መንግሥት “ጁንታ” ብሎ በሚጠራው የሕወሓት አመራር እና ባሰለፈው የልዩ ኀይልና ሚሊሻ ላይ የሕግ ማስከበር እርምጃዬን በይፋ ጨርሻለሁ ካለ ኹለት ሳምንታት አልፈዋል። ይህ ሕግ የማስከበር ተልዕኮ በተሳካ ኹኔታ፣ በመንግሥት በኩል ንጹሃን ዜጎች ላይ ከባድ ኪሳራ ሳያስከትል መጠናቀቁን የዘመቻውን ስኬት ማሳያ አድርጎ በአጽንዖት መግለጹም ይታወሳል።
ከሕግ ማስከበሩ ተልዕኮ በስኬት መጠናቀቅ በኋላ እስካሁን በመካሄድ ላይ ያለውን ቀንደኛ የጁንታውን አመራር እና ርዝራዥ ታጣቂዎችን የማደንና በሕይወት የተገኙትን ለፍርድ እንዲቀርቡ ከተደበቁበት ጓዳ ጎድጓዳ፣ ምሽግ ወይም ጎሬ አነፍንፎ በመፈለግ እና በማፈላለግ ሕግ ፊት እንዲቀርቡ፣ ፍትሕ እንዲሰፍን በአጭሩ በሰፈሩት ቁና እንዲሰፈሩ በማድረግ ላይ ነኝ ሲል በመግለጽ ላይ ይገኛል።
የሆነው ሆኖ መንግሥት ሕግ የማስከበር እርምጃ ብሎ ከጀመረ በኋላ በየቀኑ በሚያስብል ሁኔታ “ሰበር” በሚባል ተደጋጋሚ ትንፋሽ በሚያሳጥሩ የድል አብሳሪ ዜና ማዳመጥ በጣም የተለመደ ሲሆን ከተልዕኮው መጠናቀቅ በኋላ ግን “ሰበር” ዜና ተናፋቂ በመሆን የውሃ ሽታ ሆኗል። የመጨረሻው ትልቅ ሰበር ዜና ከቀናት በፊት ከአንድ ሺሕ በላይ የታገቱ የሰሜን ዕዝ ምክትል አዛዥ የሆኑትን ጀነራል ጨምሮ ከፍተኛ መስመራዊ መኮንንች በፌደራል ፖሊስ ልዩ ጀግንነት በታየበት ሁኔታ ነፃ ማውጣቱን የተመለከተው ነው።
ይሁንና የብዙዎች ጥያቄ እየታደኑ ያሉት አንጋፋዎቹ፣ ቀንደኛዎቹ የሕወሓት አመራሮች እጣ ፈንታ ምን ይሆን የሚል ሲሆን እስካሁን እርግጠኛ ምላሽ ግን አላገኘም።
የመከላከያ ሠራዊት የተለያዩ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች በተናጠል እንዲሁም ተቋሙን ወክለው ደግሞ የመከላካያ ኢንዶክትርኔሽን ዋና ዳይሬክተር ሜ/ጀነራል መሐመድ ተሰማ ለመገናኛ ብዙኀን በመስጠት ላይ የሚገኙ ሲሆን ይህንንም መግለጫዎቻቸውን አንዳንዶች በመተንተን የሕወሓት ቀንደኛ አመራር እጣ ፈንታን በመተንበይ ላይ ይገኛሉ። በተለይ ደግሞ የምዕራብ ዕዝ አዛዥ ሜ/ጀ መሰለ መሰረት ለኢሳት ቴሌቪዥን “የያዝናቸው የሕወሓት አመራሮች አሉ፤ ሌሎችንም ለመያዝ እያሰስን ነው። እየሸሹ ያሉትን እጅ እንዲሰጡ ደጋግመን ጠይቀናል፤ እምቢ ካሉ ልንደመስሳቸው ተዘጋጅተናል።” በሚል የሰጡት ማብራሪያ በከፍተኛ ደረጃ የማኅበራዊ ትስስር መድረኮች አጨናንቋል። በርግጥ ጀነራሉ ዝርዝሩን መንግሥት በይፋ የተደራጀ መግለጫ ይሰጥበታል ሲሉ ዝርዝር ጉዳዮችን ከማንሳት ተቆጥበዋል።
ይህንን የጀነራሉን መግለጫ ተከትሎም ያልተረጋገጡ ወሬዎች በሠፊው በመናፈስ ላይ ይገኛሉ። ለአብነት ለመጥቀስ የሕወሓት ሊቀ መንበር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል ኹለቱንም ታፋቸውን ተመው በቁጥጥር ሥር ውለዋል፤ አብረዋቸው ነበሩ የተባሉት ጌታቸው ረዳ፣ አቦይ ስብሃት፣ አባይ ጸሐዬ፣ ዐይነ ስውሩ አስመላሽ ወልደሥላሴ (አባ ነፍሶ) እና ፈትለወርቅ ገብረእግዚያብሔር (ሞንጆሪኖ) ከቀላል መጋጋጥ ውጪ ምንም ሳይደርስባቸው በሕይወት ተይዘዋል የሚለው ይገኝበታል፤ ምንም እንኳን ጌታቸው ረዳ እና ስዩም መስፍን ተገለዋል የሚል ወሬ አብሮ በመነሳት ላይ ቢሆንም። በተጨማሪም ከደብረፂዮን ያልተናነሰ ወይም የበለጠ ሥልጣን አላቸው የሚባሉት የሕወሓት አስፈጻሚ አባል ዓለም ገብረዋህድ መገደላቸውም በሰፊው እየተናፈሰ ይገኛል።
እምጥ ይግቡ ስምጥ እስካሁን ያልታወቀው የቀድሞው የደህንነት ሹም ጌታቸው አሰፋ እጣ ፈንታ ላይ ግን እስካሁን ምንም አልተባለም። አንዳንዶች ስለ ጌታቸው ምንም አለመሰማቱን ተከትሎ ሰውየው የስለላ ባለሙያ በመሆናቸው ምናልባትም መከላከያው፣ ፖሊሱ ወይም ደህንነቱ ከፍተኛ ከበባ ባደረጉበት አፍንጫቸው ሥር ሊሆኑ ይችላሉ ሲሉ መላምታቸውን አስቀምጠዋል። ለዚህም አመክንዮዋቸው እንደ አብንት የሚጠቅሱት ኦሳማ ቢን ላደንን ነው። ቢን ላደን እስከሚገደሉ ድረስ ለዓመታት የፓኪስታን ትልቁ የጦር ሠፈር አቅራቢያ በሚገኝ ቤት ውስጥ ተደብቀው መኖራቸውን አስታውሰዋል።
ይኹንና እነዚህ ሁሉ ያልተረጋገጡ ወሬዎች የሚያስተባብል ይሁን የሚያረጋግጥ ይፋዊ የመንግሥት መግለጫ አዲስ ማለዳ ለኅትመት እስከገባችበት ድረስ አልተሰማም። ይሁንና ከጉዳዮ ክብደት ጋር በማያያዝ መንግሥት በተደራጀ መልኩ ምናልባትም የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማ የኦሳማ ቢን ላደንን ታድኖ መግደል ባስታወቁበት መንገድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሕወሓት አመራሮች ላይ የተወሰደውን እርምጃ፣ በሕይወት የተያዙትንና የተገደሉትን ማንነቶች በተመለከተ መግለጫ ሊሰጡ ይችላሉ የሚል መላ ምቶች ተሰጥተዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 110 ታህሳስ 3 2013


