የቱሉ ሞዬ ጂኦተርማል (እንፋሎት ሀይል ማመንጫ) ሀይል ለማመንጨት ከሚያስፈልገው ሦስት ጉድጓድ መሀል አንድን ጉድጓድ አስገንብቶ መጨረሱን እና ይህንንም ተከትሎ የእንፋሎት ኃይል ማመንጫው ግንባታ በተያዘለት ጊዜ እየተከናወነ እንደሆነም የእንፋሎት ኃይል ማመንቻው ዋና ስራ አስፈጻሚ ዳረል ቦይድ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
የተቆፈረው ጉድጓድ 1500 ሜትር ርቀት እንዳለውም ተመላክቷል።የጉድጓዱን ግንባታ ለማከናወን 40 ሚሊየን ዶላር እንደፈጀበትም ታውቋል።
እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 2023 ሙሉ በሙሉ ኃይል ማመንጨት ለመጀመር ዕቅድ ይዞ እየሰራ የሚገኘው ቱሉ ሞዬ ጂኦተርማል በመጀመሪያው ዙር 50 ሚጋ ዋት ኃይል እንደሚያመነጭ ዕቅድም ተይዞለታል። በሙሉ አቅም ወደ ስራ ሲገባም 150 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚያመነጭም ይጠበቃል። ሰባት ሳንቲም በኪሎ ዋት ሀወር ለመሸጥ ከወዲሁ ውል የገባው ቱሉ ሞዬ ለ25 ዓመታት በባለቤትነት ያስተዳድረዋል።
ዳረል ቦይድ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቁት ቱሉ ሞዬ በግንባታው አካባቢ ባሉ ነዋሪዎች ዘንድ ያለውን ትስስርም ለማጠናከር ለአካባቢው ተወላጆች ነጻ የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ እና ሰልጥነው ሲመለሱም በኩባንያው ውስጥ ስራ የሚያገኑበትን እድል እያመቻቸ እንደሆነም ገልጸዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 112 ታኅሣሥ 17 2013


