ብልጽግና ውስጡን ያጥራ፤ መንግሥትም አቋሙን ያስተካክል!!

0
644

የኹለተኛ ዓመቱን ጉዞ አጠናቆ ወደ ሦስተኛው እየተንደረደረ ያለው የለውጡ መንግሥት በርካታ ውጣ ውረዶችን ሲያስተናግድ እና ሲታዘብ እንዲሁም በተለያዩ ጊዜያትም ራሱን እያጠራ የነበረበት መንገድም እንዳለ ሲነሳ ይሰማል። ምንም እንኳን አገርን እና ሕዝብ የማስተዳደር ኃላፊነቱን ተረክቦ በትረ ስልጣንን ቢረከብም በትክክል አይደለም የሚሉ ወቀሳዎች እና ትችቶች ይሰማሉ ይህንንም እንደ ግብዓት መውሰድም መጀመሩን በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ስንታዘብ ቆይተናል።

አራቱን እህት ፓርቲዎች አቅፎ እና በአራት የአጋር ድርጅቶች የተዋቀረው ኢህአዴግን በአደባባይ አፍርሶ አንድ ወጥ ፓርቲ ለመሆን የተደረገው እንቅስቃሴም ሰምሮ ብልጽግና የተባለ ፓርቲን መመስረት ተችሎ አገርን ማስተዳደር ቀጥሏል። አሁንም ድረስ ከቀደመው የኢህአዴግ አስተሳሰብ እምብዛም አልተላቀቀም የሚያስብሉ አካሔዶችን አሁንም መመልከት ይቻላ ይህም ክልሎችን ከአንድ ወጥነተር ፓርቲ ይልቅ እንደቀደሙት አመታት የአማራ ብልጽግና ፣ የኦሮሞ ብልጽግና እተባለ አንድ ወጥ ፓርቲው አሁንም በክልሎች ተከፋፍሎ መመልከትም ያልጠራ ጉዳይ ለመኖሩ አመላካች ናቸው ስትል አዲስ ማለዳ ታምናለች።

ይህ ብቻም አይደለም ከጊዜያት በፊት የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመገናኛ ብዙኃን ቀርበው መከላከያው ከዚህ በፊት በተዋቀረበት ሳይሆን ከፍኛ ሪፎርም የተካሔደበት እንደነበር እና ይህም ደግሞ መፈንቅለ መንግሥት እንኳን ማድረግ ማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል ብለው ሲናገሩ እና የስርጸት ስራ መሰራቱንም ሲያስታውቁ ነበር። በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ተቃኝቶ ነው የኖረው የተባለው መከላከያ የአገር መከላከያ ሰራዊት ለማድረግ እና ሕገ መንግሥቱን እንጂ አንድን ፓርቲ ብቻ እንዳያገለግል ተደርጓል ተብሎ በቅንነት ሲነገር ቢቆይም በሰሜን እዝ ላይ በተቃጣው ጥቃት ላይ ከመከላከያ ዋና መምሪያ ጀምሮ እስከ ሰሜን እዝ ካምፕ ድረስ ተዘረጋ መረብ እና ይለተበተሰ ሰንሰለት መኖሩን ማሳያ እንደነበር ለማወቅ ይቻላል። ይህ ደግሞ የተደረገው ርብርብ እና ስርጸት በትክክል ላለመሰራቱ ወይም ደግ ድብቅ አጀንዳቸውን ለማስፈጸም አሁንም በመንግሥት እና በፓርቲ ውስጥ ያሉ አካላት ስራቸውን እየሰሩ መሆናቸውን መገመት አያዳጋትም።

በቅርቡ ደግሞ የብሄራዊ መረጃ እና ደኅንነት ዋና መስሪያ ቤት በርካታ ባለደረቦቹን በማጽዳት 200 የሚሆኑ ሰራተኞች እና የደኅንነት ባልደረቦች ከስራቸው እንዲታገዱ እና በግዴታ እረፍትም እዲወጡ ተደረጉ መኖራቸውን ዋዜማ ሬዲዮ መዘገቡ ይታወሳል። ‹‹በብሄራዊ የመረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ውስጥ ካሉ አመራሮች ውስጥ ለቀጠራቸው ሀገርና መንግስት ታማኝ ሆኖ ከመስራት ይልቅ ለቡድኖች አገልጋይ መሆን ሲስተዋል መቆየቱን የግምገማ ሪፖርቶች ያመለክታሉ። በአገሪቱ በንፁሐን ላይ ማንነትን መሰረት ያደረገ ጭፍጨፋ እንዲፈፀም፣ ታጣቂ ቡድኖች ላይ እርምጃ እንዳይወሰድ መረጃ የማሾለክና የተሳሳተ መረጃ በመሰጠት የደህንነት መስሪያቤቱ የከፋ ጥልፍልፍ ውስጥ ገብቶ መቆየቱም ተነግሯል።

በደህንነት መስሪያ ቤቱ ውስጥ ሲሰሩ የነበሩ በኢትዮጵያ ተከስተው በነበሩ የጸጥታ ችግሮች ውስጥ ተሳታፊ ናቸው በሚል ጥርጣሬ አሁንም እረፍት ወጥተው ደሞዝ የሚከፈላቸው 27 ሰዎች ስም ዝርዝርም ዋዜማ ራዲዮ ደርሷታል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ በተለያየ ጊዜ ንጹሀን ዜጎች ላይ ግድያ ሲፈጸም በዚህ ድርጊት ውስጥ እጃቸው አለበት ተብለው ከተጠረጠሩ የክልሉ ባለስልጣናት በተጨማሪ ጌታቸው ብርሀነ (ጌታቸው ታክሲ) የተባለ በብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልን ደህንነት እንዲመራ ሀላፊነት የተሰጠው ግለሰብ አሁን በተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች ተሳትፏል በሚል ከስራ እንዲታገድ የተደረገ ነው››። ሲል የዘገበው ዋዜማ በእርግጥም እስካሁን ባሉት አመታት የለውጡን መንግስት ወደ ፊት መምጣት ተከትሎ በርካታ ግጭቶች እና አለመግባባቶች በሰዎች ላይ ተፈጸመው ግድያ እና መፈናቀሎች እንዲፈጸሙ ምክንያት ቢሆኑም በጎን ግን መንግሥት ከፍተኛ ሪፎርም እና ለውጦችን እያካሔደ እንደሚገኝ ደግሞ ሲናገር መቆየቱ ይታወሳል። ይህ ጉዳይ ግን ከዚህ በኋላ መቀጠል እደሌለበት አዲስ ማለዳ ታምናለች። በተለይም ደግሞ ለብ ለብ ስርጸት እና የይድረስ ይድረስ ለውጥ በጭራሽ አስፈላጊ አይደለም።

በእርግጥ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ እንዳሉት አንድን የደኅንነት ባለሙያን ለመተካት በርካታ የሰለጠኑ የሰው ኃይል እንደሚያስፈልግ መናገራቸው አሳማኝ ቢሆንም ነገር ግን ባለው የሰው ኃይል እና እግረ መንገድም አዳዲስ ሰልጣኞችን እና የበቁ የሰው ኃይል በማሰልጠን ወደ ተፈለገው ግብ ለመድረስ ያስፈልጋል።
በሌላ በኩል ደግሞ በብልጽግና ከፍተኛ ባለስልጣናት በኩልም ያለው እንቅስቃሴም ከወዲሁ መላ ሊበጅለት የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ አዲስ ማለዳ ታምናለች። ይህም ማለት አንደንዶች በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ላይ የሚጽፉት እና ሊያገለግሉት የተቀመጡበትን ሕዝብ የማይመጥን እሰጥ አገባ በእጅጉ የተቀመጡበትን የኃላፊነት ስፍራ የማይመጥን እና ተገቢ ያልሆነ መሆኑን ሊታወቅበት እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ታምናለች።

ከትልቅ የኃላፊነት ስፍራ ተቀምጠው ሕግን በተከተለ መንገድ ሀሳባቸውን ከመግለጽ ባለፈ ወደ ተርታ አካሔድ በመሔድ የእንካ ስላንትያ ማምራት ፓርቲውን ብቻ ሳይሆነ ፓርቲ ሚስተዳድረውን አገረ መንግሥት እና ሕዝብ መናቅም ስለሚሆን በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል። ብልጽግና ፓርቲም በውስጡ ያሉትን አባላት ሊገመግም እና ሊያጠራ እንደሚገባው አዲስ ማለዳ ታሳስባለች። ነገር ግን አሁንም በቸልተኝነትም ሆነ ከዚህ በፊት እንደተደረጉት የግምገማ፣ የሪፎርም እና ስርጸቶች አለባብሶ መቀጠል ከፍተኛ ዋጋ የሚስከትል ጉዳይ ነው። መጪው ምርጫን የሚክል አገራዊ ኹነት ከመኖሩ ጋር ተዳ፣ሮ አገሪቱ ምንም አይነት አለመረጋጋቶችን እና ውጣ ውረዶችን የምትሸከምበት እና የዜጎችን ደም መፋሰስ ምትቋቋምበት ችሎታ ላይ ባለመሆኗ ሊታሰብብት እንደሚገባ አዲስ ማለዳ በጽኑ ታሳስባለች።

የእስካሁኖችን አካሄዶች እየደገሙ መሔድ እና ሌላ የሐዘን ወይም የመግለቻ ጋጋታ ሳይሆን የሚገባው ቆራጥ እና ውስጡ ከተጠላለፈ ፓርቲነት በመውጣት ኢትዮጵያን ቀና አድርጎ ከአገር ውስጥ አልፎ በቀጠናው እና በአለም ላይ ባለው ዲፕሎማሲ በኩል ጠንካራ አገርን መመስረት ያስፈልጋል። ችግሮችን በማደባበስ እና የመሐል አገሩ ፖለቲካ በተለይም በብልጽግና ውስጥ ያለው አለመግባባት እና ሽኩቻ ዳር አገር ያትን ዙጎች ሰላም የሚነሳ በመሆኑ በአዲስ ጉልበት እና በተንካራ መሰረት ላይ አገረ መንግስትን ለመገንባት ጠራ ፓርቲ እንዲኖር ግድ በመሆኑ ብልጽግናም ውስጡን ያጥራ፤ መንግስትም አስተዳደራዊ ስራውን በተገቢው መንገድ ይስራ።

ቅጽ 2 ቁጥር 114 ጥር 1 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here