በባሕር ዳር ከተማ በአንድ የፖሊስ አባል መኖሪያ ቤት 498 ሽጉጦች መገኘታቸውን የከተማው ፖሊስ መምሪያ ማሳወቁ አነጋጋሪ ሆኗል።
‹‹ፀጥታን ለማስከበር ይሰራል›› በሚባል የፖሊስ ኮማንደር ቤት ይህ ሁሉ መሳሪያ መገኘቱ ብዙዎችን ቢያስገርምም በመምሪያው የወንጀል ምርመራ ኃላፊ ምክትል ኮማደር አየልኝ ተክሌ ግን የተያዘው የጦር መሳሪያ ቁጥር ብዙ በመሆኑ ድርጊቱ በአንድ ሰው ብቻ ይፈጸማል ተብሎ እንደማታመን ተናግረዋል።
ለጊዜው አንድ ተጠርጣሪ ተይዞ ምርመራ እየተደረገበት መሆኑን በመጥቀስም በምርመራ ሒደት ነገሮች እየጠሩ ይሔዳሉ የሚል ተስፋ ኃላፊው ገልጸዋል። ለዚህም የተለያዩ ማስረጃዎችን በመሰብሰብ ላይ እንደሆኑ አክለዋል።
በቁጥጥር ስር የዋለው ቱርክ ሰራሽ መሣሪያ ‹‹በሕገ ወጥ መንገድ የገባ ነው›› ያሉት ምክትል ኮማደሩ ከየት አገር ስለሚለው ግን በግልጽ ያሉት ነገር የለም። መሳሪያው በቁጥጥር ስር የዋለው ፖሊስ ከኅብረተሰቡ በደረሰው ትቆማ መሆኑን በመግለጽም ነዋሪው ላደረገው ተሳትፎ አመስግነዋል።
ቅጽ 1 ቁጥር 8 ታኅሣሥ 27 ቀን 2011