ቡና ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር የሕይወት መድን አገልግሎት ለመጀመር መሰረታዊ ሥራዎችን ማጠናቀቁን አስታወቀ።
ኢንሹራንሱ ከተመሰረተ ስድስተኛ ዓመቱን አጠናቆ ሰባተኛ ዓመት ባስቆጠረበት በተያዘው 2013 በጀት ዓመት የሕይወት መድን አገልግሎት ለመስጠት ባለፈው 2012 በጀት ዓመት አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎችን ሲከናውን መቆየቱን የኢንሹራንሱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዳኛቸው መሃሪ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።
ዋና ሥራ አስፈጻሚው እንዳስታወቁት ኢንሹራንሱ እስካሁን ከሚሰጣቸው ጠቅላላ የመድን አገልግሎቶች በተጨማሪ የሕይወት መድን አገልግሎት ለማቅረብ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አሠራር ማሟላት የሚገባውን መስፈርት መሟላቱን ገልጸዋል።
ኢንሹራንሱ የሕይወት መድን አገልግሎት ለመጀመር ብሔራዊ ባንክ የሚጠይቃቸውን የበጀት፣ የመመሪያና ሌሎች ቴክኒካል ሥራዎችን ማጠናቀቁ የተገለጸ ሲሆን፣ ብሔራዊ ባንክ የሕይወት መድን ለመጀመር የሚጠይቀው 15 ሚሊዮን ብር መሟላቱ ተመላክቷል። እንዲሁም ከሕይወት መድን አገልገሎት ለመስጠት ከብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ለማግኘት አንዱ መስፈርት የሆነውን ቴክኒካል የአዋጭነት ጥናት በውጭ ባለሙያዎች ተጠንቶ ማለቁን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።
ከብሔራዊ ባንክ ፈቃድ አግኝቶ የሕይወት መድን አገልግቱን ለማስጀመር ኢንሹራንሱ የቀረውን አዋጭ የሆነ የጠለፋ ዋስትና ሰጭ ድርጅት(re-insurance) የመለየት ሥራ እየሠራ መሆኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚው አመላክተዋል።
ለዚህም ኢንሹራንሱ ግልጽ ጨረታ አውጥቶ የተሻለ እና አዋጭ የዋስትና አገልግሎት የሚገባለትን ድርጅት በመለየት ሂደት ላይ ነው ብለዋል። ኢንሹራንሱ የሕይወት መድን አገልግሎቱን ለመስጠት ፈቃድ ለማግኘት የቀረው የመጨረሻ ሂደት የሆነውን የጠለፋ ዋስትና ስምምነት በአንድ ወር ውስጥ እነደሚጠናቅቅ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ጠቁመዋል።
ኢንሹራንሱ የሕይወት መድን አገልግሎቱን መስጠት በሚጀምርበት ጊዜ በኢትዮጵያ ደረጃ እስካሁን የሚሰጡ የሕይወት መድን አገልግሎቶችን እንደሚሰጥ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አመላክተዋል። ለመጀመሪያ ጊዜ የሕይወት መድን አገልግት ኢንሹራንሱ የሚሰጠው በዋናው መሥሪያ ቤት መሆኑን የጠቆሙት ዋና ሥራ አስፈጻሚው ወደፊት እንደ የአስፈላጊነቱ የሚሰፋ ይሆናል ብለዋል።
ቡና ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር የሕይወት መድን አገልገሎት ለመጀመር አንድ ወር ከግማሽ ባለበለጠ ጊዜ ውስጥ ቅድመ ሁኔታዎችን በማጠናቀቅ በሚቀጥሉት ኹለት ወራት ውስጥ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር አስታውቋል። በተጨማሪም ኢንሹራንሱ ወደፊት ማይክሮ ኢንሹራንስ የመስጠት አቅድ እንዳለውም ዋና ሥራ አስፈጻሚው ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።
እንደ ዳኛቸው ገለጻ ከሆነ በኢትዮጵያ የሕይወትና የማይክሮ ኢንሹራንስ በብዛት የተለመደ እንዳልሆነ ጠቁመዋል። ለዚህም እንደ ምክንያት የሚነሱት በማኅበረሰቡ ዘንድ የሕይወት እና ማይክሮ ኢንሹራንስ ያለው ጠቀሜታ ላይ የግንዛቤ ክፍተት ሥላለ ነው ብለዋል። ማይክሮ ኢንሹራንስ በዝቅተኛ ኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኘው የማኀበረሰብ ክፍል አስፈላጊ መሆኑን ያነሱት ዳኛቸው ብሔራዊ ባንክ እያወጣቸው ያሉትን የፋይናንስ ኣካትች መመሪያዎች በመከተል በስፋት መሥራት ይገባል ብለዋል።
ቡና ኢንሹራን እስካሁን ከሚሰጣቸው መድን አገልግሎቶች ውስጥ የንብረት፣ የምህንድስና፣ የገንዘብ እና የጉዞ ኢንሹራንስ ይገኙበታል።
ኢንሹራንሱ በ2012 በጀት ዓመት 249 ሚሊዮን ብር አጠቃላይ የመድን አረቦን ገቢ ማግኘቱን በዓመታዊ ሪፖርቱ ላይ አስፍሯል። በበጀት ዓመቱ ያገኘው ገቢ ከ2011 በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ45 ሚሊዮን ብር ብልጫ አሳይቷል። ከፍተኛውን ገቢ ያገኘውም ከትራንስፖርት ዋስትና መሆኑን ኢንሹራንሱ በሪፖርቱ አመላክቷል። በሌላ በኩል ኢንሹራንሱ 127 ሚሊዮን ብር የካሳ ክፍያ መፈጸሙን የገለጸ ሲሆን፣ ይህም ከባለፈው 2011 ከከፈለው 119 ሚሊዮን ብር ካሳ ጋር ሲነጻጸር የሥምንት ሚሊዮን ብር ብልጫ አሳይቷል።
ቅጽ 2 ቁጥር 108 ኅዳር 19 2013



