በአዲስ አበባ ከ10 በላይ ጥምቀት ማክበሪያ ቦታዎች የወሰን ማስከበር ጥያቄ እንዳለባቸው ተገለፀ

0
980
የከተማ አስተዳደሩ ጥያቄዎቹን ለመፍታት እየሠራ ነው

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ይዞታቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሆኑ 12 የጥምቀት በዓል ይከበርባቸው የነበሩ ቦታዎች ላይ የወሰን ማስከበር ጥያቄ እንዳለባቸው የአዲስ አበባ አገረ ስብከት ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

ቦታዎቹ ባለፉት አመታት ጥምቀት ሲከበርባቸው የነበሩ ሲሆን ይዞታዎቹ መካከል ሕጋዊ ካርታ ያላቸው እና ካርታ ሊሰራላቸው በሂደት ላይ የነበሩ እንደሚገኙበትም ከአገረ ስብከቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎች ጥምቀት ሲያከብሩባቸው የቆዩ ከ20 በላይ የሚሆኑ አብያተ ክርስቲያናት የሚያድሩባቸው እንደሆኑም ለማወቅ ተችሏል።
የወሰን ማስከበሩ ችግሩን ለመፍታት ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤተክርስቲያኗ ማሳወቋን የአዲስ አበባ አገረ ስብከት የካህናት አስተዳደር ዋና ክፍል ኃላፊ እና የአገረ ስብከቱ ዋና ፕሮቶኮል መላከ ሕይወት ቆሞስ አባ ወልደ ኢየሱስ ሰይፉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ጥር 11 የሚከበረው የጥምቀት በዓልን ተከትሎ ጥምቀት የሚከበርባቸው ታቦታቱ የሚያድሩባቸው 12 ቦታዎች በግለሰብ ፣ በልማት እና በመንግስትም የተያዙ ቦታዎች መገኘታቸውን አስታውቀዋል።

እንደ አገረ ስብከት ቦታዎቹ በዓሉን ለማክበር ፈተና ያለበት ቦታ እንደሆኑ ተገንዝበናል ብለዋል።
ፈተና ካለባቸው ቦታዎች መካከል ለአብነትም ጀሞ ቁጥር ኹለት አካባቢ የሚገኝ የቤተክርስቲያንዋ ይዞታ ወደ አራት የሚሆኑ ታቦታት የሚያርፉበት ህጋዊ ካርታ በቤተክርስቲያኗ የተያዘለት የታቦት ማደሪያ ቦታ እንዳለ እና ነገር ግን አሁን ካርታውን አምክነው የኛ ነው የሚሉ አርሶ አደሮች እንደያዙት ተናግረዋል።
እነዚህ አርሶ አደሮች በቦታው ላይ ይኖሩ የነበሩ ኮንዶሚኒየሞቹ ሲሰሩ መንግሰት ካሳ ከፍሎ በልማት ያስነሳቸው ሲሆኑ አሁን ላይ የኛ መሬት ነው በሚል የመብት ጥያቄ ይዘው ካርታውን አምክነው በቦታው ላይ ይገኛሉ ብለዋል።

አርሶ አደሩም ያልተፈታ የሚለው ችግር ካለ መጠየቅ ያለበት ቤተክርስቲያንን ሳይሆን መንግስትን ነው፤የቤተክስቲያኗን ቦታ መውሰድ አግባብነት የለውም ብለዋል።
ሌላኛው ጥያቄ ያለበት በአዲሱ ገበያ አካባቢ ያለ ጥምቀት የሚከበርበት ቦታ ነው ያሉት አስተዳዳሪው እሱንም ለመፍታት ከጉለሌ ክፍለ ከተማ ጋር እና ከመዘጋጃ ቤት ጋር እየሰሩ እንዳሉም ጠቁመዋል።

ስለዚህም ቤተክርስቲያኗ ጥምቀትን ለማክበር ቦታዎቹን ምቹ ለማድረግ ከፍተኛ ስራዎችን እየሰራን ነው ብለዋል።
በዚህ ጉዳይም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በተለይም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር ውይይት በማድረግ መፍትሄ በመፈለግ ላይ እንዳሉ ጠቅሰዋል።
ክብርት ከንቲባዋ አደነች አበቤ በተቻላቸው ሁሉ እየረዱን ነው ያሉት አስተዳዳሪው ለአብነትም ጃንሜዳን ለማስተካከል አብረውን እየሰሩ ነው አሁን ጥያቄ ላለባቸው ቦታዎች በአስቸኳያ መልስ እንደሚሰጡን ቃል ገብተውልናል ብለዋል።

ከመጋቢት 28 ቀን 2012 ዓመት የኮሮና ቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን ተከትሎ በአትክልት ተራ ያለው የተጨናነቀ የግብይት ሥርዓት የኮሮና ቫይረስን ለማሠራጨት አጋጣሚ ስለሚፈጥር በጊዜያዊነት ወደ ጃንሜዳ እንዲዘዋወር ተደርጎ እንደነበረ ይታወሳል።

በአሁኑ ሰዓትም የጥምቀት በዓል መድረሱን ተከትሎ ጃንሜዳ ለጥምቀት በዓል ማክበሪያ ዝግጁ እንዲሆን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አትክልት ተራውን ወደ ሀይሌ ጋርመንት በማዞር የማፅዳት ስራውን ከህብረተሰቡ ጋር በተደረገ ትብብር መከናወኑ ያተወቃል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሚያደርግላቸው እንዲሁም ላደረገላቸው ትብብር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ አገረ ስብከት ምስጋና አቅርባለች።

ጥምቀት በዓል መዳረሱን ምክንያት በማድረግ ማክበሪያ ቦታዎቹ ለበዓሉ ዝግጁ የማድረጉ ስራ ተጠናክሮ እንደቀጠለ እና ጥያቄ ያለባቸው ቦታዎችም በቅርብ ጊዜ ውስጥ መፍተቀሄ እንደሚገኝለት እምነት አለን ሲሉ ለአዲስ ማለዳ የአዲስ አበባ አገረ ስብከት የካህናት አስተዳደር እና የአገረ ስብከቱ ዋና ፕሮቶኮል ተናግረዋል።
አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር ፕሬስ ሴክሬታሪ የሆኑት አንቺነሽ ተስፋዮ ጋር የስልክ ጥሪ እና አጭር የፅሁፍ መልክትም አድርጋ ምላሽ ማግኘት አልቻልንም።

አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር ፕሬስ ሴክሬታሪ የሆኑት አንቺነሽ ተስፋዬ ጋር የስልክ ጥሪ እና አጭር የፅሁፍ መልክትም አድርጋ ምላሽ ማግኘት አልቻልንም።

ቅጽ 2 ቁጥር 114 ጥር 1 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here