መነሻ ገጽማረፊያሰሞነኛ“መተከል - ምድራዊ ሲኦል”

“መተከል – ምድራዊ ሲኦል”

ሰሞኑን በጣም ብዙ ትኩረት የሚስቡ መነጋገሪያ ጉዳዮች ኢትዮጵያ ውስጥ ተከስተዋል። ከእነዚህ መካከል በዋናነት ተጠቃሾቹ የሕወሓት መሥራች እና የጡት አባት የሚባሉት አቦይ ስብሃት ነጋን ጨምሮ ሌሎች የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች መማረክ እንዲሁም አባይ ጸሐዬን እና ስዩም መስፍንን ጨምሮ ከነጋሻ ጃግሬዎቻቸው መደምሰስ፣ የሱዳን ጦር የኢትዮጵያን ድንበር ተሸግራ የእርሻ ቦታዎችን መቆጣጠሯ እና ችግሩን ለመፍታት የኢትዮጵያ ዲፕሎማሳዊ ጥረት እንዲሁም በቤኔሻንጉል ክልል የመተከል ዞን ውስጥ በሚገኙ ወረዳዎች የንጹሃን ሰዎች መገደላቸውና ከቤት ንብረታቸው መፈናቀል መቀጠለሉ ዋና ዋናዎቹ ናቸው። ይሁንና የዚህ ሰሞነኛ ርዕሰ ጉዳይ ትኩረት ግን የቤኔሻንጉል የንጽሃን ጭፍጨፋ ላይ ትኩረቱን አድርጓል።

ቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተለይ መተከል በሚባለው ዞን ውስጥ ያሉ ወረዳዎች ዘርን መሰረት ያደረገ ግድያዎች፣ መፈናቀሎች እና የንብረት ውድመት መሰማት ከጀመረ ዋል አደር ብሏል። ባለፉት ሦስት ዓመታት በሶማሌ፣ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በደቡብ፣ በአፋር ክልሎች አንዴ ሞቅ ሌላ ጊዜ ደግሞ ቀዝቀዝ እያሉ የሚከሰቱ ግድያዎች፣ ግጭቶች፣ መፈናቀሎች፣ የተከሰቱ ሲሆን በቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግን ያለምንም መቀዛቀዝ እነዚህ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች ተባብሰው ቀጥለዋል።

ረቡዕ፣ ጥር 5 የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) ባወጣው መግለጫ “በቤኔሻንጉል ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት፤ መተከል ዞን፤ በቡለን፣ በድባጤ እና ዳንጉር ወረዳዎች ላይ በንጹሃን ሰዎች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት አሁንም ተባብሶ መቀጠሉ እጅግ አሳስቦኛል” ሲል አስታውቋል። መግለጫው ማክሰኞ፣ ጥር 4 በድባጤ ወረዳ፤ ቆርቃ ቀበሌ፤ ዳሌቲ በተባለች መንድር ከሌሊቱ 11፡30 ጀምሮ የኦነግ ሸኔ እና ቤኒ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ሰዎች መገደላቸውን እና የ82 ሰዎች አስክሬን በፍለጋ መገኘቱን እና የቀብር ቦታዎች የተዘጋጁ መሆኑን አይቻለሁ ያሉ አንድ የዓይን እማኝ ምስክርነት አካቷል። በተጨማሪም ከጥር 2 እስከ 3 በቡለን እና ጉባ ወረዳዎች፤ ኦሜድላ እና አይነሽምስ በተባሉ ቀበሌዎች ላይ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ከ50 በላይ ሰዎች መገደላቸውን እና መኖሪያ ቤቶችም መቃጠላቸውን የሚያመለክቱ መረጃዎች እንደረሱት አስታውቋል።

በዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) የሚመራው የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብቶች ኮሚሽን በበኩሉ በሲቪል ሰዎች ላይ በተፈጸመው ጥቃቶች እጅግ ማዘኑን ገልፆ፥ “በዞኑ የሲቪል ሰዎች ደህንነት መጠበቅ አለመቻሉ ዞኑ በፌደራል መንግሥት ሥር የሚሆንበት መንገድ እንዲመከርበት የሚጋብዝ ነው” በማለት ለመፍትሔ የሚረዳ ያለውን ምክረ ሐሳብም አቅርቧል።

በመተከል የንጹሃን ሰዎች ግድያን በማውገዝ ብዙዎች በማኅበራዊ ትስስር መድረክ በምስል በተደገፈ ሁኔታ ሐዘናቸውን ገልጸዋል። ከታዋቂው ጋዜጠኛ እና የመብት ተሟጋች የሆነው አበበ ገላው በፌስ ቡክ ገጹ ላይ “ማቆሚያ ያጣው ግፍ የንጹሃን ዜጎችን ሕይወት መቅጠፉ፣ ጥረው ግረው ያፈሩትን ንብረት እንዲወድም ማድረጉና ድሃ በግፍ ማፈናቀሉ ተባብሶ ቀጥላል። . . . ለዚህ ግፍ ተጠያቂ ናቸው የተባሉ የበታች ባለሥልጣናትና የወንጀሉ ፈጻሚና አስተባባሪ ናቸው የተባሉ ግለሰቦች ቢታሰሩም፣ የኮማንድ ፖስት መዋቅር ቢዋቀርም ግፉ ቀጥሏል።” ሲል ምሬቱን ገልጿል።

አበበ ገላው ለችግሩ መፍትሔው ብሎ ያስቀመጠው ቤኔሻንጉል ክልል “. . .እንደ ሌሎች ክልሎች ሁሉ፣ ሕወሓት ተከል መርዛማ የዘር ፌደራሊዝም ውርዴ ልጅ የሆነ በመሆኑ መፍረስና እንደገና መዋቀር ይገባዋል። እነ ስብሃት ነጋና መለስ ዜናዊ ከፋፍሎ ለመግዛት በጥላቻና እኩይነት ታውረው ያዋቀሩት የዘር ፌደራሊዝም ሙሉ በሙሉ ከሽፏል።” በማለት ምን እንጠብቃለን ሲልም አጽንዖት ሰጥቷል።

ሌላው ታዋቂው የሰብኣዊ መብቶች ተሟጋች እና የግሎባል አሊያንስ መስራችና አመራር ታማኝ በየነ በክልሉ የንጹሃን ግድያዎች መገደል መቀጠሉን አሳዘኝ መሆኑን በመግለጽ “. . . እየደረሰ ያለውን ነገር በማዘን ብቻ የምንወጣው ሳይሆን በተግባር ስንንቀሳቀስ ነውና፣ ግሎባል አሊያንስን እርዱ፤ ለዘላቂ መፍትሔም አብረን እንሥራ” የሚል ጥሪ አስተላልፏል።

ከፖለቲካ ፓርቲዎች ድምጹን ያሰማው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ሲሆን ሐሙስ፣ ጥር 6 ባወጣው መግለጫ በቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን በተደጋጋሚያ እየተከሰተ የሚገኘውን የዜጎች ሞትና መፈናቀል እንዲሁም በኦሮሚያ መፍትሔ ያልተገኘለት የሰላም መደፍረስና የሰዎች ጥቃት በአገራችን ሊመሰረት ያለውን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የማደናቀፍ ዓላማ ጭምር እንዳላቸው እንረዳላን ሲል ጠቅሷል። ኢዜማ በእነዚህ እና ሌሎች የሰላም መደፍረስ በሚታይባቸው ክልሎች በከፍተኛ አመራሮች የሚመራ ቡድን ችግር ወደ ተፈጠረባቸው አካባቢዎች የሚልክ መሆኑን አስታውቆ፥ ችግሮቹን በተመለከተ የሚደርስባቸውን ድምዳሜ ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግ ጨምሮ አስታውቋል።

መስከረም ከጠባ በኋላ ባለፉት አምስት ወራት ውስጥ ብቻ መተከል ዞንን በተመለከተ በወጡት የኢሰመጉ መግለጫዎች ከ500 ባለይ ሰዎች ተገድለዋል፤ ከ100 ሺሕ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን የሰሙ ብዙዎች “መተከል – ምድራዊ ሲኦል” ሲሉ ኡኡታቸውን አሰምተዋል፤ የጥቃቱ ማብቂያው መቼ ነው ሲሉም ጠይቀዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 118 ጥር 8 2013

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች