ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ በዚህ ሰሞን

Views: 439

በዚህ ሰሞን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አንድነቴን እና ህልውናዬን የሚፈታተን አንድ ጉዳይ ገጥሞኛል ስትል አስታውቃለች። ምክንያቱ ደግሞ ቀሲስ በላይ መኮንን አማካኝነት በኦሮምኛ ካልተቀደሰ ምኑን ፀሎታችን መንግሥተ ሰማያት ገባ ዓይነት አመክንዮ ያለው እና አዲስ ስርዓት ኦሮምኛን ማዕከል ያደረገ በኢትጵያ ኦርቶዶክስ ሊገነባ ይገባል ሲሉ ተደምጠዋል።

በተቃራኒው ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ይሔን ቡድን አናውቀውም መንግሥት ይህን ያለ ማንም ዕውቅና የሚንቀሳቀሰውን አካል ሃይ ሊለው ይገባል ስትል ጪኸቷን አሰምታለች። በተለይ ደግሞ በእሁድ፣ ነሐሴ 26/2011 በአዲስ አበባ ከተማ በኦሮሚያ ባሕል ማዕከል የተሰጠው መግለጫ ገና ከጅምሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ዕውቅና እንደሌለው ዓርብ፣ ነሐሴ 24/2011 መግለጫ አውጥታ ነበር።

ኹለቱን ወገኖች ውዝግብ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ የሆነውም ሆነ የሌላ እምነት ተከታይ በንቃት ሲከታተልና የተለያዩ አስተያየቶችን በመንግሥትም ላይ ጨምሮ ሲሰነዝሩ ነበር። አንዳንዶቹ እንዲያውም ከኹለቱ ቡድኖች አልፈው በመሔድ ጠቅላይ ሚንስትሩንም በጥያቄያቸው ነክተዋል። ከአገረ አሜሪካ ድረስ ሔደው ለበርካታ ዓመታት ተከፍሎ የነበረውን ሲኖዶስ በማስታረቅ ትልቅ ነገር የሠሩ ሰው እንዴት አፍንጫቸው ሥር ይህ ነገር ሲካሔድ ጆሮ ዳባ ልበስ ይላሉ ሲሉ ሞግተዋል።

በተቃራኒው ደግሞ የለም ኦሮሚያ ላለፉት ዓመታት በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አልተወከለችም፣ ቅዳሴም የሚቀደሰው በግዕዝ፣ በአማረኛ እንጂ በኦሮምኛ ተቀድሶ አያውቅም ስለዚህ የአሁኑ እንቅስቃሴ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታው የጎላ ነው ሲሉ ቀሲስ በላይን ቡድን ሽንጣቸውን ገትረው ደግፈዋል።

ይሁንና አንድ ሊቃነ ጳጳስ ቤተክርስቲያኒቱ በኦሮምኛ እንደምትቀድስ እንዲሁም ስብከት እንደምታካሒድ በማስታወቅ የነቀሲስ በላይን ቡድን ክፍኛ ተችተዋል፤ እንደሚፋለሟቸውም አውጀዋል። በተጨማሪም አንዳንድ ቁጭት የተሰማቸው የቤተክርስቲያኒቱ ምእመናን በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች የኦሮምኛ ቅዳሴ ቪዲዮ ሲጋሩት ከርመዋል።

ሌላው መስከረም 4/2012 የነበላይን ቤተክርስቲያን የመከፋፈልን ሴራ በተቃውሞ ለመግለጽ ሰልፍ እንደሚደረግ በሰፊው የማኅበራዊ ትስስር መድረኮች የውይይት ማሟሟቂያ ሆኖም ከርሟል።

በቀሲስ በላይ መኮንን የተመራው ቡድን ግን ከሃይማኖት ጉዳይ ውጭ መግለጫ በሰጡበት ወቅት ስለ አዲስ አበባ ባለቤትነት ጉዳይም ማንሳቱ ብዙዎችን አሰቆጥቶ በማኅበራዊ መገናኛውን እልፍ አስተያየቶች ከፍ ሲልም ዘላፋዎች ሲስተዋሉ ሰንብተዋል። ከመግለጫቸው ጋር በተያያዘ አንዳንዶች አጀንዳው የነቀሲስ በላይ ሳይሆን እነቀሲስ በላይ በተላላኪነት የሚያስፈጽሙት ነው ሲሉ ጣታቸውን በተዋቂው የኦሮሞ መብት ተሟጋች እና የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ዋና ዳይሬክትር በሆነው ጃዋር መሐመድ ላይ ጠቁመዋል። እንደማስረጃም ጃዋር መሐመድ ከቀሲስ በላይ ጋር የተነሳውን ፎቶ በማቅረብ ብዙዎች እንዲጋሩት አድርገዋል።

በሳምንቱ ሐሙስ፣ ነሐሴ 30 በማኅበራዊ ትስስር አውታሮች ሌላው የመነጋገሪያ መድረክ የሆነው የኦሮምያ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳና ዳንኤል ክብረት ከፓትሪያሪክ ማትያስ ጋር በተፈጠረው ፉዳይ ዙሪያ መነጋገራቸው ተወርቷል። ይሁንና ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ “በክልላችን የኦሮሚያ ቤተክህነት አይቋቋምም” ብለዋል አላሉም በሚል ብዙዎች ቃላት ሰሰናዘሩ ውለዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 44 ጳጉሜ 2 2011

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com