0
682

በአዲስ አበባ የተለያዩ ጥቃቶችን ለመፈፀም እና ፀጥታን ለማደፍረስ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ከ700 በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለፀ

የሕወሓትን ተልዕኮ ተቀብለው በአዲስ አበባ የተለያዩ ጥቃቶችን ለመፈፀም እና የፀጥታ መደፍረስ እንዲከሰት አቅደው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ከ700 በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

በሰሜን ዕዝ የሀገር መከላከያ ሰራዊታችን ላይ ሀገሩን በካደው የህወሃት ጁንታ ቡድን የተፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ መንግስት እየወሰደ ባለው ህግን የማስከበር እና የህልውና ዘመቻ በተለያዩ የሃገራችን አካባቢዎች የታሰቡ የጥፋ ሴራዎች በህብረተሰቡ እና በፀጥታ አካላት ትብብር መምከናቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡

ቡድኑ ላለፉት 27 አመታት የዘረጋውን የግንኙነት መረብ ተጠቅሞ በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ሊፈፅም ያሰበው የሽብር ጥቃት እንዳይሳካ ከጥቅምት 25 ቀን 2013 ዓ/ም ጀምሮ በተደረገ ጠንካራ የክትትል እና የቁጥጥር ስራ ከከሃዲው የህወሃት ጁንታ ተልዕኮ ተቀብለው የተለያዩ ጥቃቶችን ለመፈፀም እና የፀጥታ መደፍረስ እንዲከሰት አቅደው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 796 ተጠርጣሪዎች ፣ በርካታ የጦር መሳሪዎች እና ሌሎች ቁሳቁሶች በፍርድ ቤት የመበርበሪያ እና የመያዣ ትዕዛዝ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የልዩ ልዩ ህገ- ወጥ ዝውውር ወንጀሎች ምርመራ ዳይሬክተር ኮማንደር ግርማ ተሰማ አስታውቀዋል፡፡

በተለያዩ የሃገራችን አካባቢዎች የሚፈፀሙ ጥቃቶች እና የሚከሰቱ ግጭቶች በሕወሃት ፊት አውራሪነት እና ድጋፊ ሰጪነት የሚፈፀሙ ስለመሆናቸው የሚያረጋግጡ እና ሃይማኖትን ከሃይማኖት፣ ብሄርን ከብሄር ለማጋጨት የተዘጋጁ ሰነዶች በብርበራ ወቅት መገኘታቸውን ኮማንደር ግርማ ተሰማ አስረድተዋል፡፡

የፀጥታ አካላትን የደንብ ልብስ በመልበስ ጭምር የጁንታውን ቡድን ተልዕኮ በአዲስ አበባም ለማስፈፀም ሲንቀሳቀሱ እና ዝግጅት ሲያደርጉ የነበሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ያስታወሱት ኮማንደር ግርማ በተለያዩ ግለሰቦች መኖሪያ ቤት እና በልዩ ልዩ ተቋማት ውስጥ በተደረገ ፍተሻ 202 የተለያዩ የፀጥታ አካላት የደንብ አልባሳት መያዛቸውን ገልፀዋል፡፡

የደንብ አልባሳቶቹ በሃይማኖት አባቶች መኖሪያ ቤቶች ጭምር መገኘታቸውን የጠቀሱት ኮማንደር ግርማ ይህ ደግሞ ህገወጡ እና ከሃዲው የህወሃት ቡድን በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ ሳይቀር ሰርጎ በመግባት ግጭት ለመቀስቀስ እየተንቀሳቀሰ አንደሚገኝ የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እስካሁን ለተገኘው ውጤት የህብረተሰቡ ተሳትፎ የጎላ ሚና እንደነበረው ያስታወሱት ኮማንደር ግርማ ተሰማ አዲስ አበባ ላይ ጀምረን አዲስ አበባ ላይ እንጨርሰዋለን በሚል ከንቱ ምኞት ላይ ታች ሲሉ ህልማቸው የመከነባቸው የጥፋት ቡድኖች ምንም አይነት ቀዳዳ እንዳይኖራቸው እና በተለያዩ ተቋማት እና አካባቢዎች ተሰግስገው የሚገኙ ሌሎች የጥፋት መልዕክተኞችን በቁጥጥር ስር ለማዋል በሚደረገው ጥረት የህብረተሰቡ ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here