አነጋጋሪው ፊልም

0
1104

ከመቶ ዓመታት በፊት – አንኮበር፤ በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ዘመነ መንግሥት፤ የቆሎ ተማሪው ጎበዜ የእብሪተኛው ጭቃሹም ጎንጤ ሚስት ከሆነችው ፍቅረኛው ዓለሜ ጋር ሲማግጥ እጅ ከፍንጅ ተይዟል። የመንደሩ ሰው ተጯጩሆ ጎበዜን በጭቃሹሙ እጅ ከመገደል ቢያስጥለውም የጭቃሹሙ ተኩስ ግራ ትከሻውን አቁስሎታል። መንደርተኛው ሁለቱን ሰዎች ገላግሎ ነጠላ እና ነጠላቸውን ቁራኛ አስሮ ዙፋን ችሎት እንዲቀርቡ ይልካቸዋል። ባላንጣዎቹ ዐሥራ አምስት ቀን ሙሉ ቁራኛ ታስረው አንድ ላይ ሲጓዙ የሚያሳልፉትን ውጣ ውረድ እና ከንግሥት ዘውዲቱ ችሎት ቀርበው የአፄ ሥርዓት ወርድ ተከትለው ሙግት ሲገጥሙ የሚያሳየው ቁራኛዬ ፊልም፤ ከዘመናት በፊት በአፄው ሥርዓት ስር በነበረው የፍትሕ ሥርዓት እና ባህል ውስጥ ሁለቱ ባላንጣዎ የሚገጥማቸውን ፍርድ ተመልካች ጓጉቶ እንዲጠብቅ ሚያደርግ ትውፊታዊ ፊልም ነው። በታሪኩ ከደብረ ሲና እስከ እንጦጦ፤ ከእንጦጦ እስከ አንኮበር፤ ከአብነት ተማሪዎች የዕለት ኑሮ እስከ ነገሥታቱ እልፍኝ ያለውን ሕይወት፣ የፍትሕ እና የፍቅር ጥማት፤ በጊዜው ከነበረው የማኅበረሰብ ውቅር እና ሥነቃል ጋር በአንድ ሰዓት ከአርባ ደቂቃ ውስጥ ለማስቃኘት ይሞክራል። ፊልሙ ከታኅሣሥ 19 ቀን ጀምሮ በተመረጡ ሲኒማ ቤቶች በመታየት ላይ የሚገኝ ሲሆን ብዙዎችን በአድናቆት እያነጋገረ ነው፡፡
የፊልሙ ደራሲና ዳይሬክተር ሞገስ ታፈሰ (ዶ/ር) በዘጋቢ ፊልሞቹና በቴሌቪዥን ፕሮግራም ዝግጅቶቹ የሚታወቅ ሲሆን ‹‹እኔ የምጠይቀዉ›› የተሰኘ ሳምንታዊ የቴሌቪዥን ፕሮግራምም በዳይሬክተርነት ያዘጋጃል፡፡ በማኅበረሰብ ጥናትና ልማት (Social Work and Social Development) የዶክትሬት ዲግሪዉን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተቀበለዉ ዶ/ር ሞገስ ከፊልም ጥበብ ጋር የተያያዙ የተለያዩ ሥልጠናዎችን ከዓለም ዐቀፍ ማሰልጠኛ ማዕከላት ወስዷል። “Dancing for Unity” የተሰኘ ስራው እ.አ.አ 2011 ዓ.ም. በፈረንሳይ አገር በተዘጋጀዉ የኬን ፊልም ፌስቲቫል ላይ የቀረበለት ሲሆን “A Season for Dancing” የተባለዉ ፊልሙም ከአምስት ዓመት በፊት በማኅበረሰብ ጥናት እና ትምህርት የፊልም ፌስቲቫል (Council for Social Work Education Virtual Film Festival) ላይ ቀርቦ ለመጨረሻ ዙር ደርሷል፡፡
ደራሲው ቁራኛዬን ፊልም ጽሁፍ ለመፃፍ አራት ዓመት የፈጀ የታሪክ የቋንቋ እና የሥነ ቃል ጥናት ያደረገ ሲሆን የፊልሙ ጽሑፍ ከ 11 ጊዜ በላይ ተከልሷል (ታርሟል)፡፡ በታሪኩ መቼት ውስጥ ያለውን ምስል፣ ቋንቋ እና ሥርዓት ተአማኒ እንዲሆን ለማድረግ ብዙ ጥረት ማድረጉን የሚናገረው ዳይሬክተሩ አፈታሪኮች ዋና ፍልስፍናዊ እሴት በሆኑበት ሀገር ውስጥ ትኩረት ያልተሰጠውን ታሪክ በፊልም መልክ አቀናብሮ ማቅረብ መቻሉን እንደእድለኝነት እንደሚቆጥረው ተናግሯል፡፡ ፊልሙን ሰርቶ ለማጠናቀቅ ዝግጅት እና ድህረ ዝግጅትን (production and post-production) ጨምሮ ሁለት ዓመት ተኩል የፈጀ ሲሆን በአጠቃላይ 4.5 ሚሊዮን ብር ገደማ ወጪ ተደርጎበታል፡፡ ፊልሙ በአብዛኞው አዳዲስ ተዋንያንን ያሳተፈ ሲሆን ዘሪሁን ሙላቱ፣ ተስፋዬ ይማም እና የምስራች ግርማ በመሪ ተዋናይነት ተሳትፈውበታል፡፡ በተጨማሪም ግሩም ብርሃነፀሐይ፣ ቢሊ መኮንን፣ መታሰብያ ሸንቁጤ፣ ሄለን ይስማው እና ሌሎች ባለሙያዎች በፊልሙ ሥራ ውስጥ ተሳትፈዋል፡፡
ፊልሙ ከታሪካዊ ክስተቶች አኳያ ቁራኛ እና የሌባ ሻይ ሥርዓቶች ልጅ እያሱ ያስቀሯቸው መሆኑ እየታወቀ እንዴት የንግሥት ዘውዲቱን ዘመን መቼቱ ያደረገ ታሪክ ላይ የቁራኛ ሥርዓት ሊኖር ቻለ የሚል ትችትም ገጥሞታል፡፡ የፊልሙ ደራሲና ዳይይክተር ግን የቁራኛ ሥርዓት በልጅ እያሱ ዘመን በትእዛዝ እንዲቆም ቢወሰንም ሥርዓቱ እስከ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንገሥት ድረስ ቀጥሎ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ የሚል አቋም ይዘዋል፡፡ የታሪክ ምሁሩ አበባው አያሌው እንደሚሉት የባርያ ንግድን እና የቁራኛ ሥርዓትን ጨምሮ በተለያየ ጊዜ እንዲቆሙ በአዋጅ የተነገሩ ሥርዓቶች ቢሆኑም ወዲያውኑ ተፈፃሚ አልሆኑም፡፡ ምሁሩ በዐሥራ ዘጠኝ ሃያዎቹ አጋማሽ ራስ ኃይሉ እና ደጅአዝማች ከበደ ተሰማ ቁራኛ ታስረው እንደነበር በመጥቀስ የቁራኛ ሥርዓት እስከ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ድረስ መቆየቱን አስረድተዋል፡፡
ፊልሙ ለዕይታ በቀረበ በአንድ ሳምንት ውስጥ ጥሩ የሚባል ተቀባይነት ያገኘ ሲሆን በማኅበራዊ አውታሮችም ብዙ የአድናቆት ድምፆች ጎርፈውለታል፡፡ በይበልጥም አንድ ዓይነት ዘውግ ይዘው ከሚሰሩት የአማርኛ ፊልሞች በተለየ መልኩ ታሪክ እና ቱባ ባህልን ለማሳየት ፊልሙ የሄደው እርምጃ እና የገበያ ድፍረት በብዙዎች ዘንድ አስመስግኖታል፡፡ ቁራኛዬ በአሁኑ ሰዓት በከተማችን ባሉ ዋና ዋና ሲኒማ ቤቶች በመታየት ላይ ይገኛል፡፡

ቅጽ 1 ቁጥር 8 ታኅሣሥ 27 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here