ትኩረት በሁሉም ማዕዘን ያስፈልጋል!!

0
440

ኢትዮጵያ ከሰሜን እስከ ደቡብ፤ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ አንድ ያደረገ እና ጉዳይ ከሰሞኑ ተፈጥሮ ነበር። ይህም ጉዳይ ለኹለት ዐስርት ዓመታት በላይ በትግራይ የቀበሮ ጉድጓድ ውስጥ በመኖር የአገርን ዳር ድንበር በማስከበር አገር ታፍራ እና ተከብራ እንድትኖር ያደረገው የሰሜን እዝ መከላከያ ሠራዊት ከባድ ጥቃት ተፈጽሞበት ነበር።
በዚህ ጉዳይ ታዲያ አገርን አንድ ያደረገው ይህ ጥቃት በተለያዩ የኢትዮጵያ ማዕዘናት ያሉ ወንድማማች ሕዝቦች በአገር ስሜት ያስተሳሰረ እና በመከዳት ቁጭትም ያስነሳ እንደነበር አይዘነጋም። ይህ አንድ ወር የተጠጋው በፌደራል መንግሥት የተወሰደው ሕግን የማስከበር ተልእኮው ታዲያ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ትኩረቱን ወደ ሰሜናዊው የኢትዮጵያ ክፍል እንዲያደርግ ሆኗል አሁንም ከዛ ቀጠና አይኑን የመለሰ ጥቂት ነው።

ከመንግሥት እስከ ተርታው ሕዝብ ድረስ ትኩረቱን ወደ ትግራይ እና አዋሳኝ ክልሎች ማድረጉ ታዲያ ሌሎች ኢትዮጵያ አካባቢዎችን ትኩረት ወደ መንፈግም የሚያደላ ጉዳይም እንደሆነ አዲስ ማለዳ ትታዘባለች። ሌሎች ክልሎች ጉዳይን እንመለስበታልን ነገር ግን በትግራይ ክልል ርእሰ መዲናም ከሕግ ማስከበሩ ትኩረት አንጻር የመቐለን ሰላም እና ጸጥታ ከመጠበቅ አኳያም ይህ ነው ሚባል ሥራ እየተሠራ እንዳልሆነ መረጃዎች እየወጡ ይገኛሉ።

የሕወሓት ከፍተኛ አመራሮችን እና ተያያዥነት ያላቸውን ግለሰቦች በማደኑ ሥራ ላይ ልቡን እና መንፈሱን የጣለው መንግሥት በትግራይ መዲና መቐለ ላይ ጁንታው የፈታቸው እና በተለያዩ ወንጀሎች ተይዘው የነበሩ ሰዎች በመቐለ ከተማ ከፍተኛ ሆነ ዝርፊያ እየፈጸሙ መሆናቸው እየተነገረ ይገኛል።

በአዲሱ ትግራይ ካቢኔ ውስጥ የመቐለ ከንቲባ አታኽልቲ ኃይለሥላሴ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቆይታ በመንግሥት የተወሰደውን ሕግን የማስከበር ዕርምጃ ተከትሎ የጁንታው አባላት በክልሉ የተለያዩ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ በተለያዩ ወንጀሎች ተይዘው የእስር ጊዜያቸውን እፈጸሙ የነበሩ ታራሚዎችን መቐለ ከተማ ለቀዋቸዋል ያሉ ሲሆን በዚህም ሕዝቡ በስጋት ውስጥ እንዲኖርም ምክንያት እንደሆኑ ጠቅሰዋል ።

መንግሥት በቅርቡ የሕግ ማስከበሩን ሒደት በሚያካሒድበት ወቅት ከጁንታው ነጻ የወጡ መሬቶችን እና ከተሞችን ፌደራል ፖሊስ እየተከታተለ ሕግን የማስከበር እና የማረጋጋት ሥራ ይሠራል በሚል መግለጫ ሲሰጥም ተሰምቷል። ነገር ግን ይህ ጉዳይ በመቐለ እየታየ ባለመሆኑ እና ሱቆች እየተዘረፉ እና ሰዎች በስጋት ውስጥ በመሆናቸው በአፋጣኝ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ስትል አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።

የመቐለ ዝርፊያ በዋናነት ደግሞ ኢላማውተቋማትን በመዝረፍ እና ሰነዶችን ለማጥፋት በሚል እንደሆነ አዲሱ የከተማዋ ከንቲባ መናገራቸው ታውቋል። ይህ ደግሞ ነገ አገር ሲረጋጋ እና ሁሉም ወደ ነበረበት ሲመለስ ተቋማት ከቆሙበት ለማስቀጠል እንዲሁም ብልሹ አሠራር የነበረባቸውን ደግሞ በሕግ አግባብ ሚዳኙበት ማስረጃ ስለሚሆኑ ከወዲሁ ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባ እና የዜጎችም ደኅንነት በዋናነት እንዲረጋገጥ ግድ ነው።

ከዚህም በተጨማሪ ደግሞ በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች በተለይም በቤንሻንጉል ጉሙዝ እና በኦሮሚያ ክልሎች ላይ ብሔርን መሰረት ያደረጉ ጉዳቶች እና ግድያዎች በየእለቱ እየተሰሙ መሆናቸው ደግሞ ትኩረት ተነፍጓል ተብሎ እንዲታሰብ ያደርጋል። ከዚህ ቀደም ትላልቅ ዘግናኝ እና አሰቃቂ ግድያዎች የተከናወኑባቸው አካባቢዎችን በሚመለከት የፌደራሉም ሆነ የክልል መንግሥታት ይሄ ነው ሚባል እርምጃ ባይወስዱም ነገር ግን በአደባባይ በመውጣት ሲያወግዙት እና ሲኮንኑ ይታይ ነበር።

ሆኖም ግን በቅርብ ጊዜ ወዲህ አንዳችም የፌደራል የመንግሥት አካል ሲያወግዝም ሆነ ወደ ሕዝብ በመውጣት መረጃዎች ሲሰጥ አልተስተዋለም ይህም በአስቸኳይ ሊሻሻል የሚገባው ጉዳይ እንደሆነ አዲስ ማለዳ ታስገነዝባለች።

በቤንሻንጉል ክልል እየተካሄደ ያለው ዘርን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች በተደጋጋሚ ሚስተዋሉ እና ዘላቂም መፍትሄ ያልተሰጣቸው ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ በተለይ ደግሞ መንግሥት የሕወሓትን ከፍተኛ አመራሮችን በሚያሳድድበት በዚህ ወቅት ጭራሹኑ ትኩረት ተነፍጎታል ብላ አዲስ ማለዳ ታምናለች። በመሆኑም ከዚህ ቀደም በሕወሓት አማካኝነት ሲደገፉ የነበሩ እና አደጋ ጣይ አካላትን በይፋ ሲፈርጅም ተስተውሏል።

ሕወሓት ከዚህ ቀደም ከኋላ ደጀን በመሆን ሲያበጣብጥ እንደቆየ የተነገረ ሲሆን ሕወሓትን እና ከፍተኛ አመራሮችን ለማጥፋት በሚደረገው ጥረት ታዲ በሌላም አካባቢ ሊኖረው የሚችለው ሕዋስ በሚገባ ትኩረት ተሰጥቶት አስቸኳይ እርምጃ ሊወሰድበት እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ታስገነዝባለች። ይህ እንቅስቃሴ እና ትኩረትም ከቤንሻንጉል ባለፈ በኦሮሚያ ክልል ወለጋ ዞንም እንዲደገም አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።

ኦነግ ሸኔ በሕወሓት እየተደገፈ ነው በሁሉም የኦሮሚያ ክልል ከተሞች እንዲሁም በተለይ በወለጋ ዞን ከፍተኛ አለመረጋጋትን ሲፈጥር የኖረው ሲባል ቆይቷል። በመሆኑም ሕወሓት እደተባለው ከመኪና ወርቦ በእርግ ሩጫ ላይ ከሆነ የኦሮሚያ ሕዋሱን ችላ ማለት አያስፈልግም ስትል አዲስ ማለዳ ታሳስባለች። ነገር ግን ይህ ባልሆነበት ሁኔታ የኦነግ ሸኔ ጥቃት ከወለጋ በተጨማሪ በጉጂም በኩል እንደሚንቀሳቀሱ በተደጋጋሚ ሲነገር ይስተዋላል።

ይህ ደግሞ ከወዲሁ ሀይ ባይ ካጣ አንደኛ የሕወሓት ርዝራዦች በኦነግ ሸኔ ይዞታ የመሸሸግ እና ድጋሚ የማንሰራራት ዕድል የሚያገኙ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ከዚህ ቀደም ያየነው የጌዴኦ ዞን መፈናቀል ሊከሰት ይችላል ስትል አዲስ ማለዳ ከወዲሁ ታስገነዝባለች። በተለያዩ አካባቢዎች የሰውልጅ ሕይወት እንደቀልድ በሚረግፍበት በዚህ ወቅት የመንግሥት ሥራ አንድን ስፍራ ብቻ ከአጥፊዎች በማላቀቅ እና ነጻ በማድረግ ሌላውን አካባቢ ከፍት ማድረግ ወይም ትኩረት መንፈግ መሆን የለበትም።

ይዋል ይደር እንጂ ይህ ጉዳይ በዳር አገር ያየነው እና በክልሎች በኩል የሚስተዋለው አለመረጋጋት እና ደኅንነት ዕጦት ቢቻል ዳግመኛ እንዳይፈጠር አድርጎ የእርምት እርምጃ መውሰድ ካልሆነ ደግሞ ባለበት ቆሞ ተጨማሪ ሕይወት እንዳይቀጠፍ ማድረግ፤ ካልተቻለ ደግሞ ወደ ፌደራል መንግሥት መቀመጫ ወደ ሆነችው እና የክልል ዋና ከተሞችም ላይ መምጣቱ ማይቀር እንደሆነ ልብ ሊባል ይገባል።

ሕዝብ ተከባብሮ እና ተዋዶ ሚኖርባትን አገር ከመገንባት እና ሊመጣ ካለው ብሩህ ተስፋ አንጻር ዜጎች ደኅንነት መረጋገጥ ቅድሚያ የሚሰጠው እና መንግሥትም በየትኛውም ጥግ ላይ የሚፈጠሩ ችግሮችን እኩል ትኩረት በመስጠት እርምጃዎችን በመውሰድ ሕግን ሊያስከብር ይገባል። አንድም ዜጋ በአገሩ ላይ ለመኖር ሊሳቀቅ እና ለወጥቶ መግባቱ ማረጋገጫ ሊያጣ እንደማይገባውም አዲስ ማለዳ በጽኑ ታምናለች።

ቅጽ 2 ቁጥር 111 ታህሳስ 10 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here