‹‹ምስጢሩ›› ቴአትር ለዕይታ በቃ

0
854

በደራሲ አለህኝ ብርሀኔ ተደርሶ ለእይታ የበቃው ‹‹ ምስጢሩ ›› የተሰኘው አዲስ ትወፊታዊ ቴአትር ወደ መድረክ ብቅ ብሏል።
የቴአትሩ ጭብጥ አውጫጪኝ (እውስ) ተብሎ በሚጠራውና በተለይም በአማራ ክልል ጎጃም አካባቢ የሚከወን የዳኝነት ስርዓት ሐገረሰበዊ ተውፊት ላይ ያተኮረ ነው። ቴአትሩ የሚዳስሰው የዳኝነት ልማዳዊ ክዋኔ በማኅበረሰቡ ውስጥ ማንኛውም ዓይነት ወንጀል ሲፈፀም ለአውጫጪኝ ወይም መረጃን ለማውጣጣት በሚል ለነዋሪው ጥሪ ተደርጎ በአካባቢው ያለ አንድ ዋርካ ስር ተሰብስቦ ወንጀለኛን ለማጋለጥ የሚደረግን ስልት ነው።
በተሰብሳቢው ወንጀለኛ ነው በሚል የሚጋለጠው ግለሰብ ጥፋቱን ካላመነ ኹለት የተቀባበሉ መሳሪያዎች መሬት ላይ ተጋድመው እንዲዘላቸው የማድረግ ልምድ ያለ ሲሆን፣ ከዋሸ መሣሪያዎቹ ይባርቃሉ ተብሎም ታመናል።
ይህን የዳኝነት ስርአት የሚመሩትም ማኅበረሰቡ ያመነባቸውና በአካባቢው ‹‹የተከበሩ›› ናቸው የሚባሉ እና በእድሜ የገፉ ሦስት አባቶች ናቸው።
ለአውጣጭኝ ጥሪ ሲደረግ ለመውለድ ከደረሰች ነፍሰ ጡር ሴት እና ህፃን ልጆች በስተቀር ሁሉም የማኅበረሰብ አባል ወጥቶ ወደ ዋርካው እንዲሰበሰብ ልማዱ ያስገድዳል።
‹‹ምስጢሩ›› የተሠኘው አዲሱ ቴአትርም እነዚሁኑ ልማዳዊ ክዋኔዎች ሲዳስስ 1፡45 ደቂቃን ይፈጃል። በቴአትሩም 35 አንጋፋና ጀማሪ ተዋናዮች የሚሳተፉበት ሲሆን፣ ሱራፌል ተካ፣ ካሌብ ዋለልኝ፣ ንጉስ ባይሌ እና እታፈራሁ መብራቱ ይገኙበታል።

ቅጽ 1 ቁጥር 8 ታኅሣሥ 27 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here