የከተማ ፖለቲካ (ክፍል ሁለት)

0
955

ከተሞች የፖለቲካ ማዕከል ናቸው የሚሉት ኢሳያስ ውብሸት፥ በኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ የፖለቲካ ሒደቶችን በመቃኘት በሚጀምሩት በዚህ ጽሑፋቸው ከተሞች የፖለቲካ ዕሳቤዎች የሚጠነሰሱባቸው መድረኮች ናቸው በማለት ይህንን ባሕሪያቸውን በነባራዊው ዐውድ አስደግፈው ያስነብቡናል።

 

 

(ክፍል ሁለት)
ቅይጥ ኅብረተሰብ
ብሪስ (እኤአ 1966) እንደሚገልጸው ሁለት ኃይሎች ለከተማ ዕድገት አስተዋፅዖ ያደርጋሉ፡፡ አንደኛው፣ ጎታች ኃይል ሲሆን፣ ይህም በከተሞች የሚታየው “የተሻለ” የሚባል የአኗኗር ዘይቤ፣ ደኅንነት እና ጥበቃ፣ መሠረተ ልማት እና ሌሎች አመላካች ሁኔታዎች መኖሩ በገጠራማው አካባቢ የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍልን ቀልብ በመግዛት እግሮቻቸውን አንስተው ወደ ከተማ እንዲጓዙ ዋንኛ ምክንያት ሆኗል ይላል፡፡ ሁለተኛው፣ ደግሞ ገፊ ኃይል ነው፤ ብሪስ እንደሚለው ይሄ ኃይል በዋናነት ሰዎችን ከሚኖሩበት አካባቢ ገፍቶ የሚያስወጣ ሲሆን ምክንያቶቹ ደግሞ ወቅታዊ የሆነ ግብርና፣ ከፍተኛ የገጠር ድኽነት እና ሌሎችም ናቸው፡፡ ከተሞች በእነዚህ ምክንያት የተለያየ ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ ማንነት ያላቸው ኅብረተሰቦች ተቀይጠው በአንድ ጥላ ሥር የሚኖሩበት ማዕከል ነው፡፡ እንደ ሶሮኪን እና ዚመርማን ጽሑፍ “ቅይጥነት” ከተሜውን ከገጠሩ ማኅበረሰብ (አንድ ዓይነትነት) ለመለየት የምንጠቀምበት መገለጫ አድርገው ይወስዱታል፡፡
ከተማን መሠረት የሚያደርጉ እንቅስቃሴዎች ፖለቲካዊ አጀንዳ የመሆን ዕድላቸው በጣም የሰፋ ነው፡፡ ከተሞች ከሚኖራቸው የምጣኔ ሀብት ጥንካሬ እና ተሰሚነት ጋር ተዳምሮ የፖለቲካ ሽኩቻዎችም ያን ያህል የጠነከረ ይሆናል፡፡ እንደ ማሪያ ጂሆርጊሆቭ (እኤአ 2009) ጥናት ከሆነ እነዚህ በፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳታፊ የሚሆኑ አካላት ዋንኛ ተግዳሮት ከደጋፊዎቻቸው “የፖለቲካ ታማኝነት” ማግኘቱ ላይ ነው፡፡ እንደ ጸሐፊው ገለጻ ለአቋም መዋዠቅ ዋናኛው ምክንያት ከተማ ሁልጊዜም የለውጥ እንቅስቃሴ ላይ የምትገኝ በመሆኑ ሰዎች ከተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የሚቀርቡላቸው አማራጭ ሐሳቦች ከፍተኛ ተፅዕኖ የሚፈጥሩባቸው ዕድል ሰፊ ከመሆኑ ጋር የተያያዘ ነው፡፡
ከዚህ አለፍ ብለን ስንመለከት ደግሞ በከተማ አካባቢ ይህ ቅይጥነት ከፖለቲካ ዕሳቤ አኳያ በሁለት መልኩ ልናየው እንችላለን፡፡ የመጀመሪያው ነዋሪዎች ከተለያየ ዳራ ከመምጣታቸው አኳያ እና ያንን ተከትሎ በሚኖረው መስተጋብር ላይ የተመሠረተ “መንሰላሰል” በሒደት የመጨረሻ ውጤቱ የነዋሪዎቹ የቀድሞው ማንነታቸው እየደበዘዘ በምትኩ አዲስ የተለየ የጋራ ማንነትን እየጎላ እና እየጎለበተ ማምጣቱ ነው፡፡ ለዚህ ጥሩ ማሳያ የምትሆነው አዲስ አበባ ነች፡፡ ከተማዋ በአገሪቱ ከአራቱም አቅጣጫዎች ከላይ በተጠቀሱት ሳቢ እና ገፊ ኃይሎች የተነሳ ነዋሪዎች የሚፈልሱባት መናኸሪያ ነች፡፡ ይሔንን ተከትሎ በከተማው የሚንፀባረቀው የኦሮሞ ወይም የአማራው አልያም ደግሞ የሌሎች ሕዝቦች ባሕል እና ማንነት ሳይሆን የእነዚህ ሁሉ ድምር ውጤት የሆነው ከተለያዩ ዳራ በመጡ ሕዝቦች መጋመድ ላይ የተመሠረተ አዲስ ማንነት ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል ላለፉት 27 ዓመታት የብሔር መታወቂያን በመምዘዝ አልያም ደግሞ ብሔርተኝነትን በማጮህ የፖለቲካ ይሁንታ አገኛለሁ ብለው የጓጉ የፓርቲ ድርጅቶችን ነዋሪዎቹ አንቅረው የተፏቸው፡፡
በተቃራኒው ደግሞ ከተሞች ‹አዲስ ማንነት› ከመፍጠር ይልቅ የተለያዩ እርስ በርስ የሚለያዩ መሥመሮችን በማሥመር የግጭት ማዕከላት በመሆን ብቻ የማይገደቡ እና አለፍ ሲሉም አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ መክፈቻ አግባብ የሚሆኑበትም ዕድል አለ፡፡ እንደ ሆሮዊተን (1985) ገለጻ በልኂቃን ፍጭት የሚነሳው መከፋፈል እና ደርዝ ፈጠራ ወደ ገጠሩም አካባቢ በመንሰራፋት አለመረጋጋትን በማምጣት የተቋማት መናጋትን ይፈጥራል፡፡ ይህ ደግሞ የጋራ ማንነቶችን በመሸርሸር እንደ ‹አገር› አብሮ መቀጠሉ ላይ ስጋት ይጋርጣል፡፡ በተለይ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ በማንነት የፖለቲካ ርዕዮት ዓለም ለሚቃኙ አገራት የፓርቲ ድርጅቶች ከፍተኛ ድጋፍ እና ተከታዮች ለማፍራት ሲሉ አክራሪ ወደ መሆኑ ስለሚያጋድሉ ያንን ተከትሎ በከተሞች በሚኖሩ ‹ሌሎች› ላይ ኢ ፍትሓዊነት ይነግሳል፤ ከተወሰነ ጊዜያት በኋላ ከተማው ‹የቅይጥነት› መገለጫውን እየቀነሰ “ተመሳሳይ” ወደ መሆኑ ያጋድላል፡፡ በቅርብ ጊዜ በሶማሌ፣ ኦሮሚያ፣ አማራ እና በአንዳንድ የደቡብ ክልልሎች ያስተዋልነው ድርጊት ይሄንን በደንብ የሚያሳይ ነው፡፡
የሰው እና የገንዘብ ሀብት ማዕከልነት
በቅድመ ካፒታሊዝም ወቅት ከተሞች የንግድ መናኸሪያ ከመሆን ባለፈ ለማዕከላዊ መንግሥት የሚፈይዱት እምብዛም ነበር፤ ሆኖም ግን የኢንዱስትሪ አብዮት ከፈነዳ በኋላ አንዱ እና ዋነኛ ሥር ነቀል ለውጥ ያመጣው ከኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ጋር በተያያዘ ነው፡፡ ኢኮኖሚውን የሚያሳልጡ አዲስ ግኝቶች ይበራከቱ ጀመር። ቀድሞ ኋላ ቀር በሆነ እርሻ ላይ ኑሮዋቸውን የሚገፉ ሰዎች በጊዜው በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ እና እየተመነደገ ባለው የኢንዱስትሪ ዘርፍ ውስጥ ተቀጠሩ፤ መደበኛ ትምህርት የሚሰጡ ተቋማት እንደ አበባ አበቡ። ሕዝብን ከሕዝብ እንደ ድልድይ ሆነው የሚያገኛኙ መሠረተ ልማቶች እና መገናኛ ዘዴዎች ይገነቡ ጀመር። ሥፍር ቁጥር የሌለው የሰው ኃይል ከገጠር ወደ ከተማ በመፍለስ የኃይል ሚዛኑ ወደ ከተሞች አጋደለ። በሀብትም ሆነ በተሰሚነት የፈረጠመ ጡንቻ ያለው “ከበርቴ” የሚባል አዲስ መደብ ተፈጠረ፡፡
የፖለቲካ መፈክርን ያነገቡ ድርጅቶች ከተማን መሠረት አድርገው ተመሠረቱ። ለዚህም ዋነኛው ምክንያት ባሰቡት መልኩ እንዲንቀሳቀሱ እና ያቀዱትን ግብ ለማሳካት የገንዘብ አስፈላጊነት ከርክር የማያሻው ሐቅ በመሆኑና ከዚሁ ጋር በተያያዘ ደግሞ ከተሞች የተሻለ የምጣኔ ሀብት ጡንቻ ያላቸው መሆኑ ነው፡፡ ሌላኛው ከኢንዱስትሪ አብዮት ጋር ተያይዘው የመጡት ማኅበረ ምጣኔ ሀብታዊ ቀውሶች አመፅን ብቻ ያስከተሉ ሳይሆን “የመንግሥት ሚና ምን መሆን አለበት?” ከሚለው ጀምሮ በምሁራን በኩል አማራጭ የፖለቲካ ሐሳቦች እና አዳዲስ ርዕዮተ ዓለሞች ብቅ ማለት የጀመሩበት ጊዜ ነው፡፡ ለምሳሌ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ጀምሮ ከፍተኛ ተቀባይነት እያገኘ የነበረው የሶሻሊዝም ርዕዮተ ዓለም ማዕዘን የተመሠረተው የከተሜው መገለጫ በሆነው የመደብ ትግል ላይ ነው፡፡
ከተሞች የትምህርት ማዕከላት ናቸው፤ መንግሥት አገልግቱን ለማሳለጥ ከፍተኛ በጀት በመመደብ የትምህርት መሠረተ ልማት በመገንባት “የተማረ” የሰው ኃይል እንዲወጣ ይቀይሳል፡፡ ከገጠር አካባቢ ነው የመጡት ብለን ብናስብ እንኳ በየጊዜው ከእነዚህ ተቋማት የሚመረቱት ኃይሎች መጨረሻቸው ምንድን ነው? ብለን ስንጠይቅ አብዛኞቹ ማለት ይቻላል ኑሮዋቸውን የሚቀጥሉት በከተማ መሆኑን እንነዘባለን፡፡ ይህ ደግሞ የገጠር አካባቢዎች ጥንካሬዎቻቸውን ለከተሞች እየሰጡ በአገሪቷ እንቅስቀሴዎች ላይ የዳር ተመልካች የሚያደርግ ነው፡፡ የመንግሥት ፖሊሲዎች ከውጥኑ ጀምሮ እስከ ትግበራው ድረስ የእነዚህ “የከተማ ልኂቃን” ነፀብራቅ ይሆናሉ፡፡
ይህ ልኂቅነት ከራስ መብት መቆም ባለፈ መልኩ ለሌሎች መሟገት የሚጨምር በመሆኑ የፖለቲካ አተያይ ዘዋሪዎችም ናቸው፡፡ ከ2006 ጀምሮ ሕዝባዊ ተቃውሞዎችን በአጋፋሪነት ከፊት ሆነው ሲመሩ የነበረው በዋናነት ተማሪዎች ሲሆኑ ከፍተኛ የሆነ ድጋፍ በአገር ውስጥ እና በውጭ ከሚገኙ አካላት ይደረግላቸው ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብቶች ፕሮጀክት (2008) የመጀመሪያዎቹን መቶ ቀናት ሕዝባዊ ተቃውሞን በዳሰሰበት ጥናት ተቃውሞውን በሦስት መልኩ በመከፋፈል ለመዘርዘር ይሞክራል፡፡ በዚሁም መሠረት በመጀመሪያው ዙር ብቻ የተከሰተው አመፅ ‹የአዲስ አበባ ማስተር ፕላንን› ተንተርሶ የነበረ ሲሆን በተቀሩት ሁለቱ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ላይ ግን በጊዜው መልስ ሳይሰጥባቸው ተንከባለው የመጡ የሕዝብ ብሶቶች የተንፀባረቁበት ነበር፡፡ ይህንን የበለጠ ግልጽ የሚያደርገው መንግሥት ‘ማስተር ፕላኑን’ እንደሰረዘው ተናግሮ እንኳ ተቃውሞው ከመዳከም ይልቅ ወደ አመፅነት በመሸጋገር የጠነከረበትና የሰፋበትን ሁኔታ እናያለን፡፡
እነዚህ የሕዝብ አመፆች በአገሪቷ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ላይ አሻራቸውን መጣል ጀመሩ፡፡ ከፍተኛ ሊባሉ የሚችሉ የመንግሥት እና የግሉ ባለሀብት ንብረቶች ወደሙ፤ ተደጋጋሚ የመንገድ መዘጋቶች በሕዝቦች መካከል የምጣኔሀብት መስተጋብሩን በማላሸቅ የመንግሥትን ገቢ አሽቆለቆለ። ለተከታታይ ዓመታት በዕድገት ሲጓዝ የነበረው የአገሪቷ ኢኮኖሚ ማንቀላፋት ጀመረ፡፡ በመጨረሻም ከሕአዴግ መንግሥት ውስጥ ይሔንን እና ሌሎች ጥያቄዎችን በአግባቡ ሊመለሰ ይገባል የሚሉ ኃይሎች መውጣት የለውጥ ጊዜ ላይ እንድንገኝ ምክንያት ሆነ፡፡
የመሠረተ ልማት መኖር
የሐሳብ ሽርሽር እና ቅይጥ ኅብረተሰብን ከሚፈጥሩ ምክንያቶች መካከል አንዱ የሠለጠነ የመገናኛ ዘዴ አውታር መኖሩ ነው። ይህ የትራንስፖርት አገልግሎትንና የመገናኛ ቴክኖሎጂን ያቀፈ ነው፡፡ በአረብ አገራት ተቀጣጥሎ ለነበረው ሕዝባዊ አመፅ ዋንኛ አሳላጭ የነበረው ዘመን አመጣሹ ማኅበራዊ ሚዲያ ነው፡፡ እነዚህ ቴክኖሎጂዎች በሰዎች መካከል መቀራረብን በመፍጠር ሐሳብን ከአንዱ ወገን ወደ ሌላኛው በማድረስ የሐሳብ መንሸራሸርን ያጎለብታሉ፡፡ በተመሳሳይም በተለይ ደግሞ ፌስቡክ በአገራችንም ቢሆን ለውጡን ለማሳለጥ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል። የኢሕአዴግ መንግሥት ተቃውሞውን ለመቀልበስ ማኅበራዊ ብዙኀን መገናኛዎችን ረዘም ላለ ጊዜ በማገድ እንዲሁም መሠረታቸውን በውጭ ያደረጉ የሳተላይት ቴሌቪዥንና የሬድዮ ጣቢያዎችን የማፈን እርምጃ ቢወሰድም፥ ተቃውሞው ሕዝባዊነት ደረጃ ላይ ደርሶ ስለነበር እርምጃው የታለመለትን ያህል ሊያሳካ አልተቻለውም፡፡
የከተማ ሥራ አጥነት
ሥራ አጥነት በማደግ ላይ ባሉ አገራት ብቻ ሳይሆን በልፅገዋል በሚባሉ አገራት ጭምር ራስ ምታት መሆን ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ ከገጠሩ ክፍል ወደ ከተማው የሚፈልሱ ሰዎች በአብዛኛው ጊዜ ከከተማው የሥራ ገበያ ጋር የሚጣጣም ዕውቀት እና ክኅሎት ይዘው አይመጡም። ከዚህ በተጨማሪ እነዚህን ታሳቢ ያደረገ የመንግሥት አገልግሎቶች በአቅም ውሱንነት እና በሌሎች ምክንያት የተነሳ ተደራሽ ስለማይሆን የመጨረሻ ዕጣ ፈንታቸው ሥራ አጥ መሆን ነው፡፡ በተለይም ደግሞ የተማረ ሥራ አጥነት እየንተሰራፋ ከመጣ “ጠያቂ ትውልድ” ከመሆኑ ጋር ተያይዞ መንግሥትን ጫና ውስጥ መክተቱ የማይቀር ጉዳይ ይሆናል፡፡ ሥራ አጥነትን ለፖለቲካ አስተሳሰባቸው መዘወሪያነት የሚጠቀሙ አካላት በሚያንፀባርቁት አስተሳሰብ ወደ ራሳቸው ከመሳብ በተጨማሪ ለሥልጣን እርከናቸው መሸጋገሪያ ድልድይ አድርገው እስከ መጠቀም ይደርሳሉ፡፡
በኢትዮጵያ በከተማ ከሚኖሩ ሰዎች ውስጥ 20 በመቶው የሚሆኑት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ሲሆኑ በአንፃራዊነት የተሻለ የመሠረተ ልማት፣ ኢንዱስትሪ እና ሌሎች አገልግሎቶች መከማቸት ከተማዋ የበላይ (primate city) እንድትሆን አድርጓታል። አፀፋው ደግሞ በተቃራኒው ሌሎች ከተሞች ጠባብ ወይም ደካማ የሆነ የምጣኔ ሀብት መሠረት እንዲኖራቸው አድርጓል፡፡ ይህ ደግሞ በአዲስ አበባም ሆነ በእነዚህ ከተሞች ከፍተኛ የሥራ አጥነት እንዲሰራፋ አድርጓል፡፡ እንደ ግሎባል ኦብዘርቫቶሪ (2009) ገለጻ በተለይ የተማረው የወጣት ሠራ አጥነት በአገሪቱ ላለፉት 5 ዓመታት ለተከሰቱት አመፆች ዋንኛ ምክንያት ብቻ ሳይሆን መሪ ተዋናይም ጭምር ነበሩ፡፡ በየክልሉ የሚገኙ ወጣቶች ራሳቸውን ቄሮ፣ ፋኖ፣ ዘርማ በማለት ራሳቸውን በማደራጀትና በዓላማ በመቃኘት ጭምር ግስጋሴያቸውን ያጠናከሩበትን ሁኔታ እናያለን፡፡ ለዚያም ይመስላል በተለመደው የኢሕአዴግ መንግሥት የሕዝብን ጥያቄ የመሸፋፈን ስትራቴጂ መሠረት ‹በተዘዋዋሪ ፈንድ› አማካይነት ለሥራ ዕድል ፈጠራ የሚውል 4 ቢሊዮን ብር የተመደበ ቢሆንም ልክ እንደሌሎቹ ውሳኔዎች ‹ጅብ ከሄደ› በመሆኑ የተደሰኮረበትን ያህል ራሱ ፋይዳ አላመጣም፡፡
ማጠቃለያ
ከላይ በዝርዝር ለማስቀመጥ እንደተሞከረው የኢትዮጵያን የቅርብ ጊዜ የፖለቲካ አካሄድን ከፊት በመሆን እየቃኘው የሚገኘው በቅጡ እንኳ 20 በመቶ በማይሞሉ የከተማ ነዋሪዎች በኩል የሚካሄዱ እንቅስቃሴዎች ናቸው፡፡ ከማኅበራዊ ሚዲያ ሽፋን በተጨማሪ በአንፃራዊነት ከገጠሩ ክፍል ይልቅ በከተማው የተሻለ የመገናኛ መሠረተ ልማት መዘርጋቱ በከተማ የሚነሱ ጥያቄዎች ተፅዕኖ ፈጣሪነታቸው እና ተደራሽነታቸው ላቅ እያለ መምጣት ችሏል፤ በተመሳሳይም ጥያቄዎቹ በሌሎች አካላት በተሳሳተ አቅጣጫ የመጠለፍ ዕድሉም ያን ያህል ሰፊ ነው፡፡ በመሆኑም ለእነዚህ ጉዳዮች ዓይንና ጆሮ በመስጠት ከጊዜ ጋር በተቃኘ ሥርዓታዊ እና ዓውዱን ባገናዘበ መልኩ መንግሥት መፍትሔ የማያበጅ ከሆነ ዙፋኑን በመነቅነቅ ብቻ የማያበቃ እና አለፍ ሲልም የአገሪቷን መፃዒ ዕድል የሚገዳደር ጭምር ነው፡፡

ቅጽ 1 ቁጥር 8 ታኅሣሥ 27 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here