መቐለ – የመጨረሻው መጨረሻ!?

0
720

መንግሥት፥ ሕወሓት ቅጽበታዊ ያለውን የጥቅምት 24ቱን የሰሜን ዕዝ ጥቃት ተከትሎ በማያዳግም መልኩ ምላሽ መስጠት በጀመረው ዘመቻ በአብዛኛው ትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኙ ከተሞችን ይህ ነው የሚባል ተግዳሮት ሳይገጥመው በቁጥጥር ሥር እያዋለ መጥቶ መቐለን በ50 ኪሎ ሜትር ቀለበት ውስጥ ካስገባ ቀናት ተቆጥረዋል።

መንግሥትም የንጹሃን እልቂትን ለማስወግ የመጨረሻ ያለውን መቐለ ለመሸጉት የሕወሓት ባለሥልጣናት እንዲሁም የሚሊሻና የልዩ ኀይል አባላት በ72 ሰዓታት ውስጥ የእጃቸውን እንዲሰጡ የሰጠው ዕድል ባለፈው ረቡዕ፣ ኅዳር 16 ተጠናቋል። በሺሕዎች የሚቆጠሩ ሚሊሻና ልዩ ኀይል አባላት በሰላም እጅ መስጠታቸውን በቴሌቪዥን ምስል በማስደገፍ ከቀረቡት ዘገባዎች በዘዘለ ከአመራሮቹ አንዱም እጅ ሲሰጡ አልታዩም።

በነጋታው ኀሙስ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የዘመቻው ኹለተኛ ምዕራፍ ተጠናቆ የመጨረሻው ወሳኝ ሦስተኛ ምዕራፍ መጀመሩን አስታውቀዋል። ሰብኣዊ እልቂትን በቀነሰ፣ ቤተ እምነቶችና ቅርሶችን ለጉዳት ባላጋለጠና የመቐለ ከተማን ከውድመት በሚታደግ የሕግ ማስከበር ዘመቻው ፍፃሜ እንደሚያገኝ ጨምረው ገልጸዋል።
ብዙዎች ዘመቻው የከተማ ውስጥ እንደሚካሄድ እንዲሁም የሕወሓት አመራር ወሳኝ ይዞታ ከመሆኑ አንጻር የሞት ሽረት ትግል ይካሄድበታል፤ በውጤቱም ከፍተኛ ሰብኣዊና ቁሳዊ እቂት ሊፈጸም ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን አጋርተዋል። አንዳንዶች የሕወሓት አመራሮች የከተማውን ሰላማዊ ነዋሪዎች እንደ ሰብኣዊ ጋሻ ከመጠቀም ወደ ኋላ እንደማይሉ የእስከዛሬ አካሄዳቸውን ምስክር ነው ሲሉ ስጋቱን አጠናክረዋል።

የበለጠ ይህንን ስጋት የሚያንረው ደግሞ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንን ጨምሮ ሌሎች የመንግሥት አካላት ሕወሓት በመቐለ ልክ እንደማይካድራው ዘርን መሰረት ያደረገ እልቂት በልዩ ኀይሉ፣ በሚሊሻው እና ባደራጃቸው ወጣቶች ለመፈጸም መዘጋጀቱን ገልጸዋል። ዓላማውም በመላው አገሪቱ ዘርን ማዕከል ያደረገ ግጭት መለኮሻ ክብሪት እንዲሆን ያለመ ነው ሲሉም የጉዳዩን አሳሳቢነት አስምረውበታል። ይሁንና በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ያቀረቡትን ጥሪ መሰረት አድርገው የመከላከያ ሠራዎቱ ከተቀላቀሉት መካከል አንዱ የሆኑት ሌተናል ጀነራል ባጫ ደበሌ ከጦር ግንባር አስተላለፉት በተባለው መልዕክት “የዘገየነው ሞትን ፈርተን ሳይሆን ጉዳት ለመቀነስ ነው” በማለት በተጠና ሁኔታ እርምጃ በመውሰድ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከተማውን እንቆጣጠራለን ሲሉ እርግጠኝት በተሞላበት መንፈስ መግለጻቸው ተዘግቧል።

መንግሥት የሕወሓት አመራሮች በመቐለ የት የት እንደመሸጉ ያውቃል የሚለውም ዜና በከፍተኛ ፍጥነት መነጋገሪያ ሲሆን ብዙዎች እያጋሩት ይገኛሉ። በከተማው የተለያዩ ቦታዎች ተበታትነው የተሸሸጉ ሲሆን የተመረጡት ደግሞ ቤተ እምነቶች እና ብዙ ነዋሪዎች ያሉበት አካባቢዎች መሆኑም ተጠቁሟል። አመራሩ ለደኅንነቱ ሲልም በወታደራዊ ሬዲዮ ብቻ ግንኙነት ያደርጋል፤ ትዕዛዝም ያስተላልፋል።

በሌላ በኩል ደግሞ የመቐለ መያዝ የሁሉ ነገር ፍፃሜ ነው ማለት አይደለም ሲሉ ጉዳዩ ተቃሎ መቅረብ የለበትም የሚሉ ወገኖችም ድምጽ እየተሰማ ነው። የሕወሓት በተለይ የላይኛው አመራር ጣጣ እንዲህ በቀላሉ የሚለቅ አይደልም፤ እጀ ረጅም መሆኑም መዘንጋት የለበትም ሲሉ አጽንዖት ይሰጣሉ። ይህንን ሐሳባቸውን በማስረጃ ለማጠናከር በሥም የተጠቀሱ ሦስት የሕወሓት አመራሮች – አቦይ ስብሃት ነጋ፣ አባይ ጸሐዬ እና ኬሪያ ኢብራሒም – በአፋር፣ በረሃሌ ወረዳ በኩል ለማስመለጥ ሴራ መሸረቡን ያነሳሉ። ሴራውም ሲገለጥ የመከላከያን ዘመቻ በመቃወም ወጣቶችን አነሳስቶ ብጥብጥ በማስነሳት እንደሽፋን በመጠቀም አመራሮቹን በማሹለክ ከአገር እንዲወጡ ማድረግ እንደሆነ ይናገራሉ። ለዚህም ተልዕኮ ሁነኛ ነው ለተባለ የጎሳ መሪ በቁጥር ያልተገለጸ፣ በርካታ ረብጣ ብርም አስታቅፈውታል ተብሏል።

የተጠቀሱት አመራሮች ከአገር መውጣት አንድምታው ተስፋ ለቆረጠው ደጋፊ ትልቅ ብታት ሲሆን በውጪ ለሚገኘው ደግሞ እንደ አዲስ ኀይሉን እንዲያሰባስብና እንዲደራጅ ሁኔታዎችን ያመቻቻል። ከዚህም ባሻገር መንግሥት በአጭር ጊዜ የሚጠናቀቅ የሕግ ማስከበር እርምጃ ነው ያለው ወደ ተራዘመ የእርስበርስ ጦርነትም ሊያስገባ ይችላል የሚል የቢሆን መላምት እንዲኖር አድርጓል።

የሆነው ሆኖ የመጨረሻ የተባለው ሦስተኛው ምዕራፍ የሕግ የማስከበር እርምጃ ውጤቱ ምን ይሆን? የሕወሓት መደምሰስ ትዕምርት የብሔር አራማጅ የፖለቲካ የመጨረሻ እስትንፍስ በመሆን ኢትዮጵያ ወደ አዲስ የፖለቲካ መስመር እንድትገባ ጥርጊያውን ያመቻቻል? በኀይልስ ማስገበር ይቻላል? የብሔር ፖለቲካ እንደ አዲስ አፈር ልሶ፣ ነብስ ዘርቶ ያብብ፣ ይጎመራ ይሆን? ብዙ ተስፋዎች ያሉትን ያክል፤ ብዙ ተስፍ አስቆራጭ ሁኔታዎች እንዳሉ ግን ብዙዎችን ያስማማል። ለሁሉም ላልተመለሱ ጥያቄዎችም ሆነ መላምቶች ጊዜ ምላሽ ይሰጣል።

ቅጽ 2 ቁጥር 108 ኅዳር 19 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here