የትኛውም የሥራ መስክ የራሱ መርህ እና የሥነ ምግባር ደንብ ሲኖረው ሥራ ጥሩ ማኅበረሰብኣዊ አስተዋጾውመ የጎላ ይሆናል። በተለይ ከተጠቃሚው ዘንድ የሚመጡበትን ጥያቄዎች በልበ ሙሉነት ለመመለስ በመርህ ላይ ተመስርቶ መሥራት ወሳኝ ጉዳይ ነው። ይህ ለመርህ እና ለሙያ ሥነ ምግባር ታማኝ ሆኖ መሥራት እንደ ጋዜጠኛ ለድርድር የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም፤ የሚለን አብርሀም ጸሐዬ ነው።
አገራችን በአሁኑ ሰዓት በመረጃ መጥለቅለቅ ተመታለች። ሕዝቡ በግራ አጋቢ ዜናዎችና ጥቆማዎች ተከቧል። ከዲጂታል ሚዲያው እስከዋና ዋና የመረጃ አውታር የሆኑት ጋዜጣ፣ ሬድዮና ቴሌቪዥን ድረስ የሚለቀቁት ዜናዎችና መረጃዎች ስፍር ቁጥር የላቸውም። ምንነታቸው እንደመገናኛ ብዙኃኑ ባለቤቶች ስሜትና ፍላጎት ይመስላል።
ሕዝብም ከዜናው ተዓማኒነት ይልቅ የየራሱን ጥግ ይዞ ከየአቅጣጫው የሚወረወረውን መረጃ ይመነዝራል። ሕዝብ ሚዲያን ይመስላልና። ጋዜጠኝነት እንደሌላው ሙያ ሁሉ የራሱ መርህ እንዳለው ግልጽ ነው። ሙያውን ወደመሬት አውርዶ ወደተፈለገበት ግብ ማድረስ ደግሞ ዋና መገምገሚያው ሆኖ እናገኘዋለን። ይህ ካልሆነ ግን መዘዙ ብዙ ነው።
መዘዙ
ዶናልድ ትራምፕ በሚመሯት አሜሪካ የማኅበረሰብ ሬድዮኖች ሥራቸውን እስከማቋረጥ ደርሰዋል።
ጉዳዮቹ ኹለት ናቸው፦
የመጀመርያው በኮቪድ 19 ወረርሽኝ የተነሳ በገንዘብ የሚደግፉ አካላት በመቀነሳቸው ሲሆን ሌላው ዶናልድ ትራምፕ የሚሰጡት ፈጣን አወዛጋቢና ተለዋዋጭ የትዊተር መልዕክታቸው እንዲሁም ሕዝቡ የየመድረክ ያልተጠበቀ ንግግራቸው ላይ ያለው መምታታት የተከታታዮችን ቀልብ ስላዛባና በዚህ የተነሳ ማኅበረሰቡ ወደዚያ በመሳቡ ለጋዜጦችና ሬድዮኖቹ መረጃ እምብዛም ሆኖ በመገኘቱ እንደሆነ ተገልጿል።
የተምታቱ መረጃዎች ብዛትና ተከታታይነት በትክክለኛ መንገድ ከሚሰሩት ልቀው በመምጣቸው እውነተኛ ዜናዎች ቦታ እያጡና ትኩረት መሳብን እየተዉ አደጋ ውስጥ ወድቀዋል። ፖለቲከኞች የፖለቲካ ቁመናቸውን ለማስቀደም የሐቀኝነት መርህን እየጣሱ ሕዝቡን ብቻ ሳይሆን በአነስተኛ የገንዘብ አቅም ላይ የነበሩትን ብዙኃን መገናኛዎች ከመስመራቸው ለማስወጣት ችለዋል።
በዚያው በአሜሪካ የማኅበረሰብ ሬድዮኖችና ጋዜጦች በተዘጋባቸው አካባቢዎች ሙስናን ጨምሮ ብልሹ አሰራሮች መስፋፋታቸው እየተነገረ ነው። ይሄ የአገሪቷን ዴሞክራሲያዊ የመባል ስም ያጎደፈ መዘዝ አስከትሏል። አገልግሎት አሰጣጥን ተከታትለው የሚዘግቡ ብዙኃን መገናኛዎች አለመኖራቸው የሚጠቅመው ሙሰኞችንና ወንጀለኞችን ወይም የተለየ ጥቅም የሚፈልጉ አካላትን በመሆኑ ጥቂቶች በማን አለብኝነት ጥፋታቸውን እየከወኑ ይገኛል። የብዙኃን መገናኛ አቅምና ነጻነት ማጣት ጉዳቱ ብዙኃኑ ላይ ነው።
የአገራችን የብዙኃን መገናኛ መዘዝ
አገራችን በብዙኃን መገናኛ ጥራት ቀድሞውንም ጥሩ ስም እንደሌላት ይታወቃል። በአሁን ሰዓት ተጽእኖ ፈጣሪ ሰዎች በተለያየ መገናኛ ብዙሃን መረጃ በመስጠት ተከታዮቻቸውን በማሰለፍና የሚቃወሟቸውን ነጥብ በማስጣል ተጠምደዋል። የመረጃ መተጋገል ሌላው ጦርነት ሆኗል።
ዋነኞቹ ሚዲያዎች እየሆነ ያለውን አንኳር ጉዳይ ለማጣራት ጊዜ እስከሚያጡ ድረስ መረጃ በአናት በአናቱ እየተቆለለባቸው ሚዛን አሳጥቷቸዋል። ፖለቲከኞች፣ የማኅበረሰብ አንቂዎችና ለየት ያለ አጀንዳን ማስፈጸም በሚፈልጉ የአገር ውስጥና የውጭ ቡድኖች መገናኛ ብዙኃኑን ቢቻል በማደናገር ወይም በጥቅም በመያዝ ካልሆነም በእጅ አዙር የሚዲያው ባለቤት በመሆን ዓላማቸውን ለማራመድ መሞከራቸው አይቀርም።
ከዚህ ባሻገርም ነገሮች ከአገራዊ ይልቅ ወደክልላዊ የጠበቡበትን መልክ ከወዲሁ ማስያዝ ካልተቻለ በሚዲያውም ዘርፍ እየታየ እንዳለው እኔ እበልጥ እኔ እሻል የሚለው አሸናፊ የሌለበት ውድድር ወዳልሆነ ውጤት እንደሚያሸጋግር ጉዳዩን በአንክሮ እየተከታተሉ ያሉ ያገባኛል ባዮች ምክር እየሰጡበት ነው።
የዚህ ተጽእኖው ሰለባ በመሆን ላይ ያሉት ብዙኃን መገናኛዎች አንድን መረጃ በተለያየ የአተያይ ቀለም እያዥጎረጎሩት ማኅበረሰቡ እየተምታታ ይገኛል። መዘዙ ቀላል አይደለም፤ ሀቅ ሳይሆን ስሜታዊነት እየነገሠ ነው። ከእውነተኛ መረጃ ይልቅ ተናጋሪውን ሰው የማመን፣ ትክክለኛ ዜናን ከመፈለግ ይልቅ ሰው በመጥላትና በመውደድ፣ ፓርቲ በማምለክና በማውገዝ፣ ቡድን በመደገፍና ባለመደገፍ መፈራረጅ ተይዟል።
በርካታ መገናኛ ብዙኃን በመርህ ከመሥራት ይልቅ የባለቤቶቹን ማንነትና ፍላጎት ተመርኩዘው እስከመሥራት ደርሰዋል። የዲጂታል ዜናዎችን ከዋናዎቹ መለየት አልተቻለም።
ሕዝብ ጋዜጠኞች የነገሩትን ይሰማል፤ ያምናል። የሰማውን አምጡ የሚለው ግን በኋላ ነው። ሰፋ አድርገን ስናየው በመረጃ መምታታት እንደአገርና ሕዝብ አደጋ አለው። ሕዝብ በተነገረው ልክ ተስፋ ያደርጋል፣ በሰማው ልክ ይጠብቃል፣ በተባለው ልክ ተስፋ ይሰንቃል። የእነዚህ ውጤቶች የሚለኩት ከጊዜ በኋላ ነው። ሕዝብ ሲሰማ የኖረውን የታለ ሲል የሚያጣ ከሆነ፣ የነገራችሁንስ ሲል ዝም ከተባለ፣ ጠብቅ ተብሎ ማጣቱ ሲታወቅ ወዳለማመን ብቻ ሳይሆን አሉታዊ ስሜት በማሳደር ወዳልሆነ መንገድ መጓዝ ይጀምራል።
ተጎጂው ተናጋሪው ጭምር ነው። ዛሬ አርቆ ማየት ያልቻለው አካል ነገ ተጠያቂ መሆኑ አይቀርም። የሚጠይቀው ደግሞ እውነት ነው። የሚጠየቀውም በማንም አይደለም የነገራችሁን እውነት የታለ በሚለው ሕዝብ ነው። ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያችን ሆኖ የነበረውም ይህ ነው።
ቤት ተሰርቶ ይሰጥሃል ሲባል ዓመታት ቆጠረ፣ ተምረህ ሥራ ተዘጋጅቷል ተብሎ ከተደጋፊነት አልወጣም፣ ኑሮህ ሰምሯል ተብሎ ነገር ግን ተሸግሮ አየው በስተመጨረሻ ላይ የእያንዳንዱ ግለሰብ ጥያቄ ታላቅ አገራዊ የሕዝብ ጥያቄ ሆኖ ተወለደ። ተያያዥ ያልተመለሱ ጉዳዮች ተነስተው ዓመጽ ለመወለዱ ማቀጣጠያ ሆኑ። ይሄ ችግር የሁልጊዜ አዙሪት እንዳይሆን ለማድረግ ግን ጊዜ አለ።
የብዙኃን መገናኛዎች መርህ
ብዙኃን መገናኛዎች በመርህ እንዲመሩ በተለይም እውነተኛ መረጃዎችን በበሰለ አሰራር ማስተላለፍ መቻል አንዱ መፍትሄ ነው። ከላይ እንደተገለጸው በእውነትና አግባብነት ላይ ተመስርተው እስካልሰሩ ድረስ በኋላ የሚፈጥሩት መዘዝ በቀላሉ የሚመለስ ብቻ ሳይሆን አገር ያፈርሳል። በብዙኃን መገናኛዎች ላይ ያለው አሉታዊ ተጽእኖ ቀላል አለመሆኑ ግልጽ ነው።
ትግሉን ማሸነፍ የሚቻለው በመርህ መሥራት ሲቻል ነው። ቢያንስ ትላልቅ የመረጃ አውታር የሆኑት ብዙኃን መገናኛዎች የየራሳቸውን ዓላማ በመርህ በማስደገፍና መሪ ዕቅድ በማውጣትና በመተግበር ሕዝብን ማገልገል ሲችሉ ተሰሚ ይሆናሉ። ለእውነተኝነት፣ ለሚዛናዊነት፣ ለእርግጠኝነት፣ ለተዓማኒነትና ላለማዳላት መርሆች መቆም አለባቸው።
መገናኛ ብዙኃን መነበብ ወይም መሰማት ብቻ የመጨረሻ ግባቸው አይደለም መነበብና መሠማትን ከመታመን ጋር ማስተሳሰር ይገባቸዋል። በአገልጋይነት መንፈስ ራሳቸውን እያስተዋወቁ በተከታታዮቻቸው ዘንድ ለመመረጥ ብዙ መሥራት ይኖርባቸዋል። ዘርፈ ብዙ፣ ቀለመ ዥንጉርጉር በሆነ የባህልና የታሪክ ስብጥር ባለባት አገር ከፍ ባለ የሙያ ብቃትና ግብረ ገብ ራስን ተመራጭ ማድረግ የተሻለና አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው።
የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ተሞክሮ
ወደዓለም አቀፉ ግዙፍ መገናኛዎች ብዙኃን እንሂድ። እንደሚታወቀው ዓለም ከዕለት ወደዕለት በምርጫ የተሞላች ዘርፈ ብዙ አቅርቦት ያላት ሆናለች። ማኅበረሰብ ከእነዚህ በርካታ ምርጫዎች ለራሱ የሚስማማውን ይወስዳል። መመረጥ የሠሪው አካል ድርሻ ነው። መምረጥ ደግሞ የሕዝብ ነው።
ብዙኃን መገናኛዎች እንደአሸን በፈሉባቸው አገራት የመመረጥ ፈተናው ከባድ ነው፤ ለዚህም ሲባል ጥራት ያለው ሙያ ወሳኝ ነው። ጋዜጠኛ መገናኛ ብዙኃኑ ካለበት ኃላፊነት አንጻር ብቁ ሆኖ መገኘት ግድ ይለዋል።
የዓለማችን ሕዝብ በዲጂታል ዘመን እንደመገኘቱ በመረጃ ከመጠቀም ተሻግሮ በመረጃ የመጥለቅለቅ ጉዳት ውስጥ ገብቷል። የትኛው ትክክል፣ የትኛው ውሸት መሆኑን መለየት ተስኖታል። ስለሆነም ተዓማኒነት ያላቸውን ብዙኃን መገናኛዎች ይፈልጋል። ሕዝብ ከዕለት በዕለት የአኗኗር ዘዬውም ይሁን ወደፊት ካነገበው የህይወት ራዕዩ ጋር የተገናኛለት፣ የሚያግዘውና የሚጠቁመውን ሚዲያ ያስሳል።
የጋዜጠኝነት ዋና መርህ የሆነውን የሕዝብ አገልጋይ ወይም ዘብ የመሆንን ዓላማና ግብ አስጠብቃለሁ በሚል አሠራር በመከተል ተመራጭና ታማኝ ለመሆን ብዙኃን መገናኛዎቹ ይጥራሉ። ሕዝብ የጣቢያው መዝጊያና መክፈቻ በእጁ እስከሆነ ድረስ ጣቢያው ላለመዘጋት መልፋት ይጠበቅበታል።
በዚህ የተነሳ ብዙኃን መገናኛዎች ቀድሞ መረጃ በማድረስ፣ ጠቃሚ ናቸው የሚባሉትን በመምረጥና በማቅረብ፣ ተዓማኒነት ያለው በመሆን እንዲሁም በቂ ትንታኔ በመስጠት ከዚህ በተጨማሪም ቀልብ ሳቢና አዝናኝነትን በመላበስ ግንባር ቀደም ተወዳዳሪ ለመሆን እንቅልፍ አጥተው ያድራሉ።
የኹለት ዓለም አቀፍ ብዙኃን መገናኛዎችን ተልዕኮ በጨረፍታ እንመልከትና የአገራችንን ብዙኃን መገናኛዎችን ቁመና በየልቦናችን እናስተያይባቸው።
‘ቢቢሲ’
ቢቢሲ የኔ ተልዕኮ ሕዝብ ተኮር ነው ይላል። ይህን ለማሳካት የጋዜጠኝነት ሥራው ወይም የመረጃ አቅርቦቱ የሕዝብን ፍላጎት በማጤን እንዲሁም ለአንድ ወገን ሳያደላ ገለልተኛ የሆነ አቀራረብን ይከተላል። ሕዝብን ለማስተማር፣ ለማሳወቅና ለማዝናናት ጥራትና ደረጃቸው ከፍተኛ የሆኑ እንዲሁም በዓይነታቸው የሕዝብን ፍላጎት ለማሟላት ለየት ያለ ፋይዳ ያላቸውን ጉዳዮች ተተንተርሶ የሚሠራ እንደሆነ ይገልጻል።
እዚህ ጋር አድማጭና ተመልካች ወይም አንባቢ በዚህ ዘመን ምን ይፈልጋል ማለት የሚዲያ አንዱ ኀላፊነት መሆኑን እናጤናለን። ዜና እና መረጃ የሚዲያው ወይም የጋዜጠኛውን ስሜትና ፍላጎት ስላሟላ ብቻ ሳይሆን ለማኅበረሰቡ በሚሰጠው ፋይዳ ላይ ተንተርሶ የሚዘጋጅ ነው።
ብዙኃን መገናኛዎች ፖሊሲያቸውን ሲቀርጹ በማኅበረሰቡ ማንነት ላይ በመንተራስ ሊሆን ይገባል። ይህም ሲባል የተሻለውን የበለጠ ለማጎልበት፣ የጎበጠውን ለማቃናት የሚያግዙ ግብዓቶችን በማቅረብ ይሆናል ማለት ነው።
ሚዲያ በሕዝቦች አእምሮ ላይ የተሻለ አስተሳሰብ እንዲፈጠር ያግዛል። ለግለሰብና አገራዊ ዕድገት የሚሆኑ ግብዓቶችን በማፈላለግ ያቀርባል። በአጠቃላይ ሚዲያ ወቅትን ያማከለ አዎንታዊ የአመለካከት ለውጥ እንዲመጣ የሚያግዝ የመረጃ ምንጭ ነው።
ቢቢሲ የማኅበረሰብ አመለካከት ከአካባቢያዊ ጉዳዮች አልፎ ዓለም አቀፍ እንዲሆን ማድረግ አንዱ ተልዕኮዬ ነውም ይላል። ይህም ማለት ዜናዎችን እና መረጃዎችን በገለልተኛነት በማቅረብ ተከታታዮቹ ዓለምን እንዲረዱና ግንዛቤያቸው እንዲዳብር በማድረግ ነው (… to provide impartial news and information to help people understand and engage with the world around them)
‘ዘ ኢኮኖሚስት’
ዘ ኢኮኖሚስት ወደላይ ቀጥ ያለ ዕድገት ያሳየ ነው ይባልለታል። መጽሔቱ ስኮትላንዳዊው የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ጄምስ ዊልሰን የዛሬ 177 ዓመት በእንግሊዝ ለንደን ሲመሰርተው ከበቆሎ ሕግና ታሪፍ ጋር አያይዞ መረጃ የሚያሰፍርበት የወረቀት ህትመቱ ነበር።
በሂደት ወደ ወቅታዊ ጉዳዮች ዘገባና ትንታኔ አደገ። በየሳምንቱ በህትመትና በዲጂታል የሚቀርበው ይህ መጽሔት ከአካባቢያዊነት ወጥቷል፤ ዛሬ ላይ ተደራሽነቱ ከሚሊየን ተሻግሯል። ዓለም አቀፋዊ ገጽታን ተላብሶ በፖለቲካና በምጣኔ ሀብት፣ በማኅበራዊና ቴክኖሎጂ ትንታኔዎቹ ላይ የተዋጣለት መጽሔት ነው።
ወቅታዊና አንኳር የሆኑ ዓለም አቀፍ ጉዳዮችን ጠባብ ከሆኑት ዘገባዎችና ዜናዎች አልፎ ዙሪያ ገባውን በመፈተሽና በመመርመር ጥልቅ የሆኑ ትንታኔዎችን ለዓለም በማበርከት ይታወቃል you have seen the news, why not discover the story በሚለው መሪ ቃሉ ይታወቃል። ከዜናው ባሻገርም ያሉትን እውነቶች ፈትሼ፣ ቆፍሬና አብጠርጥሬ አጋራለሁ ማለቱ ነው።
በኛ አገር እግር ኳሱን አይተን ነገር ግን በንጋታው የመንሱርን ወይም የአበበን ዕይታ እንደምንፈልገው ማለት ነው። ከዕይታችን ባሻገር ያሉ ተያያዥ ክስተቶች በባለሙያ ሲተነተን መስማት በጉዳዩ ላይ የጠራ መረጃ እንዲኖረን ያደርጋል። ክስተቶችን ሰዎች ሊያዩ ወይም ሊሰሙ ይችላሉ። ለምሳሌ የዋጋ ንረት የተከሰተባቸውን የምርት ዓይነቶች ሸማቾች ሊያውቁት ይችላሉ።
የዜና አውታሮችም ይህንኑ የዋጋ ንረት ይዘግቡታል። ይህ ንረት ግን በማኅበረሰቡ ላይ የፈጠረውን ትክክለኛ ጫና አስመልክቶ በተለይም የንረቱን ምክንያቶች ከሌሎች የሚጠበቁና የማይጠበቁ ምክንያቶች ጋር በማያያዝ ሰው ሰራሽ የሆኑ አሻጥሮችን እስከማጋለጥ ጭምር መጓዝ ያስፈልጋል።
ጠንካራ ብዙኃን መገናኛዎች የአንድ ችግር ትክክለኛው ምክንያት እስከሚገኝለት ድረስ መረጃ ይፈትሻሉ። እልህ አስጨራሽ ምርመራዎችን ያደርጋሉ። ውጤት እስከሚመጣ ድረስም ስለነገሩ ከሥር ከሥር ተከታትለው በየወቅቱ ይፋ ያደርጋሉ። ፖሊሲ አውጪዎችና ሕግ አስፈጻሚዎች ላይ ተጽእኖ በመፍጠር ማኅበረሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ የጋዜጠኝነት አንዱ ኀላፊነት ነው። በበቂ መረጃ ላይ ተንተርሶ በባለሙያ የተደገፈ ትንታኔ ይፋ ማድረግ የጠንካራ ብዙኃን መገናኛዎች ብቃት መለኪያ ነው።
ዘ ኢኮኖሚስት የሚሆኑ ነገሮች ለምን እንደሆኑ፣ እንዴት እንደተፈጸሙና ምን ሊያስከትሉ እንደሚችሉ እንዲሁም መደረግ ስለሚገባቸው የመፍትሄ ጥቆማ በመስጠት ይታወቃል። ነገሮች ከመከሰታቸው በፊት ያሉትን ምልክቶች እየተመለከተ ጠቃሚ መረጃዎችን ያቀብላል። መጽሔቱን አንባቢዎቹ ብቻ ሳይሆኑ ብዙኃን መገናኛዎችም ጥንካሬውን ይመሰክሩለታል፤ በዋና እና ተዓማኒነት ያለው ነው በሚል በምንጭነትም ይጠቀሙበታል።
የዚህ ዓይነት ቁመናን መፍጠር የሚቻለው ደግሞ ለሙያው መታመን ሲቻል ነው። ከምንም ነገር ሙሉ ለሙሉ የጸዱ ተቋማት ላይኖሩ ይችላል። ያንን በይፋ ያልተገለጸ ዓላማ ለማስፈጸም ሲሉ ግን ቢያንስ ማኅበረሰብን መያዣ መጨበጫ በሌለው መረጃ ውስጥ አይዘፍቁትም። በተቻለ መጠን የሙያ መርህ ከሚባሉት ውስጥ እውነተኝነት፣ ሚዛናዊነት፣ እርግጠኝነት፣ ተዓማኒነትን ማክበርና መፈጸም መልካም ይሆናል።
Abraham Tsehaye, [10.12.20 14:47]
(Email፡ geraramc@gmail.com)
ቅጽ 2 ቁጥር 111 ታህሳስ 10 2013