በኤልሻዳይ ድርጅት ታቅፈው የነበሩ ወጣቶች ወደ አዲስ አበባ እየፈለሱ ነው

0
714

በኤልሻዳይ ሪሊፍ ኤንድ ዲቨሎፕመንታል አሶሴሽን ከጎዳና ላይ ተነስተው በአፋር ክልል ካምፕ ውስጥ ከ2007 ጀምሮ ሲኖሩ የነበሩ ወጣቶች ከመስከረም ወር ጀምሮ ክፍያ እንዳልተከፈላቸው እና ለችግር እና ለረሀብ በመጋለጣቸው ወደ መሐል ከተማ እየመጡ እንዳሉ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸዉ የአይን እማኞች ተናገሩ።
ታህሳስ ኹለት 2013 24 የሚሆኑ ወጣቶች በአዲስ አባባ ሠራተኛና ማኅበራዊ በኩል መቆያ ቦታ እንደተሰጣቸው እና አሁን ደግሞ 22 የሚሆኑ ወጣቶች መጥተው በጎዳና ላይ እንዳሉ ሌሎችም እየመጡ እንደሆነ አዲስ ማለዳ ካየቻቸው ማስረጃዎች ለማወቅ ችላለች።

ሚያዚያ 23 2007 ላይ ኤልሻዳይ ሪሊፍ ኤንድ ዲቨሎፕመንታል አሶሴሽን የሚባል አገር በቀል ግብረ ሰናይ ድርጅት፤ የጎዳና ተዳዳሪዎችን አንስቼ ሕይወታቸውን እቀይራለሁ በሚል ከሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ጋር በመቀናጀት ብዙ ልጆችን ከጎዳና አንስቶ እንደወሰደ ከጎዳና ተነስተው አፋር ክልል ሄደው እንደ ነበር አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ጉደታ ትርፌ ተናግረዋል።

በአፋር ክልል ዞን ሦስት አሚባራ ወረዳ አዋሽ አርባ አካባቢ ከከተማው ራቅ ብሎ በሚገኝ ጫካ ላይ አንድ ካምፕ ውስጥ አስገብቶ በተለያዩ ትምህርቶች አሠልጥኖ እንዳስመረቀ እና በተለያዩ የሥራ መስኮች ሊያሰማራቸው ቃል ቢገባላቸውም ካሠለጠናቸው በኋላ ሳያስቀጥራቸው እንደቀረ ተናግረዋል።
ከጎዳና ሲያነሳቸው ለሦስት ዓመት ብቻ ሠርተው 150 ሺሕ ብር ሰጥቶ እንደሚያስወጣን በውል ተፈራርመው እንደነበር እና ምንም አይነት ገንዘብም ሆነ ወደ ሥራ ሳያሠማራቸው መቅረቱን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ሰባት ዓመታትን ከዕድሜያችን ላይ በልቶናል ያሉት ጉደታ በዋናነት አሁን አዲስ አበባ መጥተን መንገድ ላይ እያደርን ነው መንግሥት በጊዜያዊነት መጠለያ ይስጠን ሕጻናት ልጆች ሴቶችን ይዘን በእንግልት ነው ያለነው ብለዋል።

መለመን አንፈልግም ሠርተን መቀየር ነው የምንፈልገው መንግሥት ሥራ እንዲሰጠን እንፈልጋለን የሰባት ዓመት በባዶ ተስፋ የቆየንበት ካሳ እንዲከፍለን እንፈልጋለን ብለዋል።

ከዚህ በፊት ለኪስ እያለ አንድ ሺሕ 450ብር ይከፍላቸው እንደነበር እና ለኛ ተብሎ የሚገባውን እህል ትተው የተበላሸ ዱቄት እየሰጡን ዳቦ እየጋገርን እንበላ ነበር፤ ምንም ዓይነት ጥያቄ ስናነሳ እስከዛሬም የቆየነው ለምንድን ነው እንደዚህ የሚሆነው ሥራ ስጡን ስንል ያስፈራሩናል ይደበድቡናል እናንተ አሸባሪዎች ናችሁ በሚል ያባርሩን ነበር ብለዋል።

በቅርብ ጊዜ ደግሞ ኹለት ሺሕ አራት መቶ ሰላሳ ብር መክፈል የጀመሩ መሆኑን የተናገሩት ጉደታ፤ ክፍያው በመቋረጡ ለችግር እንደተዳረጉና ግብርና ሚኒስቴር ከኤልሻዳይ ጋር በጋራ በመሆን ይሰሩ እንደነበር ስለዚህም መንግሥት ባፋጣኝ ምላሽ ይስጠን ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ ያነጋገረቻቸው በግብርና ሚኒስቴር የፕሮጀክቱ መሪ ውድነህ ጨንገሬ እንደተናገሩት ኤልሻዳይ የተባለው ድርጅት በ2007 ከጎዳና አንስቶ ወጣቶችን ለሥራ አሰማራለሁ በሚል ወስዶ እንደነበር እና በተለያየ የሥራ ዘርፍ ሥልጠና እንዳሠለጠናቸው ተናግረዋል።

ምንም እንኳ ሥራ እፈጥራለሁ ቢልም ግን ምንም ዓይነት የሥራ ዕድል ሳይፈጥርላቸው እንደቆየ ነገር ግን በወር 1 ሺሕ 450ብር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በወር ኹለት ሺሕ ሦስት መቶ ሀያ ብር እየከፈላቸው እንደቆዩ ተናግረዋል።

ይህ ፕሮጀክት ኤልሻዳይ ሲይዘው ወጣቶችን ብቁ አደርጋለሁ ብሎ እንደነበር አስታውሰው ነገር ግን ከማሠልጠን የዘለለ ምንም የሥራ ዕድል ሳይፈጥርላቸው ቆይቷል። አሁን ደግሞ በሕግ የባንክ ሂሳቡ እንዳይንቀሳቀስበት ስለታገደ ክፍያ እንዳልተከፈላቸው እና ለግብርና ሚኒስቴር እንዳሳወቁ ለአዲስ ማለዳ አረጋግጠዋል።
በባንክ ያለውን ሂሳቡ እንዳይንቀሳቀስ በሕግ በመታደጉ ምክንያት ከመስከረም ወር ጀምሮ ክፍያ እንዳልከፈላችውና ለችግር በመጋለጣቸው ይከፈለን የሚል ጥያቄ እንዳላቸው እና ጥያቄውም አግባብነት እንዳለውም ተናግረዋል።

በዚህም ግብርና ሚኒስቴር በረሀብ እየተቸገሩ በመሆናቸው ከብሔራዊ አደጋና ስጋት ጋር በመነጋገር ስንዴ እየተላከላቸው እንደሆነ እና የሕዳር ወርም እንደተላከላቸው ተናግረዋል።

በካምፑም 425 የሚሆኑ ሰዎች እንዳሉ የተናገሩት ውድነህ ወደ አዲስ አበባ እየመጡ እንደሆነ እንደሰሙና ይህም አግባብነት እንደሌለው በሕግ የተያዘ ጉዳይ ስለሆነ የሚሻለው እዛው ተቀምጦ ከመንግሥት የሚሰጠውን ምላሽ መጠባበቅ እንደሆነ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።
ወደ አዲስ አበባ መምጣት መፍትሄ አይደለም ያሉት ውድነህ ለእንግልት ነው የሚዳረጉት በማለት ለአዲስ ማለዳ አሳውቀዋል።

እንደ ውድነህ ገለፃ አሁን አሳሳቢ የሆነው ችግር ውሀ የሚያቀርብላቸው ቦቲ መኪና ክፍያ አልተከፈለኝም በሚል ጥሎ መውጣቱ እንደሆነ ተናግረዋል።
በዛ በረሀ ላይ ደግሞ ያለ ውሀ መኖር በጣም ከባድ ነው፤ ይህንን ለማስተካከል ግብርና ሚኒስቴር የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራን እንደሆነም ተናግረዋል።
ግብርና ሚኒስቴር ችግሮቻቸውን ተረድቶ መፍትሄ ለመስጠት ለጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ ደብዳቤ ያስገባ እንደሆነና ምላሽ በመጠባበቅ ላይ እንዳለ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ያነጋገረቻቸው ኤልሻዳይ ሪሊፍ ኤንድ ዲቨሎፕመንታል አሶሴሽን ተጠባባቂ ዳይሬክተር ቅድስት በቀለ እንደተናገሩት የኤልሻዳይ ዳይሬክተር የነበሩት የማነ ወልደአማኑኤል ጨምሮ ኹለት የማኔጅመንት አካላት ሥራውን ለቀው እንደሄዱ ተናግረዋል።

የማነ በደብዳቤ በሕመም ምክንያት ሥራውን መቀጠል እንደማይችሉ አሳውቀው ሀምሌ መጀመሪያ አካባቢ እንደጠፉን በድርጅቱ ቦርድ አማካኝነት ከሠራተኞች መሀል ተጠባበቂ ዳይሬክተር እንደሆኑ ተናግረዋል።

ኹለቱ የማኔጅመንት አመራሮች መቀሌ ነን ክስ ስለተከፈተብን እና ለደህንነታችን ስለምንሰጋ አንመጣም የሚል ምላሽ ሰጥተው የድርጅቱን ንብረት መኪና ሳይመልሱ እንደጠፉ በተደጋጋሚ መልሱ የሚል ደብዳቤ ብንልክም መልስ አላገኘንም በዚህም ክስ መስርተናል ብለዋል።

አፋር ክልል ላይ የሚገኙት ሰዎች ችግር ላይ መሆናቸውን እንደሚያውቁና ነገር ግን በጠቅላይ አቃቤ ሕግ የባንክ አካውንቱ ስለተያዘ ምንም መክፈል እንዳልቻለ ተናግረዋል።

በኤልሻዳይ ውስጥ አንድ ሺሕ ሃያ አምስት የሚሆኑ ሰዎች እንዳሉ እና ችግር ውስጥ እንዳሉ ጠቁመዋል።
በተቻለ ድጋፍ ለማድረግ እየተሞከረ ነው ያሉት ቅድስት የኤልሻዳይ ህልውና ምን እንደሆነ የሚወሰነው ከምርመራው በኋላ እንደሆነ ተናግረዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 111 ታህሳስ 10 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here