የኹለቱ ንግድ ትርዒቶች ወግ

0
548

ፍሬወይኒ አለማየሁ ትባላለች ከመርካቶ የምትሸጣቸውን እቃዎች ይዛ በሚሊንየም አዳራሽ በተዘጋጀው ኤግዚቢሽን እና ባዛር ላይ የተገኘችው ሰው ሰራሽ አበባዎችና የቤት ማሳመሪያ ጌጣጌጦች በብዛት በንጽጽር አነስተኛ በሆነ ዋጋ ሸጣ ትርፍ ለማግኘት በማሰብ ነው።
ኤግዚቢሽኑ በተከፈተበት በመጀመሪያዎቹ ቀናት የጎብኚዎችም ሆነ የሸማቾች ቁጥር ከጠበቀችው በታች መቀነስ ፍርሃት አሳድሮባት ነበር። በእንደዚህ ዓይነት ዝግጅት ስትሳተፍ የመጀመርያዋ ቢሆንም አሁን በሚሊኒየም አዳራሽ ያለው የገበያ ሁኔታ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ቢሆንም ያን ያህል ግን አጥጋቢ የሚባል እንዳልሆነ ትናገራለች።
ከሚሊኒየም አዳራሽ 6ኪሎ ሜትር ራቅ ብሎ በሚገኘው በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ደግሞ ያለው ሁኔታ ከዚህ በተቃራኒው ነው። ኤግዚቢሽን ማዕከል በተዘጋጀው ኤግዚቢሽን እና ባዛር ላይ የዉበት መጠበቂያ የምትሸጠው ማህሌት እናዳሻው ለዚህ ምስክር ናት።
ማህሌት እንደሻው በዐሉ ከመቃረቡ በፊት ገበያው ሞቅ ሞቅ ማለቱን የምታነሳው ማህሌት በቀን ቢያንስ በሰዐት ቢያንስ 8 ሰዎች የተለያዩ ዕቃዎችን እንደሚገዟት ትገልፃለች። እንደ ማህሌት ያሉ በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል በነበረው የገበያ እንቅስቃሴ ደስተኛ የነበሩ ነጋዴዎች ቁጥራቸው ቀላል አይባልም።
የኤግዚቢሽን በማዕከሉን አግዚቢሽን ያዘጋጀው ሀበሻ ዊክሊ የሚባል ድርጅት ሲሆን 500 አገልግሎት ሰጪ እና እቃ አቅራቢ ድርጅቶች ተሳታፊዎች መሆናቸውን አዘጋጆቹ ይናገራሉ። በሌላ በኩል በሚሊንየም አዳራሽ ላይ በነበረው ባዛር፤ ከዚህ በግማሽ ያነሰ ተሳታፊዎች ነበሩ የያዙትም ዕቃዎችና ግርግሩ በኤግዚቢሽን ማዕከል ከነበረው በጣም ያነሰ ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም። ይህንን ሁኔታ እንደ እንዳሻው በለጠ ያሉ ጎብኚዎች የተረዱት ይመስላል።
እንዳሻው ኤግዚቢሽን ማዕከል የተገኘው ከጓደኞቹ ጋር ለመዝናናት እና ቀልቡ የወደደውን ነገር ካገኘ ሸምቶ ለመመለስ ነው። ከሌላው ቦታ ይልቅ ኤግዚቢሽን ማዕከልን የሚመርጥበትን ምክንያት በውል ባያውቀውም የሰው ተርምስ ቀልቡን መሳቡን ግን አልደበቀም፤ በዓል በዓል የሚመስለው ትርምሱን ሲያይ እንደሆነ ይናገራል።
ከቦታ እና ከአማራጭ ብዛት አንፃር በሚሊንየም አዳራሽ የተዘጋጀው ኤግዚቢሽን እና ባዛር ላይ ተሳታፊ ድርጅቶች አንሰው የመታየታቸውን ምክንያት የጆርካ ኢቬንትስ የኹነት ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ብሩክ ዘነበ “በርከት ያሉ ጥያቄዎች ቢቀርቡልንም ሁሉንም ማስተናገድ አልፈለግንም ምክንያቱም አዲስ ማስለመድ ከምንፈልገው ዘመናዊ የገበያ ባሕል አንፃር በሁሉም ዘርፍ ጥቂት አገልግሎት ሰጪዎችን በመያዝ ለተሳታፊው ምቹ እና ደህንነቱን የጠበቀ ኢቬንት ለማድረግ በማሰብ ነው” በሚል ሐሳባቸውን አጋርተዋል። ብሩክ አክለውም የጆርካ ሚሊኒየም ባዛርን በቀን በአማካይ እስከ ስምንት ሺህ ያህል ታዳሚዎች እንደሚጎበኙት ተኛግረዋል።
ይህ በኤግዚቢሽን ማዕከል ከተመዘገበው ቁጥር አንፃር አራት እጥፍ ቢያነስም፤ የሚሊኒየሙን ባዛር አዘጋጅ የሆኑት ብሩክ በማስተዋወቅ በኩል በደንብ ማስታወቂያ መሥራታቸውን እና ከሚጠብቁት አንፃር ግን ገና እንደሆነ ተናግረው እስከ በዓሉ ዋዜማ ድረስ የዕቅዳቸውን ያህል ጎብኚ ይመጣል ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።
የትኛውንም ፕሮግራም ለማዘጋጀት የሚያወጡትን የገንዘብ መጠን ይፋ እንደማያደርጉና ይህም የሆነው ምንም ያህል ወጪ ቢወጣበትም አገልግሎት ተጠቃሚው እና አገልግሎት ሰጪው ተደስተው መሄዳቸው ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ስለምንፈልግ ነው ብለዋል።
ወደሚሊኒየሙ አዳራሽ ከሚመጡት ታዳሚዎች ውስጥ በርከት ያሉቱ ከቤተሰቦቻቸው ጋር የሚመጡ ሲሆን፤ የመኪና ማቆሚያ ስፍራውም በመኪና ተሞልቷል። ኤግዚቢሽንና ባዛሩ በሚደረግበት በሚሊንየም አዳራሽ ውስጥም በመሸጫ ቦታዎቹ መሃል ባለው ሰፊ መተላለፊያ ታዳሚዎች በነፃነት እንደልብ ሲዘዋወሩ ማስተዋል ተችሏል።
በሌላ በኩል ተጨናንቆ የሰነበተው በኤግዚቢሽን ማዕከል ባዛር ያዘጋጁት የሐበሻ ዊክሊ የፕሮሞሽን እና ኢንተርቴይመንት ኃላፊ የሆኑት ሳምሶን ሽፈራው አገላለፅ 500 ያህል አገልግሎት ሰጪዎችን ያሳተፈው ሐበሻ የገና ኤክስፖ ብዙ አገልግሎት ሰጪዎችን በማካተት በኢትዮጵያ የመጀመርያው እንደሆነ ተናግረዋል።
ይህንንም ማድረግ ያስፈለገበት ምክንያት ሸማቹ አማርጦ የመግዛት ነፃነትን ለመስጠት እንደሆነ የሚናገሩት ሳምሶን በዚህም የተነሳ በርከት ያለ ጎብኚን እያስተናገዱ እንዳሉ ተናግረዋል። ይህም በቀን በአማካይ ከ15 እስከ 30 ሺህ ሰው እንደሚደርስ ተናግረው እስከ በዓሉ ዋዜማ ድረስም ቁጥሩ በእጥፍ ሊጨምር እንደሚችል ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
በሚሊንየም አዳራሽ የተዘጋጀውን ዐውደ ርዕይ ለመታደም ወደ አዳራሹ ሲገቡ የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ፣ የወጥ ቤትና የፅዳት እቃዎች፣ የጨርቃ ጨርቅ ምርቶች፣ የእንጨት ውጤቶች፣ የመዋቢያ ምርቶችንና የበጎ አድራጎት ሥራ የሚሰሩ አካላትን ጨምሮ ሌሎች አገልግሎቶችን የሚሰጡ እንደ ሪል እስቴቶችና ባንኮች የመሳሰሉ ተቋማት ተሰድረው ይስተዋላሉሉ። በተመሳሳይም በኤግዚብሽን ማዕከልም እነዚህኑ መሰል እቃዎችና አገልግሎት አቅራቢዎች የሚገኙ ሲሆን በመካከላቸው ያለው ልዩነት በሚሊንየም አዳራሽ ያሉት የአገልግሎት ሰጪዎች ቁጥር አናሳ፣ በኤግዚብሽን ማዕከል ያሉት ደግሞ በርከት ብለው መገኘት ነው።
ኤግዚቢሽኑን ለማዘጋጀት ሐበሻ ዊክሊ 26 ነጥብ ሁለት ሚሊየን ብር ወጪ አድርጓል በአንፃሩ ሚሊኒየም አዳራሽ የነበረውም ባዛር ለማዘጋጀት ከ3 እስከ 5 ሚሊየን ብር እንደሚወስድ ይገመታል።
የዝግጅት ገንዘቡ ይለያይ እንጂ በሁለቱም የኤግዚቢሽን እና ባዛር ቦታች ላይ ይህ ነው የሚባል የዋጋ ልዩነት የለም።
ይሁን እንጂ፤ ትልቅ የሚባል የዋጋ ልዩነት በሌለበት ሁኔታ ውስጥ የታዳሚው ቁጥር መለያየት ምክንያት ምን እንደሆነ የሚያብራሩት የገበያ ጥናት ባለሙያ የሆነው ተግባር ናቃቸው፤ ቀደም ሲል ቦታዎቹ በተደጋጋሚ ያስተናግዱ የነበሩት ዝግጅቶች ተፅዕኖ አሳድሮባቸዋል ብለው ኤግዚቢሽን ማዕከል ከረጅም ጊዜ ጀምሮ በተለይ በበዐላት ወቅት ኤግዚቢሽኖች ይዘጋጅበት የነበረ ከመሆኑ የተነሳ በሰው አእምሮ ውስጥ በዐል ሲነሳ አብሮ መታወሱ አይቀርም። በአንፃሩ ሚሊንየም አዳራሽ የተለያዩ ሕዝባዊ በዓላት ማክበሪያ እንዲሁም የሙዚቃ ዝግጅቶች ማከናወኛ ስለነበረ ኅብረተሰቡ ሚሊንየም አዳራሽ የሚዘጋጀውን ኤግዚቢሽን እና ባዛር ለመልመድ የተወሰነ ጊዜ ይፈልጋል ሲሉ ሐሳባቸውን አካፍለውናል።

ቅጽ 1 ቁጥር 8 ታኅሣሥ 27 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here