ኮቪድ19 ተጠቂዎች ቁጥር ብዛት 16ኛው አገር መሆን ይችላል

0
573

ባለፈው ዓመት በቻይናዋ ውሃን ግዛት የጀመረው መድኅኒት አልባው ወረርሽኝ ኮቨድ 19 ወረርሽኝ ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ ለመብረር እና ዓለምን ለማዳረስ የፈጀበት ጊዜ በእጅጉ ያጠረ እንደሆነ ይታወቃል። ከሩቅ ምስራቋ ቻይና እስከ ምዕራቡ ዓለም መቀመጫ ልዕለ ኃያሏ አሜሪካ ድረስ ዘልቆ ለመግባት እና የሞት ጥላውን ለማሳረፍ ቀናት ብቻ ነበር የበቁት።

በአገረ አሜሪካ በርካታ ነብሳት ተቀጥፈዋል የምጣኔ ሀብት ድቀቱ ምንም እንኳን በውል ባይታወቅም ከፍተኛ የሆነ ተጽዕኖ እንደደረሰበት የሚገመት ነው። በአነጋጋሪነታቸው የሚታወቁት እና ወደ ስልጣን ከመጡባት ቅጽበት ጀምሮ ለአንድም መአልት ሳይነቀፉ እና መከራከሪያ ሳይሆኑ የስልጣን ዘመናቸው ተጠናቀቀው ተሰናባቹ የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ አንድ ጊዜ ቻይና ቫይረስ ሲሉ ሌላ ጊዜ ደግሞ አሜሪካ በቫይረሱ ምንም አይነት ጉዳት እየደረሰባት አይደለም እየተነገረ ያለውም ጉዳይ በእጅጉ ከእውነት የራቀ ነው ሲሉ ተደምጠው ነበር። በእርግጥ ጉዳዩን ለማድበስበስ ሄዱበትን መንገድ ትኩረት ቢሰጡት ኖሮ ይህን ያህል ቁጥር ያለው ሕዝባችንን ማዳን ይቻል ነበር የሚሉ ሞጋቾች ከአገረ አሜሪካ ሰማይ ስር መታዘብም ሚቻልበት አጋጣሚም ነበር።

ይህ ወረርሽኝ የትኛውንም አገር በየትኛውም ሴክተር ላይ የተሰማራውን ሕዝብ እና በየትኛውም ጥግ ላይ ሚገኘውን የማኅበረሰብ ክፍል ማወክ የቻለ እና አለም ትሸሸግበት ጉድጓድ የሻተችበትም ቸነፈር ነው። ኢጣልያ፣ ስፔን፣ አሜሪካ እና በሽታው መነሻ አገር ቻይና በወረርሽኙ ከባዱን ዱላ ያረፈባቸው ቢሆኑም እና በርካታ ዜጎቻቸው ቢረግፉም አፍሪካን እና አገራችን ኢትዮጵያንም የሞት ጅራፉ አልማረንም። ካለፈው ወርሃ መጋቢት ጀምሮ በኢትዮጵያ መከሰቱ የተነገረው ኮቪድ 19 ወረርሽኝ በየእለቱ የሰዎችን ነብስ ለመቅጠፍ የቦዘነበት ቀን እንደሌለ በየእለቱ የጤና ሚንስቴር የሚያወጣቸው ሪፖርቶች ምስክር ናቸው።

ይባስ ብሎ እንዲያውም ወደ ጽኑ ሕሙማን ክፍል የሚገቡት ታማሚዎች ቁጥር እየቸመረ መምጣቱም እየተነገረ ይገኛል። ከሁሉም የሚብሰው እና በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ የሚሆንነበት ጉዳይ ደግሞ በአገር አቀፍ ደረጃ ያለው ለጽኑ ሕሙማን መርጃ የሚውለው የሜካኒካል ቬንትሌተር ብዛት በሙሉ በታማሚዎች በመያዛቸው በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ወረፋ እንዲጠብቁ መደረጋቸው ነው። ይህ ደግሞ የመዳን እድላቸውን በብዙ ሊቀንሰው የሚችል እና ሕይወታቸውን ሊያጡ የሚችሉ ሰዎችን ቁጥር ሊጨምረው እንደሚችልም በሕክምና ባለሙያዎች ዘንድ ይነገራል። አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ ያነጋገረቻቸው በሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኮቪድ 19 መከላከል ግብረ ኃይል አባላት እንደሚሉት ከሕብረተሰቡ ቸልተኝነት አንጻር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የመጣው የኮቪድ ወረርሽኝ አሁንም ከፍተኛ ትኩረት ሚያሻው ጉዳይ ለመሆኑ በአጽንኦት ይናገራሉ።

በተለይም ደግሞ የግብረ ኃይሉ አባላት እንደሚሉት ከመጀመሪያው ዙር በላይ ደግሞ በኹለተኛው ምእራፍ በአገረ እንግሊዝ የታየው የኮቪድ 19 አዲሱ ወረርሽኝ ጭራሹኑ ካለው ችግር ላይ ከፍተኛ ችግር እንዳይፈጥር እና እንዳይደራረብ ብሎም ከቁጥጥር ውጭ እንዳይወጣ ከወዲሁ መላ ሊባል እንደሚገባ እና በተለይም ደግሞ ሕብረተሰቡ ይህን ጉዳይ በከፍተኛ መነቃቃት ራሱን እና ቤተሰቦቹን ሊጠብቅ እንደሚገባም ከወዲሁ እየተነገረ ይገኛል።

በዚህም ረገድ የኢፌዴሪ የጤና ሚንስቴር በጉዳዩ ላይ አዲስ መነቃቃቶችን በሕብረተሰቡ ላይ እንዲታይ እና እንዲዳረስ ‹‹እንድናገለግልዎ ማስክዎን ያድርጉ›› በሚል መሪ ቃል በየአገልግሎት መስጫው ላይ ሰዎች የፊት መሸፈኛ ጭንብል ካላደረጉ አገልግሎት ማግኘት እደማይችሉ የሚገልጽ ምልዕክት እየተስተጋባ ይገኛል።
በአሁኑ ወቅት ይህ ጽሑፍ እስከተጠናቀረበት ድረስ በኣለም አቀፍ ደረጃ ከመጀመሪያው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ በወረርሽኙ ተጠቁት ሰዎች ቁጥር 86 ነጥብ 8 ሚሊዮን መድረሱን ወርልዶ ሜትር የተባለው ድረ ገጽ እያስነበበ ይገኛል። በዚሁ በተጓዳኝም በወረርሽኙ ከ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ሰዎችም በዓለም ላይ ውድ ሕይወታቸውን አጥተዋል። እነዚህን እና መሰል ሪፖርቶች በእክጉ የሚያሳቅቁ በመሆናቸው የትኛውም ሰው ወረርሽኙን ለመግታት መደረግ ያለበትን ቅድመ ዝግጅት በሚገባ እንዲያከናውን ባለሙያዎች ሳይታክቱ እያሳሰቡም ይገኛሉ።

አንድ እውነታ ማስቀመጥ ያህልም በኣለም አቀፍ ደረጃ በኮቪድ 19 የተያዙት የሕብረተሰብ ክፍል ቁጥር በእጅጉ ከመጨመሩ የተነሳ በአሁኑ ሰኣት ያለው ቁጥር ከመላው ዓለም ሰዎችን በመሰብሰብ በአንድ ስፍራ ቢቀመጡ ከዓለም አቀፍ አገራት በሕዝብ ቁጥሩ በ16ኛ ደረጃ ላይ ሊገኝ የሚችል አገር መፍጠር ይቻላል። ይህን ማየት ሚቻለው ደግሞ የወረርሽኙ ስርጭት በከፍተኛ ፍጥነት መሆኑ እና አዲሱ የኮቪድ 19 ዝርያ ደግሞ በ70 በመቶ ከቀዳሚው በላቀ ሁኔታ ስርጭቱ ስለሚጨምር ይህ ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት ሊያሻቅብ እንደሚችልም ተገምቷል።

በቅርቡ በኢትዮጵያ የኢፌዲሬ ጤና ሚንስቴር ባወጣው ሪፖርት መሰረት በመጀመሪያውቹ የኮቪድ 19 በኢትዮጵያ ተከሰተባቸው ቀናት ላይ በሕብረተሰቡ ዘንድ ታይቶ የነበረው ጥንቃቄ እና ትኩረት የአፍ እና አፍንቻ መሸፈኛ ተጠቃሚዎችን 74 በመቶ አድርሶ የነበረ ሲሆን ከዛ ወዲህ ግን በሕብረተሰቡ ዘንድ የታየው መዘናጋት የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ተጠቃሚዎችን ወደ 52 በመቶ እንዲቀንስ ማድረጉን በሪፖርቱ ተመላክቷል።

ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ በአገር አቀፍ ደረጃ ከዚህ ቀደም መመርመር ይቻል የነበረው ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት መቀነሱ ደግሞ በሽታው በሕብረተሰቡ ዘንድ ሳይታወቅ እንዲዛመትም በር ሊከፍትለት እንደሚችል ስማቸው እንዳይጠቀስ ፈለጉ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የወረርሽኙ ግብረ ኃይል አባል ለአዲስ ማለዳ ይናገራሉ።
ለምርመራ ቁጥሩ መቀነስን በተመለከተ ጤና ሚኒስቴር ከተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን አባላት ዘንድ ለቀረበለት ጥያቄ እንደ ምክንያት ያነሳው ጉዳይ ደግሞ መመርመሪያ መሳሪያው እና ናሙና መቀበያው ዘንድ ያለው መጣጣም አለመገጣጠሙ ነው። ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? የሚለውን ጥያቄም አሁንም በጤና ሚኒስቴር በኩል ሊመለስ ያልቻለ ጥያቄ ሆኗል።

ይህ ወረርሽኝ ከሚያደርሰው የጤና ዕክል ባለፈ በሌሎች ሕክምናዎችም ላይ አሁንም ድረስ ከፍተኛ ጫና በኢትዮጵያ ውስጥ እያሳደረ ይገኛል። ከዚህም ባለፈ ደግሞ በንግድ ዘርፉ ላይም ይህ ነው ማይባል ተጽዕኖ ማድረሱ ታውቋል። ይህ ጽሑፍ የተዘጋጀበት የገና ዋዜማ ላይ እንኳን ከዚህ ቀደም ይታዩ የነበሩ የንግድ ባዛሮች ወረርሽኙን ተከትሎው ደብዛቸው እንዲጠፋ ሆኗል።

ቅጽ 2 ቁጥር 114 ጥር 1 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here