ጥበብ በ2011

Views: 450

ዘመን ዘመንን እያስረጀ ደግሞም እያደሰ የ2011 የመጨረሻው ሳምንት ላይ ተገኝተናል። ትርጉም ያልተበየነለትና ረቂቅ የሆነው ጊዜ እንዲህ በዘመን ተከፍሎ 365 ቀናትን ሲሻገር እንደ አዲስ በምዕራፍ ይከፈታል። አሮጌ ሲሸኝ አዲስ ይተካል፤ የቀደመው ቢያልፍም ለነገ መሠረት ስለሚሆን በታሪክነት ግን ይመዘገባል።
2011 በኢትዮጵያ እጅግ ብዙና የተለያዩ ዜናዎች የተሰሙበት ዓመት ነበር። በተለይም ፖለቲካው ሳይተኛ የከረመበት ነው ማለት ይቻላል። በፖለቲካ ሰበብ እንደ አገር ሕዝቡ፣ እንደ ሙያ ደግሞ በርካታ ዘርፎች ተፈትነዋል። ከዚህም መካከል የጥበቡ ዘርፍ አንዱ ሳይሆን አልቀረም። በተለያየ የጥበብ መስክ ላይ የተሰማሩ የጥበብ ባለሙያዎችም በዓመቱ ያለፈውን የጥበብ ነገር ሲያነሱ የአገርን ነባራዊ ሁኔታና ክስተቶችን መጠቃቀሳቸው አልቀረም። ፖለቲካው ማንም ሊያመልጠው የማይችለው ነዋ!

አዲስ ማለዳ በዓመቱ በኢትዮጵያ በዋናነት የሚጠቀሱ የጥበብ ዘርፎች ያለፉትን ክዋኔዎች፣ የተገኙትን አዳዲስ ነገሮችና የሚሻገሩ ፈተናዎችም ይሁን ስኬቶችን ልትመዘግብ ወደደች።

ሙዚቃ

በ2011 እጅግ በርካታ ነጠላ ዜማዎችና በድምሩ 15 የሚጠጉ አልበሞች ለአድማጭ ቀርበዋል። ከነ “ምን ላድርግልህ?” ውዝግብ ጀምሮ ነጠላ ዜማዎችን በሚመለከት ፌዝና ቀልድ መሰል ሥራዎች ሙዚቃ ተብለው ተሠርተዋል። አንዳንዴም “ወዴት እየሔድን ነው?” የሚል ጥያቄ የሚያስነሱና የያዙት ጭብጥ ኢትዮጵያዊ ሥነ ምግባር የጎደለው “ዘፈኖች” ተሰምተዋል።

በአንጻሩ በዳዊት ጽጌ “አማን አማን” የተሰኘ ሙዚቃ የከፈተው 2011፣ አዳዲስ አቀራረብ፣ ዕይታና ጭብጥ የያዙና አተያይን የቀየሩ እንደ አብርሃም በላይነህ “እቴ አባይ” ዓይነት በጣት ሊቆጠሩ ከሚችሉ የሙዚቃ ሥራዎች በርካታ ተመልካችን ማግኘት እስከቻለው የዘቢባ ግርማ “ገራገር” ድረስ ብዙ ያሳየ ነው።
የሙዚቃ ባለሙያዎች ከነጠላ የዜማ ሥራዎች ይልቅ በአልበሞች ላይ አስተያየት መስጠት መርጠዋል። እርግጥም ነው ለነጠላ ዜማዎቹ መካሻ የመሰሉ በጠራራ ፀሐይ መካከል ጥላ እንደሚሆን ደመና ደርሰው ያረጋጉ አልበሞችም ተሰምተዋል። ግጥምና ዜማ ደራሲ እንዲሁም የሙዚቃ አቀናባሪ አማኑኤል ይልማ በበኩሉ በ2011 የነበረውን የሙዚቃ ሁኔታ ከአገር ሰላምና መረጋጋት ጋር አስተሳስሮታል።

“አገር ሲረጋጋ ነው ሙዚቃ መስማትም ሆነ መጨፈር የሚቻለው፤ ይህ መረጋጋት በብዙ የአገራችን አካባቢዎች ባለመሆኑ ግን በ2011 ብዙ አልበሞች የወጡ ቢሆንም አልተሰሙም” ብሏል። በሰላም ማጣት ምክንያት የተሰረዙ ኮንሰርቶችን፣ የአስቴር አወቀን የአልበም ሥራ ጨምሮ ተራዝመው የቆዩ ሥራዎች መኖራቸውንም ያስታውሳል። ይህም ሁሉ ሲደማመር 2011 ለሙዚቃው ጥሩ ዓመት ነበር ለማለት እንደማያስደፍረው አማኑኤል ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ትንሳኤ ነው የተባለለት “አውታር” የተሰኘው የሙዚቃ መገበያያ መተግበሪያ የተዋወቀውና ወደ አገልግሎት የገባው በ2011 ነው። ይህም ሕገወጥ ቅጂን ለመቆጣጠር ይረዳል የተባለለት ነው። ከ50 ዓመታት በፊት የተሠሩ የኢትዮጵያ ሙዚቃዎችን የቅጂ መብት የሚጠብቅ መሆኑንም ከዚህ ቀደም አዲስ ማለዳ ማስነበቧ ይታወሳል።

ቴአትር

አዲስ አበባ ላይ ብቻ “ተበራክተው” የሚገኙት ቴአትር ቤቶቻችን፣ በርካታ ተብሎ በቁጥር ሊጠቀስ በማያስደፍር መልኩ ልንሸኘው በዝግጅት ላይ ባለው 2011 አዳዲስና ነባር ተውኔቶች ተዘጋጅተው አቅርበዋል። አዲስ አበባ ቴአትርና ባሕል አዳራሽ መቅረብ ከጀመረው “አሉላ አባ ነጋ” ታሪካዊ ቴአትር አንስቶ ለኹለተኛ ጊዜ በብሔራዊ ቴአትር መድረክ የወጣው “ባቢሎን በሳሎን”፤ ከአዲስ አበባ ውጪ በኢትዮጵያ የተለያዩ ክፍሎች እየተንቀሳቀሰ ለዕይታ እስከቀረበው የአገር ፍቅር ቴአትር የተመደረከው “ከመጋረጃው ጀርባ” ድረስ ለተመልካች ቀርበዋል።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ምክትል ዋና ዳይሬክተር እና የቴአትር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ደስታ አስረስ፤ 2011 ለቴአትር ወርቃማው ዓመት ነበር ብለዋል። ለዚህም ምክንያታቸው ታግደው የነበሩ ቴአትሮች ለዕይታ ፈቃድ ማግኘታቸው ነው። ለዚህም በቴአትር ቤቱ አሁን በዕይታ ላይ ያለው የተክሌ ደስታ “መንታ መንገድ” ቴአትር ተጠቃሽ ነው።

“ይህ ጥበብ በነጻነት መሠራት መጀመሩን ማብሰሪያ ነው” ያሉት ደስታ፤ በታገዱ ቴአትሮች ምክንያት 2010 ከ2011 አንጻር ድብታ የነበረበት መሆኑን አስታውሰዋል። ከዛም ባሻገር ከበርካታ ዓመታት በኋላ ወደ አገራቸው የተመለሱ የቴአትር ቤቱ የቀድሞ ባለሙያዎች ጋር የተደረጉ ምክክሮችና የሐሳብ ልውውጦች ጠቃሚ እንደነበሩም ጠቅሰዋል።

ከዚህም ሁሉ በኋላ ሃያስያን ሊመሰክሩላቸው የሚችሉ የቴአትር ሥራዎች መውጣታቸውን አያይዘው አንስተዋል። በቴአትር ቤቱ ደረጃውን የጠበቀና ለቴአትር ሥራ የተመቸ ግንባታ ሥራ መጀመሩም በ2011 የተመዘገበ ነው። ዓመቱ በብሔራዊ ቴአትር የተመልካች ቁጥር የጨመረበትና ጥበባዊ ፋይዳቸው ከፍተኛ የሆኑ ቴአትሮች የቀረቡበት እንደነበር በፍቃዱ ከፈለኝ፤ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊው ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። በተለይም “ባዶ እግር” የተሰኘው ቴአትር ግሪክ ድረስ ሔዶ ለዕይታ መቅረቡም በዓመቱ ከተከናወኑ አበይት ኩነቶች መካከል ይጠቀሳል።

አገር ፍቅር ቴአትር ሌላው በስስት የሚታይ አንጋፋ ቴአትር ቤት ነው። በተመሳሳይ ራስ ቴአትርንም ማንሳት ይቻላል። ቴአትር ቤቶች ለቴአትሩ ዕድገት ያላቸው አስተዋጽዖ ከፍተኛ እንደመሆኑ፤ ለቴአትር ቤቶች የሚሰጠው ትኩረት መጠንም ቀላል ግምት የሚሰጠው አይሆንም። በዚህ መሰረት 2011 ራስ ቴአትር ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እንዲገነባ ለግንባታ የሚሆን ቦታ ያገኘበት፣ አገር ፍቅር ቴአትርም ይዞታውን በማሻሻል ታሪካዊ ቅርጹን ሳይለቅቅ እድሳትና መስፋፊያ እንዲያገኝ ከከተማ አስተዳደሩ ትኩረት እንዲሁም ፈቃድ ያገኙበት ዓመት ነው።

ብሔራዊ ቴአትር “አልቃሽና ዘፋኝ” ከበርካታ ዓመታት በኋላ እንዲሁም “ባቢሎነ በሳሎን” ዳግም ለዕይታ ቀርበዋል። “አንድ ለአንድ”፣ “ምስጢሩ” እና “እምዬ ብረቷ” በዓመቱ የታዩ አዳዲስ ቴአትሮች ሲሆኑ፤ “ባዶ እግር” 2011ን ከቀደመው ዓመት ተሸጋግሯል። በአገር ፍቅር ቴአትር “ነቃሽ”፣ “ሰፈረ ጎድጓዳ” እና “የመንግሥት ሥራ” አዲስ የገቡ ቴአትሮች ሲሆኑ ተሻግረው 2011 ላይ የታዩት ቴአትሮች “የጉድ ቀን”፣ “ገራገሩ” እና “ከመጋረጃው ጀርባ” ናቸው።

ስዕል

የሥዕል ጥበብ በቅርበት ከሚያውቁት ውጪ ብዙ ትኩረት የሚሰጠው ዘርፍ ባይመስልም ብዙዎች ግን ባዩበት አጋጣሚ ማድነቃቸው አይቀርም። ከስዕል ጥበብ ባሻገር በጥቅሉ የዕይታዊ ጥበባት ነገር የሚያስጨንቃቸው ጥቂት አይደሉም። ከዚህ አንጻር በተለይም በአዲስ አበባ ሊከናወኑ ዕቅድ የተያዘላቸው ከተማዋን የማስዋብ ሥራዎች ለዕይታ ጥበብ ምላሽ ሊሰጡ እንደሚችሉ ይገመታል። ይህን ተከትሎ በመስታወት የታጠሩ የሚመስሉ ሕንጻዎች ግንባታ ተገትቶ በዲዛይን ሥራ ጥበብና ኢትዮጵያዊነት የታከለበት ሥራ የሚጠበቅ ይሆናል።

እስከዛው ወደ ስዕል ጥበብ ብቻ ስናተኩር፤ ምንም እንኳን የተሠራ ዳሰሳ ባይኖርም ስዕል ከሌሎች የጥበብ ውጤቶች በተሻለ ብዙ ዓውደ ርዕዮች የሚስተናገዱበት መስክ ይመስላል። በመደበኛነት መስቀል አደባባይ በሚገኘው አዲስ አበባ ሙዝየም፣ ብሔራዊ ሙዝየም፣ ጀርመን የባሕል ማዕከል፣ ጉራማይሌ አርት ጋለሪ፣ ፈንድቃ የባሕል ማዕከል፣ ብሔራዊ ቴአትር፣ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚና ሌሎችም ማዕከላት ከሚገኙት ባሻገር በተለያየ ጊዜ አዳዲስ የስዕል ዓውደ ርዕዮች ለዕይታ ቀርበዋል።
“ሰዓሊ እንደ ዜጋ የማኅበረሰቡ አካል ነውና አገራዊ ጫናን ይካፈላል” ያለው እያዩ ገነት፣ ሰዓሊና መምህር ነው። በዚህም ምክንያት በቋሚነት የስዕል ዓውደ ርዕይ ከሚያቀርብባትና ከሚያስተምርባት ባሕር ዳር ከተማ ጨምሮ በአገር ውስጥ የተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩ ክስተቶች በዚህ የጥበብ መስክ ላይ ተጽዕኖ መፍጠራቸውን ይገልጻል። ይህም በግሉ ማለትም በስዕል ማሳያው ከገጠመው የተመልካች ቁጥር መቀነስ ጀምሮ በሰዓልያን ላይ የተፈጠረው አገራዊ ምስል ድረስ የሚዘልቅ ነው ብሏል።

“ጥበብ በባሕሪው መነካትን ይጠይቃል” የሚለው እያዩ፤ እየታዩ ያሉ ኩነቶች መካከል ለሰዓሊው ግብዓት የሚሆኑ እንዳሉ ይጠቅሳል። በዓመቱ በተፈጠሩ አገራዊ ቀውሶች ምክንያት “ፍቅር ያሸንፋል” የሚሉ እንዲሁም ዛሬን መሻገርና ነገን በተስፋ መጠበቅን የሚያመላክቱ የስዕል ሥራዎች እንደተሠሩም አያይዞ ያነሳል።
በመጠን ከሚያይለው መጥፎ ነገር ትንሽ በሆነ ጥሩ ነገር ላይ ማተኮርን እመርጣለሁ የሚለው እያዩ፤ በ2011 የሆኑ ክስተቶች ሁሉ ራሱን ጨምሮ አርቲስቱ እንደ አስታራቂ ዳኛ እንዲሆን አድርጓል ባይ ነው። በተለይም “ኢትዮጵያ” የሚለው ሥም ከዓመታት በኋላ ደጋግሞ መጠራት መጀመሩ በሰዓሊ ልብ ውስጥ እንዲሁም ሸራ ላይ ቀለም ጨምሯል ሲል ለአዲስ ማለዳ አስተያየቱን አካፍሏል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ “ነጻ ጥበብን ፍለጋ – ማንነት” የተሰኘ ዓውደ ጥናት በ2011 ከቀረቡ ስዕል ተኮር መድረኮቸ መካከል ተጠቃሽ ነው። በዚህ ዓውደ ጥናት ላይ ከአለ የስዕል ትምህርት ቤት፣ ከሰዓሊያን ማኅበር እንዲሁም ከኦሮምያ የሰዓልያን ማኅበር የተውጣጡ ባለሙያዎችና ሌሎችም የተሳተፉበት መድረክ ነው። በዚህም ዓውደ ጥናት ላይ አገር በቀል የአሳሳል ጥበብን ይዞ ስለመገኘት፣ ስለቅጂ ሥራዎች አግባብ አለመሆን፣ ሰዓሊ የራሱን አሻራና ፈጠራ የሚያክልበት ሥራዎችን ከማበርከት አንጻር ባለሙያዎችና የኪነ ጥበብ ሰዎች ተወያይተዋል።

ፊልም

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የፊልም ገበያው እየተቀዛቀዘ እንደሆነ ቢነገርም በዚሁ ወቅት የኢትዮጵያን የፊልም ኢንዱስትሪ ከአውሮፓ የፊልም ተጽዕኖ ይልቁንም ይስተዋል ከነበረው የታሪክ ጭብጥ መመሳሰል ነጻ በማድረግ ረገድ ጠንካራ ሥራዎች ተሠርተዋል። “ቁራኛዬ” እንዲሁም “ሦስተኛው ዓይን” ዓይነት ፊልሞች ለዚህ ተጠቃሽ ምሳሌ ሆነው መቅረብ ይችላሉ። በተመሳሳይ በተከታታይ የቴሌቭዥን ድራማ ረገድም የነበሩት የዘለቁበት አዳዲስ ተከታታይ የቴሌቭዥን ፊልሞችና ድራማዎችም ለዕይታ የቀረቡበት ዓመት ነው፤ 2011።

ከአላቲኖስ የፊልም ሠሪዎች ማኅበር ምኒልክ መርዕድ፤ በዓመቱ ጥሩ ፊልሞች ለዕይታ መቅረባቸውን ጠቅሷል። ከታሪክ፣ ከገጻ ባሕሪ ግንባታ፣ ከካሜራ ቴክኒክና መሰል የፊልም ሥራ ከሚፈልጋቸው ሥራዎች አንጻር የተሻሉ የሚባሉ ፊልሞች ተሠርተዋል ብሏል። ከጭብጥ አኳያም ቀድሞ የነበረው የሮማንቲክ ኮሜዲ ዘውግ በ2011 ብዙ እንዳልታየና ይልቁንም አገራዊና ፖለቲካዊ ምልከታ እንደነበራቸው አንስቷል። በአንጻሩ የፊልም መሰረቆች በዓመቱ ለፊልሙ ዘርፍ መጥፎ ጎን ሆኖ እንዳለፈ ያወሳው ምኒልክ፤ “ፊልሞች ሲኒማ ቤት ታይተው ሠሪዎቹ ዲቪዲ ወይም ሌላ መንገድ ተከትለው ፊልሙን ለማከፋፈል ሳያስቡ ሲሰረቁ ነበር” ሲል ለአዲስ ማለዳ አስታውሷል።

ይህን በተመለከተ በቅርቡ ከሲኒማ ቤት በሞባይል ቅጂ ተሰርቆ የወጣው “ሦስተኛው ዓይን” ፊልምን የሰረቀው ሰው ለፍርድ መቅረቡን እንደማሳያ ያነሳችው የፊልም ፕሮድዮሰሮች ማኅበር ፕሬዝዳንት አርሴማ ወርቁ ናት። ለማኅበሩ አቤቱታ ይዘው ከቀረቡ ኹለት የተሰረቁ ፊልሞች መካከል ነበር፤ “ሦስተኛው ዓይን”።

እንደ አርሴማ ገለጻ፣ ዓመቱ የተመልካች ቁጥር የጨመረበት ነው። በፊልም ዘርፉ በዓመቱ በፊልም ማሳያ ቤቶች ማሰራጫ መንገዶችና ከማዘመን ጀምሮ ፊልሞች ሲሰረቁ ከምንጩ መያዝ የሚችልበት አሠራር መፈጠሩም በ2011 የተመዘገበ ስኬት መሆኑን ጠቅሳለች። መገናኛ ብዙኀን የቀደመውን ትችት ትተው፤ አዳዲስ ዘውግና ሐሳብ በያዙ ፊልሞች ምክንያት ለዘርፉ የሰጡት ትኩረትም የላቀ ሚና አለው ብላለች።

መጻሕፍት

“አንባቢ ጠፋ፤ የለም” በሚባልበትና ስለንባብ በሚሰበክበት ጊዜ የመጻሕፍት ነገርም ከዚህ የራቀ አይደለም። ሞቅ ያለውን የፖለቲካ እንቅስቃሴ ተከትለው የሚወጡ የመጻሕፍት ሥራዎች ብዙውን ጊዜ እንደጋዜጣ ወቅታዊ ጉዳይን የያዙ፤ እንደማኅበራዊ ገጽ የግለሰቦችን ግላዊ ዕይታ ብቻ ያቀፉ በመሆናቸው ለታሪክ ግብዓት ወይም ለእውቀት ተጨማሪ ፋይዳ ሳይሰጡ ለገበያ ፍጆታ ብቻ ሆነው ሲቀሩ ታዝበናል።

የእነሆ መጻሕፍት ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ ኤርምያስ በላይነህ፤ እንደውም በአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር ሰፋ እንደመባሉና በርካቶችም ከውጪ እንደመምጣታቸው ፖለቲካ ቀመስ ሥራዎች በበቂ ሁኔታ ተሠርተዋል ማለት እንደማይቻል ይጠቅሳል። በአንጻሩ በ2010 ከፖለቲካው ጋር ተያይዞ ይወጡ የነበሩ መጻሕፍት የተሻለ ተነባቢ እንደነበሩ ነው የጠቀሰው። ከዛ በኋላ ግን የትርጉም፣ የልብወለድ፣ ፍልስፍና እና ሥነ ልቦና ባሻገር ሲልም የታሪክ መጻሕፍት የአንባቢን ትኩረት ስበዋል ይላል። በድምሩ ግን የመጻሕፍ ገበያው ጥሩ አልነበረም፤ እንደ ኤርምያስ ገለጻ።

የታሪክ ባለሙያ እና የቋንቋ መምህር እንዲሁም በሚዩዚክ ሜይዴይ የመጻሕፍት ውይይት መድረክ ላይ በአወያይነት የሚታወቀው ሰለሞን ተሰማ ጂ. ከ2010 በተሻለ ጠቃሚ ሐሳቦች በመጻሕፍት የተነሱበት ዓመት ነው ይላል። ይልቁን ከኅትመትና ስርጭት ጋር በተያያዘ የመጻሕፍት ዋጋ በእጥፍ መጨመሩ፣ በሰላምና መረጋጋት እጦት ምክንያት ስርጭት ላይ መስተጓጎል መፈጠሩን እንደችግር ያነሳል።

በዓመቱ ትኩረት ያገኙ መጻሕፍትም መኖራቸው አልቀረም። አንዳርጋቸው ጽጌ በእስር ቆይታቸው ያዘጋጁት ‹‹ትውልድ አይደናገር፤ እኛም እንናገር›› በዚህ የሚጠቀስ ነው። አልፎም የቀረ የመሰለን አሳታሚ የማይጠቀስበት የመጽሐፍ ሕትመትም በተስፋዬ ገብረአብ ‹‹የቲራቮሎ ዋሻ›› ተመልሷል። የሙሉጌታ አረጋዊ ታሪክ ቀመስ ልብወለድ ‹‹አብራክ›› ለውይይት የቀረበ፤ በጄኔራል መርዕድ ንጉሤ ሕይወት ዙሪያ የተዘጋጀው ‹‹ለአገር ክብር ለወገን ፍቅር›› መጽሐፍም ያነጋገረ ነበር። አዲስ ማለዳ ባላት መረጃ ሕይወት እምሻው እና ዓለማየሁ ገላጋይ ባልተለመደ ሁኔታ እያንዳንዳቸው ሁለት መጻሕፍትን ለአንባብያን ያበረከቱት በዚሁ ዓመት ነው።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com