አደገኛ እጽ ስታዘዋውር እጅ ከፍንጅ የተያዘችው ሴት ተለቀቀች

0
669

አደገኛ እጽ ስታዘዋውር ቦሌ ዓለም ዐቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እጅ ከፍንጅ የተያዘችው ዛምቢያዊት ሴት ዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን ማቅረብ ባለመቻሉ ተለቀቀች።
የፌድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ስምንተኛ ወንጀል ችሎት ሐምሌ 16/2010 በቦሌ ዓለም ዐቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ፣ በወንጀል ሕጉ አንቀፅ 525 (1) የተደነገገውን በመተላለፍ አራት ሺሕ 100 ግራም ኮኬይን የተባለ አደንዛዥ ዕፅ በሻንጣዋ ይዛ ለመግባት ስትሞክር በቁጥጥር ስር የዋለችው ዛንቢያዊቷ ፓሜላ ናማስኩ ናኬዌቲንን ክስ አቋርጣል።
የ29 ዓመቷ ግለሰብ አደንዛዥ ዕፅን ይዛ ከደቡብ አፍሪካ ወደ ሕንድ ኒውደሊህ ለመሄድ በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ትራንዚት ላይ እያለች ነበር በቁጥጥር ስር የዋለችው። ግለሰቧን በአደገኛ ዕፅ ዝውውር ወንጀል እንደጠረጠራት የገለጸው መርማሪ ፖሊስ የተለያዩ የሰነድና የሰው ማስረጃዎችን አቅርቦ ሕገ ፊት ቢያቀርባትም ልትለቀቅ ችላለች። ለመለቀቋ ምክንያት የተባለው ደግሞ ዐቃቤ ሕግ በተከታታይ ሦስት ቀጠሮዎች ተሰጥተውት ምስክሮችን ማቅረብ ባለመቻሉ እንደሆነም ተመልክቷል። በዚህም መዝገቡ እንዲቋረጥና ምስክሮች በሚሟሉበት ጊዜ ክሱ እንዲንቀሳቀስ ፍርድ ቤቱም ትእዛዝ ሰጥቷል።
ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ ምስክሮች ታስረው ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ጠይቋል። ፍርድ ቤቱ ታኅሣሥ 23/2011 በዋለው ችሎት መዝገቡ ተዘግቶ ተከሳሽ ከእስር እንድትፈታ ሲል ወስኗል።
የፌድራል ፖሊስ መረጃ እንደሚያሳየው ባለፉት ስድስት ወራት 56 ግለሰቦች በአደገኛ ዕፅ ዝውውር ተጠርጥረው በሕግ ከለላ ስር ውለዋል። በተለያዩ ጊዜያትም የውጭ አገራት ዜጎች በቦሌ ዓለም ዐቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በኩል የተለያዩ አደገኛ ዕፆችን ይዘው ሲገቡ በቁጥጥር ስር እንደሚውሉ በተደጋጋሚ የሚሠጡ መግለጫዎች ያመለክታሉ። አብዛኞቹም ፍርድ አግኝተው በማረሚያ ቤት እንደሚገኙ የተለያዩ ማስረጃዎች አሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 8 ታኅሣሥ 27 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here