ሕብረት ባንክ ትርፋቸው አንድ ቢሊዮን ካለፉ ባንኮች መካከል አንዱ ሆነ

0
988

ሕብረት ባንክ በ2012 በጀት ዓመት ባንኩ ከግብር በፊት ያስመዘገበው የትርፍ መጠን አንድ ነጥብ አንድ ሦሥት ቢሊዮን ብር መሆኑን እና ትርፋቸው ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ካስመዘገቡ ባንኮች መሀከል አንዱ መሆኑን ሕብረት ባንክ አክሲዮን ማኅበር ከባለአክሲዮኖች ጋር ባካሄደው 23ኛ ጠቅላላ መደበኛ ጉባዔ ላይ አስታውቋል።
ይህም የትርፍ መጠን ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ 15 ነጥብ አንድ ሦሥት በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ ይህም በጣም ጥሩ የሚባል ውጤት እንደሆነ ይፋ ተደርጓል።
ከአንድ ቢሊየን ብር በላይ ትርፋማ ከሆኑ ባንኮች መካከል አዋሽ ባንክ ፣ ዳሽን ባንክ ፣ አቢሲኒያ ባንክ ፣ ንብ ባንክ ይገኙበታል ።

የበጀት ዓመቱን የፋይናንስ እንቅስቃሴ ስንመለከት ባንኩ አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ከ29 ነጥብ ዘጠኝ ሁለት ቢሊዮን ብር ወደ 34 ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር አድጓል። ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ 19 ነጥብ አራት አምስት በመቶ ጭማሪም አሳይቷል።

የአክሲዮን ድርሻ ክፍፍል በእያንዳንዳቸው ባለአክሲዮች ባለፈው ዓመት ከነበረው 39 ነጥብ አንድ ዘጠኝ ብር ወደ 29 ነጥብ ሰባት ዘጠኝ ብር የቀነሰ መሆኑን ነገር ግን በአጠቃላይ የባንኩ 2012 በጀት ዓመት ለባለ አክሲዮኖች ክፍፍል ብር 615ነጥብ አንድ ኹለት ሚሊዮን ብር ሲሆን ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር ያለፈው 389 ነጥብ አንድ ሰባት ሚሊዮን እንደነበር እና በዚህም የ 58 ነጥብ አንድ በመቶ ብልጫ አስመዝግቧል።

የእያንዳንዳቸው ባለአክሲዮች ድርሻ ክፍፍል የቀነሰበት ምክንያት ባለድርሻዎቹ በ2011 ዓመት 19 ሚሊዮን የነበሩ ሲሆን በ2012 በጀት ዓመት ግን ወደ 29 ሚሊዮን ስለጨመሩ መሆኑ ታውቋል።

ባንኩ ከወለድ ነፃ በሚሰጣቸው አገልግሎት ባንኩ በቀደመው ዓመት ከሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ላይ የ 40 ነጥብ አንድ ሰባት በመቶ ጭማሪ በማሳየት በብር አንድ ነጥብ ኹለት ሦስት ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን ለማወቅ ተችሏል።

በብሔራዊ ባንክ ኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ቀጥተኛ የኢኮኖሚ ጫና ያረፈባቸውን የንግድ ተቋማት ባንኮች እንዲያግዙ ባቀረበው ሐሳብ ተስማምቶ እንደ ሌሎች ባንኮች ሁሉ ሕብረት ባንክ የበኩሉን አስተዋፅዖ እንዳደረገ ተጠቁሟል።

በዚህም የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከፍተኛ ተፅዕኖ ላሳረፈባቸው የሥራ ዘርፎች ማለትም ለሆቴል እና ቱሪዝም ፣ለኮንስትራክሽን እና ለአበባ እርሻዎች ባንኩ የብድር ወለድ ምጣኔ ቅናሽ እና የክፍያ ጊዜ የማራዘም እፎይታ በማድረግ በድምሩ ወደ 50 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ ማድረጉን አሳውቀዋል።

በሌላ በኩል በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነው እና በኢትዮጵያ አየር መንገድ እና በሕብረት ባንክ ትብብር የሕብረት ሼባ ማይልስ በሚል ስያሜ የቀረበው የኮ¬-ብራንድ ካርድ ከስህተት በፀዳ ሁኔታ መተግበሩ በደንበኞችና በኹለቱ ድርጅቶች በኩል እርካታን የፈጠረ እንደነበር ተጠቅሷል።

ሦስት መቶ 35 ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶች ያሉት ባንኩ የሥራ ዕድልን ከመፍጠር አኳያ ሕብረት ባንክ ከ2011 በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ 13 ነጥብ ሰባት ሦስት በመቶ ብልጫ እንዳለው እና ስድስት ሺሕ 536 ብዛት ያላቸው ሠራተኞች እንዳሉት ተመላክቷል።

በጉዳዩ ላይ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት ዛፉ ኢየሱስወርቅ እንዳሉት ባንኩ በብዙ መለኪያዎች ያስመዘገበው ውጤት ጥሩ የሚባል እናደሆነ ተናግረዋል።

ብዙ ካፒታል ይዞ አንድ ቢሊየን ትርፍ ማግኘት ብዙ የሚባል ባይሆንም በዚህም ረገድ መልካም የሚባል የትርፍ መጠን ለማስመዝገብ የቻለ ሲሆን በቀጣይ ዓመታትም የተሻለ እድገት ለማስመዝገብ የሚያስችለውን አቅም መገንባት መቻሉን የምናውቅበት ነው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 109 ኅዳር 26 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here