የወጣቶች ምክር ቤት ሊቋቋም ነው

0
372

በኢትዮጵያ ጤናማ ትውልድን ለመፍጠር ያለመ የወጣቶች ምክር ቤት ለማቋቋም የኢትዮጵያ ሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር እየሠራ መሆኑን አስታወቀ’
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቀው በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የወጣቶች የተሳታፊነት ፍላጎት ሊያግዝ የሚችል አሠራርን በውስጡ ያነገበ ምክር ቤት እንደሚመሰረት ጠቁሟል።

ይመሰረታል የተባለው የወጣቶች ምክር ቤት ከአገር ውስጥ ባለ ሐብቶችና ከውጭ አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር የወጣቱን ፍላጎት መሰረት ያደረገ ሥራ ለመሥራት መሆኑን የኢትዮጵያ ሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አድነው አበራ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

ምክር ቤቱ በዋናነት የሚሠራው ወጣቶችን በማጎልበት ጤናማ ትውልድ መፍጠር ነው ተብሏል። እንዲሁም የምክር ቤቱ መቋቋም የወጣቱን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተሳትፎ ከማሳደግ ባሻገር የጎዳና ተዳዳሪዎችን ሕይወት ለማሻሻል ይሠራል ተብሎ ይጠበቃል።

ምክር ቤቱ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ሕይወት በዘላቂነት ለማሻሻል እስካሁን እየተሠራበት ያለውን የአጭር ጊዜ ሥልጠና በማጠናከር ሙሉ በሙሉ ከሱስ ነጻ እስከሚሆኑና አጠቃላይ የሥነ ልቦና ዝግጅታቸው እንደ ማንኛውም ሰው ብቁ እስከሚሆኑ ድረስ አሰፈላጊውን እገዛ እንደሚደርግ የሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጠቁመዋል።
ምክር ቤቱ ገለልተኛ ተቋም በመሆን መሥራት የሚገባውን ሥራ በገለልተኝነት እና በነጻነት መከወን እንዲችል የታሰበ ነው ተብሏል’ምክር ቤቱ የሚሠራቸው ሥራዎች በአገር ደረጃ ትኩረት አድርጎ እንደሚሠራ የገለጹት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ምክር ቤቱን ለማቋቋም የሌሎች አገሮች የወጣቶች ምክር ቤት ጥናት ዋቢ ተደርጓል ብለዋል።

የወጣቶች ምክር ቤቱ ሲቋቋም ዕድሜያቸው ከ 16 አስከ 25 ዓመት የሆኑ ወጣቶችን ማዕከል ያደረገ መሆኑን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ተናግረዋል። በዚህም ማንኛውም ዕድሜው ከ16 ዓመት በላይ የሆነ ወጣት ትምህርት መማር የማያስችል ሁኔታ ሲገጥመው መማር የሚችልበት ሁኔታዎችን የሚያመቻች ምክር ቤት እንደሚሆን ተመላክቷል።

ምክር ቤቱ የሚቋቋምበት ዓላማ ዕድሜያቸው ከ 16 አስከ 25 ዓመት የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ፍላጎታቸውን በራሳቸው ፍላጎት ማሟላት የሚችሉበትን ዕድል ለመፍጠር መሆኑን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ተናግረዋል።

የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ከአዲስ ማለዳ ጋር መነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት የወጣቶች ምክር ቤት መመሥረትን ተከትሎ በየወረዳው የወጣቶች ግንኙነት ማዕከል(youth connection center) እንደሚቋቋም ጠቁመዋል።

የምክር ቤቱን ምስረታ በተመለከተ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ለሚመለከታቸው ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎችና የክልል አመራሮች የተደራጀ ሐሳብ አቅርቦ ተቀባይነት ማግኘቱን ኃላፊው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የወጣቶች ግንኙነት ማዕከሉ(youth connection center) የእያንዳንዱ ወጣት ችግሮች ሊፈታ የሚችል ነው ተብሏል። ማዕከሉ የወጣቶች ምክር ቤት አንዱ አካል መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ አንድ ወጣት 16 ዓመት ሞልቶት ትምህርት መማር የሚችልበት አቅም ከሌለው ትምህርት መማር የሚችልበት እድል የሚያመቻችበት የመሰረተ ልማት ማዕከል መሆኑ ተመክቷል።

የወጣቶች ግንኙነት ማዕከሉም በአስሩም ክልሎችና በኹለቱም የከተማ አስተዳደሮች እንደሚቋቋም አድነው ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል በኢትዮጵያ በወረዳ ደረጃ የወጣቶች ማዕከል ለመገንባት ኢትዮጵያዊ ባለ ሐብት ሼሕ መሀመድ ሁሴን አላሙዲ በተወካዮቻቸው በኩል ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ማስታወቃቸውን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 109 ኅዳር 26 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here