሽ ሆኖታል የተባለው አዋጅ በሚጽድቅበት ጊዜ አሁን በሥራ ላይ ባለው አዋጅ ቁጥር 541/1999 ላይ የሚታዩ የትርጉም ችግሮችን፣ የዓላማ ግልጸኝነት እና መጣጣም፣ ኢትዮጵያ ከፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ የዱር አንሰሳት ጥበቃ ሕጎች ጋር የሚጣጣም፣ በፓርኮች አካባቢ የሚኖሩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ከፓርኮች ገቢ በቀጥታ ተጠቃሚ የሚደርግ መሆኑን ምትኩ ጠቁመዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 107 ኅዳር 12 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here