“የ1952ቱ የንግድ ሕግ ከዓለም የንግድ ድርጅት አባል ከመሆን ሊያግድ ይችላል”

0
1067

መላኩ አለበል የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር

ኢትዮጵያ ላለፉት 60 ዓመታት የተጠቀመችበት የንግድ ሕግ በ1952 የተዘጋጀ በመሆኑ ከአሁኑ የዓለም የንግድ እድገት ደረጃ ጋር ስለማይጣጣም ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት ዓባል ለመሆን የጀመረችውን ሥራ ሊያግድ እንደሚችል የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መላኩ አለበል ለአዲስ ማለዳ አስታወቁ።

የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የዓለም አገራት የደረሱበትን ዘመናዊ የንግድ ስርዓት ለመከተል ኢትዮጵያ በረቂቅ ደረጃ የተዘጋጀውን የንግድ ሕግ ማጽደቋ ወሳኝ መሆኑን ሚኒስቴሩ ጠቁመዋል። በ1952 የወጣው የኢትዮጵያ የንግድ ሕግ ኢትዮጵያ የጀመረችውን የዓለም የንግድ ድርጅት ዓባልነት ሂደት ከማገዱ በተጨማሪ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ የንግድ ስርዓቶችን ተከትሎ የገብያ ትስስር ከመፍጠር ያግዳል ብለዋል።

“የንግድ ሕግ ከሕገ መንግሥት ቀጥሎ ትልቅ ሕግ ነው” ሲሉ የገለጹት ሚኒስቴሩ ኢትዮጵያ ለጀመረችው የምጣኔ ሀብት ለውጥ አዲሱ ረቂቅ የንግድ ሕግ ማሻሻያ በሕግ የተደገፈ እንዲሆን ያደርገዋል ብለዋል። እንዲሁም አሁን ላይ በፍጥነት እየገሰገስ የሚገኘው የዓለም ዘመናዊ የንግድ ስርዓት በኢትዮጵያ ተግባራዊ በማድረግ የሥራ ዕድል ፈጠራን ለማሰፋፋት አበረታች ሕግ ነው ብለውታል ሚኒስቴሩ።

ኢትዮጵያ የጀመረችው የዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት ሂደት ድንገት ተከስቶ በዓለም ላይ በርካታ ሁኔታዎችን የቀየረው ኮቪድ-19 በሂደት ላይ የነበረውን ቅድመ ዝግጅት እንዲዘገይ እንዳደረገው ሚኒስቴሩ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል አገር የምትሆን ከሆነ አዋጭ በሆኑ ዘርፎች ላይ የገብያ ትስስር እንደምታገኝ የጠቆሙት ሚኒስቴሩ ዓለም አቀፍ ተደራሽነትን ለማሳለጥ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው አብራርተዋል። የኢትዮጵያ የንግድ ስርዓት የሻጭ ገብያ ዝንባሌ የተከተለ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስቴሩ የገብያ ትስስር በስፋት በሚፈጠርበት የንግድ ሥርዓት የሻጭ የበላይነት ወደ ሽማች የበላይነት እንደሚቀየር ተናግረዋል። ይህም ለገብያ ፍለጋ የተገናኙ ሻጮች ሸማቹ በሚፈልገው ሁኔታ ተወዳድረው እንዲያቀርቡ ያግዛል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን በሂደት ላይ መሆኗን የጠቆመት ሚኒስቴሩ በረቂቅ ደረጃ የተዘጋጀው የኢትዮጵያ የንግድ ሕግ አሁን ላይ ዓለም የደረሰበትን የንግድ ዘመናዊነት መሰረት ያደረገና ወደፊትም በሰፊው ዘመናዊ የንግድ ሥርዓት ለመከተል ያለመ ነው ብለዋል።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት ዓባል በመሆኗ የተወዳዳሪነት አቅም ውስንነት ሊጋጥም እንደሚችል ሚኒስቴሩ ሥጋታቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። ለዚህም ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ሥትሆን የምታቀርባቸውን ምርቶች በቅድሚያ አዋጭ የሆኑትን በመለየት እንደምታካትት ሚኒስቴሩ ጠቁመዋል።
በ1952 የወጣው የኢትዮጵያ የንግድ ሕግ ከዘመኑ የኢትዮጵያ ዕድገት ደረጃ አኳያ ሲታይ ከጊዜው በእጅጉ የቀደመ ቢሆንም ሕጉ ሲወጣ እንዲያገለግል የተያዘለት ከፍተኛ 50 ዓመት መሆኑን ያስታወሱት በጠቅላይ አቃቢ ሕግ የሕግ ጥናት እና ዝግጅት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በላይሁን ይርጋ ናቸው። ዳይሬክተሩ እንደሚሉት ዘመናዊ የንግድ ሕግ ለኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ አስፈላጊ ነው ብለዋል። ዘመናዊ የንግድ ሥርዓት ለመከተል ዘመናዊ የንግድ ሕግ አስፈላጊ መሆኑንም ዳይሬክተሩ አክለዋል።

ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን አሁን በረቂቅ ላይ የሚገኘው የንግድ ሕግ አንድ እራሱን የቻለ መስፈርት መሆኑን ጠበቃና የሕግ አማካሪ መታሰቢያ ሀይሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። መታሰቢያ የንግድ ሚኒስቴሩን ሀሳብ በመጋራት የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ዘመናዊ እና ከዓለም አገራት ጋር የሚጣጣም የንግድ ሕግ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

አማካሪው አንደሚሉት የዓለም የንግድ ድርጀት ዓባል ለመሆን ኢትዮጵያ ከንግድ ሕግ ማሻሻያ በተጨማሪ ሌሎች መሰረታዊ የቀድሞ ሕጎችን ማሻሻል ይጠበቅባታል ይላሉ። እስካሁን የተደረጉ የኢንቨስትመንት አዋጅና የደረጃ ምደባ ማሻሻያዎች የዓአባልነት ሂደቱን ያፋጥኑታል ብለዋል አማካሪው። ይበልጥ ሂደቱ እንዲፋጠን ለማድረግ ደግሞ በሂደት ላይ የሚገኙ የሕግ መሻሻያዎችን በፍጥነት ማጽደቅ እንደሚገባ አመላክተዋል።
አዲሱ የንግድ ሕግ የነጋዴዎቸን፣ የባለሀብቶችን እና በሕጉ ጥቅማቸው በቀጥታ የሚነካ ባለ ድርሻ አካላት
መብቶችን በሚዛናዊ ሁኔታ ለማስተናገድ፣ የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት በማረጋገጥ
የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን ለማስፋፋት ብሎም የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ለማሳደግ የንግድ ሕጉን
ዘመናዊ ማድረግ የግድ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱ በረቂቁ ሕጉ በግቢያ ላይ ተብራርቷል።

ቅጽ 2 ቁጥር 108 ኅዳር 19 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here