በቅርቡ ለሕትመት የበቃውን ‘አብራክ’ የተሰኘ የሙሉጌታ አረጋዊ ልቦለድ ድርሰት ያነበቡት እና ዋሽንግተን ዲሲ ለነበረው የመጽሐፉ ግምገማ አስተያየታቸውን ያቀረቡት ሶሊያና ሽመልስ፥ መጽሐፉ የዘመናችንን ፖለቲካዊ ስርዓተ ማኅበር በመሰነድ መልሶ ለእኛ እና ለቀጣዩም ትውልድ እንዲነበብ አድርጎታል ይላሉ።
ርዕስ፦ አብራክ
ደራሲ፦ ሙሉጌታ አረጋዊ
የመጽሐፉ ዓይነት፦ ልቦለድ
የገጽ ብዛት፦ 453
የታተመበት ጊዜ፦ ነሐሴ 2010 (ዋሽንግተን ዲሲ)፣ ጥቅምት 2011 (አዲስ አበባ)
ከጥቂት ወራት በፊት ዋሽንግተን ዲሲ ላይ ወዳጆቼ ‘አብራክ’ ከተሰኘ አዲስ የልብወለድ መጽሐፍ በኅትመት ላይ እንዳለ ነገሩኝ። የተመረጡ ልብወለዶችን ለሚያነብ የእኔን ዓይነቱን ሰው መጽሐፉን እንዳነበው፣ ብሎም የመጽሐፍ ግምገው ላይ እንድሳተፍ ማሳመን ቀላል አልነበረም። 453 ገጾች ያሉትን መጽሐፍ ለማንበብ የፈጀብኝ ጥቂት ቀናት ሲሆን በወቅቱ የመጽሐፍ ግምገማው ላይ ለመሳተፍም ጉጉት እንዲያድርብኝም አድርጓል። ‘አብራክ’ ረጅም ከሚባሉ ልቦለዶች የሚመደብ ቢሆንም ከሚያነሳው ጭብጥና የገጸ ባሕሪያቶቹ መስተጋብር ውስብስብነት አንፃር አንባቢ ርዝመቱን ሳያስተውል ሊጨርሰው የሚችለው ዓይነት መጽሐፍ ነው። እንደ አገር የዘረጋነው የፓለቲካ ስርዓት ከፍቅር እስከ ቤተሰብ፣ ከፓርቲ እስከ ማኅረሰብ በረጅሙ የሚመዘዘውን ተፅዕኖ ተነባቢ በሆነ መልኩ በማሳየት በኩል ‘አብራክ’ ተሳክቶለታል ቢባል ማጋነን አይሆንም።
የፖለቲካ ስርዓትና ፍቅር
የ’አብራክ’ ዋና ገጸ ባሕሪያት አርካኒ እና ዋርካ ፍቅረኛሞች ናቸው። የመጡበት ማኅበረሰብ አንዳቸው ስለሌላቸው ከሚያስበው ተነጥለው የቆሙት እኒህ ወጣቶች አንዳቸው ለሌላቸው ጠንካራ ስብእና መማረካቸውና ፍቅራቸው ጣጣ ያመጣባቸው ገና የትውውቃቸው ዕለት ነው። ከቤተሰብ እስከ ማኅበረሰብ የብሔር አመጣጣቸውን መሠረት አድርጎ የሚደርስባቸው መገለልና የየዕለቱን ፈተናቸውን ለማለፍ የሚያደርጉት ጥረት በወቅቱ (በመጽሐፉ መቼት) ኢትዮጵያ ከምትታመስበት የተቃውሞ ፖለቲካና የተካረረ ብሔርተኝነት ተደምሮ ፖለቲካ የእያንዳንዳችን የግል ሕይወት ላይ ምን ዓይነት ተፅዕኖ እንደሚያመጣና የብዙዎችን ቤት እንደሚነካካ ‘አብራክ’ ፍንትው አድርጎ ያሳያል።
የፖለቲካ ውይይት፣ ክርክርና ትንታኔዎች በተሳካ ሁኔታ ሊገልጹት የማይችሉትን ፖለቲካ የግለሰቦች ሕይወት ላይ ያለውን ተፅዕኖ በማስረዳት በኩል (በልብወለድ መልክ መጻፉም ረድቶት) መጽሐፉ የተሳካለት ነው። የሰው ልጆች እውነተኛ ግንኙነት (በብሔር) ፖለቲካ ዓይን ሲመዘን ሊያነሳ የሚችለውን ሚዛን ለማሳየት ደራሲው የተወሳሰቡ፣ ከተለያዩ ብሔር አባላት መካከል የተውጣጡ ግለሰቦችን ማኅበራዊ ግንኙነት፥ ከማኅበረሰባዊ የፖለቲካ አመለካከቶቻቸው ጋር ለመነጠል ያደረገው ጥረት ተሳክቶለታል። ገጸ ባሕሪያቱ ቀልድንና የዕለት ሰዋዊ ግንኙነትን ከፖለቲካ አመለካከቶቻቸው ጋር አጣምረው ማሳየታቸው የማንነትን ተለዋዋጭነት ለማሳየት ምሳሌ ሆነው ከመቅረባቸውም በተጨማሪ፥ የሰው ልጆች ግንኙነትን ከፖለቲካ በልጦ ይመዝናል የሚል አዎንታዊ ስሜትን ለመፍጠር መሞከሩ በዘመናችን በየማኅበረሰቦቻችን ላይ ለምናሳየው ተስፋ መቁረጥ ለማከም ሊረዳን ይችል ይሆናል የሚል ግምትም አለኝ።
የዘመኑ መንፈስ
የዘመናችንን የፖለቲካ ስርዓተ ማኅበር፣ ብሔር ተኮር ፌደራሊዝምን እና በተግባር ሲፈተሽ ያሉበትን ተግዳሮቶች ‘አብራክ’ በሚገባ ሰንዶታል። ይህንን ማሳያ ለመጥቀስ ያክል፣ በዋናነት የመጽሐፉ ትሩፋትና የወደፊት መታወሻ ሊሆን የሚችለው ዘመኑንና መሠረታዊ ኹነቶቹን ጠቅልሎ በአራት መቶ ገጽ ማቅረቡ ነው። ልብወለዱ በቅርብ የአገራችን የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ያሉትን ኹነቶች የታሪኩ አካል አድጎ ማቅረቡ እና የዘመናችንን ተግባር እና መንፈስ ማሳየቱ ዓመታት በኋላ ለምታነበው/የሚያነበው ማንኛውም ሰው ከዚህ ቀደም አገራዊ የፖለቲካ ኹነቶችን ተንተርሰው ከተሠሩ እንደ ‘አብዮቱ መባቻ’፣ ‘ዋዜማ’ እና የመሳሰሉት ዓይነት የፖለቲካዊ ኹነቶችን በልብወለድ መልክ ሰንደው ካኖሩ መጽሐፍት ጋር የሚጋራው ባሕሪይ መኖሩ አይቀርም።
በመጽሐፉ ፍቅረኞቹ አርካኒ እና ዋልታ ከመምህርነታቸው በተጨማሪ ከሰብኣዊ መብቶች ጋር የተያያዙ የፍርድ ቤት ኬዞችን ለመወከል ጥረት ሲያደርጉ፣ የሕግ የበላይነት በዘመናችን ያለውን/የነበረውን ቦታ፣ የፀረ-ሽብር ሕጉን ሚና፣ የፖለቲካ እስርን እና የብሔር አመጣጥ የፖለቲካዊ እስር ላይ ያለውን ተፅዕኖ፣ በየክልሎቹ የነበረውን ተቃውሞ እና የማኅበራዊ ሚዲያ ሚናን ተጠቃሎ ‘አብራክ’ ላይ ማግኘት ይቻላል። ገጸ ባሕሪያቶቹ በቅርብ የምናውቃቸው የሚመስሉ፣ የምንኖረውን ዓይነት ኑሮ የሚኖሩ የምናውቃቸው ቦታዎች ውስጥ ቡና የሚጠጡ መሆናቸው መጽሐፉን ዘመኑን የዋጀ ያደርገዋል።
ከዓመታት በኋላ፣ በነበረው የፖለቲካ ምኅዳርና ተያያዥ ጉዳዮች ምክንያት የጋዜጣ እና የሚዲያ ሰነዶች የፖለቲካ ሁኔታውን ባልዘገቡበትና ለታሪክ ለማስቀመጥ ባልቻሉበት ሁኔታ በልብወለድ መልኩም ቢሆን ዘመኑ ምን እንደነበር ለማሳየት ‘አብራክ’ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያደርጋል። ዘመኑን መሰነድ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ፖለቲካዊ ሁኔታዎች የተነሳ የምናሳቸውና በፖለቲካ ክርክር ሥር ተቀብረው የቀሩ መሠረታዊ ጥያቄዎችን ቢቻል ለመመለስ፣ ባይቻል ደሞ ጥያቄዎቹን ለማንሳት ወደኋላ አይልም። የትግራይ ሕዝብ ለምን በአደባባይ ሕወሓን አይቃወምም፣ የሕወሓት በትግራይ ሕዝብ ላይ ያለውን ሚና የመሳሰሉትን ዓይነት ውስብስብ ጥያቄዎች በሐፍረትና በመሽኮርመም ከማለፍ ይልቅ ድምፃቸው የማይሰማ የማኅበረሰብ ክፍሎችን እና የሚያልፉበትን የፖለቲካ ልምድ በልብወለድ መልኩ ለማቅረብ ይሞክራል። የደራሲው ስሱ የሆኑ ጉዳዮችን ያለማፈር እና ውስብስብ ጉዳዮችን ያለመሸሽ ድፍረት፣ ዘመኑን ለመሰነዱ ከፍተኛ አስተዋፅዖ አድርጓል።
የ’አብራክ’ ሴት ገጸ ባሕሪያት
በቅርቡ ካነበብኳቸው የፈጠራ ሥራዎች ውስጥ የ’አብራክ’ን ሴት ገጸ ባሕሪያት ያክል የበቁ ፣ ሚናቸውን ያወቁ፣ ከማኅበረሰባዊ እና ግላዊ ችግሮች ያልራቁ ነገር ግን ችግሮቹን ለመፍታት ጠንካራ ሚና ያላቸው ሴት ገጸ ባሕሪያትን ሌላ የፈጠራ ሥራ ላይ አላየሁም። የ’አብራክ’ ሴት ገጸ ባሕሪያት ደግ፣ ክፉ፣ ተሳሳች፣ እና አስደሳች ናቸው። አንድ ዓይነት ሆነው ካመቀረፃቸውም በተጨማሪ፣ ሴትነታቸው ብቻ የሚታይ፣ ፍቅርን ለመፍጠር ወይም ታሪክ ለማሳመር የተቀረፁ ገጸ ባሕሪያት አይደሉም። የሥነ ተዋልዶ ጤና፣ ፅንስ ማቋረጥ፣ የሴቶች በሥራ እና በቤተሰብ መመሥረት መካከል ያለውን ሚዛን የመሳሰሉት ጉዳዮች እንደመሠረታዊ ጉዳዮች ሆነው በመጽሐፉ ውስጥ በተለያየ ሁኔታ ብቅ ብቅ ይላሉ። ሴት ገጸ ባሕሪያቶቹም ስሜት ሳያንሳቸው፣ ነገር ግን ጥንካሬም ሳያሳጣቸው የሚያጋጥሟቸውን ፖለቲካዊም ሆነ ሥነ ተዋልዷዊ ጤና ጉዳዮች ሲፈቱ፣ ሲወስኑ ይታያሉ። ሴቶች የሚያልፉባቸውን የግልና ማኅበረሰባዊ ጫናዎች ሳያሳንስ አቅማቸውም ሳይገደብ፣ የውሳኔ ሰጪነታቸው ሚናም ሳይስተጓጎል በፈጠራ ሥራዎቻችን እና ምናባዊ ፈጠራዎቻችን ላይ መታየታቸው ይበል የሚያሰኝ፣ ለሌሎች ደራሲዎቻችን ዓይኖቻቸውን እንዲስተካክሉ ምሳሌ ሁሉ ሊሆን የሚችል ነው።
የልኂቃን ንግግር
ድክመት መሆን አለመሆኑ አነጋጋሪ ቢሆንም መጽሐፉ ፖለቲካን በዋናነት ከፍተኛ የዕውቀትና የኢኮኖሚ ደረጃ የሚገኙ የማኅበረሰብ ከፍሎች ጉዳይ ብቻ አድርጎ አቅርቦታል። የኢኮኖሚ የፖለቲካ እና የመሳሰሉት ሰፊው ሕዝብ ጥያቄዎች በተለያየ መልኩ በልኂቃን ገጸ ባሕሪያቱ በኩል ቢጠቀሱም፥ ከሰፊው የዕለት ተለት ማኅበረሰባዊ ጉዳዮች ይልቅ በጣም ውስብስብ የሆኑ ብሔርተኝነት፣ የሕግ የበላይነት፣ የማንነት ጉዳዮች እና የመሳሰሉት የልኂቃን ውይይት ጉዳዮች የመጽሐፉ አጀንዳዎች ናቸው። በኢኮኖሚ ረገድም ቢሆን የዩኒቨርሲቲ መምህራን ሆነው ፍፁም ምቾት ያለው ከፍተኛ ገቢ ያለው ሰው ኑሮ የሚኖረውን ኑሮ ሲኖሩ በመጽሐፉ መታየቱ፣ የማንነትና የብሔር ፖለቲካ ቁርቁዝ በአገራችን እንዲረሳ ያደረገውን የመደብ ጉዳይ ደራሲውንም እንዲረሳው አድርጎታል ያስብላል። ይህ መጽሐፉን የልኂቃን ድምፅ ብቻ ሆነና ከዕለት ተዕለት የኑሮ ሁኔታና ችግር የራቀ ነው የሚል ስሜት ሊፈጥር ይችላል።
መጽሐፉን አንብቦ የጨረሰ ሰው ‘አብራክ’ ጨለምተኛና አሁን በአገራችን የተንሰራፋውን የብሔርተኝነት ጣጣ በጣም በተጋነነ እና ጥፋቱን ባከበደ የስጋት ዓይን ከማየት ውጪ ያመላከተው የመፍትሔ መንገድ የለም የሚል ስሜት ሊሰማው ይችል ይሆናል። ኑሯችን እንደ መጽሐፉም ሆነ፣ እንደ አገር ወይም እንደ ፖለቲካ ማኅበረሰብ ‘ተስፋ የለንም’ የሚል የስጋት ስሜት ይፈጥራል። የ‘አብራክ’ ዓይነት መጽሐፍት ዋና ጥቅማቸውም የዕለት ተለት የፖለቲካና የማኅበራዊ ገጠመኞቻችንን በተሰባሰበ መልኩ በማሳየት አገራዊ አደጋን ወይም ዕድልን በትልቅ ምስል ውስጥ መከሰታቸው ነው። መጽሐፉ ለሚያሳየው አደጋ መፍትሔውን ማሳየት ባይችልም እንኳን ማኅረሰባዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮቻችንን በአትኩሮት ዓይተን ሳይረፍድ እንድናርቅ የማንቂያ ደወል ማስተላለፉ (ለዚያውም የልብወለድ ቅርፅን ተጠቅሞ) በራሱ ለዘመኑ የሚመጥን ሥራ በመሆኑ አገር፣ ብሔርተኝነት፣ የሕግ የበላይት እና ዜግነት የመሳሰሉ ጉዳዮች የሚያሳስቡት ሰው ሁሉ ሊያነበው የሚገባ ነው።
ሶሊያና ሽመልስ ጦማሪ፣ የመብቶች ተሟጋች እና የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብቶች ፕሮጀክት (ኢሰመፕ) ዋና አስተባባሪ ናቸው። በኢሜይል አድራሻቸው soliyesami@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።
ቅጽ 1 ቁጥር 8 ታኅሣሥ 27 ቀን 2011