የየዘመኑ ሴት!

0
592

ተፈጥሮ በሰው ልጅ ላይ እጇን ካነሳችባቸው ጊዜያት አንጻር የሰው ልጅ እርስ በእርሱ የተጋጨበት ጊዜ የሚበዛ ይመስለኛል። ለሥልጣን የሚደረግ ወንድም በወንድሙ የሚነሳበት ትግል፣ አንዱ መንግሥት በሌላው ላይ ለመሠልጠን የሚያደርገው ፍልሚያ፣ አንዱ አገር ከሌላው አገር ለአንዳች ጥቅም ሲል የሚያደርገው ወረራ እና አንዱ ከአንዱ ነጻ ለመውጣት የሚያደርገው ውጊያ፤ እነዚህና ሌሎች ተመሳሳይ የሆኑ ኹነቶች ሰዎች በሰዎች ላይ ያደረጉት ነው።

በእነዚህ ክስተቶች ውስጥ ብዙ ሕይወቶች አልፈዋል። ተስፋ አድርገው ሕልማቸውን አንግበው የወጡ ወጣቶች ዓለም በዓላማ ሥም ተሰውቷል። ስለሚያራምዱት ርእዮተ ዓለም ወይም ስለሚከተሉት ፍልስፍና አይደለም የምናነሳው፣ ስለአቋማቸው ጽናትና ስላመኑበት ነገር ብቻ ወደማይመለሱበት ዓለም፣ ወደሞት ለመሄድ ግን አልሳሱም።

በመሳፍንት ዘመን የነበሩ ግጭቶች ከዛሬው የዴሞክራሲ ዘመን ግጭቶች ጋር ተመሳሳይ አይደሉም። ሐሳቦች፣ ግቦችና ዓላማዎች በየዘመኑ እየተቀየሩ፣ ሁሉም ሲያልፍ ተራ እና ቀላል እየመሰለ ይታወሳል። በዚህ መካከል ሁሉ ግን በየዘመኑ ሕመሙን የምትሸከም ሴት አለች። እናት፣ እህት እና ሴት ልጅ።

የየዘመኑ ኢትዮጵያዊት ሴት እንባ ከዐይኗ ነጥፎ አያውቅም። ያኔ ሽብር ቀለሙን እየቀያየረ ልጆቿን ሲነጥቃት፣ ‹ላም እሳት ወለደች…› ሲሆንባት፣ ሐሳቡን ብትደግፍም ባትደግፍም ልጇን በረሃ ልትልክ ስትቆርጥ፣ በተራ ግጭት ‹መጣሁ› ያለ ልጇ ሳይመለስላት ሲቀር፣ ከእርሷ ፍቅር ይልቅ አገሩን አስቀድሞ ትቷት ሲሄድ ደጋግሞ ልቧ ተሰብሯል። የበለጠ ግን የሚያሳዝነው ምንድን ነው ካላችሁ፣ ይህ ሁሉ ለከንቱ ሲሆን ነው።

ግንቦት 20 በ2012 29ኛ ዓመቱን ሲይዝ፣ እያስታወሱ የሚኮንኑት እንዲሁም የሚያሞግሱትን እንሰማለን። ታድያ የሚኮንኑትና የጨለማ ቀን የሚሉትን ስናነሳ፣ በማኅበራዊ ድረ ገጾችም ይህንኑ የሚያስተጋቡትን ስመለከት፣ ለዛ ጊዜ ልጇን የሰዋች፣ ባሏን ያጣች፣ ወንድሟ የቀረባትን ሴት አሰብኩ። እነዚህ ሰዎች ምን ይሰማቸዋል? ልጆቻቸው የሞቱለትን ሐሳብ እኛ ስለደገፍን ወይም ስለተቃወምን አይደለም፣ ግን ስለሐዘናቸው።

በነገራችን ላይ ያንንም ለፖለቲካ ትርፍ የሚጠቀሙ አሉ። ‹ልጆቻችሁን የገበራችሁለት ትግል ነው!› እያሉ የሴቷን ሕመም ቀስቅሰው የራሳቸውን ሥልጣን ማራዘም የሚሹ። እነዚህ የዛሬዋ እናትም ልጇን እንድትሰዋ ሊያደርጉ የሚከጅሉ ናቸው። ወደኋላ የሚመልሱ። ይህን ላነሳ የወደድኩት እንዲያ ባለ መልኩ አይደለም፤ የየዘመኑ ኢትዮጵያዊት ሴት ግን ይህን ሕማም እንደተጋራች ለማውሳት ነው።

የየዘመኑ ኢትዮጵያዊት ሴት ልጅን፣ ወንድምን፣ ባልን የማጣትን ሕማም ተጋርታለች። ስጋት ቤቷ ነው። ደክማ ያሳደገችውን ልጅ ነጥቀው ዱላና ድንጋይ ያስይዙባታል። በየነገሩ ሁሉ ልጇን ሲማግዱት ታያለች። ለትምህርት የላከችውን በጥቁር ካባ ልታስመርቀው ስትጠብቅ ጥቁሩን ካባ እርሷ ቀድማ በሐዘን ለብሳዋለች፣ አገሬን ብሎ የወጣ ልጇን አገሩ ስትበላው ታዝባለች፣ ይህን ሕመም የየዘመኑ ኢትዮጵያዊነት እናት ቀምሳዋለች።

ይህን የምንለው እንደሚታወቀው በጦርነት የሚያልቁት፣ በብጥብጥና አለመረጋጋት ከፍተኛ ጉዳት የሚደርስባቸው ወንዶች ስለሆኑ ነው። ሴቶችም ለከፋ ጉዳት፣ ለአስገድዶ መደፈርና ለመከራ መዳረጋቸው የታወቀ ነው። እናማ የትላንትናዋ እናት/ሚስት/እህት ሐዘን አይበቃም ወይ? ነው ጥያቄው።

የየዘመኑ ሴት ትላለች፤ ‹‹ሰላምን ስመኝና ስጠይቅ ደካማ ስለሆንኩ አይደለም። ጠመንጃ ይዞ መተኮስ፣ ድንጋይ ተወራውሮ መደማማት፣ ጨለማን ጠብቆ በስለት መወጋጋት፣ መሰደድ፣ በስጋት መኖርን በየዘመኑ አይቻለሁ፤ ከባድ አይሉም። ግን መፍትሄ ቢያመጡ ኖሮ ዛሬ ከዓለም ቀዳሚ ሰላማዊትና ባለጸጋ፣ የሠለጠነች አገር ትኖረን ነበር። እነዚህ የሚያስከትሉት አንድ ነገር ብቻ ነው፣ የወጣትን ሕልም ይበላሉ፣ የአገርን ሀብት ያጎድላሉ፣ የየዘመኗን ሴት ልብ ይሰብራሉ።››

ቅጽ 2 ቁጥር 111 ታህሳስ 10 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here