ልማት በግርድፉ ሲበየን ሰብኣዊ እና ምጣኔሀብታዊ ብልፅግናዎችን ያካትታል። የምጣኔ ሀብት ዕድገቱ መቀዛቀዝ ሁለገብ ልማትን ስለሚያቀዛቅዘው ተፅዕኖው የጎላ ነው የሚሆነው። ይህ ጉዳይ በተዘዋዋሪ የዴሞክራሲ ሒደቱን ሊያደናቅፈው ይችል ይሆን?
‘ዴሞክራሲ ለልማት አስፈላጊ ነው ወይስ አይደለም?’ የሚለው ርዕሰ ጉዳይ የምጣኔ ሀብት እና የፖለቲካ ተንታኞችን ሁሌም እንዳከራከረ ነው። የቀድሞው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በዓለም የምጣኔ ሀብት ፎረም ላይ ‘ዴሞክራሲ ለልማት አስፈላጊ ነው የሚለው ተረክ የመኝታ ሰዓት ተረት ነው’ ማለታቸው ይታወሳል፤ ዴሞክራሲያዊም፣ አምባገነናዊም የሆኑ አገሮች ፈጣን የሆነ የምጣኔ ሀብት ዕድገት ያስመዘገቡበት ታሪክ መኖሩን አስታውሰው፣ ዴሞክራሲያዊ አለመሆን በልማት ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ የሚያሳይ ‘ኢምፔሪካል’ የምርምር ውጤት የለም ብለዋል። ይሁን እንጂ ድምዳሜያቸው በብዙ ምሁራን ከትችት አልዳነም።
ማይክል ቶዴሮ እና ስቴፈን ስሚዝ የተባሉ ዕውቅ ጸሐፍት “ኢኮኖሚክ ደቨሎፕመንት” (2012) በሚለው መጽሐፋቸው ላይ ዴሞክራሲ ልማት ላይ የሚያሳደድረውን ተፅዕኖ በተመለከተ ‘ኢምፔሪካል’ ጥናቶች የተለያየ ውጤት እንደሚያሳዩ ያመኑ ቢሆንም፥ ከነዚህ ጥናቶች ውስጥ ሲሦዎቹ ብቻ ‘ዴሞክራሲ ልማት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያደርስ’ መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል። ሲሦዎቹ ‘አዎንታዊ’ ተፅዕኖ አለው ሲሉ፤ ቀሪዎቹ ሲሦዎች ምንም ዓይነት ተፅዕኖ ‘የለውም’ ብለዋል። ይህም ማለት ሁለት ሦስተኛ ያክሉ ጥናቶች ዴሞክራሲ መኖሩ ልማቱን ባይጠቅመውም እንደማይጎዳው የሚያረጋግጡ ናቸው ማለት ነው። (በሌላ አገላለጽ ይኸው ግኝት ሁለት ሦስተኛው ዴሞክራሲ አለመኖሩ ልማቱን እንደማይጠቅመው መከራከር ይቻላል፤ ሆኖም ዴሞክራሲ በራሱ መንገድ ተመራጭ መሆኑ እንደ ተጨማሪ እሴት ሊወሰድ ይችላል።)
“ኋይ አፍሪካ ኢዝ ፑር” የሚል መጽሐፍ የጻፉት ግሬጅ ሚልስ የእነማይክል ቶዴሮን ሐሳብ የሚያጠናክር ነገር ጽፈዋል። “ዴሞክራሲ ለዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት አስፈላጊ የሚሆነው ለሰብኣዊ መብቶች መከበር ሲባል ብቻ ‘ቢኖር ጥሩ የሆነ’ ነገር ስለሆነ አይደለም። ከምሥራቅ እስያ ውጭ ባሉ ታዳጊ አገራት እ.ኤ.አ. ከ1960 እስከ 2003 ባለው ጊዜ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ አገሮች ከ’አውቶክራሲዎች’ አንፃር 50 በመቶ የፈጠነ ዕድገት ማስመዝገብ ችለዋል” ብለዋል።
በተመሳሳይ የኢኮኖሚ ዕድገትም ዴሞክራሲያዊነትን ያበረታታዋል የሚል ተረክ አለ። ከቻይና (እና ከትንሽዋ ሲንጋፖር) በስተቀር እስካሁን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ በመሰለፍ ላይ ያሉ አገራት በሙሉ ተገደው ወደ ዴሞክራሲ ይሸጋገራሉ የሚል ክርክር አለ። ዕውቁ ተንታኝ ፋሪድ ዘካሪያ “ዘ ፖስት አሜሪካን ዎርልድ” ባሉት መጽሐፋቸው ላይ ቻይናም ብትሆን ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ አማካይ ገቢያ ከ5 ሺሕ እስከ 10 ሺሕ ሲሆን የዴሞክራሲ ጥያቄ አፍጥጦ ይመጣባታል ብለው ጽፈዋል። ይሁን እንጂ ቻይና ይህንን ተሻግራዋለች ብለው የሚከራከሩም አሉ።
በአገራችን ዴሞክራሲን እና ልማትን ወይም የኢኮኖሚን ዕድገት ነጣጥሎ የመመልከት ልማድ አለ። ይሁን እንጂ አንዳቸው፣ ከሌላኛቸው ጋር ግልጽ ባልሆነ ገመድ የተሳሰሩ መሆናቸውን የሚያረጋግጡ በርካታ ጥናቶች አሉ። ስለሆነም ነጣጥሎ መመልከቱ አደጋ ሊኖረው ይችላል።
ዴሞክራሲ ለልማት እንደ ቅድመ ሁኔታ…?