የኢትዮ- ሱዳን ነገር

0
887

በኢትዮጵያ የተካሄደውን የሕግ ማስከበር እርምጃ ተከትሎ ሱዳን ፤የሚታወቀውን ግን ያልተከለለውን ድንበር እስከ 40 ኪሎ ሜትር ጥሳ በመግባት ነዋሪዎችን አፈናቅላለች።
ጉዳዩ ከዚህ በፊት ከነበረው መጎሻሸም በጠባዩ የተለይ እንደሆነ እና ኢትዮጵያም ከጀርባ የውጪ ኃይሎች ከፍተኛ ግፊት እንዳለበት ተናግራለች።ከሰሞኑ በተከታታይ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ቃል አቀባይ የሰጧቸውን መግለጫዎች በመንተራስ ዳዊት አስታጥቄ በሐተታ ዘ ማለዳ ቃኝቶታል።

አሊ ማዙሪ ፣ታዋቂ የስነ ሰብ እና ፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ናቸው።እርሳቸው ቀይ ባህር በአካባቢው አገራት ላይ ያለውን የሰላም እና ደኅንነት እክል አስኳል ነው ይሉና ከማንኛውም ባህር ይልቅ”ጠንቀኛ ባህር ነው ይሉታል”።
የኛው አባይ ወይም ናይል ደግሞ ከእልፍ ዘመናት አንስቶ እስከ ዛሬም ድረስ የኢትዮጵያ ሰላም እና ደኀንነት”ጠንቀኛው ወንዝ “እንደሆነብን ዘልቋል።
የሰሞኑ የኢትዮ- ሱዳን ድንበር ግጭት ያልተካለለው የኢትዮ-ሱዳን ድንበር ዋናው ምክንያት እንዳልሆነ አንባቢው ይረዳል።ይልቁንም ይሄው ጠንቀኛ ውሃ ይዞት የመጣው ጉዳይ እንደሆነ ሁሉም ሰው ይገነዘባል።

የኢትዮ- ሱዳን ነገር
ከሶስት ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያ እና ሱዳንን ዘለግ ላሉ ዓመታት በአንባገነንነት ሲያስተዳድሩ የነበሩ ገዢዎች ተወገደዋል። አገራቱ ግን ከፈተና መውጣት አልቻሉም። በሱዳን በሁለት ወገኖች የሚዘወር አስተዳደር የተነሳ ጠንካራ መንግሥት መፍጠር ያልተቻለበት፤ በኢትዮጵያ ደግሞ ውስጣዊ ግጭቶች እና መፈናቀሎችን ብሎም ግድያዎችን ማቆም ያልቻለበተ እና በየቀኑ ፈተናዎች የሚፈለፈሉበት አስተዳደር ሥልጣን የያዘበት ሁነት ነው ያለው።

አገራቱ ብዙ ኪሎ ሜትሮችን የሚያካልል ድንበርን ይጋራሉ።ግን ድንበሩ አልተካለለም፤ ይህ ደግሞ የሁለቱ አገራት ገበሬዎች በተለይ በእርሻ መሬት ምክንያት ግጭቶች እንዲነሱ እና የሰው ሕይወት እና ንብረት እንዲወድም ምክንያት መሆኑ ቀጥሏል። በተለይ ደግሞ በአጨዳ እና በእርሻ ጊዜያት ላይ ደግሞ ችግሩ ከተዳፈነበት ይነሳል። በሁነቱም ወገኖች አልፎ አልፎ የሚኖሩ ትንኮሳዎች ብሎም የጥይት ድምፅ እና ሞት የተለመደ ነው የሰሞናዊው ሁኔታ ግን ትንሽ ከፍ ያለ እና በጠባዩም የተለየ እንደሆነ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ይናገራል።

በወታደራዊ እና ሜሪቶክራሲ ኃይል ተወጥራ ሕዝባዊ መንግስት ልታቃቁም እየተውተረተረች ያለቸው ሱዳን ከሰሞኑ የሕዝብ ግፊትአደባባይ መጥቶባታል፤የተገባልን ቃል እየተፈጸም አይደለም የሚል።ኢትዮጵም በአንድ በኩል በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በተከሰተው ሕገወጥነት በሕግ ማስከበር ዘመቻ በሌላ በኩል የሕዝብን ሞትን እና መፈናቀልን ለማስቆም በኮማንድፖስት ተወጥራ ትገኛለች።ኹለቱም አገራት ለጦርነት እና ለግጭት አቅም የላቸውም ምናልባትም ውስጣዊ አንድነታቸውን ከማናጋት በስተቀር ከግጭቱ እንደ ሕዝብም ፣እንደ አገረርም አይጠቀሙም ።ጉዳዩን ግን ከኃላ ሆነው የሚገፉ ውስጥ ሀሆነው ደግም ጥቅምን ለማጋበስ የሚሰሩ ኃይሎች ግን እያቀጣጠሉት 15 ቀናት አለፉ።

የኢትዮጵያ እና የሱዳን የሚጋሩት ድንበር ወደው የፈጠሩት ሳይሆን የቅኝ ግዛት ክፉ ውርስ ነው። ይህን የድንበር እና መሬት ይገባኛል ጥያቄን በፓለቲካዊ ውይይት እና በህግ ማዕቀፍ ለመፍታት የነበረው ቁርጠኝነት ማነስ ድንበሩ እስከ ዛሬም እንዳይካለል መሆኑ አካባቢውን ለማተራመስ ለሚፈልጉ ኃይሎች መልካም ሁኔታን ፈጥሮላቸዋል።

በእነዚህ ቦታዎች የሚከሰቱ ችግሮች ስትራክቸራል ናቸው።በድንበር የሰፈሩ ሕዝቦች በባህሪ ደረጃ ውሃ/ መሬት/ ለእርሻ፤ ለከብት ግጦሽ ይፈልጉታል። የተሻለ ውሃ እና ለም መሬት ወደ አለበትም ጉዞ እና ሠፈራ ይደረጋል። በዚህ ጊዜ ውስጥ ግጭቶች(የቀለሃ ንግግሮች) ይኖራል። (Structural scarcity) አንደኛው ምክንያት መሬቱ(ውሃው)የኔ ነው የሚል ነው። ኹለተኛው ከመሬቱ( ከውሃው) አካባቢው ላይ ካለው ሪሶርስ አንፃር ከማንነት ጋር ራስን የማስተሳሰር ባህሪዎች ስለሚኖሩ እነዚህ ባህላዊ እና ማህበራዊ እውነታዎች መረዳት ግድ ነው።
ከሱዳን ጋር ያለው የድንበር(የመሬት)ጥያቄዎች ሙግቶች ከኤርትራም) ከኬንያም ጋር ያደረ የቤት ሥራችን ነው። ሥለዚህም እጅግ ጥበብ( እርጋታ) እውቀት ይፈልጋል።

የህግ ማከበር እርምጃው የሱዳን ጸብ አጫሪነት
የኢትዮጵያ ም/ጠ/ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ፣ የሱዳን ጦር ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል የሕግ ማስከበር ዘመቻ ከጀመረች ከ 6 ቀናት በኋላ ታህሣሥ 30 / 2013 በኢትዮጵያ ላይ በከባድ መሳሪያ የታገዘ ጥቃት መክፈቱን እና በዚህም የንጹሃንን ሞት ጨምሮ በርካታ ጉዳት ማድረሱን ገልጸዋል።
በሰሞኑ በተፈጠረው ጉዳይ እንኳን ከአካባቢያቸው ከአሥር በላይ ሰዎች ታፍነው መወሰዳቸውን፣ ከሱዳን የሚነሱ ታጣቂዎች ከ2008 ጀምሮ ድንበር እያለፉ እንደሚገቡና ሁኔታውንም ለመንግሥት በተደጋጋሚ ሲያሳውቁ መቆታቸውን ቪኦኤ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ጠቁመዋል።

“የሱዳን ጦር የኢትዮጵያ አዋሳኝ በሆኑ አካባቢዎች እየሠፈረና በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ጥቃት እየፈፀመ ነው” ሲል የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አቤቱታ ማሰማቱን እና የፌደራል መንግሥቱ እርምጃ እንዲወስድም ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል ።

የሱዳን የደህንነትና መከላከያ ም/ቤት ስብሰባ ታህሣሥ 20/2013 የሱዳን የደህንነትና መከላከያ ም/ቤት ከኢትዮጵያ ጋር ባለው የድንበር ውዝግብ ዙሪያ አስቸኳይ ስብሰባ አድርጎ ነበር። በአገሪቱ ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀመንበር ሌ/ጄኔራል አብደል ፈታህ አል ቡርሃን መሪነት በተካሔደው ስብሰባ የተለያዩ ውሳኔዎች መተላለፋቸው ተገልጿል። ይሁንና ስለውሳኔዎቹ በግልጽ የተባለ ነገር የለም።

በሌላ በኩል ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግጭት በተመለከተ ፣ “አል ፋሻቃ አካባቢ የሱዳን ጦር የሀገሪቱን ድንበር ለማስከበር እና ለመከላከል የወሰደውን እርምጃ የደህንነትና መከላከያ ምክር ቤቱ ማድነቁን” የመከላከያ ሚኒስትሩ ጄኔራል ያሲን ኢብራሂም ተናግረዋል።

አንድ የሱዳን ባለሥልጣን ማክሰኞ ታህሣሥ 20 /2013 ከአል አረብያ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ላለው የድንበር ውጥረት ሰላማዊ መፍትሄዎችን እንደምትቀበል አስታውቀዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ጁማህ ኪንዳ እንደተናገሩት ሀገራቸው “ከኢትዮጵያ ጋር ሰላም ትፈልጋለች ፣ ግን ድንበሯን ታስከብራለች” ሲሉም ተናግረዋል። ኪንዳ “የኢትዮጵያ ሚሊሻዎች በድንበር ላይ የተደረገው ውጊያ እንዲባባስ ምክንያት ሆነዋል” ሲል የከሰሰ ሲሆን “የሱዳን ጦር ምላሽ መስጠት ነበረበት” ብሏል።በኢትዮጵያ ተይዞብኝ ቆይቷል ካለችው ቦታ እስከ 70 በመቶ የሚሆነውን በኃይል አስመልሻለሁ ያለችው ሱዳን ፣ ከኢትዮጵያ ጋር በሚያዋስናት የአል ፋሻቃ አካባቢ ከፍተኛ ጦር ማሰማራቷ ይታወቃል።

በኢትዮጵያ በኩል ምን ያህል ኪሎ ሜትር መሬት በሱዳን ወታደሮች እንደተያዘ ባይነገርም እስከ 50 ኪሎ ሜትር ዘልቀው እንደያዙ ግን የተለያዩ መረጃዎች ያሳያሉ።

ግብፅ ዓለም አቀፋዊ የኃይል ማዕከል ለመሆን መጣር
ኢትዮጵያ ተፈጥሯዊ ሀብቷን በመጠቀም ሀይል ለማመንጨት የምታደርገውን ጥረት በተለያዩ መንገዶች ለማደናቀፍ በርካታ ጥረቶችን እያደረገች የምትገኘው ግብፅ ቀጠናዊ የሀይል ማዕከል ለመሆን እየጣርኩ ነው ብላለች። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጉባ ወረዳ እየተገነባ የሚገኘው የህዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ 6 ሺህ ሜጋዋት ያመነጫል ተብሎ ይጠበቃል። ግድቡ ለኢትዮጵያውያን የዘመናት የሀይል ጥያቄ ምላሽ እንደሚሰጥ የሚጠበቅ ቢሆንም የኢትዮጵያ እድገት እና ለውጥ በበጎ ጎኑ የማታየው ግብፅ የግንባታ ሂደቱን ለማደናቀፍ ስትሰራ ማየቱ የተለመደ ነው። በዚህም የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ ለግድቡ ግንባታ ከሀገራት እና ከተቋማት ብድር እንዳታገኝ እያደረገች ቆይታለች። ሆኖም ይህ ጫና ያልበገራት ኢትዮጵያ ከመንግሥት በጀት እና በኢትዮጵያ ህዝቦች ድጋፍ ብርሃንን በተስፋ ለሚጠብቁት ኢትዮጵያውን ለመስጠት የህዳሴ ግድብ ግንባታ እየተሰራ ይገኛል።

የህዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደትን ለማደናቀፍ ከኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጀምሮ በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲው ላይም ጫና ለመፍጠር እየጣረች የምትገኘው ግብፅ ራሷን ቀጠናዊ የሀይል ማዕከል ለማድረግ እየሰራች መሆኑን አህራም አስነብቧል።

የመንግሥት ምላሽ
የኢፌድሪ የዉጪ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳስታወቀዉ ሱዳን በድንበር አካባቢ እያደረሰች ያለዉን ህገወጥ ድርጊት የማታቆም ከሆነ ኢትዮጵያ ሉኣላዊነቷን ለመጠበቅ ስትል እርምጃ ያሉት አምባሳደር ዲና የሱዳን ኃይል የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ በመግባት በርካታ ህገወጥ ድርጊቶችን ፈፅሟል።

ይኸም የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በትግራይ ክልል እያደረገ ያለዉን የህግ ማስከበር ተልዕኮ እንደ ክፍተት ተጠቅመዉ ኢትዮጵያን እና ሱዳንን ወደ ግጭት እንዲያመሩ ከከሚፈልጉ ሃይሎች የመነጨ ነዉ ብለዋል።“ኢትዮጵያ ሉኣላዊነቷን ለማስጠበቅ ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል።

ችግሩ እንዲፈጠር ያደረጉት ቀጠናው እንዳይረጋጋ የሚፈልጉ ኃይሎች መሆናቸውን ጠቅሰው፣ የሱዳን የተወሰኑ ልሂቃኖችም ከእነዚህ ኃይሎች ጋር መወገናቸውን አመልክተዋል። “እነዚህ ኃይሎች በግልጽ የሚታወቁ ናቸው” ያሉት ቃል አቀባዩ፣ በትርምሱ የራሳቸውን አጀንዳ ለማስፈጸምና ጥቅማቸውን ለማስከበር ያለሙ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

እነዚህ ኃይሎች ለሱዳን ህዝብም ሆነ ለቀጠናው ጠቃሚ አለመሆናቸውን መንግሥት በተለይ ለሱዳን ህዝብ መልዕክት የማስተላለፍ ሥራ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ጎን ለጎንም እነዚህን ኃይሎችን የማጋለጥ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው፣ ችግሮቹን በሠላማዊ መንገድ ለመፍታት ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች መቀጠላቸውን ገልጸዋል። ይሄንን ወረራ የሚያቀነቅኑ የሱዳን የፖለቲካና ወታደራዊ ሊሂቃን ቢኖሩም የአካባቢውንና የኢትዮጵያን መረጋጋት የማይሹ ሦስተኛ ወገኖች እንደሚገፉት ተጠቁሟል።

ሱዳንን ለጦርነት የሚገፋፏት አካላት “ሀገሪቱን በቅኝ አገዛዝ መንፈስ የሚያይዋት ፣ ከዚህ ቀደምም ከቅኝ ገዢዋ ጋር ሆነው ሲያስተዳድሯት የነበሩ ፣ አሁንም የሱዳንን ሰፊ መሬት የያዙ እና የሱዳንን ህዝብ እንደሰው የማያዩ ናቸው” ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ተናግረዋል። እነዚህን አካላት በስም መጥራት ከተቻለ በሚል ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ “እኔ መናገር አልፈልግም እናንተው ታውቋቸዋላችሁ” ያሉት ቃል አቀባዩ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ይሁንና የተወሰኑ የሱዳን ባለሥልጣናትም ጸብ አጫሪ መግለጫ በመስጠት ላይ መሆናቸውን በመጥቀስ በድርጊቱ ተሳትፎ እንዳላቸው አንስተዋል። ሆኖም “ኢትዮጵያ እነዚህ አካላት በከፈቱላት በር እንደማትገባ” እና ከሱዳን ጋር ያላትን ወዳጅነት እንደምትንከባከብ ገልጸዋል። አካባቢውን ማተራመስ የሚፈልጉ ኃይሎች “በሱዳን በኩል ባይሳካላቸው እንኳን ከሌሎች ጎረቤቶቻችን ጋር ሊያጋጩን ጥረት ማድረጋቸው አይቀርም” ሲሉም ነው የተናገሩት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተፈጠረውን ክስተት በማስመልከት በሰጡት መግለጫ በሁለቱ ሀገራት መካከል ጦርነት እንዲፈጠር የሚፈልጉ የውጭ ሀይሎች መኖራቸውን አንስተው ፣ ሰሞኑን በተፈጠረው ክስተት የኢትዮጵያና ሱዳን ግንኑነት እንደማይቋረጥ እንዲሁም ችግሩን በሰላም ለመፍታት ኢትዮጵያ ሙሉ ዝግጁነት እንዳላት መግለጻቸው ይታወሳል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ባሳለፍነው ሳምንት በሰጡት መግለጫ፣ በኢትዮጵያ እና ሱዳን ድንበር አካባቢ ተፈጥሮ የነበረው ችግር በአሁኑ ሰዓት ውጥረቱ ቢቀንስም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ችግሩን ለመፍታት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።የእኛ አቋም አሁንም የኢትዮጵያ እና የሱዳንን ታሪካዊ ግንኙነት መንከባከብ ነው።እነሱ የሚፈልጉትን ጭካ ማቡካት ስለሆነ እኛ እዛ ውስጥ ላለመግባት ጥረት እናደርጋለን ብለዋል ቃል አቀባዩ።
የእነዚህ ኃይሎች ጥረት እዚህ ቢከሽፍ እንኳ በሌላ በኩል ሊቀጥል የሚችል እንደሆነ ስለምንረዳ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ስራዎች እንደሚፈልጉም አንረዳለን ፤ለእሱም እንሰራለን ብለዋል ዲና ።

የልምምጥ ፖሊሲ
ኢትዮጵያና ሱዳን በድንበር ጉዳይ የጋራ መፍትሄ ለማበጀት የተፈራረሙትን ስምምነት ሱዳን መጣሷን የኢትዮ-ሱዳን ድንበር ኮሚሽን አባላት በኮሚሽኑ አባል አምባሳደር ኢብራሂም እንድሪስ በኩል ገልጸው ፤ሁለቱ አገራት በፈረንጆቹ 1972 በድንበር ጉዳይ የጋራ መፍትሄ ለማበጀት የተፈራረሙትን ስምምነት ሱዳን መጣሷን አብራርተዋል።

በስምምነቱ መሰረት ሃገራቱ በድንበር ጉዳይ የጋራ መፍትሄ እስከሚያስቀምጡ ድረስ መሬት ላይ ያለው ነባራዊ ሁኔታ እንዲቀጥል ያስገድዳል።ሆኖም ሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር ጥሳ በመግባት የያዘችው መሬት ይህንን ስምምነት የሚጥስ መሆኑን አስረድተዋል።

የድንበር ጥሰቱ በግብርና ምርትና በንብረት ላይ ጉዳት በማድረስ ዜጎችን ማፈናቀሉን እና ዓለም አቀፍ ህግንና የድንበር ስምምነትን በማክበር በሰላማዊ መንገድ በውይይት መፍታ እንደሚያስፈልግ አምባሳደር ኢብራሂም ተናግረዋል።

ሱዳን በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ ገብታ የያዘችውን መሬት በህግ የሚያስጠይቃት በመሆኑ በአስቸኳይ ለቃ ወደ ነባራዊ ሁኔታዋ መመለስና በ1972 የተደረሰውን ስምምነት እንድታከብርም ጠይቀዋል።

ነገሩ የልምምጥ ሳይሆን ጭቃ ማቡካት የሚፈልጉ ኃይሎች አንዳሉ ስለምናውቅ እና አብረን መፍሰስ ስለሌለብን ነው ያሉት ዲና ኢትዮጵያ “ሱዳንን ወደ ነበርንበት እንመለስና ድንበሩን እናካልላለን” ብለናታል ሲሉ ከ አላይን ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ገልጸዋል። አክለውም የድንበር ጉዳይ በግርግር ሳይሆን በንግግር እንዲፈታ ኢትዮጵያ ፍላጎት ያላት መሆኑን ነገር ግን ኢትዮጵያ በሕግ ማስከበር ሥራ ላይ በነበረችበት ወቅት እንደዚህ አይነት ነገር ማድረግ ተገቢ እንዳልሆነ ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።
ይህ ካልሆነ ግን ሕዝብ ሉዓላዊነቱን ዝም ብሎ ሜዳ ላይ አይተውም ያሉት አምባሳደር ዲና ችግሩ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ፍላጎታችን ነው ብለዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 114 ጥር 1 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here