የሕወሓት ወድቀትና የነገዋ ኢትዮጵያ የፖለቲካ አሰላለፍ

0
1488
የኢትዮጵያ ፖለቲካ በድሕረ-ሕወሓት በርካታ ጉዳዮችን መዳሰስ እንዳለበት ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡ በድሕረ-ሕወሓት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ መታየት ያለባቸው ጉዳዮች ኢትዮጵያ የተከተለችው ፌደራሊዝም፣ የሕገ መንግሥትና የብሔር ፓለቲካ ፓርቲዎች የወደፊት እጣ ፋንታ በጥናትና ላይ የተመሰረተ አሠራር መከተል እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ባለሙዎች ይመክራሉ፡፡ እውን ኢትዮጵያ የምትከተለው የብሔር ፌደራሊዝም ነው? ኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር ፌደራሊዝም ተግባራዊ መደረጉን የሚምኑ እና የማያምኑ ባለሙዎች ሐሳባቸውን በምክንያት ሞግተዋል፡፡
ከሞጋቾቹ ውስጥ ኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር ፌደራሊዝምን መንካት ትልቅ ችግር ያስከትላል ብለው የሞገቱ ፖለቲከኞች ለኢትዮጵያ ይበጃል ያሉትን ሐሳብ አጋርተዋል፡፡ የብሔር ፖለቲካ ኢትዮጵያ ውስጥ መነሻው የሕወሓት አገዛዝ ስርዓት መሆኑን የሚምኑ ፖለቲከኞችና ባለሙያዎች የብሔር ፓርቲዎች በድሕረ-ሕወሓት እጣ ፋንታቸው ምን ይሁን ሚለው ጉዳይ ለነገዋ ኢትዮጵያ ወሳኝ ነጥብ መሆኑን ያነሳሉ፡፡ ሌላው በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ትኩረት የሚሻው ጉዳይ ሕወሓት ያረቀቀው ሕገ መንግሥት የወደፊት እጣ ፋንታ ነው፡፡ የአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ በሦሥቱ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ፖለቲከኞችንና ባለሙያዎችን በማነጋገር ጉዳዩን የሐተታ ዘማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል፡፡

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ለሦስትዐስርት ዓመታተት ለተጠጋ ጊዜያት መዘወር የቻለው ሕወሓት ባለፉት ኹለት ዓመታት በአፈንጋጭነት እራሱን ሲከረክር ቆይቶ በመጨረሻ ባሳለፍነው ጥቅምት 24/2013 በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሰሜን እዝ ላይ ጥቃት መፈጸሙ የመጨረሻ ውድቀቱን አፋጥኖታል።

የሕወሓት ውድቀት ለ27 ዓመታት የኢትዮጵያን መንበረ ሥልጣን ያለ ማንም ተቀናቃኝ ተቆጣጥሮ እንደቆየ ባለፉት ኹለት ዓመታት ሲተረክ ቆይታል። ላለፉት ኹለት ዓመታት እራሳቸውን ከፌደራል መንግሥት በሂደት በማግለል በአንድ ወር ጦርነት ወይም ሕግ ማስከበር ሂደት ከሕወሓት መስራቾች እስከ ግንባር ቀደም መሪዎች በወንጀል ተጠርጥረው እየታደኑ ይገኛሉ።

ለ27 ዓመታት ሕወሓት የኢትዮጵያን ፖለቲካ በመዘወር በርካታ ግፍና በደል በኢትዮጵያውያን ላይ እንደፈጸመ ከጠቅላይ ሚኒስቴሩ እስከ ፖለቲከኛች እንደ ድርጅት የፈጽማቸውን ድርጊቶች በመጥቀስ ጭምር ተነግሮለታል ። ሕወሓት መሰረቱ ትግራይ ክልል ቢሆንም የኢትዮጵያን ፖለቲካ በተቆጣጠረባቸው ዓመታት በትግራይ ሕዝብ ስም ከመነገድ ውጭ አንዳችም ያተረፈለት ነገር እንደሌለ ከራሱ የቀድሞ አባላትና ፖለቲከኞች ጭምር ምስክርነት እየተሰጠ ነው።

ኢትዮጵያ አሁን ለደረሰችበት የብሔር ፖለቲካ ሽኩቻና ልዩነት የሕወሓት ሴራ መሆኑን በርካቶች አምነውበታል። ያለፉት 27 ዓመታት በከፍተኛ ደረጃ የብሔር ሽኩቻ ውስጥ ግባታችን የማይካድ ሀቅ መሆኑን ብዙዎቹ ፖለቲከኞችና ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ ሲገልጹ ተደምጠዋል።

ሕወሃት ሲፈጽማቸው የነበሩትን ሴራዎች በሕገ መንግሥት ሳይቀር በማስደገፍ ይፈጽም እበንደነበር እና የሕውሓት ከመንግሥትነት ውደ ጁንታነት ወርዶ ላለፉት ሁለት ኣመታት ሲያስተዳድር ከቆየው የትግረይ ክልል ለቆ በወንወጀል እየታደነ መሆኑ መጻኢውን የአገራችን ፖለቲካ ላይ ምን አንድምታ ይኖረው ይሆን የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው።

የሕወሓት መወገድ ብሔር ተኮር ፖለቲካ ላይ የሚኖረው አንደምታ ?
የኢትዮጵያ ፖለቲካ በሕወሓት የሥልጣን ዘመን ከዜግነት ፖለቲካ ይልቅ የብሔር ፖለቲካን በማቀንቀን የሕዝቡን ሥነ ልቦና በብሔር ፖለቲካ ቅኝት መበረዙን ብዙዎች ያምናሉ። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሙሳ አደም ሕወሓት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የራሱን ፖለቲካዊ ቁማር ተጫውቶ ማለፉን ይገልጻሉ።

ሙሳ እንደሚሉት ሕወሓት የሠራው ሥራ ዞሮ ዞሮ ለራሱ ውድቀት ምክንያት ሆኖታል ይላሉ። ሕወሓት በኢትዮጵያ ፖለቲካ የመሪነት ሚናውን በተቆናጠጠበት ጊዜ አማራጭ ፖለቲካዊ ሐሳብ ይዞ ለመቅረብ እድሉ የጠበበ እና አሽባሪ በሚል ቋት ፓርቲዎችን በማከማቸት የፈለገውን ሲያደርግ እንደነበር ያስታወሱት ሙሳ “የሕወሓት ተግባርና ውድቀት ለፖለቲካ ፓርቲዎች ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው” ነው ይላሉ።

ሙሳ እንደሚሉት ከሆነ ኢትዮጵያ ላለፉት 27 ዓመታት የተጓዘችበት የፖለቲካ መስመር መርህ አልባ እንደነበር በማንሳት የሕወሓት መክሰም ለነገዋ ኢትዮጵያ የተረጋጋ ፖለቲካዊ ሥነ ምህዳር ለመፍጠር ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራል ብለዋል። ነገር ግን የሕወሓት መክሰም ብቻውን የኢትዮጵያን ፖለቲካ የተረጋጋ አያደርገውም ይላሉ ሙሳ፤ ይልቁንም የብሔር ፓርቲዎች የኋሊት ታሪክን መሰረት ያደረገ አሰላለፋቸውን ማስቀረት ይገባቸዋል ይላሉ።፡ ይህ ካልሆነ የሕወሓትን ፈለግ ከመከተል የዘለለ ነገር አይኖረውም ይላሉ ሙሳ።

የኮተቤ ዩኒቨርስቲ የፌደራሊዝምና ፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ አያሌው ብርሃኑ(ዶ/ር) በበኩላቸው ሕወሓት ከኢትዮጵያ ፖለቲካ መገለል በርካታ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳዎች እንደሚኖረው ይናገራሉ። የኢትዮጵያ ዕድገት ላለፉት ኹለት አስርት ዓመታት በሕወሓት እጅ ላይ ወድቆ ሕወሓት ከሌለ ኢትዮጵያ አታድግም በሚል አሳሪ አስተሳሰብ የአገሪቱን ሕልውና በአንድ ፓርቲ ብቻ የተወሰነ እንዲሆን ያደረገ ነበር ይላሉ።

የኢትዮጵያን ሕልውና በሕወሓት እጅ ላይ እንደሆነ በማስመሰል የኢትዮጵያን ሕዝብ አንድነት በእጅጉ የሚሸረሽሩ አሠራሮችን በመከተላቸው የሕዝብ አንድነት እንደ ተናደ የሚያነሱት የፌዴራሊዝምና የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ የሕወሓት ውድቀት የሕዝብን አንድነት ወደ ቀድሞው ለመመለስ የመጀመሪያው መስፈርት ሊሆን ይችላል ብለዋል።

ነገር ግን የሕወሓት ውድቀት ብቻውን የኢትዮጵያን ፖለቲካ እንደማይቀይር አያሌው ይናገራሉ። አያሌው እንደሚሉት አሁን በሥልጣን ላይ ያለው ገዥ መንግሥት አደረጃጀቱ ከብሔር አቀንቃኝነት የጸዳ አለመሆኑን ያነሳሉ፣ በመሆኑም የብሔር አደረጃጀትን ገዥው ፓርቲ እስካልቀየረ ድረስ ችግሮች ሊቀጥሉ ይችላሉ ባይ ናቸው።

የሕወሓትን ዕድሜ ያሳጠረው ጦርነት በበርካቶቹ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ትልቅ አድናቆት ተቸሮታል። የወደፊቷን ኢትዮጵያን ተስፋም ሊለመልም የሚችል ጭላንጭል የሚሳይ ተግባር መሆኑን በመልካምነት የሚወሳ ተግባር ነው። ነገር ግን የሕወሓት ውድቀት ብቻውን የኢትዮጵያን ፖለቲካ ሊቀይረው እንደማይችል ብዙዎቹ ያመናሉ።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ(ኢዜማ) የኮሙኒኬሽን ክፍል ኀላፊ ዘላለም ወረቅአገኘሁ እንደሚሉት ደግሞ የሕወሓት ውድቀት ለአንዳንዶች ችግር ይዞባቸው ሊመጣ ቢችልም፣ የሕወሓት መውደቅ ግን በራሱ ለኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እንቅፋት የነበሩት ጉዳዮች እንደተወገዱ እንደሚቆጠር አብራርተዋል።

የሕወሓት የተበረዘ ሐሳብ ከፖለቲካ መውጣት ነገ ለምትቀጥለው ኢትዮጵያ ትልቅ ሚና እንዳለው ዘላለም ያምናሉ። ነገር ግን የሕወሓት ውድቀት ብቻውን የኢትዮጵያን የተረጋጋ ዲሞክራሲ ለማስፈን ውጤት አያመጣም ባይ ናቸው።

ዘላለም እንደሚሉት ከሆነ ሕወሓት እንደ ድርጅት ጠፍቶ ሌሎች ፓርቲዎች መንገዱን ከተከተሉ አሁንም የኢትዮጵያ ችግር አይፈታም የሚል እምነት አላቸው። የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ(ኦፌኮ) ሊቀመንበር መረራ ጉዲና(ፕ/ር) በበኩላቸው የኢትዮጵያን ፖለቲካ በሕወሓት ውድቀት ብቻ እንደማይወሰን የሌሎቹን ሐሳብ ይጋራሉ። መረራ እንደሚሉት ከሆነ “ሕወሓት ሙሉ በሙሉ ጡረታ ወጥቷል አልወጣም?” የሚለውን ጥያቄ በሚገባ ማረጋገጥ አንድ ትልቅ ሥራ ነው ባይ ናቸው።

ሌላኛው መረራ የሚያነሱት ጉዳይ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ሕወሓት ብቻ ነው ወይስ ሌሎች ከሕወሓት ያላነሱ አሉ? የሚለው ሌላኛ ችግር እንደሆነ ያነሳሉ፣ መረራ አክለውም የኢትዮጵያ ፖለቲካ እስካሁን እንደመጣበት በኃይል የሚቀጥል ከሆነና የሐሳብ ፖለቲካ አሸናፊ ካልሆነ ችግሮች ሊቀረፉ አይችሉም የሚል እምነት አላቸው።

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፖርቲ ሊቀመንበር አረጋዊ በርሔ(ዶ/ር) በበኩላቸው የሕወሓት ውድቀት ለኢትዮጵያዊያን የአንድነት በሮች እንደተከፈቱ እምነታቸው መሆኑን ያነሳሉ። ሕወሓት የተጓዘበት የተሳሳተ መንገድ ኢትዮጵያዊያንን አንድነት አደጋ ውስጥ ከመክተቱ በተጨማሪ ኢትዮጵያ አማራጭ እንድታጣ የሠራ ግንባር እንደነበር የሚያነሱት አረጋዊ፣ ኢትዮጵያዊያንን በብሔር ከፋፍሎ ከመግዛቱ በላይ የትግራይን ሕዝብ ከኢትዮጵያ ለመገንጠል በከፍተኛ ደረጃ ጥረት በሚያደርግበት ጊዜ መውደቁ የኢትዮጵያን የአንድነት ህልውና ከሞት አፋፍ ያተረፈ ነው ብለዋል።

እውን ፌደራሊዝም ነበር?
የኢትዮጵያ ፈደራሊዝም የብሔር ፈደራሊዝም መሆኑን በርካቶች ይስማማሉ። በሌላ በኩል አንዳንድ የፖለቲካና ፌደራሊዝም ባለሙዎች ደግሞ የኢትዮጵያ ስርዓት የብሔር ፌደራሊዝምን መስፈርት ያሟላ አይደለም ብለው ይሞግታሉ።

የኢትጵያ ፌደራሊዝም ስርዓት የብሔር ፌደራሊዝም መስፈርትን አያሟላም ብለው ከሚሞግቱ ባለሙዎች መካከል የፌደራሊዝምና የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ አያሌው ብርሃን(ዶ/ር) አንዱ ናቸው። አያሌው እንደሚሉት ከሆነ ኢትዮጵያ እስካሁን የተከተለችው ፌደራሊዝም ሙሉ የብሔር ፌደራሊዝም አይደልም ይላሉ። ምናልባት የብሔር ፌደራሊዝም የሚመስል ዝንባሌ ተከትሎ ይሆናል ባይ ናቸው።

በምክንያትነት የሚነሱት የብሔር ፌደራሊዝም በኢትዮጵያ ውስጥ ተተግብሯል ለማለት ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ብሔሮች እኩል የተቃኙበት አለመሆኑን በማንሳት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ የተተገበረው ፌደራሊዝም በፖለቲካ መሪነት በቀዳሚነት በተሰለፉ ከአምስት ባልበለጡ ብሔሮች ላይ ብቻ ነው ይላሉ።

“የፌደራሊዝም ጽንስ ሐሳብ በአንድ አገር ውስጥ የሚኖሩ ልዩነቶችንና አንድነቶችን አጣጥሞ ማስቀጠል ነው።”የሚሉት አያሌው፤ ከዚህ አንጻር በኢትዮጵያ ፌደራሊዝም ልዩነት ብቻ እንደሆነ ሲሠራ የነበረ መሆኑን አስታውሰዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ የፌደራሊዝም አረዳድ መስመሩን የሳተ ነው ሲሉ አያሌው ይሞግታሉ። በመሆኑም ኢትዮጵያ ውስጥ የዲሞክራሲ ስርዓትን ያማከለ ፌደራሊዝም ሊተገበር ይገባል የሚል አቋም አላቸው።

በሌላ በኩል የኢዜማ የኮሙኒኬሽን ክፍል ኀላፊው ዘላላም በበኩላቸው ኢትዮጵያ እስካሁን የተከተለችው ፌደራሊዝም የብሔር ፌደራሊዝም ነው ሲሉ ይሞግታሉ። ነገር ግን የአያሌውን ሐሳብ በመደገፍ በሁሉም ቦታዎች እንዳልተተገበረ ዘላለም ይናገራሉ።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢው ሙሳ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር ፌደራሊዝም ተተግብራል ባይ ናቸው። ሙሳ እንደሚሉት ከሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር ፌደራሊዝም ቢፈርስ ከባድ ቀውስ ሊፈጠር ይችላል የሚል ሐሳብ አላቸው። ኢትዮጵያ ላለፉት ሦስት ዐስርት ዓመታት ለተጠጋ ጊዜ የተከተለችው የብሔር ፌደራሊዝም የሕዝቡን ሥነ ልቦና በእጅጉ የቀየረ ነው የሚሉት ሙሳ ከብሔር ፌደራሊዝም ለመውጣት የሕዝቡን ግንዛቤ ማስተካክል እንደሚጠይቅ ያመካክታሉ።

የፌደራሊዝም መምህሩ አያሌው በበኩላቸው ኢትዮጵያ የተከተለችው ፌደራሊዝም ምድብ ሊሰጠው የማይችል ነው ይላሉ። ይህም የሆነበት የብሔር ወይም የቦታ አቀማመጥን መሰረት ያደረገ ፌደራሊዝም በሁሉም ብሔሮች ዘንድ ስላልተተገበረ ነው ይላሉ። ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እስካልተከተለች ድረስ ምንም ዓይነት ፌደራሊዝም ብትከተል ውጤት ሊመጣ እንደማይችል አያሌው ይጠቁማሉ።

የመጀመሪያው መሰረት ዲሞክራሲያዊ ስርዓት በአገሪቱ መገንባት የፌደራሊዝም ቀዳሚ ሥራ መሆኑን የሚናገሩት አያሌው ኢትዮጵያ አስካሁን ዲሞክራሲያዊ ስርዓት መስመር ውስጥ ስላልገባች ወደ ዲሞክራሲያዊ መንገድ መግባት ይገባታል ሲሉ ምክረ ሐሳባቸውን አካፍለዋል።

የብሔር ፌደራሊዝም በራሱ ችግር የለውም ሲሉ የሚሞግቱት ሙሳ አደም ኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር ፌደራሊዝም ችግር የሆነው የተቃኘበት መንገድ መሆኑን ያምናሉ። በመሆኑም የብሔር ፌደራሊዝም በተገቢው መንገድ ተግባራዊ ከተደረገ በራሱ ችግር ሊሆን እንደማይችል ሙሳ ያምናሉ።

አያሌው በበኩላቸው ፌደራሊዝም ብቻውን የችግሮች መፍትሔ ሊሆን አይችልም ባይ ናቸው። ፌደራሊዝም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ሚናው የጎላ ሊሆን የሚችለው እና አሁን ኢትዮጵያ ካለችበት ችግር የምትወጣው ዲሞክራሲያዊ ስርዓት፣ ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ምህዳር፣ ጠንካራ ተቋማት፣ መድብለ ፓርቲ ስርዓቶችና የምጣኔ ሀብት እድገት ማምጣት ሲችሉ ነው ብለዋል።

ሕገ መንግሥት ከሕውሓት ውድቀት ማግስት
ኢትዮጵያ እየተመራችበት የሚገኘው ሕገ መንግሥት ሕወሓት መንበረ ሥልጣኑን ከተቆናጠጠበት ጊዜ አንስቶ ከዘመኑ ጋር ለማዘመንና አሉበት ተብለው የሚነሱ ችግሮችን ለማረም በብዙዎች በኩል ከፍተኛ ፍላጎት ቢኖርም አስካሁን የደፈረው አካል የለም።

ሕገ መንግሥቱ ለበርካታ ዓመታት ለኢትዮጵያ ፖለቲካ መዛባት እንደ አንድ ምክንያት ሲነሳ መቆየቱ የሚታወስ ነው። በርካታ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ተሳታፊ የሆኑ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሕወሓት የደነገገውን ሕገ መንግሥት አግላይና ብሔር ተኮር በማለት ይኮንኑታል። ከመኮነንም አልፎ ሕግ መንግሥቱ መቀየር እንዳለበት ድምዳሜ ላይ የተደረሱም አሉ።

የኢዜማው ኮሙኒኬሽን ክፍል ኃላፊ ዘላላም የኢትዮጵያ ሕግ መንግሥት መሻሻል እንዳለበት በአብዛኛዎቹ ፓርቲዎችና በገዥው ፓርቲም ጭምር ድምዳሜ ላይ የተደረሰበት ጉዳይ መሆኑን ያምናሉ። የሕገ መንግሥት ማሻሻል የማያሻማ ጉዳይ መሆኑን የሚናገሩት ዘላለም ሕገ መንግሥቱ መላው የኢትዮጵያን ሕዝብን ያማከለና በጋራ ሊዋቀር የሚገባው ጉዳይ ነው ይላሉ።

የፌደራሊዝም መምህሩ አያሌው በበኩላቸው የሕገ መንግሥት ጉዳይ ኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን ለተፈጠሩት ችግሮች አንዱ ምክንያት መሆኑን ያስታውሳሉ። አያሌውን እንደሚሉት ሕገ መንግሥቱ ብሔርን መሰረት ባደረገ መልክ ስለተዋቀረ ሕዝቡን የሚመስል ሕገ መንግሥት ማዋቀር አስፈላጊ መሆኑን ያነሳሉ። የሕገ መንገሥቱን ችግሮች በተገቢው ነቅሶ ማውጣት እና ማሻሻል ለወደፊቷ ኢትዮጵያ የተረጋጋ ፖለቲካዊ ሥነ ምህዳር ለመፍጠር የራሱ ሚና ይጫወታል ብለዋል አያሌው።

ሙሳ አደም በበኩላቸው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ችግር እንዳበት ግለጽ ነው ይላሉ። “ጠማማ ሕገ መንግሥታዊነት ከሕገ መንግሥት አልባነት የተሻለ ነው።” የሚሉት ሙሳ የሕገ መንገሥት መሻሻል ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ባይሆንም ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ላይ የሚታዩት “ሕገ መንግሥት አይነካም” እና “ሕገ መንግሥት ቀዶ መጣል” የሚሉ ሐሳቦች ኹለቱም አያስኬዱም የሚል አቋም አላቸው። ሙሳ እንደሚሉት ከሆነ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ በጋራ መግባባት ላይ የተመሰረተ መሆን አንደሚገባው ያሳስባሉ።

የሕወሓት መውደቅና የብሔር ፓርቲዎች እጣ ፈንታ
ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱት ከ100 በላይ ፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ከተወሰኑት በስተቀር አብዛኛዎቹ ብሔርን መሠረት አድርገው የሚንቀሳቀሱ ናቸው። የብሔር ፓርቲዎች በተጋነነ ቁጥር መብዛት እንደ ምክንያትነት የሚነሳው የሕወሓት ብሔር ተኮር አገዛዝ የፈጠረው ጭቆናን ተከትሎ መሆኑን ፓርቲዎች እራሳቸው ሲመሰክሩ ይሰማሉ።

የብሔር ፖለቲካ ፓርቲዎች በብዛት መወለድ የኢትዮጵያን ሕዝብ ችግርና ብሶት አስካሁን ድረስ ሲፈታ ባይታይም የብሔር ፓርቲዎች ኢትዮጵያ ውስጥ አያስፈልጉም የሚል ሐሳብ በአንድ በኩል ይሰማል። በሌላ በኩል ደግሞ የብሔር ፖለቲካ ፓርቲዎች ያስፈልጋሉ የሚል ሐሳብ የሚከተሉ አሉ።

ኢትዮጵያ ውስጥ ከ100 የዘለለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥር አብዛኛው ብሔር ተኮር ከመሆኑም በላይ ብዛቱ አስፈላጊ አለመሆኑን የሚምኑት ሙሳ አደም ናቸው። ሙሳ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ በርካታ ፓርቲዎች ለኢትዮጵያ ሕዝብ አይጠቅሙም የሚል ሐሳብ አላቸው። እንደ ሙሳ ገልጻ ከሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚስፈልጉት ኹለትና ሦስት በሐሳብ ፖለቲካ የተደራጁ ፓርቲዎች መሆን ይገባቸዋል ባይ ናቸው።

የብሔር ፓርቲዎች መሰረታቸውን ያደረጉት የኋላ ታሪክ ላይ መሆኑን የሚገልጹት ሙሳ ትናንትን መሰረት ያደረገ ፖለቲካዊ ትግል ለኢትዮጵያ አዋጭ አይደለም የሚል አቋም አላቸው።

የፌደራሊዝም መምህሩ አያሌው በበኩላቸው ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ፓርቲዎች አያስፈልጉም በሚለው ሐሳብ አይስማሙም። ይልቁንም ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ብሔሮች እንደመኖራቸው መጠን የሕዝቡን ሥነ ልቦና በቅርበት የሚረዱ ፓርቲዎች ያስፈልጋሉ የሚል ሐሳብ አላቸው። ነገር ግን መሰረታቸው የሐሳብ ፖለቲካ ብቻና ብቻ መሆን እንደሚገባው አያሌው ይመክራሉ። የብሔር ፓርቲዎች በብዛት የተፈጠሩት ብሔርን መሰረት ያደረገ ፖለቲካ ሲተገበር ስለነበር እና አዋጭ ስለሆነ መሆኑን አያሌው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል ።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ፖለቲካ ፓርቲዎች የዜግነት ፖለቲካን ላይ ትኩረት አድርገው መሥራት እንዳለባቸው የኢዜማው ዘላለም ይብራራሉ። ለኢትዮጵያ ሕዝብ የብሔር ፖለቲካ ውጤት አለማምጣቱን የሚናገሩት ዘላልም ሕዝቡ የብሔር ፖለቲካ አቀንቃኞችን ከፖለቲካ ጨዋታው ሊያስወጣቸው ይገባል የሚል ሐሳብ አላቸው።

አንዳንዶች ኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር ፖለቲካ በሕግ መታገድ አለብት የሚል ሐሳብ ያራምዳሉ። ዘላለም ይህን ሐሳብ አይደግፉም። የብሔር ፖለቲካ ፓርቲዎችን ወደ ዜግነት ፖለቲካ ለመመለስ ወይም ከፖለቲካው ለማስወጣት በምርጫ ሕዝብ እንደማይጠቅሙት ተረድቶ በምርጫ ሲቀጣቸው ብቻ መሆኑን ያምናሉ። በሕግ ማገድ አስፈላጊ አይደለም የሚሉት ዘላለም እንዴት ከብሔር ፖለቲካ መውጣት እንደሚቻል በትኩረት ሊታይ የሚገባው ጉዳይ ነው ብለዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢው ሙሳ በበኩላቸው በመርህ ላይ የተመሰረተ ፖለቲካን በመፍጠር የባላንጣነት ፖለቲካን በመጠየፍ የትብብር ፖለቲካን መፍጠር ሁነኛ መፍትሔ እንደሆነ ያምናሉ። ለዚህም ፓርቲዎች የፖለቲካ ፓርቲ ቁመና ሊኖራቸው የግድ ነው የሚሉት ሙሳ፣ የሕዝቡን ግንዛቤ በማሳደግ ፖለቲካዊ ምህርዳሩን ማስተካከል እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ከሕወሓት ውድቀት ማግስት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምን መምሰል አለበት በሚለው ጉዳይ ሐሳባቸውን ያጋሩት ፖለቲከኞችና ባለሙያዎች የኢትዮጵያን ችግር ለመፍታት የጋራ የሆነ ሰፊ ሥራ መሥራት ይጠይቃል በሚለው የጋራ ሐሳብ ይስማማሉ።

የፌደራሊዝም መምህሩ አያሌው የኢትዮጵያ ችግር በሕወሓት ውድቀት ብቻ ሊፈታ የሚችል ባለመሆኑ የጋራ ችግሮችን የጋራ መፍትሔ ለመስጠት በጋራ መሥራት ያስፈልጋል የሚል ምክረ ሐሳባቸውን አካፍለዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ለመለየት ጥናት ማድረግ እንደሚገባ አያሌው ያምናሉ።

ሙሳ አደም በበኩላቸው የጋራ በሆኑ ጉዳዮች ላይ አገራዊ ሥራዎችን በጋራ በመሥራት ከችግሮች ለመውጣት ይቻላል ብለዋል። የበዳይ ተበዳ ፖለቲካ የኢትዮጵያ ትልቁ ችግር በመሆኑ ከሕወሓት ውድቀት ማግስት ሌሎች ፓርቲዎች እንዳይደግሙት የጋራ የሆነ ሥራ በመሥራት የሕዝቡን ግንዛቤ በሂደት በማሳደግ ወደ አንድነት የፖለቲካ ምህዳር መምጣት እንደሚጠይቅ ሙሳ ሐሳባቸውን አካፍለዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 111 ታህሳስ 10 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here