የሱር ኮንስትራክሽን ሠራተኞች የኹለት ወር ደምወዝ አልተከፈለንም አሉ

በአዲስ አበባ በሱር ኮንስትራክሽን ዋናው መሥሪያ ቤት የሚሠሩ ሠራተኞች የኹለት ወር ደምወዝ እንዳልተከፈላቸው እና ችግር ላይ እንደሆኑ ለአዲስ ማለዳ ገልጹ።
አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው በመሥሪያ ቤቱ በተለያየ የኀላፊነት ቦታ የሚሠሩ ሠራተኞች ቅሬታቸውን ሲገልጹ ላለፉት ኹለት ወራት ምንም ዓይነት ክፍያ ስላልተሰጠን ችግር ውስጥ ወድቀናል ብለዋል።

በዚህ ምክንያትም የቤት ኪራይ እና ሌሎች ወጪዎቻቸውን ለመሸፈን አለመቻላቸውን ተናግረዋል። ሠራተኞቹ አክውም አሁን ላይ ከአንዳንድ የአስተዳደር ሠራተኞች ውጭ የመጓጓዣ ገንዘብ ስለሌለን ወደ መሥሪያቤት እየሄድን አይደለም ሲሉ ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

ድርጅቱ የገጠመውን ችግር በመረዳት እና አሁን ላይ የድርጅቱ የባንክ ሒሳብ እንዳይንቀሳቀስ እንዲሁም ማንኛቸውም የተቋሙ ንብረቶች ለሦስተኛ ወገን ተላልፈው እንዳይሰጡ መታገዳቸውን ስለምናውቅ መፍትሄ እየጠየቅን ያለነው ከመንግሥት አካል ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የዘር ተኮር ጥቃት እና የሽብር ድርጊት እንዲፈጸም የገንዘብ ድጋፍ በማቅረብ፣ ሕገ-መንግሥታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመናድ ከሚንቀሳቀሰው የሕወሓት ኃይል ጋር ግንኙነት በመፍጠር እንዲሁም የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ የተሳተፉ ስለመሆናቸው እና በግብር ስወራ እና የሙስና ወንጀል ድርጊቶች ውስጥ ስለመሳተፋቸው ምርመራ ለመጀመር የሚያበቃ በቂ ማስረጃ የተገኘባቸውን ድርጅቶች የሚንቀሳቀሱ እና የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን በባንክ ያለቸውን ገንዘብ ጨምሮ ከህዳር 07/ 2013 ጀምሮ ማገዱን በማኅበራዊ የትስስር ገጹ ገልጿል።

እገዳው ከተጣለባቸው 34 ድርጅቶች መካከል ሱር ኮንስትራክሽን ፣ ጉና የንግድ ሥራዎች ፣ ሰላም የሕዝብ ማመላለሻ ፣ መስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግ እና አልመዳ ጨርቃ ጨርቅ ይገኙበታል። በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አወል ሱልጣን ስለ ሱር ኮንስትራክሽን ሠራተኞች የደምወዝ አለመከፈል ቅሬታ ለአዲስ ማለዳ ምላሽ ሲሰጡ በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እገዳ የተጣለባቸው ተቋማት የአብዛኛዎቹ ኀላፊዎች ከጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የበላይ አመራሮች ጋር በመነጋገር ለሠራኞች ደምወዝ መክፈል የሚችሉበትን ሁኔታ በማመቻቸት ላይ እንደሆኑ ገልጸዋል።

የታገዱ ንብረቶችን በሚመለከት የበላይ ጠባቂ እንዲቋቋም እንደሚያስፈልግ የተጠቆመ ሲሆን ይህ እንዲሆን የሚያደርገው የፍርድ ቤት ውሳኔ እስኪወሰን ድረስ እነዚህ ሠራተኞች ቤተሰብ ያላቸው እና ችግር ውስጥ ሊወድቁ የሚችሉ ስለሆኑ ጊዜያዊ መፍትሄ ለመስጠት ምርመራውን ከሚመራው ወይንም የንብረት ማስመለስ ሥራውን ከሚሠራው የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ክፍል ጋር በመነጋገር የሠራተኞች ደምወዝ በዘላቂነት እንዲከፈል ይደረጋል ብለዋል።

አወል የሱር ኮንስትራክሽን አመራሮችም በዚህ አሠራር መሰረት ወደ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በመቅረብ እና በመነጋገር የሠራተኞቻቸውን ችግር መፍታት ይችላሉ ሲሉ ገልጸዋል።

በእነዚህ ተቋማት በሚንቀሳቀሱ እና በማይንቀሳቀሱ ንብረቶቻቸው እንዲሁም በባንክ የሒሳብ ደብተራቸው ላይ የተደረገው እገዳ አስፈላጊ የሆነበት ምክንያት በተቋማቱ ላይ እየተደረገ ያለ ምርመራ እስኪጠናቀቅ ድረስ ድርጅቶቹ ሀብታቸውን እንዳያሸሹ ለሦስተኛ ወገን ተላፈው እንዳይሰጡ መሆኑን አሳውቀዋል። ይህ የተደረገው በትግራይ ክልል እየተካሄደ በነበረው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ጋር በቀጥታ የተገናኘ ሳይሆን በማዕከላዊ መንግሥት በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች ለተነሱ የሁከት ተግባሮች እንደተሳተፉ እና በገንዘብ እንደደገፉ በወንጀል ተጠርጥረው ምርመራ እንዲደረግባቸው እና የሀብት ምንጫቸው እንዲጣራ በመወሰኑ ጭምር ነው ብለዋል።

በሰው ሕይወት እና በንብረት ላይ የደረሰ ጉዳት መኖሩ ከተረጋገጠ ደግሞ ለካሳ ክፍያ እነዲሁም ከግብር ስወራ ጋር በተያያዘ ያለባቸውን ያልተከፈለ የግብር እዳ ለመክፈል እና በስተመጨረሻ የእነዚህ ተቋማት ሀብት በመንግሥ ከተወረሰ የእነዚህ ንብረቶች ዕጣ ፈንታም የሚወሰነው በፍርድ ቤት ውሳኔ ነው ብለዋል። የፕሬስ ሴክሬታሪያቱ ይህ አሠራር በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል ያለ ግለሰብ ወይንም የመንግሥት ባለሥልጣን ያለ አግባብ ያካበተው ሀብት ወይንም ንብረት ካለ የሚያጣራ ነው ጥቆማዎችንም እየተቀበልን እንገኛለን ሲሉ አሳውቀዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 111 ታህሳስ 10 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here