ገብረመድህን አርዓያ የሕወሓት ነባር ታጋይ ሲሆኑ አሁን ፐርዝ፣ አውስትራሊያ በስደት ላይ ይገኛሉ።
ወታደራዊ ሥልጠና በመውሰድ ከተራ አባልነት ጀምሮ የሕክምና ክፍል ኀላፊ፣ የኢኮኖሚ ዘርፍ ኀላፊ እንዲሁም በስንቅና ንብረት ሥራ መደቦች ሕወሓት ሲያካሂድ በነበረውን ትግል ተሳትፈዋል። ዘግይተውም ቢሆን ሕወሓት በተለይም ከፍተኛ አመራሩ ቆሜለታለው ለሚለው የትግራይ ሕዝብ እንኳ የማይመለስ መሆኑን ከ1970ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ በድርቅ ምክንያት የተከሰተውን ረሃብ ለማስታገስ የተለገሱ እህሎችን ዓየር ባየር ሲነግድ የነበረ መሆኑን እንዲሁም የትግራይ ሕዝብን በሰብኣዊ ጋሻነት በተደጋጋሚ መጠቀሙን በማረጋገጣቸው አመቺ ጊዜና ሁኔታ ጠብቀው ከድርጅቱ በመክዳት ካርቱም፣ ሱዳን ላይ በፈቃዳቸው ለደርግ መንግሥት መስከረም፣ 1981 እጃቸውን ሰጥተዋል።
ገብረመድህን እጃቸውን ከሰጡበት ጊዜ አንስቶ እስከ ግንቦት 1983 በአገር ውስጥ፣ እንዲሁም ከዚያም በኋላ በስደት ላይ ሆነው ላለፉት 32 ዓመታት ያለመታከት የሕወሓት ድብቅ ተልዕኮ እና የ“ኢትዮጵያ ጠልነት” የሚሉትን ሴራ በማጋለጥ በይበልጥ ይታወቃሉ።
ትግራይ፣ ዓድዋ ከተማ የተወለዱት ገብረመድህን፥ በአድዋ ውስጥ በሚገኘው ንግሥተ ሳባ ትምህርት ቤት የመጀመሪያና ኹለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታለው ከጨረሱ በኋላ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በ1960ዎቹ የመጀመሪያ አጋማሽ የአዲስ አበባ ንግድ ሥራ ትምህርት ቤት የከፍተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለው ተመርቀዋል። በሥራ ዓለምም በገንዘብ ሚኒስትር ዋና መሥሪያ ቤት ተቀጥረው አገልግለዋል።
አዲስ ማለዳ ጋዜጣ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ዙሪያ በተለይም የፌደራል መንግሥት ትግራይን ያስተዳድር በነበረው ሕወሓት ላይ እየወሰደ ያለውን ሕግ የማስከበር እርምጃ፣ ስለትግራይ ሕዝብ፣ የሕወሓት አመራር እጣ ፈንታን በተመለከተ ከገብረመድህን አርዓያ ጋር የሚከተለውን ቆይታ አድርጋለች።
አዲስ ማለዳ፡ ሕወሓት ከመነሻው የነበረው እንቅስቃሴ ምን ይመስል ነበር?
ገብረመድህን አርዓያ፡ ሕወሓት የተጠነሰሰው አዲስ አበባ ፒያሳ መብራት ኀይል ሕንፃ አካባቢ የሚገኝ አንድ ቡና ቤት ውስጥ ነበር። በምስረታው ላይ በአረጋዊ በርሄ ሰብሳቢነት ግደይ ዘርአፂዮን፣ ዘርኡ ገሰሰ (አግአዚ)፣ ስዩም መስፍን፣ ብርሃነ እያሱ እና አባይ ፀሀዬ ተሳትፈዋል።
በዚህ ወቅት ትልቁ የመወያያ አጀንዳ የነበረው ኢትዮጵያን የሚገነጣጥል እና የሚያፈራርስ ፕሮግራም በማውጣት ብሔር ብሔረሰቦችን በመከፋፈል ወደ ሕዝባዊ ሽኩቻ የሚገቡበትን መንገድ ካመቻቹ በኋላ ወታደራዊ ሥልጠና ለማግኘት ወደ ሻአቢያ ሄደው ከተመለተሱ በኋላ በወርሃ የካቲት 1967 ወደ ደደቢት በርሃ በመግባት የትጥቅ ትግላቸውን በይፋ ጀመሩ።
ከኹለት ወር ቆይታ በኋላ ለገሰ ዜናዊ (መለስ) እና አቦይ ስብሃት ነበር የተቀላቀሏቸው። በዚህ የትግል ወቅት የትግራይ ሕዝብ ከእነርሱ ጋር አልነበረም ምንም ዓይነት ድጋፍ ሊያደርግላቸው ፈቃደኛ አልነበረም። ይልቁንም የተወሰኑ የአረብ አገራት ኢራቅን ጨምሮ የተወሰነ ድጋፎች ያደርጉላቸው ነበር። በምስረታው ወቅት ከነበሩት አባላቶች መሀከል አሁን ሦስቱ በሕይወት የሉም።
ሕወሓት በ17 ዓመታት በትጥቅ ትግል፣ ለ27 ዓመታት በገዢ መንግሥትነት እንዲሁም ላለፉት ኹለት ዓመት ተኩል ገደማ በትግራይ ተወስኖ ከቆየ በኋላ የሰሜን እዝ ላይ ያልተጠበቀ ጥቃት በመሰንዘሩ የፌዴራል መንግሥት ሕግን ለማስከበር በወሰደው የአፀፋ ምላሽ ትግራይን ከማስተዳደርም ተባሯል። የዚህ ሽንፈት አንድምታው ምንድነው?
ሕወሓት ለሽብር የተፈጠረ ተቋም ነው። ይህንንም አጀንዳውን በ17ቱ የትጥቅ ትግል ዓመታት በትግራይ ሕዝብ ላይ የጭቆናና የአፈና መዋቅር በመዘርጋት ሲያስጨንቅ ከርሟል። በሌላም በኩል የአማራን ሕዝብ ላይም በተመሣሣይ ጭቆናውን አሣርፏል። በተለይ በአማራው ሕዝብ ላይ ከነበረው ከፍተኛ የጥላቻ ስሜት በመነሳት ጨቋኝ ገዢ መደብ አድርጎ በመፈረጅ የትግሉ ትልቅ አጀንዳ አድርጎ ሲንቀሳቀስበት ቆይቷል።
ሌላው ሕወሓት ለ27 ዓመት በሥልጣን ላይ በሚቆይበት ጊዜም የመንግሥት ተቋማትን በቁጥጥር ሥር በማዋል በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ በፕሮፓጋንዳ እና ባለው አማራጭ ሁሉ ተጠቅሞ የኢትዮጵያን ሕዝቦች ሲጨቁንና ሲረግጥ የቆየ ስርዓት የፈጠረ ነው። በዚህ ሁኔታ ጭቆናው የበዛበት የኢትዮጵያን ህልውና ሲያራክስ ቆይቷል።
ሕዝቡንም በቋንቋ በክልል፣ በጎሳ ከፋፍሏል። ብሔር ተኮር ስርዓቱ ለአገሪቱ የሰላም እጦት ገፊ ምክንያት እየሆነ በመምጣቱ የሕዝብ አልገዛም ባይነት እንዲጨምርና የሕወሓትም የአገዛዝ ስርዓት ላይ እንዲያምጽ በማስገደድ ለእድሜው ማብቃት ትልቅ አስተዋጽዖ አበርክቷል።
ከዚህም በኋላ ያለውን ነገር ሁሉ ሰብስቦ መቐለ እንዲገባ ሆኗል። ሕወሓት መቐለ ከገባም በኋላ ለፌዴራል መንግሥት አልገዛም። ነፃ አገር ነኝ፤ የትግራይን መንግሥት አቋቁማለሁ ብሎ በማሰብ ይህን ግቡን ለማሳካትም የፌዴራል መንግሥቱን ለማወክ ሲንቀሳቀስ የቆየ አሸባሪዎች ቡድን ነው።
ሕወሓት የሰሜን ዕዝ ላይ ጦርነት መክፈቱ ከአፈጣጠሩ አንጻር አያይዘው ቢለልጹልን?
ከሕወሓት አፈጣጠር ባህሪው አንጻር በሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመውን ክህደት ስናየው የሚያስገርም አይሆንም። ሕወሓት ሽብርተኛ ስለሆነ እና በሽብር ተግባር ላይ የተሰማራ በመሆኑ ከ20 ዓመት በላይ ሲጠብቀው በነበረው ሠራዊት ላይ ያደረገው ጽዩፍ ተግባር በትክክል ያደገበት ባህሪው መሆኑን ነው የሚያሳየው።
እንደማሳያ ለመጥቀስ ያክል በ1968 ግንባር ሃርነት ገስገስቲ ትግራይ የሚባል ድርጅት ነበር። የዚህን ድርጅት አመራሮች በሙሉ “ኑ እና እንወያይ” ብሎ ከጠራቸው በኋላ በተኙበት ጥይት በማርከፍከፍ ፈጅቷቸዋል። ይህ የሚያሳየው ሁሌም ከኋላ ዞሮ የሚሠራቸው ደባዎች ለእርሱ መገለጫ ባህሪያቶቹ እንደሆኑ ነው ።
በሰሜን ዕዝ ላይም የፈፀመው ይህንኑ ነበር። ይህንንም ያደረገበት ዋና ዓላማ ሠራዊቱን ገድዬ የጦር መሣሪያውን ማርኬ ትግራይን ነፃ አወጣለሁ ብሎ በማሰቡ የወሰደው የሸፍጥ እርምጃ ነው። ይህ አድራጎቱ ሽብረተኝነቱን ቁልጭ አድርጎ ያሳየበት በመሆኑ በሽብርተኝነት እንዲፈረጅ እና እንዲቀጣም ያስፈልጋል።
አንዳንድ ተቺዎች የትግራይ ሕዝብ ከአራት ዐሥርታት በላይ በሕወሓት አስከፊ አገዛዝ ሥር ቆይቷል ይላሉ። የሕወሓት መደምሰስ ለትግራይ ሕዝብ ምን ፋይዳ ይኖረዋል?
ይህ አጋጣሚ ለትግራይ ሕዝብ አንድምታ በጣም ትልቅ ነው። የሕወሓት መደምሰስ የትግራይ ሕዝብ ሙሉ በሙሉ የሚደግፈው ጉዳይ ነው። ምክንያቱም በመጀመሪያ ደረጃ ለ46 ዓመት በባርነት ሲገዛው የነበረ ስርዓት ነው። ከላዩ ላይ የተነሳለት የትግራይ ሕዝብ የመናገር መብቱን ተገፎ በጭቆና በችግርና በመከራ ሲረገጥ የኖረ ሕዝብ ነው። ስለዚህ ይህ ድል ለሕዝቡ እንደ ከፍተኛ ድል ነው የሚቆጠረው።
ከዚህም ባለፈ ድሉ ለኢትዮጵያ ሕዝብም ከፍተኛ አንድምታ አለው። የዚህ ስርዓት መደምሰስ ትልቅ አስተዋጽዖ ይኖረዋል። ከአሁን በኋላ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሕወሓት የሚባል ስርዓት “ነበር” ተብሎ እንዲዘጋለት የሚፈልግ እንጂ በድጋሚ ሥሙን ለመስማት ፍላጎት ያለው አካል አለ ብዬ አላምንም።
ለዚህ ትልቅ ምክንያቱ ደግሞ ሕወሓት በሥልጣን ዘመኑ ሲገድል፣ ሲያባር እንዲሁም የአገርን ሀብት ሲዘርፍ የቆየ ማፊያ ቡድን በመሆኑ ሽንፈቱ ለአገር ትልቅ ድል ነው።
ለብዙ ዓመታት በውጭ ሆነው ሲታገሉት የነበረው ጨቋኝና ነጣጣይ የሚሉት ስርዓት ተደምስሷል። ታዲያ በአገር ውስጥም ሆነ በውጪም ካሉ ቤተሰብ ወዳጅ ዘመዶችዎ ጋር ተገናኝነተዋል?
እስከአሁን አልተገናኘሁም።
የሕወሓት ከፍተኛ አመራሮች በቁጥጥር ሥር መዋል ጀምረዋል። አንዳንዶችም በቀጥታ እጅ እየሰጡ ይገኛሉ። አዲስ አለም ባሌማ (ዶ/ር) እና ኬሪያ ኢብራሒም በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ናቸው። በእርሶ አተያይ የሌሎች አመራሮች እጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል?
ሌሎች አመራሮች መያዝ ወይም መደምሰስ አለባቸው። ከተቻለ ከተሸሸጉ የቀበሮ ጉድጓድ ቆፍሮ በማውጣት ለሕግ መቅረብም ይኖርባቸዋል። በሠሩት ወንጀል ሁሉ መጠየቅ አለባቸው። በቆዩበት ዘመን ሁሉ የኢትዮጵያን ሀብት የመዘበሩ፣ ዜጎችን የበደሉና ያሰቃዩ በመሆናቸው ከተተዉም ሌላ ጠንቅ ስለሚሆኑ መደምሰስ እንዳለባቸው አምናለሁ።
ሕወሓት ከትግል ዘመኑ ጀምሮ ህልውናው አደጋ ውስጥ የሚወድቁበት አጋጣሚዎች እንደ “ሕንፍሽፍሽ” ያሉ ታሪኮችን ያለፈበት አጋጣሚዎች እናስታውሳለን።
በሥልጣን ዘመኑም በ1993 ላይ የደረሰበትን የውስጥ የመፈረካከስ አደጋ የተቆጣጠረበትን አጋጣሚ እናስታውሳለን። ከዚህ በመነሳት አሁን የገባበትን አዘቅትና ውድቀት ተቋቁሞ የማገገም አቅም ይኖረዋል? ወደ ሽምቅ ውጊያስ ይገባል?
በፍፁም አላስበውም፤ ሊሆንም አይችልም። የሕወሓት አመራር ከዚህ በኋላ ወደ በርሀ በመግባት የሚችል አቅም የሌለው የሞተ ሬሳ ቡድን ነው። ወደ ሽምቅ ውጊያ እንገባለን የሚሉትም ለጉራ እና ለውሸት ነው። የሚያወሩት ነገር በሙሉ ሕዝብን በማደናገጥ ውዥንብር ለመፍጠር ካልሆነ በስተቀር የሚፈጥሩት አንድም ነገር አለ ብዬ አላምንም።
በርሀ ወጥተው ለመዋጋት አቅምም የላቸውም፤ የሕዝብ ድጋፍም አያገኙም በምንም ተዓምር የትም ቦታ ተንቀሣቀሰው ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያን ህልውና አደጋ ላይ ይጥላሉ ተብሎ አይታሰብም። ይህን የሚሉት ሰዎች እድሜያቸውም የገፋ፤ አንድ እግራቸው ወደ ጉድጓድ የገባ፤ የሕይወት ዘመናቸው የጨረሱ በመሆናቸው ይህን ሊያደርጉ የሚችሉበት ምንም ዓይነት አቅምና ድጋፍ የላቸውም ባይ ነኝ።
ዐቢይ አሕመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ መምጣትን እንዴት ተቀበሉት?
ዐቢይ አሕመድ በጣም የበሰሉ እና በሚገርም ሁኔታ አስተዋይ ሰው ናቸው። በፖለቲካም ሆነ በወታደራዊ አመራር እጅግ የላቀ እውቀት ያላቸው ትልቅ መሪ ሊባሉ ይችላሉ። ዐቢይ ላይ ይደርሱ የነበሩት ተጽዕኖዎች ምንጫቸው ደግሞ ይታወቃል። ሕወሓቶች “ሥልጣኑ ከእጃችን ሲወጣ ምን እንሆናለን” ከሚል ስጋት የመነጨ ነው። ሕወሓት የዘላለም ህልሙ እርሱ ብቸኛ ገዢ ሆኖ መቀጠል ነው። በዚህ የሞተና ኋላ ቀር አስተሳሰበቸው የተነሳ ዐቢይ በከፍተኛ ሁኔታ ችግር አጋጥሟቸዋል።
ይሁንና ጠቅላይ ሚንስትሩ በሳልና ብልህ የአመራር ብቃት ስለነበራቸው ተቆጣጥረውታል ብዬ አምናለሁ። አሁን ላይ እኔ ስለ ዐቢይ የሚሰማኝ በጣም ትልቅ አስተዋይ መሪ መሆናቸው ነው። እነኚህን የሕወሓት ማፊያ አመራሮች በዚህ ደረጃ ለመጣል የሄዱባቸው ስልቶች ትልቅነታቸውን ያሳያሉ። በውትድርና ዓለምም ያላቸው የጦር አመራር እውቀታቸው በተለይ ትልቅ መሪ መሆናቸው የሚያመስክር ጉዳይ ነው። ዐቢይ የትግራይንም ሆነ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከሕወሓት አገዛዝ ነፃ በማውጣታቸው ትልቅ ባለውለተኛ ተደርገው ሊቆጠሩ ይገባቸዋል ባይ ነኝ።
የሕወሓት አመራሮች ከምስረታው ጀምሮ የነበሩ ናቸው። ሌላ ተተኪ ትውልድ የድርጅቱን ህልውና የሚያስጠብቅ አላፈሩም የሚባል ትች ይሰነዘርባቸዋል። በእርግጥ ለዘመናቸው መጠናቀቅ ተተኪ አለማፍራታቸው አንዱ ምክንያት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል?
እነኚህ ሰዎች መሣፍንት ናቸው። እነኚህ ሰዎች ከእኛ በቀር ሌላ ሰው ሊመራ አይችልም ብለው የሚያምኑ ሰዎች ናቸው። በትምክህት የተወጠሩ ዓይነት ሰዎች ናቸው። ሌላውን ሰው አያከብሩም። ዋና ተልዕኳቸው መስፍናዊ ስርዓት መመስረት እና በዚያ መቀጠል ነው። በዚህም ምክንያት ሁሉ ጊዜ የሚያስቡት ስለራሳቸው ጥቅም እንጂ ስለሌላው የኅብረተሰብ አንድም ቀን ተጨንቀው አያውቁም ሌላ ሰው ሥልጣናቸውን እንዲጋራም ሆነ እንዲመራ አይፈልጉም።
ከስደት መቼ ለመመለስ አሰቡ?
እኔ ኢትዮጵያ የምመጣው ለቁም ነገር ብቻ ነው። መንግሥትን ለማገዝ እመጣለሁ። ሕወሓቶች የዘረፉት እና ያደረጉትን እኩይ ተግባራት ሁሉ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ልነገረው፣ ሴራቸውን ለማጋለጥ እመጣለሁ። ብዙ ሰዎች ገድለዋል። በጀምላ ጉድጓድ ውስጥ ቀብረዋል። ሀብት ዘርፈዋል፤ ሕዝብን ጨቁነዋል፤ ገድለዋል። እነዚህን ሁሉ ለማጋለጥ እመጣለሁ። እነኚህ በወንጀል የተጨማለቁ የሕወሓት አመራሮች ከባድ በደል ለማጋለጥ እመጣለሁ።
በመጨረሻ ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልዕክት ምንድን ነው?
የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይ የትግራይ ሕዝብ አሁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሚመሩት መንግሥት ከዘመናት ጨቋኝ ስርዓት ነጻ አውጦተሃል። የመናገር፣ የመንቀሳቀስ ነፃነትን አግኝተሃል። ከዚህ መንግሥት ጋር በኅብረት በመቆም እንድትተባበር፤ የዘመናት ጠላትህ የተደበቀበት ጉድጓድን አጋልጠህ እንድትሰጥ አደራ ልልህ እወዳለሁ። ከአራት ዐሥርት ዓመታት በላይ የታገልከው ትግል መደምደሚያ ላይ ደርሰሀልና በርትተህ ቀጥል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ያለህን ድጋፍ በመስጠት ለውጡ በተያዘለት መንገድ እንዲቀጥል ከጎናቸው እንድትቆም አደራ ልልህ እወዳለሁ።
ቅጽ 2 ቁጥር 109 ኅዳር 26 2013



