“ከየትኞቹም ሥራዎቼ ውስጥ ያለ ምንም ጥያቄ ‹ምን ልታዘዝ?›ን ነው የምወደው”

0
847

እንደ ደራሲው በኃይሉ ሐሳብ “ምን ልታዘዝ?” ብዙ ዓመት ቆይቶ የመሰልቸት ዕጣ እንዳይገጥመው 4 ምዕራፎችን በቆንጆ ሁናቴ ከተጓዘ፣ ምናልባት ሊቆም ይችላል፤ ‘እኛም ከምን ልታዘዝ ሴትኮም ድራማ ባለፈ ከጊዜው ጋር አብረው ሊሔዱ የሚችሉ፣ የማኅበረሰቡን ፍላጎት መሠረት ያደረጉ፣ አብሮነታችንን የሚዘክሩ፣ ማኅበራዊ ጉዳዮችን የሚዳስሱ ሥራዎችን ለመሥራትም እናስባለን’ በማለት የድራማው ደራሲና ፕሮዲውሰር ተናግሯል::
“ምን ልታዘዝ? ካፌ” የአገሪቱን የትምህርት ስርዓት፣ የፖለቲካውን ሥነ ምኅዳር፣ የሕግን ክፍተት፣ የሥራ አጡን ሁኔታ እንዲሁም በርካታ የማኅበረሰቡን ክፍተቶች በጥበብ ዓይን ከሽኖ በደግሰው ደግነት፣ በዕድል ተጫዋችነትና ተፈቃሪነት፣ በባሬስታው ዳኜ ቀማሚነት፣ በንጉሥነሽ የሙዚቃ ፍቅርና ልክፍት፣ በአቶ አያልቅበት የመሪነት ጉጉት የቤቱን ምሰሦና ማገርነት አቁመውታል።
የ“ምን ልታዘዝ?” ድራማ ዋና ጭብጥ ወይም መልዕክት ማኅበራዊ ጉዳዮችን መሠረት ያደረገ ሲሆን፥ ከዚህም ጋር ተያይዞ አገራዊ እና ወቅታዊ ጉዳዮችን አብሮ ይዳስሳል፤ ታዲያ በዚህ ኹነት ውስጥ ፖለቲካዊ ጉዳዮችም በማኅበረሰቡ ዘንድ የራሳቸው ሚና አላቸውና በትንሹም ቢሆን ይዳሰሳሉ። ይሁንና አሁን ላይ ካለው የአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር እና የሕዝቡ ዕይታ ጋር ተዳምሮ ድራማው ፖለቲካዊ አንድምታ ያለው ቢመስልም እንኳን፣ በመሠረታዊነት ማኅበራዊ ሐሳቦችን ይዳስሳል። ‘የድራማውም መቼት ከካፌ ውስጥ ያደረገበት ምክንያት እነዚህኑ ሐሳቦች በስፋት የምናነሳው፣ ምንወያየውና የምንከራከረው በዚሁ ካፌ ውስጥ በመሆኑ ነው’ ይላሉ አዘጋጆቹ።
በ“ምን ልታዘዝ?” ድራማ ውስጥ ዓይነተኛ ሚና ካላቸው ገጸ ባሕርያት መካከል አንዱ ጋሽ አያልቅበት ናቸው። ጋሽ አያልቅበት እንደ ሥማቸው ሁሉ ተንኮል የማያልቅባቸው የካፌው አስተዳዳሪ የነበሩ፣ በኋላም ከማዕረጋቸው ወርደው በአስተናጋጅነት ሲሠሩ ይታያሉ፤ እኚህን ገጸ ባሕርያት ሁነኛ አድርጎ እየተጫወታቸው ያለው አርቲስት ሚካኤል ታምሬ የዚህኛው እትማችን እንግዳ ነው።
አርቲስት ሚካኤል ታምሬ እዚሁ አዲስ አበባ እንግሊዝ ኤምባሲ አካባቢ ነው የተወለደው። የ‘ኤለመንተሪ’ ትምህርቱን በቀበና አድቬንቲስት የተማረ ሲሆን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በአቃቂ አድቬንቲስት (boarding school) አዳሪ ትምህርት ቤት ተምሯል። ቀጥሎም ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመግባት የቴያትር ዲፓርመንት ተማሪ እንደነበር ይናገራል።
በትወናው ዓለም ወደ ዐሥራ አምስት ዓመታት አካባቢ ያስቆጠረው ሚካኤል ከዩኒቨርሲቲ ተመርቆ ከወጣ በኋላ ወደ ትወናው አለመቀላቀሉን ይናገራል፤ ይልቁንም አምስት፣ ስድስት ዓመታት ከሙያው ጋር የተያያዙ ሥራዎችን በመሥራት አሳልፏል። ሚካኤል የትወናውን ሕይወት ከተቀላቀለ በኋላ ከ35 በላይ ፊልሞች፣ አምስት ቲያትሮች እና ሁለት የቴሌቪዥን ድራማዎች ላይ በመሳተፍ የተዋጣለት ተዋናይ መሆኑን አስመስክሯል።
ይህንን በአጭር ጊዜ ውስጥ ተወዳጅነት ያተረፈ ‘ሲትኮም’ አስመልክቶ የአዲስ ማለዳው ሳምሶን ገድሉ የጋሽ አያልቅበትን ገጸ ባሕሪይ ተላብሶ የሚጫወተው ሚካኤል ታምሬ ጋር ቆይታ አድርጓል።
አዲስ ማለዳ፦ አሁን እየሠራችሁ ስላላችሁት ሲትኮም ድራማ እናውራ፥ በሚካኤል ታምሬ ዓይን ጋሽ አያልቅበት ምን ዓይነት ሰው ናቸው?
ሚካኤል ታምሬ፦ በሚካኤል ታምሬ ዓይን ብቻም ሳይሆን ‘ካራክተር አናሊሲስ’ ስንሠራ፣ ከዳሬክተሩና ከጸሐፊውም ጋር ስናወራ አቶ አያልቅበት የአንድ ካፌ አስተዳዳሪ የነበሩ ሰውዬ ናቸው። በየትኛውም መስክ ላይ ያለን የአመራር ጥበብ ያለውን ሰውም ይወክላሉ ብለን እናስባለን። አሁን ለምሳሌ በጣም ባሕላዊ የሆነ የአመራር ሁኔታ አለ፤ በጣም አምባገነናዊ የሆነም የአመራር ጥበብ አለ። ጋሽ አያልቅበትን የመሰሉ ሰዎችንም በየመሥሪያ ቤቱ፣ በየካምፓኒው፣ ቀበሌ ውስጥ እንዲሁም በአገር ደረጃም ልታገኛቸው ትችላለህ። እና የአቶ አያልቅበት መንገድ የተለመደውና ብዙ ጊዜ አብረን የኖርነው ዓይነት የአመራር መንገድ ነው ብዬ ነው የማስበው።
ከተቀባይነት አንፃር ሲትኮሙና ጋሽ አያልቅበት ምን ደረጃ ላይ ነው ያሉት ትላለህ?
በጣም ጥሩ ነው! እኛ ከጠበቅነው በላይ ነው የሆነው። እውነት ለመናገር ሥራውን ስንጀምረው ጥሩ ሥራ ለመሥራት አስበን ነበረ። ከተቀባይነት አንፃርም መሰናክል ሊገጥመው እንደሚችል ተሰምቶን ነበር። ይሔ የሆነውም ለምንድነው? እዛች አንድ ካፌ ውስጥ ወጣ ያሉ ገጸ ባሕርያትን ይዘን ስንመጣ፥ ሰው መረዳት ከቻለና ራሱን ከገጸ ባሕርያቱ ጋር ማገናኘት ከቻለ ራሱን ውስጥ ስለሚያገኘው ውጤታማ እንሆናለን የሚል ሐሳብ ነበረን። ካልሆነ ግን የልጆች እቃቃ ጨዋታ ሊመስል እንደሚችልም እናውቅ ነበረና ስታየው የሚመጣው ችግር መሐል ላይ አይደለም፤ ወይ ቆንጆ ይሆናል ወይ መጥፎ ይሆናል የምትለው ነገር አይደለም። ግን ምንድነው ነው ተቀባይነት ሊኖረው ይችላል የሚለው ስሜት እንዲኖረኝ ያደረገኝ ስንሠራው እኛ ራሳችን በጣም ዘና እንልበት ነበረ። እና ይሄ ሁኔታ ሌላ ሰውም ቢያየው ሊዝናናበት ይችላል ወደሚል ሐሳብ ገፍቶናል።
በአገራችን እንዲህ ዓይነት ማኅበራዊ ሒስ ላይ የሚያተኩሩ ‘ሲትኮሞች’ ብዙም አልተለመዱም። ታዲያ የ“ምን ልታዘዝ?” ወደ ቴሌቪዥን መምጣት ፋይዳው ምንድነው?
የ“ምን ልታዘዝ?” ፋይዳ ከማኅበራዊ ጉዳይ ብሎም ብዙም የማይደፈሩ የፖለቲካ ጉዳዮችን ከነአስተሳሰባቸው መተቸት መጀመር ነው። ይሔ ሁለት ፋይዳ አለው ብዬ አስባለሁ፣ አንደኛ አስተዳደር ላይ ያሉ ሰዎች ምን ዓይነት ነገር ውስጥ እንዳሉ፣ ምን እየሠሩ እንደሆነ፣ ኅብረተሰቡ በምን ዓይን እያያቸው እንደሆነ፣ በጣም ቀለል ባለ መንገድ መግለጽ ትችላለህ። ሁለተኛ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም የሚሉት ነገር አለ “እዚህ ሀገር ዕውቀት ከሥልጣን ይመነጫል እንጂ፣ ሥልጣን ከዕውቀት አይመነጭም”። ሥልጣን ላይ ወጣህ ማለት ሁሉን ነገር ታውቃለህ ማለት አይደለም። ብዙ ጊዜ የምናየው መሪዎቻችን ሥልጣን ላይ ሲወጡ የማዳመጥ አቅማቸው እየቀነሰ እየቀነሰ ይመጣል። ስለዚህ በእንደዚህ አይነት ቀላል መንገድ ስህተታቸውን መንቀስ ብቻም ሳይሆን እነሱም ሰው እንደሆኑ እንዲያስቡ ማድረግ ትልቅ የመነጋገሪያ በር ይከፍታል። ስለዚህ ትልቅ ማኅበራዊ ፋይዳ አለው ብለን የምናስበው ምንድነው? ያሉትም ያለፉት ላይም ስህተት መስሎ የታየንን ነገር መተቸት ነው። ይሄ ደሞ እነሱን ወደ ሰውነት ያመጣቸዋል። ሕዝቡም ደሞ በአንፃሩ መተንፈሻ ያገኛል ማለት ነው።
ጋሽ አያልቅበትን ሆነህ ከሠራህ በኋላ ወደ የዕለት ተለት የግል ኑሮህ ላይ ስትገባ ያመጣብህ ተፅዕኖ አለ?
አይ ብዙም የለም። እውነት ለመናገር በግል ህይወቴ ከጋሽ አያልቅበት ጋር በጣም ተቃራኒ ነን።
“ምን ልታዘዝ?” ላንተ የጨመረልህ ነገር አለ?
አለ፤ እውነት ለመናገር “ምን ልታዘዝ?”ን እንደሥራ አይቼ የምሠራው ነገር አይደለም። “ምን ልታዘዝ?” የራሴ ሥራ እንደሆነ ነው የማስበው። አንደኛ በ“ምን ልታዘዝ?” ውስጥ በኪነ ጥበብ ምን ያክል መሥራት እንደሚቻል አይቼበታለሁ። ሁለተኛ እዛ ያሉትን የተለያየ ከለር ያላቸውን ገጸ ባሕርያት የማጣጣምና እና የማመጣጠን ጉዳይ ለዳይሬክተሩና ለጸሐፊው ብቻ የምተወው ነገር አይደለም፤ ምክንያቱም ምን ልታዘዝ የራሴ ነው። አሁን ለምሳሌ ስክሪፕት ተቀብለን ዓይተን ከተስማማን በኋላ ነው ወደ ሥራ የምንገባው። የጋራ ሥራና የጋራ ውጤት የሆነ ጥሩ ልምድ አግኝቼበታለሁ።
“ምን ልታዘዝ?”ን ስትሠሩ እና ወደ ስርጭት ስትገቡ ኢትዮጵያ ውስጥ አለመረጋጋት የነበረበት ጊዜ እንደመሆኑ እና ማኅበራዊ ሒሶችን ስታነሱ ፖለቲካውም አንዱ ጉዳይ ነውና በወቅቱ ያጋጠማችሁ ችግር አለ?
እንደ እውነቱ “ምን ልታዘዝ?”ን የጀመርነው ዶ/ር ዐብይ ሥልጣን ላይ ከወጡ በኋላ ነው፤ ወደ አየር ላይ የተለቀቀው ከዛ በኋላ ነው ነገር ግን ከዚያ በፊት ተከልክለን አልነበረም። በዝግጅት ነበር ያሳለፍነው። ይሄም ረዘም ያለ ግዜ ወስዷል። ስንጀምረው ለምሳሌ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ሒስ የምንሰጥበት ‘ሲትኮም’ ሆኖ ነው፤ ያ ‘ሲትኮም’ ደግሞ በፋና ቴሌቪዥን ላይ ነው የሚታየው፤ ይህም ማለት እንግዲህ ከገዢው ፓርቲ ጋር የጥቅም ትስስር ወይም ግንኙነት አለው ተብሎ ከሚታሰብ ድርጅት ጋር ነውና ሰዎች በሁለት ዓይነት የጥርጣሬ ዓይን ነበር የሚያዩን። አንደኛው፣ አውርቶ አስወርቶ የሆነ ችግር ለማምጣት ዓይነት ነው የሚልም ነገር አላቸው፤ ምን ለማለት ነው? መጀመሪያ ላይ ሐሳቡም አልገባቸውም ነበር። ራሳቸውም ሚዲያውን እንደ ገለልተኛ የሚዲያ ተቋም የማየትም ችግር ነበረባቸው፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ይህንን እነርሱ ጋር ልታሳዩ ነው እንጂ ሌላ የግል የሚዲያ ተቋም ብትወስዱት ማን ያሳይላችኋል? ባለቤቷን የተማመነች በግ ላቷን ውጭ ታሳድራለች ዓይነት ነገር ተማምናችሁ ነው እንጂ፣ ሌላ ቦታ ቢሆን አትሠሩትም ነበር ዓይነት ነገር ነበር። እናም የመጀመሪያው እርምጃ ድፍረቱ ነው፤ ፕሮዲዩሰሩ፣ ዋና አዘጋጁና ጸሐፊው በኃይሉ ዋሴ (ዋጄ) እንዲሁም እኛ ኃላፊነቱን ወስደን ነበር። ካልሆነ ሦስትና አራት ክፍል አሳይተን ከፈለገ ይዘጋ የሚል ዓይነት ሥምምነት ነበረን። በዛ ዓይነት ሁኔታ ስንሠራ የመጀመሪያዎቹ ክፍሎች ላይ ሰው የመደናገጥ እና የመደናገር እና ግራ የመጋባት ሁኔታዎች ነበሩት።
ሰዉ እየለመደንና ተመልካች እየጨመረ ሲመጣ አንዱ ችግር የሆነብን ነገር መጀመሪያ ላይ የገዢውን ስርዓት የምንደግፍና ለእርሱ የምንሠራ፣ ከዚያም ደግሞ የገዢውን ስርዓት የዶክተር ዐቢይን ንግግር አሳምራለሁ ብለው አበላሽተዋል ብለን ካመንን እርሳቸውን ለመተቸት ወደኋላ አንልም፣ ቲም ለማን ለመተቸት ወደኋላ አንልም፣ ዲያስፖራውንም ለመተቸት ወደኋላ አንልም ነበር፤ እናም ባለፈው ሳምንት በቃ ድራማ ማለት ይሄ ነው ብሎ ሲያወድሰን የነበረው ሰው፣ በሚቀጥለው እኔምኮ ድሮም ጠርጥሬ ነበር እነዚኮ’ የውስጥ አርበኞች ናቸው ነገር አለው። በወቅቱ ቋሚ ተመልካች አልነበረንም። ይህንን መሸከም የሚችል ማኅበረሰብ ገና አልገነባንም፣ አላፈራንም እና የተለያየ ሐሳብ ለመተቸት ስትሞክር የሚኮረኩምህን ሰው ትቀይራለህ እንጂ ኮርኳሚው አይጠፋም፤ ባጠቃላይ ግን ብዙ ወዳጆችን አፍርተናል።
ወቅታዊ ጉዳዮችን ነው ከሳምንት፣ ሳምንት የምታነሱት እና ይሄ በሥራችሁ ጥራት ላይ የራሱ የሆነ ተፅዕኖ የለውም?
ተፅዕኖ አለው። በመሠረቱ ሁሉንም የማኅበራዊ ጉዳይ አይደለም ከሳምንት ሳምንት አንስተን የምናልፈው፤ ከመነሻው “ምን ልታዘዝ?” ቅርፅ (ፍሬም) አለው። ለምሳሌ ምዕራፍ አንድ የት ተጀምሮ የት እንደሚጠናቀቅ፣ ምዕራፍ ሁለትም የት ተጀምሮ የት እንደሚጠናቀቅ ቀድመን ያስቀመጥነው ቅርፅ አለን። የመጀመሪያው ምዕራፍ ሲያልቅ ካፌው ምን ይሆናል? ምዕራፍ ሁለት ሲጠናቀቅ የካፌው ዕጣ ፈንታ ምን እንደሚሆን በቅርፁ መሠረት ነው የምንሔደው። ለሚፈጠረው አዳዲስ ነገር ቦታ ትተን እናልፋለን፤ እነዚህ ባዶ ቦታዎች ላይ ካስቀመጥነው ቅርፅ አንፃር ካፌው ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ ምንድነው ብለን ነው የምናስገባው እንጂ፣ ልክ እንደ ‘ስታንድ አፕ ኮሜዲ’ ዓይነት ቅርፅ አይደለም ያለው። ቅርፁ ውስጥ እያመጣን ነው እነዚህን አዳዲስ ጉዳዮች የምንሰካው፤ አንዳንዶቹ ጉዳዮች የግድ ተዳሰው መታለፍ ያለባቸው ስለሆኑ ማለት ነው።
የ“ምን ልታዘዝ?” ግብ ሰዎች ቁጭ ብለው የሚያወሩበትን ርዕሰ ጉዳይ አጀንዳ አበጅቶ መስጠት ነው እንጂ ለችግሮች መፍትሔ ማመላከት አይደለም ማለት ነው?
እውነት ነው፤ የሚያወሩበትን አጀንዳ ማበጀት ነው። ከዚያ አልፈን የመፍትሔ ሐሳብ ለመጠቆም አቅሙም ያለን አይመስለኝም፤ በአገራችን በዚህ ደረጃ የሚታየውን ችግር በዚህ መልኩ መፍትሔ ስጡት፣ በዚህ መልኩ ፍቱት ማለት ነው እና ያንን ማለት የምንችል አይመስለኝም ። ችግሩ ምን ያክል የተወሳሰበ መሆኑን እያየን ነው። ነገር ግን ከዚህ ድራማ ሰው እንዲያገኝ ያሰብነው አጀንዳ ፈጥረን ማለፍና እንዲያወራበት ማድረግ ነው።
‘ምን ልታዘዝ?” ብዙ ሽልማቶችን አፍሷል። መሸለማችሁ ምን ለውጥ አመጣ?
እውነት ለመናገር መሸለማችን የድካማችን ውጤት ነው። ትልቁ ሽልማታችን ደሞ ሰዉ መቀበሉ ነው። ለምሳሌ ‘የተመልካቾች ምርጫ’ ላይ ብዙ ሰው መርጦታል። ስለዚህ ሰዉ ገብቶታል ማለት ነው። ‘ሰው ይረዳን ይሆን?’ የሚል ፍራቻ ነበረብን።
የምን ልታዘዝ መጨረሻ መቼ ነው ሚሆነው?
ፕሮዳክሽን ስብስብ ውስጥ ስላለሁበት በእርግጠኝት የምነገርህ ሦስት፣ አራት ዓመት የሚቀጥል ዓይነት ሲትኮም እንደማይሆን ነው። ለራሳችን በጣም ታማኝ መሆን እንፈልጋለን። ስለዚህ ሰዎች እንደሚሉት እየተፈጠሩ ያሉትን ነገሮች ለሕዝቡ በተገቢው ሁኔታ እያስተጋባንና እያሳየን እንደሆነ ሲሰማን ታማኝ ሆነን እናቆመዋለን።
እስኪ ወደ አንተ እንመለስ እና ምን ያህል የኪነ ጥበብ ሥራዎች ላይ ተሳትፈሃል?
ፊልም ከ35 በላይ የሚሆን ሠርቻለው፤ ምን ያክሉ ጥሩ ነው የሚለውን እንጂ በቮሊዩም ብዙ ሰርቻለሁ። ቴአትር አሁን እየሠራሁ ያለሁት አምስተኛዬ ነው። የቴሌቪዥን ድራማ ከዚህ በፊት ሁለት ሰርቻለው። ዋናው ሥራ አስኪያጅ የሚል እና በመቀጠል ደሞ ዳና ላይ ሠርቻለሁ።
የትኛው ሥራህ በደንብ ከሰው ጋር አስተዋውቆሀል?
ያው የቴሌቪዥን ድራማ ቴሌቪዥን በየቤቱ ስለሚገባና በየሳምንቱ ስለምትታይ እሱ በደንብ ያስተዋውቅሀል። እውነቱን ለመናገር ግን ደስ እያለኝ የምሠራው የመድረኩን ሥራ ነው።
እስካሁን ከሠራሃቸው ሥራዎች አወዳድር ብትባል የትኛውን ትመርጣለህ?
ከየትኞቹም ሥራዎቼ ያለምንም ጥያቄ “ምን ልታዘዝ?”ን ነው የምወደው። ከዛ ቀጥሎ ‘የሚስት ያለህ’ የሚለውን ቴአትር በጣም ነው የምወደው። በጣም ከምወዳቸው አርቲስቶች ከነ ሽመልስ አበራ፣ አዜብ ወርቁ፣ ፈለቀ አበበን ከመሳሰሉት ጋር ትልቁን ድርሻ ወስጄ በመሥራቴ በጣም ነው የምወደው፤ ቢሆንም ግን ከ“ምን ልታዘዝ?” ጋር አይወዳደርም።
ጋሽ አያልቅበት የሰው ልብ ውስጥ ያሉ ሰው ይመስላሉ፤ እንደው የገጠመህ ነገር ካለ?
ጋሽ አያልቅበት በጣም አምባገነን ሰውዬ ናቸው፤ ተንኮልን ሥራዬ ብለው የሚሠሩ ሰውዬ ናቸው። ግን እንዳልከው ሰው ልብ ውስጥ ያሉ ሰው ናቸው መሰለኝ ጋሽ አያልቅበትን ብዙ ሰው አይጠላቸውም። በሆነ መንገድ የሚያውቀውን ሰው ወይ ራሱን አገናኝቶ ያስባል እንጂ አይጠላቸውም። አንዳንዴ እኩይ ገጸ ባሕርይ ስትሠራ ሰው ይጠላሀል። መንገድ ላይ ሲያይህም ‘ይሄ ክፉ’ ምናምን ነው የሚልህ፤ ለኔ ግን ተመልካች እንደዛ ዓይነት ነገር የለውም። አምባገነንነታቸውን ሳይደብቁ ፊት ለፊት የሚያደርጉ ሰው ስለሆኑ የሕይወት አንድ አካል እንደሆኑ አስቦ ብዙ ሰው ዘና ሲልባቸው ነው የማየው።
በመጨረሻም ማለት የምትፈልገው ነገር ካለ…?
በ“ምን ልታዘዝ?” ብዙ ተከታታይ ማግኘታችን በጣም ደስ ይለናል። ሦስተኛውን ምዕራፍ ደሞ የተመልካቹን ክብር በሚመጥን መልኩ ለመሥራት ትንፋሽ ወስደን ልንመጣ ነው እና ጠብቁን ነው የምለው። በመጨረሻም መልካም የገና በዓል ይሁንላችሁ!

ቅጽ 1 ቁጥር 8 ታኅሣሥ 27 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here