በአዲስ አበባ የኤሌክትሪክ አውቶብስ የሙከራ ትግበራ ሊደረግ ነው

0
918

በአዲስ አበባ ከተማ የኤሌክትሪክ አውቶብስ የሙከራ ትግበራ ለማድረግ የዝግጅት ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸው ታውቋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ የፋይናንስ እና የቴክኒካል ድጋፍ ለማግኘት ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር እየሠራ እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን በዚህም የኤሌክትሪክ አውቶብስ በከተማው ላይ የሙከራ ትግበራ ለማከናወን ተቀማጭነቱ እንግሊዝ አገር ካደረገው ሲ40 ሲቲስ ጋር በቅንጅት በመሥራት ላይ ይገኛል ተብሏል።
ቢሮው ከሲ40 ሲቲስ ጋር በመተባበርም የኤሌክትሪክ አውቶብስ የሙከራ ትግበራ በከተማዋ ፈጣን አውቶብስ ኮሪደር ላይ እንዴት እንደሚተገበር አለም አቀፋዊ የኹለት ቀናት የቪዲዮ ኮንፈረንስ አውደ ጥናት አካሂዷል።
በአውደ ጥናቱ ላይ ከተለያዩ የመንግሥት፣ የግል፣ የምርምር ተቋማት፣ የአውቶቡስ አምራቾች እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የተሳተፉ ሲሆን፤ ተሳታፊዎች በቴክኖሎጂ፣ በፋይናንስ፣ በፖሊሲ፣ በመረጃ አሰባሰብ እና በባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ዙሪያ ውይይት አድርገዋል፡፡
በተጨማሪም ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶችን ለይተው የመፍትሔ አቅጣጫ ያስቀመጡ ሲሆን፤ በፕሮጀክቱ ቀጣይ መረሃ ግብሮች ላይ ምክክር አካሂደዋል፡፡
የአዲስ አበባ መስተዳድር እና የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የተለያዩ የመፍትሄ ሐሳቦችን ተግባራዊ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል።
በመሪ እቅዱ ላይ የተቀመጡ የከተማ ፈጣን አውቶብስ ኮሪደሮች የማልማት ሥራዎችን በማከናወን ለችግሩ የመፍትሄ አካል የሆኑትን የከተማ ፈጣን አውቶብስ የሚጠቀምባቸውን በናፍጣ የሚሠሩ እና ሌሎቹን አውቶቡሶች በቀጣይ ወደ ኤሌክትሪክ የመቀየር እቅድ አንዱ ነው፡፡

ቅጽ 2 ቁጥር 108 ኅዳር 19 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here