የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ያልተገባ 1.5 ሚሊዮን ብር ለስልክ ከፈለ

0
750

የመሥሪያ ቤቱ ላልሆኑ ስልኮች 271 ሽሕ ብር መክፈሉ በኦዲት ተረጋግጧል

የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በ2011 በጀት ዓመት ተገቢ ያልሆነ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ለስልክ ክፍያ መፈጸሙን በኦዲት ግኝት መረጋገጡ ታወቀ፡፡

ባልተገባ መንገድ ክፍያ የፈጸመባቸው ስልኮች መገኘታቸው የተገለጸው ኅዳር 16/2013 በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ቋሚ ኮሚቴ የፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፖብሊክ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የ2011 በጀት ዓመት የሒሳብ ኦዲት ሪፖርት ግኝት በተገመገመበት መድረክ ነው፡፡

ተፈጽሟል የተባለው ተገቢ ያልሆነ የስልክ ክፍያ የመስሪያ ቤቱ ስልክ ቁጥር መሆናቸው ባልተረጋገጡ መስመሮች 271 ሺሕ ብር የተከፈለ ሲሆን፣ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሥር የሚገኙ የስልክ ቁጥሮች ተመን እንዲወጣላቸው በዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት አስተያየት የተሰጠ ቢሆንም ተመን ያልወጣላቸው ከአንድ ነጥብ ኹለት ሚሊዮን ብር በላይ ክፍያ ተፈጽሟል ተብሏል። በአጠቃላይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር የስልክ ክፍያ መፈጸሙ ተረጋግጧል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከመንግሥት አሰራርና ስርዓት ውጭ ሲተገብራቸው የነበሩ ለብክነት የተጋለጡ አሠራሮችን እንዲያርም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማሳሰቢያ ተሰጥቶታል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ቋሚ ኮሚቴና የፌዴራል ዋና ኦዲተር የሚንስቴሩን የ2011 በጀት ዓመት የሒሳብ ኦዲት ሪፖርት ገምግመዋል። በግምገማው ቋሚ ኮሚቴው በፌዴራል ዋና ኦዲተር በሚኒስቴሩ የተከናወነውን የ2011 በጀት ዓመት የሒሳብ ኦዲት ግኝት አቅርቧል።

በዚህም የሚንስቴሩ የሒሳብ አሰራር የመንግሥትን የሒሳብ አያያዝ አዋጅ፣ ደንብና መመሪያን ያልተከለ መሆኑ ተገልጿል። “ሚንስቴሩ በ2011 በጀት ዓመት የ916 ሺሕ 996 ብር አላቂና ቋሚ ዕቃዎች ከመንግሥት ደንብና መመሪያ ወጪ ግዥ ፈፅሟል” ነው የተባለው። በ2011 በጀት ዓመት መጨረሻ መወራረድ ሲገባው ያልተወራረደ ኹለት ሚሊዮን 528 ሺሕ 116 ብር ተሰብሳቢ ኦዲት መገኘቱም ተመላክቷል። በተጨማሪም አንድ ሚሊዮን 852 ሺሕ 243 ብር ተከፋይ ሒሳቦች በባለመብቱ ተከፍሎ መወራረድ ሲገባው ሳይወራረድ ተገኝቷል። ሚኒስቴሩ አገልግሎት የማይሰጡ እቃዎችን በተገቢው መንገድ እንደማያስወግድና የንብረት ቆጠራ እንደማያከናውንም ተጠቁሟል።

የፌደራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በየዓመቱ ለመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚቀርበው የሒሳብ እና የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት የባለበጀት መሥሪያ ቤቶች የሐብት አስተዳደርና አጠቃቀም በአብዛኛው መሥሪያ ቤቶች መንግሥት ከዘረጋው አሠራር ሥርዓት ውጭ ያፈነገጠ መሆኑን ኦዲት ግኝቶችን ተከትሎ ተጠያቂነትን እንዲረጋገጥ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውሳኔ ሐሳብ አቅርቧል።

አሠራሩ ከተዘረጋው ሥርዓት ያፈነገጠ በመሆኑ ከተስተዋሉ ችግሮች መካከል የመንግሥት የግዥና የፋይናንስ ስርዓት ባልተከተለ መልኩ ግዥና ክፍያ መፈጸም፣ በሥራ ላይ ላልተገኘ ወይም ከሥራው ለለቀቀ ሠራተኛ ደምወዝ መክፈል፣ ለመንግሥት መሰብሰብ የሚገባው ገቢ ሕጉ በሚፈቅደው መሰረት አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች አለመሰብሰብና የክፍያ ተመን ሳይኖራቸው ወጭ አድርጎ ከሕግ ውጭ መክፈል የሚጠቀሱ ናቸው።

በተጨማሪም ከዘገዩ ግንባታዎች መንግሥት ባወጣው የግዥ አፈጻጸም መመሪያ መሠረት የጉዳት ካሳ አለመሰብሰብ፣ የውዝፍ ተሰብሳቢ ሒሳብ ላይ ተገቢውን እርምጃ አለመውሰድ፣ የመንግሥት ንብረት በአግባቡ አለመያዝ እና የጥሬ ገንዘብ ጉድለትና የመሰብሰብ ችግሮች ተብለው ተለይተው።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ መሐመድ ዩሱፍ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከመንግሥት አስራርና ስርዓት ውጭ ሲተገብራቸው የነበሩ ለብክነት የተጋለጡ አሠራሮችን በማረም የተገኘበትን የኦዲት ክፍተት መሙላት እንዳለበት አሳስበዋል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በበኩሉ ተገቢ ባልሆነ መንገድ ክፍያ ሲከፈልባቸው ተገኝተዋል የተባሉትን ስልኮች በአሁኑ ጊዜ ከቴሌ ጋር በመተባበር እንዲቋረጡ ማድረጉን አስታውቋል። እንዲሁም ጀነራል ኦዲተር ያስቀመጣቸውን ክፍተቶች እንደሚስተካክል ያስታወቀ ሲሆን፣ ያላለቁ ሥራዎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማከናወን እየሠሠራ መሆኑን ገልጿል።

ቅጽ 2 ቁጥር 108 ኅዳር 19 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here