የልደት ካርድ ለሌላቸው ተማሪዎች ሊሰጥ ነው

0
1951

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ለሚገኙ የልደት ካርድ ለሌላቸው ተማሪዎች ከአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ጋር በመተባበር የልደት ካርድ ሊሰጥ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ወሳኝ ኩነት ምዝገባ እና መረጃ ኤጀንሲ ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

በአዲስ አበባ ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ የልደት ካርድ አገልግሎት ዘርፍ ዳይሬክተር ግርማ መኮንን እንደተናገሩት የልደት ካርድ ማለት የአንድን ግለሰብ ትክክለኛ ዕድሜ ከማወቅም በዘለለ ለአንድ አገር የተስተካከለ የሕዝብ ብዛት ለማወቅ ፣ ትምህርት ቤቶች እንዲሠሩ ፣ ልጁ መብቱ እንዲከበርለት የሚያስችለው ፣ ዜግነት የሚያገኙበት መሆኑን ተናግረዋል።

የልደት ካርድ ያለው ልጅ ዕድሜው ሲደርስ መታወቂያ ለማውጣት ሆነ የሚያስፈልጉትን ነገሮች ለማግኘት ምንም አይቸገርም እንዲሁም ብልሹ አሠራሮችን ከማስወገድ አንፃርም ከልጅነት ዕድሜያቸው ጀምሮ የልደት ካርድ መያዛቸው ጠቀሜታ አለው ሲሉም አስታውቀዋል።

ለአብነትም ዕድሜያቸው ሳይደርስ መታወቂያ አውጥተው የመንጃ ፍቃድ ትምህርት የሚማሩ ልጆች እንዳሉ ይህም የሚሆነው በልጅነታቸው የልደት ካርድ ስለማይኖራቸው ዕድሜያቸውን ለማወቅ አስቸጋሪ ስለሆነ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህ የልደት ካርድ የመስጠት ሂደትም ከአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ጋር በመሆን እንደሚሠራ የተናገሪት ዳይሬክተሩ ከኹለቱም መሥሪያ ቤቶች ቡድኖች ተቋቁመው በመጀመሪያ ምን ያህል ተማሪዎች የልደት ካርድ እንደሌላቸው የማጣራት ሥራ ይሠራል ብለዋል።

የልደት ካርድ የመስጠት ሂደቱም ረዘም ያለ ጊዜ ይፈልጋል ያሉት ዳይሬክተሩ በመጀመሪያም ምን ያክል ተማሪ የልደት ካርድ እንደሌለው የማጣራት ሥራ እንደሚሠራ እሱም አድካሚና የሰው ኃይል የሚጠይቅ ሥራ መሆኑን ተናግረዋል።

በመቀጠል ደግሞ ለተለዩት ተማሪዎች የልደት ካርዱን የመስጠት ሥራ እንደሆነ ይህም ከፍተኛ ወጪ እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።
ሁሉም ሰው የልደት ካርድ ሊኖረው እንደሚገባ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 36 ቁጥር አንድ /ሐ ማንኛውም ሕፃን ስምና ዜግነት የማግኘት መብቱን፣ ሕፃናት ወላጆቻቸውን የማወቅና በወላጆቻቸው የመጠበቅ መብት ፣ ዜግነት የማግኘት መብት እንዳላቸው ተደንግጓል።

በዚህም ለሁሉም ኅብተረተሰብ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ መሠራት አለበት እየተሠራም ይገኛል በተለይም ሚዲያው የወሳኝ ኩነት ምዝገባዎች የልደት ሰርተፍኬት ፣ የሞት እና ጋብቻ ሰርተፍኬት ጠቀሜታ እንዳለው ለማኅበረሰቡ ከማሳወቅ አንፃር አብሮን ሊሠራ ይገባል ብለዋል።

አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ ያነጋገረቻቸው በአዲስ አበባ ወሳኝ ኩነት ምዝገባ እና መረጃ ኤጀንሲ የነዋሪዎች አገልግሎት ዘርፍ ኀላፊ የሆኑት ዮሀንስ አምባቸው እንዳሉት የልደት ካርድ ሁሉም ማኅበረሰብ ሊኖረው ይገባል ብለዋል።

አያይዘውም 500ሺህ የሚሆኑ የልደት ካርዶችን እንደታተሙና የልደት ካርድ የሌላቸው ተማሪዎች ተለይተው ሲያልቁ የመስጠት ሥራው እንደሚሠራ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

የወሳኝ ኩነት ምዝገባ በሌሎች አገራት ትኩረት ተሰጥቶት የሚሠራ ሥራ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ በአገራችን ግን ገና ብዙ ሥራ የሚያስፈልገው ጉዳይ ነው ብለዋል።
ወደ ዲጂታል በመለወጥ ሂደት ውስጥም ከፍተኛ ሥራዎች እየሠራን ነው በዚህም በኹለት ወር ብቻ ለ35 ሺሕ ነዋሪዎች ዲጂታል መታወቂያ ማዳረሳቸውንም አያይዘው ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ውስጥ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ መደበኛ ተማሪዎች እንዳሉ አዲስ ማለዳ ከትምህርት ሚኒስቴር ያገኘችው መረጃ ያሳያል።
በጉዳዩ ላይ አዲስ ማለዳ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮን ለማነጋገር በተደጋጋሚ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ የሆኑትን አበበ ቸርነት ጋር የስልክ ሙከራ በተደጋጋሚ ብታደርግም ምላሽ ማግኘት አልቻለችም።

ቅጽ 2 ቁጥር 110 ታህሳስ 3 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here