በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ተደራጅተው በዜጎች ጥቃት የሚፈጽሙ የታጠቁ ኃይሎችን በሰላማዊ መንገድ ትጥቅ ካልፈቱ መንግሥት የመጨረሻ ሕግ የማስከበር ሥራ እርምጃ እንደሚወስድ መወሰኑን የክልሉ መንግሥት ኮሙኒኬሽን አስታወቀ፡፡
በክልሉ መተከል ዞን በተደጋጋሚ በታጠቁ ኃይሎች በንጹሐን ዜጎች ላይ ግድያ መፈጸሙን አሁንም ድረስ ሊገታ ባለመቻሉ የክልሉ መንግሥት የታጠቁ ኃይሎች ትጥቅ ፈትተው በሰላማዊ መንገድ እጃውን እንዲሰጡ ጥሪ ማስተላለፉንና የቀረበላቸውን ሰላማዊ ጥሪ ተቀብለው ትጥቅ የማይፈቱ ከሆነ የክልሉ መንግሥት የመጨረሻ እርምጃ ኦፕሬሽን እንደሚጀመር የክልሉ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ኀላፊ መለስ በየነ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል፡፡
ኀላፊው ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቁት በዞኑ በተደጋጋሚ በንጹሐን ዜጎች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ሊገታ ባለመቻሉ የክልሉ መንግሥት ከፌደራል ፖሊስ፣ ከመከላከያ ከክልሉ የጸጥታ ኃይል ጋር በጋራ በመሆን የታጠቁ አጥቂዎችን ለማስወገድ ቅደመ ሁኔታዎች እየተመቻቹ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በዞኑ ታጥቆ ጥቃት የሚፈጽመውን ኃይል እስካሁን ማስወገድ ያልተቻለው የአካባቢው መልክአምድር ምቹ አለመሆኑ አንድ እንቅፋት እንደነበረበት መለስ ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም አሁን ላይ እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ ሁኔታዎችን ክልሉ በማጽዳት ላይ እንደሚገኝ ተመላክቷል፡፡
የክልሉ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቀው ከሆነ የክልሉ መንግሥት በዞኑ 280 የታጠቁ ኃይሎችን እንደደመሰሰ መለስ ተናግረዋል፡፡ እንዲሁም 277 ታጣቂዎች የተማረኩ ሲሆን፣ በጥቃት ተሳትፈዋል ተብለው የተጠረጠሩ 66 በክልሉ መንግሥት መዋቅር ሥር የነበሩ አመራሮችም ተይዘዋል ተብሏል፡፡
ችግሩ ሲቆይ የብሔር መልክ እየያዘ መምጣቱን የጠቆሙት ኀላፊው የክልሉ መንግሥት ችግሩን ለመቅረፍ ሌሎች እንደሚሉት ቁርጠኛ ሳይሆን ቀርቶ አይደለም ብለዋል፡፡
የክልሉ መንግሥት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ቁርጠኛ አይደለም የሚል ሐሳብ ከአጎራባች ክልል መነሳቱን የጠቆሙት መለስ፤ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት መተባበር የተሻለ ነው ብለዋል፡፡ “ችግሮች የሚፈቱት መግለጫ ጋጋታ ሳይሆን ተጋግዞ ችግሮችን መቅረፍ ይበጃል፡፡” ሲሉ መለስ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን በተለያዩ ወረዳዎች ላይ በተደጋጋሚ የሚደርሰውን ግድያ ተከትሎ የአማራ ክልል መንግሥት የቤኒሻንጉል ክልል መንግሥት የመግለጫ ልውውጥ ውጥረቱ እንዲባባስ እንዳደረገው ኗሪዎች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡
አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይጠቀስ ያሳሰቡ በቡለን ወረዳ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የሚሠሩ ግለሰብ የኹለቱ ክልል መንግሥታት የመግለጫ ልውውጥ መካረር በአካባቢው በየጊዜው የሚስተዋለውን ችግር እንዲባባስ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡ እንደማሳያነትም በቡለን ወረዳ ባለፉት ኹለትና ሦስት ቀናት ውስጥ የክልሎችን መካረር ተከትሎ ነጭና ጥቁር በሚል በግልጽ ለይቶ ጥቃት እየተፈጸመ ነው ሲሉ አስረድትዋል፡፡
የአማራ ክልል መንግሥት በክልሉ ኩሙኒኬሽን ኀላፊ ሥም ያወጣው መግለጫ “የአማራና የአገው ሕዝብ የሚደርስበትን ግፍ ለአገር አንድነት በሚል በበዛ ትዕግስት ማሳለፋችን እንደፍርሀትና ኃጢአት ተቆጥሮ ያለከልካይ በሺዎች የሚቆጠሩ በግፍ ተገድለዋል፣ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻችን ተፈናቅለዋል፣ ሀብትና ንብረታቸውን በግፈኞች ተዘርፈዋል። ስለሆነም እኛ ግፉን እንደወትሮው ሁሉ አዝነንና መግለጫ አውጥተን የቤንሻንጉል ጉምዝ መንግሥትን ተለማምጠን የምናልፍበት ጊዜ አብቅቷል።” የሚል ነበር፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብልጽግና ፓርቲ በአጻፋው ባወጣው መግለጫ “በሕገ መንግሥት የተደራጀ ክልል ውስጥ ከፌደራል መንግሥት ዕውቅና ውጭ ገብቼ እዋጋለሁ ብሎ በተደጋጋሚ ዛቻ እና ማስፈራሪያ አዘል ቃላቶች ጭምር በመጠቀም መግለጫ መስጠት በሕዝቦች መካከል ግልፅ ጦርነት ማወጅ ነው፡፡” ሲል የአማራ ክልል መንግሥትን መግለጫ ማጣጣሉ የሚታወስ ነው፡፡
ፓርቲው በመግለጫው “አንዳንድ የአሮጌ ሥርዓት ናፋቂዎች አሁንም ኅብረ ብሔራዊ ፌደራሊዝም በጉልበት በማፍረስና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን በመናድ በሕዝቦች መካከል ለዘመናት የቆየውን አብሮነትና ወድማማችነት እንዲሻክር ይባስ ብሎም የብሔረሰብ ስም በመጥቀስ ጥላቻና ግጭት እንዲበረታ አልመው በመሥራት ላይ እንደሚገኙ ለማስተዋል ችለናል፡፡” ሲል መግለጹ የሚታወስ ነው፡፡
ቅጽ 2 ቁጥር 111 ታህሳስ 10 2013


