ምርጫ እና የምርጫ ተዋናዮች ሚና

0
713

ስለ ሰላም እና መረጋጋት ሲባል ምርጫው ይራዘም ወይስ በጊዜው ይካሄድ የሚለው ጉዳይ ፖለቲከኞችን ለሁለት ከፍሎ እያሟገታቸው መሆኑ የአደባባይ ምሥጢር ነው። ግርማ ሰይፉ ሰላም እና መረጋጋትን የማምጣቱ ኃላፊነቱም ቢሆን በምርጫ ተዋናዮች በጎ ፈቃድ ላይ የተንጠለጠለ መሆኑን በማስታወስ ሙግታቸውን ያቀርባሉ።

 

“ምርጫ ይራዘም ወይስ አይራዘም?” የሚለው ጥያቄ ፋሽን በሚመስል መልኩ እየቀረበ ያለ ጥያቄ ነው። ምርጫ የሚራዘምበትን ምክንያት ቆጥሮ ለምን ያህል ጊዜ መራዘም እንዳለበት የሚያስረዳን ሰው ግን ጠፍቷል። ይልቁንም በቀሪው ጊዜ ምን፣ ምን ተግባራትን በፍጥነት ማከናወን እንዳለብን የሚያሳስብ አካልም ሆነ ግለሰብ የጠፋ ይመስለኛል። ምርጫ ማራዘሚያ ምክንያቶች ካሉ እና አሳማኝ ከሆኑ ምርጫ የማይራዘምበት አንድም ምድራዊ ምክንያት ሊቀርብ አይችልም። ‘ሕገ መንግሥት ይከበር!’ የሚለውም መፈክር ቢሆን ብዙ ርቀት የሚያስኬድ አይደለም።
ምርጫ ይራዘም ከሚሉት ጥቂቶች መካከል ምርጫ ለማካሄድ የሚያስፈልገው ሰላም እጅግ ወሳኝ ነው በሚል ነው። ይህ ጉዳይ እውነት ነው። ምርጫ ለማካሄድ ሰላማዊ ድባብ ይፈልጋል። ይህን ድባብ ለመፍጠር ማን ምን ማድረግ ይኖርበታል የሚለውን ግን በዝርዝር ማየት ያስፈልጋል። በእኔ ዕይታ ከምርጫ ተዋናዮች አንፃር የሚከተሉትን ነጥቦች ላጋራችሁ ወደድኩ።
ምርጫ የሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነት የሚረጋገጥበት ዋንኛው መንገድ ነው። ሕዝብ የፈለገውን ቡድን ወደ ሥልጣን ለማምጣት ወይም በቃህ ብሎ ለማውረድ የሚጠቀምበት ሥልጡን መንገድ ነው። “ሕዝብ ታዲያ ምርጫ ይፈልጋል? አይፈልግም?” የሚል ጥያቄ ማንሳት ማለት “ሕዝብ ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤት መሆኑን ይፈልጋል? አይፈልግም?” ብሎ እንደመጠየቅ ነው። ይህ ደግሞ ተገቢ አይደለም። ሕዝብ ሰላምንም መፈለጉ የሚጠየቅ ጉዳይ አይደለም። ስለዚህ ሕዝብ ለሰላም እና ለሥልጣን ባለቤትነት ዘብ ይቆማል ማለት ነው። መቼም ሰላምን የሚነሱ ግጭቶች የሚካሄዱት በሕዝብ ውስጥ ባሉ ሰዎች ነው። “ይህ ለምን ይሆናል?” የሚል የሚሊዮን ብር ጥያቄ ማንሳት ይቻላል። በእኔ እምነት በግጭት ውስጥ የሚሳተፉ ሰዎችን ወደ ግጭት የሚመሩ፣ ስሜት ኮርኳሪ ጉዳዮችን የሚያነሱ ኃይሎች አሉ ማለት ነው። ይህ እውነት ነው። ስለዚህ ሥራችን መሆን ያለበት በሕዝብ ውስጥ ሆነው ሰላም የሚነሱትን አደብ ማስገዛት ላይ መሆን ይኖርበታል።
በሕዝብ ውስጥ ስሜት ኮርኳሪ ጉዳዮች የሚያነሱት በዋነኝነት በምርጫ ተፎካካሪ ሆነው መቅረብ ያለባቸው ኃይሎች ናቸው፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች። የፖለቲካ ፓርቲዎች ሥልጡን በሆነ መንገድ ማሸነፍ እና መሸነፍ በክብር የሚታይበት ሁኔታ በአገራችን ተፈጥሯል ብለን ለማመን እንቸገራለን። “እኔ ካልተመረጥኩ ምርጫው ተጭበርብሯል” ከሚለው ትንሽ መተንኮሻ ጀምሮ፣ “የሕዝባችን ጥቅም አደጋ ላይ ነው” እስከሚል ጡዘት በማድረስ ብጥብጥ ሊጫር የሚቻልበት ዕድል አለ። ከላይ ለማንሳት እንደሞከርኩት በግጭት የሚሳተፉ ኃይሎች አሉ። እነዚህ ኃይሎች የሕዝብ ወኪሎች ሳይሆኑ የፓርቲ ደጋፊ ነን ባዮች ናቸው። በትንንሽ ለግጭት መንስዔ በሚሆኑ ኮርኳሪ ምክንያቶች ነው ወደ ግጭት የሚገቡት። ስለዚህ ፓርቲዎች “ምርጫው ይራዘም፣ አይራዘም” ከሚል እሰጥ አገባ ወጥተው የምርጫ ውጤትን በፀጋ ስለመቀበል ደፊዎቻቸውን ማስተማር ማስልጠን ይጠበቅባቸዋል። በምርጫ ውጤት አሸናፊው ጮቤ የሚረግጥበት ብቻ ሳይሆን ተሸናፊም “እንኳን ደስ ያላችሁ” የሚሉበት ድባብ መፍጠር የግድ ይላል። ይህ የፓርቲዎችና ደጋፊዎች ሚና ምርጫን በሰላም ጀምሮ በሰላም ለማጠናቀቅ ወሳኝ ግብዓት ነው። ይህን በማድረግ ላይ ላሉ ፓርቲዎች ሚዲያ ተገቢውነን ትኩረት ሊሰጣቸው እና ለአገር ሰላም የሚጨነቁ ኃላፊነት የሚሰማቸው መሆኑን ማሳወቅ ይጠበቅበታል። ፓርቲዎች ደጋፊዎቻችሁን አስተምሩ ይህ ወሳኙ መልዕክት ነው።
በ1997 በነበረው ምርጫ ወቅት ብዙ ሰው ትኩረት ያልሰጠው ነገር ግን ለምርጫው ከፍተኛ ሚና የነበራቸው የሲቪል ማኅበራት ነበሩ። በዛን ወቅት እነዚህ ማኅበራት በምርጫ ማስፈፀም ወቅቅ የሰጡት ድጋፍ ባይኖር ኖሮ በወረቀት የተመዘገበው ውጤት ለመመዝገብ የሚያስችል የተቃዋሚ ፓርቲዎች ዝግጅት አልነበረም። ይህን በደንብ የተረዳው ገዢው ፓርቲ እነዚህን ሲቪል ማኅበራት በቻለው መንገድ ሁሉ አጠፋቸው። ዛሬ ባለንበት ሁኔታ ደግሞ እነዚህ ሲቪል ማኅበራት “ቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ ጊዜና ድኅረ ምርጫ በአገራችን ሰላም እንዳይናጋ ምን ማድረግ አለባቸው?” የሚለውን ጉዳይ ማንሳት እጅግ አስፈላጊ ነው። ተፎካካሪ ፓርቲዎች ደጋፊዎቻቸውን ከማሠልጠን ጎን ለጎን እነዚህ ሲቪል ማኅበራት በአስቸኳይ ወደ ሲቪክ ትምህርት እንዲገቡና መላውን ኅብረተሰብ ግንዛቤ እንዲያሳድጉ ማድረግ ያስፈልጋል። በአገራችን በሁሉም የምርጫ ክልሎችና ከዚያም ወርዶ ቀበሌዎች የሲቪል ማኅበራትን በማሠማራት ዜጎች በምርጫ ሂደቱና ውጤቱ ላይ ሊኖራቸው የሚችለውን ሚና ማስተማር ይኖርባቸዋል። ከውጭም ሆነ ከአገር ውስጥ የሚገኝም ሀብት ለዚህ ጉዳይ ማዋል ለሰላማችን የምንመድበው ትልቅ ኢንቨስትመንት መሆኑ መታወቅ አለበት። ሲቪል ማኅበራት ያለምንም ፖለቲካዊ ወገንተኝነት በመንቀሳቀስ ታሪካዊ ተግባራትን ማከናወን ይጠበቅባቸዋል። በዚህ ወቅት ከዚህ የተሻለ ሌላ የሚከውኑት ተግባር ይኖራል የሚል ምልከታ የለኝም። ሲቨል ማኅበራት በዚህ ደረጃ እየተዘጋጁ እንዳልሆነ ይልቁንም በማኅበራት ሕግ ውስጥ ያሉ ማሻሻያዎች “ምን፣ ምን ጥቅም ይዘው ይመጣሉ?” በሚል ስሜት ውስጥ እንደሚገኙ ይታወቃል። ሲቪል ማኅበራት ይህን ታሪካዊ ድርሻቸውን ለመወጣት ከምን ጊዜውም በላይ ሊተጉ ይገባል። ሲቨል ማኅበራት ለሰላምና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል።
መንግሥት እንደ መንግሥት ከፍተኛ ኃላፊነት አለበት። ገዢው ፓርቲ በቁርጠኝነት የመንግሥትንና የፓርቲውን ሚና መቀላቀሉን ማቆም የግድ ነው። የፈለገ በጎ ሥራዎች ተሠርተው በመጨረሻ መንግሥት ሥልጣኑን ለፓርቲው ጥቅም ማግኛ አውላለሁ ብሎ ከተነሳ ግጭት የማይቀር ነው። ምርጫው የሕዝብ ይሁንታ የሚያገኝበት ካልሆነ ለሰላም ስትሉ ዝም በሉ የሚል ተረት አይሠራም። ሰላማችን እንዲጠብቅ ኃላፊነት ያለበት መንግሥት ሰላም በመንሳት መሳተፍ የለበትም። በቀጣይም ሰላማዊ አገር መምራት የማያስችል ሥልጣን ከታሪክ ተጠያቂነት አያድንም። የመንግሥት ድርሻን በአግባቡ በመወጣት ላይ ያተኮረ እንቅስቃሴ ማድረግ የግድ ነው። መንግሥት ምርጫ ቦርድ፣ የፍትሕ ተቋማት፣ ፖሊሲ የደኅንነት ተቋሙ እና መከላከያ በተጠናከረ መንገድ በገለልተኝነት ሚናቸውን እንዲወጡ የሚያስፈልጋቸውን ግብዓት ከማቅረብ በዘለለ፣ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ጣልቃ የሚገባ ከሆነ ሁሉም ተዋናዮች ከሚሠሩት በላይ ለሰላም መደፍረስ ምክንያት ሊሆን ይችላል። ምርጫ ቦርድም ይሁን የፍትሕ ሥርዓቱ በተሟላ ሁኔታ አቅም ላይኖራቸው ይችላል። ይህ ግን ምርጫውን የጥራት ደረጃውን ከመቀነስ አልፎ የምርጫውን ተቀባይነት የሚያሳጣ ሊሆን አይችልም። መንግሥት ጣልቃ የሚገባ ከሆነ ግን ሁሉም ነገር ዜሮ ይሆናል። የዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መንግሥት በዚህ ጉዳይ የሚወስደውን አቋም በጥንቃቄ መከታተል እና መደገፍ አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን ለአገር ሰላም የሚያስብ ሁሉ እንደ ግዴታ ሊወስደው ይገባል።
ሚዲያዎች በተከታታይ ከሚያቀርቧቸው የኅብረተሰቡን ግንዛቤ የሚያዳብሩ መርሃ ግብራት በተጨማሪ ከላይ ያነሳናቸው ተዋናዮች የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ እግር በእግር እየተከታተሉ መዘገብ ይጠበቅባቸዋል። ዘገባው ተጠያቂነትን በሚያሰፍን መልኩ ተግባራቸውን በአግባቡ የማይወጡትን ተዋናዮች ማጋለጥ የሚጨምር መሆን አለበት። በተለይ ሆንብለው ለግል ጥቅማቸው ሲሉ የሕዝብን ጥቅም (ሰላም) አደጋ ላይ የሚጥሉትን ሁሉ ማጋለጥ ይጠበቅበታል። ራሳቸው ሚዲያዎቹ በሰላም ማደፍረስ ላለመሳተፍ ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግና በኃላፊነት ስሜት መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል።
ሁሉም ኃይሎች በቅንንት ሕዝብን የሥልጣኑ ባለቤት ለማድረግ የሚተጉ ከሆነ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በደረቅ ሳር ላይ ክብሪት ላለመጫር ከሆነ በአገራችን ለአፍሪካ ምሳሌ የሚሆን ምርጫ ማካሄድ እና ሁላችንም አሸናፊ የምንሆንበት ውጤት ልናስመዘግብ እንችላለን። ይህን ማድረግ ደግሞ እኛ ኢትዮጵያውያ አያቅተንም። እንችላለን!!!

ግርማ ሰይፉ የቀድሞው የአንድነት ለዴሞክራሲ እና ፍትሕ ፓርቲ አመራር እና ከ2002-2007 የፓርላማ አባል በመሆን ያገለገሉ ፖለቲከኛ ናቸው። በኢሜይል አድራሻቸው girmaseifu@gmail.com ሊያገኟቸው ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 8 ታኅሣሥ 27 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here