“ዐቢይ ወደ ሥልጣን ሲመጣ ብሔርተኛነት እና ኢትዮጵያዊነት እኩል ተፋጠጡ። ኢትዮጵያዊነት የፖለቲካ ሥራ አቆመ፤ ዘረኝነት ግን የፖለቲካውን ሥራ ቀጠለ”

0
1109

ብርሃነ መዋ የኢትዮጵያ እና የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤቶች የቀድሞ ፕሬዘዳንት ናቸው። የደርግ መንግሥት በ1981 ላይ ያወጀውን የቅይጥ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ተከትሎ ከአጋሮቻቸው ጋር በመሆን ባቋቋሙት የግል ኢንዱስትሪዎች ማኅበርም ሆነ ንቁ ተሳታፊና አመራር በነበሩበት የንግድ ምክር ቤቶች በርካታ የነጋዴው ማኅበረሰብ መብቶች እንዲከበሩ ታግለዋል። በተለይ ንግድ ምክር ቤቶቹ ጥርስ አውጥተው መንግሥት ላይ ተጽዕኖ ማድረስ በጀመሩበት በ1990ዎቹ፥ የንግዱ ማኅበረሰብ በምርጫ 1992 ላይ ይበጀኛል ያለውን እንዲመርጥ የማንቃት ቅስቀሳዎችን በማድረግ በልዩነት በአዲስ አበባ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል። ይህ የንግድ ምክር ቤቶቹ አካሄድ ያላማረው መንግሥት፥ ከ1997 አገራዊ ምርጫ መቃረብ ጋር በተያያዘ ምክር ቤቶቹ ላይ ሠፊ የመከፋፈል ሥራዎችን ሠርቷል፤ አመራሩን በተለይ የወቅቱን ፕሬዚዳንት ብርሃነን ከታክስ ማጭበርበር ጋር በተያያዘ አንገላቷል፤ አስሯል። ክስ መስርቶ እስር ቤት ለመወርወር በተዘጋጀበት ወቅት አገር ጥለው ለመሰደድም ተገድደዋል።

ብርሃነ በ1997 በተካሄደው አገራዊ ምርጫ ላይ በቀጥታ በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ ተሳትፎ በማድረግ በሰሜን አሜሪካ የቅንጅት ዋና ተወካይ በመሆን አገር ውስጥ ይካሄድ የነበረውን ትግል ደግፈዋል። በወቅቱ የተቃዋሚው ኀይል ላገኘው ያልተጠበቀ ድል የራሳቸውን አሻራ አኑረዋል። ውጤቱንም ተከትሎ የቅንጅት አመራሮች በታሰሩበት ወቅትም ድጋፋቸውን ቀጥለውል። ይሁንና ከአመራሮቹ ከእስር መለቀቅ ጋር ተያይዞ፥ ከፖለቲካ ፓርቲ ቀጥተኛ ተሳትፎ ጋር ፍቺ ፈጽመዋል። ይሁንና አገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ በተለያዮ መድረኮች ላይ በሳል ትችት መሰንዘር ግን በንቃት መሳተፋቸውን ግን ቀጥለውበታል። የአዲስ ማለዳው ኤርሚያስ ሙሉጌታ በቅርቡ በቋሚነት ከሚኖሩበት ሰሜን አሜሪካ ለአጭር ጊዜ ቆይታ ወደ ኢትዮጵያ ከመጡትን ብርሃነ መዋ ጋር በተለያዩ ወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ሰፋ ያለ ቆይታ አድርጓል።

የኢትዮጵያ ንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የማቋቋሚያ አዋጅ ውይይት ላይ እርሶን ጨምሮ የቀድሞ ፕሬዘዳንቶች መጋበዛቸውን አድንቀው፤ ነገር ግን የአዲስ አበባ ንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አለመወከሉ ያሳደርብዎት ቅሬታ ምንድን ነበር?
ቀድሞ ተሞልቶ እና ክፍተቱን ለማጥበብ በርካታ ሥራዎችን ሰርተን ነበር ነገር ግን አሁንም በአዲስ አበባ እና በኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤቶች መካከል ክፍተት መኖሩን ተረድቻለሁ፤ ምንም እንኳን ክፍተቱን ምን እንደሆነ በውል ባላውቀውም። ይሁንና እንዲህ ያለ ዓይነት ነገር ግን መፈጠር አልነበረበትም።

በአንድ ነገር አገራዊ በሆነ ጉዳይ ላይ ስትወስን፣ ከራስህ የግል ፍላጎት፣ ከድርጅትህ እና ከአገር አንጻር ማየት ይገባሃል። ስለዚህ እንዲህ ዓይነት ነገር በሚፈጠርበት ጊዜ ሰዎች ከኹለቱ ወጥተው ለአገር ምን ይጠቅማል፤ ለአባላት ምን ይጠቅማል የሚለውን ማየት አለባቸው። የእኔ ንግድ ምክር ቤት ብቻ ምን ይጠቅማል፣ ምን ይጎዳል አይደለም መሆን ያለበት። ወይም ደግሞ እኔ እንደተመራጭ ምን ይጠቅመኛል ወይም ይጎዳኛል ሳይሆን በአጠቃላይ ለአገር ምጣኔ ሀብት፣ ለግሉ ዘርፍ እንዲሁም በአጠቃላይ ለነጋዴው ምንድነው የሚጠቅመው ብለው ማሰብ አለባቸው። በዚህ አካሄድ ከተሄደ የማይግባቡበት ምንም ምክንያት የለም ብዬ አስባለሁ። ምናልባት ግን ታሪካዊ ዳራቸው የተወሰነ ተጽዕኖ አድርሶባቸዋል ብዬም አስባለሁ። እርስበርሳቸው ሲጠላለፉ የጋራ ጥቅማቸውን ግን እያጡ ነው።

አንዳንድ ሰዎች ለቡድናቸው በከፍተኛ ሁኔታ ታማኝ ይሆናሉ። የፖለቲካም ከሆነ ለፓርቲው ሊሞትለት ይዘጋጃል፣ ብሔር ከሆነ ለብሔሩ ተመሳሳይ ዓይነት ታማኝነት ሊኖረው ይችላል፤ ማኅበርም ከሆነ እንደዛው። ነገር ግን ይህ በአገራዊ ጉዳይ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያመጣሉ። ስለዚህ በዋናነት ይህ በኹለቱ ቡድኖች መካከል ያለው ክፍተት ለንግድ ማኅበረሰቡ ሲባል መፈታት ይኖርበታል። እከሌ ልክ ነው እከሌ ልክ አይደለም ለማለት ሳይሆን ውስጤን የነካኝን እና የሆነው ነገር ትክክል አይደለም አዲስ አበባ ንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት መጋበዝ ነበረበት ባይ ነኝ ።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የእርስዎን ተሰሚነት እና ተጽዕኖ ፈጣሪነት በመጠቀም በኹለቱ ምክር ቤቶች መካከል ያለውን ክፍተት ለማቀራረብ እና ለማስማማት የጀመሩት መነሳሳት ይኖር ይሆን ?
አሁን እየሠራሁበት ያለሁት ጉዳይ ነው። ይሁንና ምን ያህል እንደሚሳካ አላውቅም።

እርስዎ የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዘዳንት በነበሩበት ጊዜ የኢትዮጵያም ንግድ ምክር ቤት ፕሬዘዳንት ነበሩ። እንዲህ ሊሆን የቻለው ክልሎች ንግድ ምክር ቤት ስሌላቸው ነው ወይስ መወዳደር ስለሚከብዳቸው ነው?
ክልሎችም ንግድ ምክር ቤት አላቸው፤ ውድድርም ያደርጋሉ። ነገር ግን በአብዛኛው የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት እዚህ ከመሆኑ ጋር ተያይዞና ተቋማዊ አቅምም ስላለው የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዘዳንት ከሆንክ በኋላ የኢትዮጵያውም ትሆናለህ።

ከዚህ ቀደም የነበረው የንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዳከመ የመጣ እና የግሉ ዘርፍም አልተወከለም በሚባልበት ደረጃ ተዋቀረ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ከመዳከሙ የተነሳም ጥርስ የሌለው አንበሳ እስከመባልም የደረሰ ነበር። አዲሱ ማሻሻያ ምን ይዞ ይመጣል?
መጀመሪያ ነገር ለንግድ ምክር ቤቱ መዳከም በርካታ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ለእኔ ግን መሰረታዊ ምክንያት የመንግሥት ፍላጎት ስለሆነ ነው። የመጀመሪያው አዋጅ የወጣው 1970 የነበረው አዋጅ ነው ከዛ በኋላ ደግሞ 1995 ኢሕአዴግ አዋጁን እቀይራለሁ ብሎ ተነሳ። እዚህ ላይ ከፍተኛ የሆነ ጭቅጭቅ ነበር። ከመንግሥት ጋራ በርካታ ሥራዎችን አብረን ሠርተናል፤ የግንዛቤ ማስጨበጫዎች፣ አብረን ሠርተናል።

ንግድ ምክር ቤቶች ጥንካሬያቸው እንዲቀንስ ለማድረግ ቅራኔ የተሞሉ መሆን አለባቸው የሚል አካሔድ ነበር። የንግድ ምክር ቤቱ ውስጥ ዘርፍ ማኅበራት የሚባሉ እንዲገቡ ተደረገ። ይህ ደግሞ የንግድ ምክር ቤቶቹን የሚከፋፍል ነው። ምክንያቱም አንደኛ ነገር ንግድ ምክር ቤቱ ለምን ከዘርፍ ማኅበራት ጋር አንድ ላይ ማድረግ ፈለጉ የሚለው ነገር ሙሉ በሙሉ የፖለቲካ አጀንዳን የያዘ ነው። ስለዚህ ደካማ ንግድ ምክር ቤት ነው የሚፈለገው፤ በአንጻራዊነት እንደ በፊቱ ጠንካራ አይደለንም ወይም አይደለም፤ ሊሄድ በሚችልበትም አቅም አልሔደም። የአሁኑን እንደገና ደግሞ ሌላ በውይይታችንም ተነስቷል ስለሆንም አሁንም ተመሳሳይ ችግር የሚኖርበት ይመስለኛል። ምክንያም የንግድ እና ኢንዱስትሪ ንግድ ምክር ቤት ተብሎ ማዋቀር ነው የተፈለገው። ይህም በቅራኔ የተሞላ ነው። ምክንያቱም ኢንዱስትሪ ወይም አምራቹ ብቻ ሳይሆን ግብርናም፣ ቱሪዝምም፣ ትራንስፖርትም ኢኮኖሚው አካል ናቸው። አሁን ወዲህ ስታመጣው እነርሱ ሁሉ የሉም ማለት ነው ምክንያም የማምረቻ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ብቻ ነው የገባው። በእኔ አመለካከት ይህ አሁንም ቅራኔ ውስጥ የሚከት ነው።

ሁሉንም የሚያግባባው እና መሆን ያለበት ማንኛውም ንግድ ፈቃድ ያለውን ሰው አባል ማድረግ ነው። በዚህ መሰረት ንግድ ፈቃድ ያለው ሁሉ በንግድ ምክር ቤቱ ይወከላል ማለት ነው። ስለዚህ ሊኖር የሚገባው የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት እንጂ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ እና ማምረቻ ዘርፍ መሆን የለበትም። ለኢንዱስሪው ከትኩረት እንስጠላን ከሆነ ለማለት የተፈለገው ኢንዱስሪውን በቁሙ ማዋቀር ይቻላል። በእርግጥ እንደሱ ዓይነት ፍላጎትም አለ እንዳይባል፥ ኢንዱስትሪያሊስቱ ያቋቋመው ማኅበር በትዕዛዝ እንዲፈርስ ተደርጓል።

አሁንም የሚመጣው አዋጅ ላይ ተመሳሳይ እና ከቅራኔ የሚያወጣ አይደለም። መጀመሪያው ላይ መንግሥት በፖለቲካው ለማሸነፍ ሲል ያደረገው ነገር ነበር፤ አሁን ያለው መንግሥት ይህ ፍላጎት ይኖረዋል ወይም አይኖረውም ማወቅ አይቻልም። ነገረ ግን እንደዛ ዓይነት ፍላጎት አይኖረውም ብዬ አምናለሁ ምክንያም በቅን መንፈስ ከተረዳው በዛ መንገድ መሔድ ያለበት ይመስለኛል። ንግድ ምክር ቤቱ ራሱን ችሎ መቆም እና ሁሉንም ነጋዴ ጉዳይ ሊመለከተው ይገባል።

የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት እንደ ነጋዴ ጥቅም አስጠባቂነቱ ውስጡ ኢንዱስትሪ፣ ትራንስፖርት፣ ቱሪዝም የመሳሳሉት አሉ። የእነዚህ ሁሉ የሚመለከት ክፍሎች ይኖሩታል እንጂ ግድ እነርሱ እዛው ውስጥ መዋቀር አለባቸው ማለት አይደለም። ላለፉት 14 ወይም 15 ዓመታት እርስርበርስ ሽኩቻ እንጂ ለንግድ ማኅበረሰቡ ይጠቅማል የሚባል ነገር ብዙ አልተሰራም።

አሁን ባለው የለውጥ (‘ሪፎርም’) ወቅት በአንጻራዊነት ነጻነቱም ስላለ በረቂቅ ደረጃ ላይ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ተጽዕኖ በማሳደር እና ያለው እውነታ ከማሳየት አንጻር መሠራት አይቻልም?
አሁን እኮ በእርግጥም እኔንም አንዱ ያበሳጨኝ እንደዚህ ዓይነቱን ነገር ኹለቱ አቅም ያላቸው ንግድ ምክር ቤቶች ቁጭ ብለው ለንግድ ማኅበረሰቡ ይሄ ነው የሚበጀው ብለው ማቅረብ ሲገባቸው፤ ብቻ ለብቻው ለምንድን ነው የሚሔዱት? ለምንድነው ቁጭ ብለው የማይነጋገሩት? ይህ ተደርጎ ግን ሳይሆን ሲቀር ወደ ሕዝብ ማውረድ ይችላሉ። ሕዝቡም እንዲጠይቅ ማድረግ ይችላሉ፤ ነገር ግን ያንን አቅም ነው ያሳጡት። አሁን ይህን አዋጅ እነርሱ ተጽዕኖ አድርገው እንዲቀር ካላደረጉ እንደሚመስለኝ ኹለቱም አካላት የሞራል ተጠያቂነት ይኖርባቸዋል ብዬ አምናለሁ።

የንግድ ማኅበረሰቡ የንግድ ምክር ቤት አባል እንዲሁን የነበረው ከዚህ ቀደም አሰራሩ ንግድ ፈቃድ ሲወጣ በቀጥታ የምክር ቤቱ አባል ይሆን ነበር። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በፈቃድ እና በምርጫ ሆኖ ነበር። በእርስዎ አመለካከት አባልነት በግዴታ ወይስ በምርጫ ይሁን?
በዓለም ላይ ኹለት ዓይነት የንግድ ምክር ቤቶች አደረጃጀት አለ። አንደኛው የንግድ ምክር ቤት አደረጃጀት፤ ነጻ አደረጃጀት ነው። በማንኛውም አካባቢ የተወሰኑ ንግድ ማኅበረሰብ ተሰባስበው ንግድ ምክር ቤት ያቋቁማሉ። አቋቋማቸውም ልክ እንደ ኩባንያም ነው። ኹለተኛው ደግሞ በሕግ ወይም በቻርተር የሚቋቋመው ነው።

እኛ አገር ንግድ ምክር ቤት በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሆነ በደርግ ዘመን መጀመሪያ ላይ በቻርተር ነበር የተቋቋመው። በኢሕአዴግ ግን ጊዜ ኹለት የሚጋጩ ነገሮች ነበሩ። በሕግ እንዲቋቋም በሚደረግበት ጊዜ አባልነት በግዴታ እንዲደረግ ማድረግ ይቻላል ምክንያቱም ለምክር ቤቱ ጥበቃ ይደረግለታል። በአሁኑ ጊዜ የሆነው ደግሞ አንደኛ አባልነት በግዴታ አልሆነም፣ ነገር ግን ምክር ቤቱ በሕግ የተቋቋመ ነው። ኹለተኛው ደግሞ አባልነት በግዴታ በሚሆንበት ጊዜ ጥቅም የማያገኝበትን ወይም ጥበቃ የማይደረግለትን ለምን አባል ይሆናል የሚል ጥያቄ ሊያስነሳ ይችላል። ይሁንና ንግድ ምክር ቤቶች አባል የሆነውን ብቻ ሳይሆን ጠቅላላ ነጋዴውን ነው ጥበቃ የሚያደርጉለት። ስለዚህ ነጻ መሆን የለበትም ተጠቃሚ ለመሆን ደግሞ ከመክፈል ይኖርበታል ማለት ነው።

እኔ የማስበው ከኹለቱ የተዳቀለ ስርዓት ማድረግ ይቻላል ባይ ነኝ። ይህም ማለት መንግሥት በጎ ፈቃድ ካለው የንግድ ምክር ቤቶችን በአዋጅ ያቋቁምና አንዳንድ ሥራዎችን እንዲያከናውኑ አሳልፎ መስጠት ይኖርበታል። ለምሳሌ የንግድ ምዝገባእና የወጪ ንግድ ፈቃድ መስጠት እንዲሁም ንግድ ፈቃድ ሲወጣ የንግድ ዕውቀት ስለሚያስፈልግ ምክር ቤቱ ሥልጠና እንዲሰጥ ቢያደርግ። ይህንን መሰል ሥራ ለንግድ ምክር ቤቱ ከተሰጠ ንግድ ምክር ቤቱ ያንን አገልግሎት ለመስጠት አባል መሆን አለባችሁ ይላቸዋል፣ ያለግዴታ አባል እንዲሆኑ አድርገህ ነገር ግን ለዛ ደግሞ አገልግሎት እንድትሰጣቸው መንግሥት በሌላ በኩል ያስገድዳል ማለት ነው።

ይህ ለነጋዴውም መንግሥለመንግሥቱም ጥሩ ነው። ምክንያቱም ንግድ ምክር ቤት ማለት ለመንግሥት ትልቅ አቅም ነው።
ባደጉት አገራት የንግዱ ማኅበረሰብ ተደራጅቶ መንግሥትን ሲሞግት እና መንግሥትም ሰምቶ ውሳኔ ሲያሳልፍ እንመለከታለን። በኢትዮጵያ ደግሞ በማደርጀት የፖለቲካ ማስፈጻሚያ ማድረግ አለበለዚያም ፖለቲካውን የሚነካው ከሆነ ተመቺ የሚሆነው ነጋዴውን ነው። ለውጡ ለንግዱ ማኅበረሰብ ምን ይዞ ይመጣል ብለው ይጠብቃሉ?
ብዙ ዝርዝር ነገሮችን አላውቅም፤ ነገር ግን ጠቅለል አድርጌ መናገር እችላለሁ። በመጀመሪያ መንግሥት የግል ዘርፍ ማለት ምን ማለት ነው የሚለው ማወቅ ይኖርበታል። ዘርፉ ምን ምን አገልግሎት መስጠት እንዳለበት ጭምር መታወቅ አለበት። አንድ ታዘብኩት ነገር፤ አንዳንድ የመንግሥት አካላት ሥልጠና እና የማማከር አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ነው። እነዚህን አገልግሎቶች የንግድ ምክር ቤቶች የሚሠሯቸው ሥራዎች ናቸው። ይህን ደግሞ ትክክለኛው መንገድ ነው ብዬ አላምንም።

በሌላ በኩል ደግሞ የግል ዘርፉ ራሱ ተጠናክሮ ብቃት ያለው አመራር ኖሮት እነዚህን አገልግሎቶች ሊሰጥ የሚችል አቅም መገንባት አለበት ብዬ አምናለሁ። ይህ ከሆነ ተቋሙ ቀጣይነት ይኖረዋል ብዬ አምናለሁ። ከመንግሥትም ጋር እየተናበበ እንደሚሄድ ይታየኛል። አሁንም ላይ አዋጁ ላይ የተደረገው አደረጃጀት ለእኔ ችግር ያለው ይመስለኛል። ቦርድ ውስጥ የሚገቡት በኮታ ዓይነት ነገር መሆኑ እና በችሎታ አለመሆኑ በራሱ ችግር ይኖረዋል ባይ ነኝ።

የግሉን የንግድ ዘርፍ መዳከምን እንደ አንድ ምክንያት የሚጠቀሰው በፓርቲ ባለቤትነት የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶቸች መኖራቸው ነው ይባላል። እዚህ ላይ ምን አስተያየት አለዎት?
እዛ ጋር ሳንደርስ አገራችን ውስጥ ያለው ልምድ በአሁኑ ጊዜ ማንነት ጥያቄ ከኢትዮጵያዊነት ጥያቄ ጎልቶ እንዲወጣ ተደርጓል። አንድ ሰው አንድ ቦታ ሲሾም ምንድነው ችሎታው ተብሎ ሳይሆን የሚጠየቀው ዘሩ ምንድነው ብለን የምንጠይቅበት ላይ ደርሰናል። ይህ ዘረኝነት አመለካከት ወደ ንግድ ምክር ቤት እንዲገባ ተደርጓል። የማንነት አመለካከት፤ ለምሳሌ አምራች አለ፣ ትራንስፖርት አለ፣ ቱሪዝም አለ።

ሁሉም በራሱ ብቻ ነው ለመቆም ፍላጎት ያለው እንጂ በአንድ ላይ በኢትዮጵያዊነት መንፈስ እና ድርጅትነት ለመሔድ አያስብም። እንደሚመስለኝ በዛ አስተሳሰብ ነው በዚህ በዘርፍ ማኅበራት ላይ ሊሰገስጉ የሚሞክሩት። መነሻው ነጋዴነት ልክ እደ ኢትዮጵያዊነት ማለት ነው፤ ለምሳሌ በፖለቲካው ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ አማራነት፣ ትግሬነት ይቀድማል እንደሚባለው አሁንም ነጋዴነትም ሳይሆን ቸርቻሪነት፣ አምራችነት እና ሌሎች ቅንጣት ክፍፍሎች ስለሚቀድሙ በጣም አደገኛ ነው፤ ጥቅምም የለውም። ምክንያቱም በኢትዮጵያዊነት መብት ሲከበር ፤ የአማራነት፣ የኦሮሞነት መብት አብሮ ነው የሚነበረው፤ በነጋዴነትም መብት ሲከበር አምራችነት፣ አገልግሎት ሰጪነት ይከበራል ማለት ነው።

ብዙ ጊዜ ብሔር ፖለቲካን ሲቃወሙ እና ኢትጵያዊነትን ሲያቀነቅኑ ይታያሉ። በእርግጥ የብሔር ፖለቲካ በሕግ እንዲታገድ ይፈልጋሉ? በአገር ውስጥስ በየትኛውም ስፍራ ላይ በኢትዮጵያዊነት ስም መደረጀት ይቻላል ብለው ያምናሉ?
በእርግጥ እኔ በሕግ ይታገድ የሚባለውን ነገር ብየም አላውቅም። ነገር ግን ስለ ብልጽግና ለምሳሌ ብናሳ ‹‹የስትራክቸር›› ችግር አለበት። የፓርቲውን ደጋፊዊች ባየን ጊዜ ድጋፋቸው ለብሔራቸው ነው። በዚህ ምክንያት ቅራኔ አላቸው ስለዚህ አገርን ለመምራት ሞራል አቅም አይኖርም ብዬ ሀሳቤን አሰምቻለሁ። ብሔርስሜት ማብቃት ነው ያለበት። ለምሳሌ በብሔር የተደራጁ ዜና ማሰራጫዎችን የብሔሩን ሥም ማስወገድ ያስፈልጋል ያም በሕግ መተግበር ያስፈልጋል። ፓርቲዎቹ ጋር ስትሄድ ለምሳሌ ብልጽግና ኢትዮጵያዊ ፓርቲ ነኝ ብሎ ራሱን ማስቀመጥ ሲፈልግ አባሎቹን በአመለካከት ነው እንዲገነቡ ማድረግ ያለበት። ለምሳሌ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድን ወደ ሥልጣን ሲመጣ የደገፉት እነማን ናቸው ቢባል ኦሮሞ ነው ግን አማራውም፣ ደቡብም፣ ሁሉም ደግፎታል የተቃወሙትም እንዳሉ ሆኖ ማለት ነው። ይህ የመሆነው ከብሔር በላይ ማሰብ ስለተቻለ ማለት ነው።

ዐቢይ መጀመሪያ “ለእኔ ከኢትዮጵያ በላይ ማንም አይበልጥብኝም” በመናገሩ፤ ብሔርን አስቀድሞ ከተመጣ ግን አገር ለመምራት የሞራል ብቃትም አይኖርም። ብሔርን መሰረት ያደረጉ ፓርቲዎች ሁልጊዜ የሚያነሱት የብሔርን ጥያቄ የበላይነት እንዲመጣ ነው፤ በርግጥ የብሔር እኩልነት መፈለግ ግን ሌላ ነገር ነው።

እነዚህ ፓርቲዎች የሚዋጡት በኢትዮጵያዊነት መጠንከር ነው። በእርግጥ ምንድነው የሆነውዐቢይ ወደ ሥልጣን ሲመጣ ብሔርተኛነት እና ኢትዮጵያዊነት እኩል ተፋጠጡ። ኢትዮጵያዊነት የፖለቲካ ሥራ አቆመ፤ ዘረኝነት ግን የፖለቲካውን ሥራ ቀጠለ። በኢትዮጵያዊነት የተደራጀው ግን 10 ሺሕ ሰው ለማስፈረም እንኳን የተቸገሩበት ጊዜ ነበር። ለምሳሌ ኢዜማ ራሱ ለመደራጀት ፖለቲካውን ትቶት ስምንት ወራት ነው የፈጀበት፤ እንደ እኔ በስትራቴጂ ትክክል አይደለም ባይ ነኝ። ይህ ደግሞ ክፍተትን በመፍጠሩ ዘረኝነት ቀድሞ የወጣበት እና ሩቅም የተጓዘበት በዚህ ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 118 ጥር 8 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here