መነሻ ገጽሐተታ ዘ ማለዳብሔራዊ መግባባት ከምርጫ በፊት?!

ብሔራዊ መግባባት ከምርጫ በፊት?!

የብሔራዊ መግባባትን አስፈላጊነት ከብዙ ዓመታት ጀምሮ ሲወተወት ቢቆይም እንደ አገር ቁጭ ብሎ በመነጋገር መሰረታዊ የሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ተነጋግሮ ዲሞክራሲያዊ አገር መገንባት አልተቻለም፡፡
አገር ለመገንባት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ሳንግባባ ለ 5 ጊዜያት ምርጫ ብናከናውንም ፍሬ ቢስ ከመሆን ሳያልፍ ሌላ ምርጫ ውስጥ ልንገባ መሆኑ ለብዙዎች ስሜት የማይሰጥ ይልቁንም ስጋት ውስጥ የሚከት እንደሆነ እና ብሔራዊ መግባባት ከምርጫ በፊት መድረስ እንደሚገባ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እና የዘርፉ ባለሙያዎች አነጋግሮ ዳዊት አስታጥቄ በሐተታ ዘ ማለዳ አቅርቦታል፡፡

አሁን ያለንበት ሁኔታ አገራዊ መግባባትን ግድ የሚልበት ወቅት ነው። እንደ አገር በእጅጉ እየተፈተንበት ያለንባቸው ውስጣዊ እና ውጫዊ ጉዳዮች በርክተዋል። በአገር ውስጥ በተለያዩ ቡድኖች እየተፈጸሙ ያሉ ግድያዎች ዛሬም አላባሩም ፤በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ዜጎችን ከቀያቸው አፈናቅሏል።መንግሥትም የዜጎችን ደህንነት መጠበቅ አዳጋች ሆኖበታል። በትግራይ የተካሄደው ሕግ ማስከበር ዘመቻም የህወሃት መስራች ግለሰቦችን እና ጉምቱ የቀድሞ ባለሥልጣናት በመደምስስ እና ለፍትህ አደባባይ በማቅረብ ላይ ቢሆንም፤ መጪው ጊዜ ግን ምን መልክ ሊኖረው እንደሚችል መገመት ቀላል አይደለም።

ከህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ በግብጽ አዝማችነት በሱዳን በኩል ከ40 ኪሎ ሜትር በላይ ዘልቆ የኢትዮጵያን መሬት በኀይል ይዞ የሚገኘው የሱዳን ጦርም የጦርነት ነጋሪት በመጎሰም ላይ ይገኛል። እንደ አገር ያሉብንን ውስጣዊ እና ውጫዊ ፈተናዎችን በተባበረ ክንድ ሳንመክት ሌላ ፈተና ተደቅኖብናል፤ አገራዊ ምርጫ።
በእርግጥ ምርጫው ፈተና ብቻ ሳይሆን መልካም እድልም ይዞ ይመጣ ይሆናል። ያለፉት ልምዶች ግን ይህን መልካም እድል ያዞ ይመጣል የሚለውን ሃሳብ በግማሽ ልብ ብቻ እንድንቀበለው የሚያስገድዱ ምክንያቶች አሉ።

መጪው 6ተኛው አገራዊ ምርጫ ግንቦት 28/2013 ሊካሄድ ቀን ተቆርጦለታል። የምርጫ ሕጎችን የማሻሻል እና ሌሎች በርካታ ሥራዎችን በመሥራት ላይ ይገኛል። ከእነዚህም መካካል በምርጫ አዋጁ በተቀመጠው መሥፈርት መነሻነት፣ መስፈርቱን አላሟላችሁም ብሎ ወደ 30 የሚጠጉ የፖለቲካ ድርጅቶችን መሰረዙንም አስታውቋል።

እንደ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ያሉ ፓርቲዎች የምርጫው ቀን ይህን ያህል ቀን ቀረው በማለት ሕዝብ እየቀሰቀሱ ይገኛሉ። በሌላ በኩል ደግሞ እንደ ኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ከአገራዊ ምርጫው ተገድጄ ልወጣ የምችልበት ዕድል አለ ሲሉ ይደመጣሉ::በምክንያትነትም የፖለቲካ ምህዳሩ መጥበቡ፣የአባሎቻቸው መዋከብ፣ እስር እና እንግልት እና እንደልብ ተንቀሳቅሶ መስራት አለመቻል እንደሆነ መሪው ፕ/ር መረራ ጉዲና ለአዲስ ማለዳ ሃሳባቸውን አጋርተውናል።

በአፍሪካ ምርጫ ማድርግ ብዙም አስቸጋሪ ነገር አይደለም። ችግሩ የሚመጣው በምርጫ ሳጥን የመንግሥትን ሥልጣን በሰላማዊ መንገድ መለወጥ መቻሉ ላይ ነው ። ይልቁንም ከምርጫው ማግሥት ጀምሮ በሚኖረው ብጥብጥ የተነሳ የብዙ ዜጎች ሕይወት ሲቀጠፍ ይሥተዋላል።

እንደ ፕ/ር መረራ ከሆነ ኢትዮጵያም ከንጉሱ መጨረሻ ዘመን አንስቶ እስከ አሁን ድረስ ምርጫ የማድረግ ነገር እንደነበር ፤ነገር ግን የሚፈለገው ውጤት እንዳልመጣ ፤አገሪቱን እና ሕዝቧን ከቀውስ አለመታደጉን ያነሳሉ። እስከ አሁን ያካሄድናቸው ምርጫዎችም መሰረታዊ በሆነ መልኩ ኢትዮጵያን ችግር የፈቱ አይደሉም ይላሉ።
ከዚህ ሁሉ በላይ እውነተኛ የብሔራዊ ምክክር መድረክ አለመኖር እና ቢያንስ መሰረታዊ በሚባሉ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባት ላይ ሳይደረስ ምርጫ ማካሔዱ ትልቅ ችግር እንደሆነ ያለሳሉ።

በተወሰነ ደረጃ ቢሆን የተሻለ ፍክክር የታየበት ነው ተብሎ የሚጠቀሰው የ1997 እንኳ ከ193 ዜጎች በላይ ሕይወታቸው እንዲቀጠፍ እንዲሁም በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች ወደ ወሕኒ ቤቶች እንዲጋዙ ከማድረግ ያለፈ ፋይዳ አልነበረውም፤ ይባሱን አሸናፊውን ቡድን ለሁለት ዓመታት ለተጠጋ እስር የደረገ ነበር። ይህም ከምርጫ ባህል ጋር አለመተዋወቅ እና የዳበረ የፖለቲካ ሥርዓት ለመፍጠር ኢትዮጵያን በተለያየ አጋጣሚ የመሩ መሪዎች ፍልጎት አለመኖር እንደሆነ ይታመናል።

ያለፉት አምስት አገራዊ ምርጫዎችን እንኳን ብንመለከት አንድም ጊዜ ትክክለኛ እና ታአማኒ ምርጫ ተከናውኖ አያውቅም ። ምርጫ የምናካሄደው ፈረንጆችን ለማስደሰት እንጂ ሀቀኛ ዲሞክራሲያዊት አገር ለመገንባት አንዳልነበረም መረራ (ፕ/ር) ያነሳሉ። ይልቁንም ምርጫው ዜጎችን በፖለቲካዊ አመለካከታቸው የተነሳ ፈርጆ ለማሰር ፣ለማንገላታት እና ለመግደል የሚያበቃ አውድ ከመፍጠር ያለፈ ፋይዳ እንዳልነበረውም ያነሳሉ።

ለዚህም በ1997 ለሶስተኛ ጊዜ በተካሄደው አገራዊ ምርጫ ከ193 በላይ ዜጎችን ሕይወት መቀጠፍ እና ከ 40 ሺሕ በላይ ወጣቶች ለግዞት መዳረጋቸውን የአለም የሳይንስ፣የቴክኖሎጂ እና ኢንጂነሪንግ አካዳሚ በ2009 በቅጽ 3፣ቁጥር 7 ያሳተመው ጥናታዊ ጽሁፉ በምንጭነት ያስቀምጣሉ ።

አንደ መንግሥት አገራዊ መግባባትን ለመፍጠር ብሔራዊ የምክክር መድረክ በማዘጋጀት ሥልጡን ዜጎችን የመፍጠር ሥራ ለመሥራት መታቀዱን የሰላም ሚንስትሯ ሙፈሪያት ካሚል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሪፖርት አቅርበው ነበር። በዚህም መድረክ ለ25 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎችን ለመድረስም መታሰቡን ጨምረው ገልጸዋል።

ለሥልጠናው ወይም ለውይይት የሚሆኑ ማኑዋሎች ከመዘጋጀታቸው በተጨማሪም ከወረዳ ጀምሮ ያሉ አመራሮችን ለማሰልጠን እንደታሰበ ሪፖርታቸውን ባቀረቡበት ወቅት ተናግረው ነበር። ይህ ግን መሰረታዊ ለውጥ አያመጣም ይላሉ የኦፌኮ ተቀዳሚ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና። አንደ ኦፌኮ በምርጫው ለማሳተፍ ግልጽ ውሳኔ ላይ ያልደረሱት በመላ ኦሮሚያ በሺዎች የሚቆጠሩ አባሎቻችን ታስረዋል፤በመቶዎች የሚቁጠሩ ቢሮዎቻችን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተዘግተዋል ፤በሰላም የመንቀሳቀሱ ጉዳይም ችግር በመኖሩ እንደሆነ በምክንያትነት አስቀምጠዋል።

ሕዝቡ ምርጫ ውስጥ አትግቡ ካለ መግባት ይቸግራል የሚሉት ፕሮፌሰር መራራ በተለያየ አጋጣሚ ደጋፊዎቻችን ሰውን እያሳሰራችሁ የት ልትገቡ ነው ?የሚል ምላሽ እየሰጡን በመሆኑ የበለጠ ችግር እንዳይከሰትም በምርጫው ላለመሳተፍ እያጤንን ነው ይላሉ።

እኛ አሁን እያሳሰበን ያለው ነገር በምርጫ መሳተፍና አለመሳተፍ ሳይሆን ቀጣዩ የሀገሪቱ አንድነት ጉዳይ ነው ይላሉ ።ሁሉም ዜጋ በጋራ የሚኖሩባት፣ የሚግባቡባት እንድትሆን ከአዳራሽ ያለፈ ብሔራዊ መግባባት የሚያመጡ መድረኮች ያስፈልጋሉ ፤ ቅድሚያ እዚያ ላይ መደረስ አለበት የሚል አቋም ፖርቲያችን እንዳለው አንስተዋል።

ባለፉት ሀምሳ አመታት የሚጋጩ ሕልሞችን ይዘን ተጉዘናል የሚሉት ፕሮፌሰር መራራ አንድ ቦታ በቃን ብለን የሁላችንም ህልም የሚስተናገድበትን ወይም የሚቀራረብበትን ሙሉ ለሙሉ እንኳን ማስታረቅ ባንችል በሰለጠነ ፖለቲካ የምንይዝበትን መንገድ ካልፈጠርን በስተቀር ከሳሽና ተከሳሸነቱ አብሮን ይቀጥላል ይላሉ።
ለዚህ ደግሞ ሁሉም ጣቱን ሌላው ላይ ከመቀሰሩ በፊት ራሱን ማየት ይኖርበታል ፤ህዝቡም አሁን የሚፈልገው ሰላም ነው፤ ለዚህ ደግሞ ፖለቲከኞችም ይሆኑ ሊሂቃኑ ራሳቸውን ከእኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ትርክት ማላቀቅ አለባቸው ብለዋል።

ነገር ግን የሰላም ሚኒስቴር ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ ለዘላቂ ሰላምና ለብሔራዊ መግባባት ትልቅ ፋይዳ ያላቸውን የብሔራዊ የበጎ ፋቃድ የማህበረሰብ አገልግሎት እና የብሔራዊ የምክከር መድረክ ፕሮግራሞችን ቀርፆ ወደ ተግባር መግባቱን ተናግረዋል።

- ይከተሉን -Social Media

የብሔራዊ የምክከር መድረክ ህብረተሰባዊና እና ሊቃን ተኮር በማድረግ እስከ ቀበሌ ድረስ ማህበረሰቡን የሚያሳትፍ ነው ያሉት ሚኒስትሯ ዓላማው በመሰረታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት መፍጠር እንደሆነ አስረድተዋል። የብሔራዊ የበጎ ፈቃድ የማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮግራም መሆኑን የገለፁት ወ/ሮ ሙፈሪሃት በአሁኑ ሰዓት ከመላው ሃገሪቱ የተወጣጡ 35ሺህ ወጣቶች በተመረጡ 22 የኒቨርስቲዎች ለስልጠና እየገቡ ይገኛሉ ብለዋል።

ለስልጠናው የተመረጡት ወጣቶች በራሳቸው ፈቃደኝነት ሲሆን ከዩኒቨርስቲ የተመረቁ ወጣቶች ናቸው። በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ለ45 ቀናት በስሜት ብስለት (Emotional Intelligence) እና በአካል ብቃት ላይ ስልጠና ከወሰዱ በኋላ ለ10 ወራት በመላው ሀገሪቱ በመዘዋዋር የበጎ ፈቃድ አግልግሎቶችን ይሰጣሉ ተብሏል።

በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በስልጠናው ወቅት እና ከስልጠናው በኋላም ለበጎ አገልግሎት በሚሰማሩባቸው አካባቢዎች ዕርስ በርስ የመተዋወቅና አዲስ ቤተሰብ የማፍራት ዕድል ይኖራቸዋል ብለዋል።

ይህ ደግሞ ብሔራዊ መግባባትን ለማሳደግ የጋራ ታሪክ እና ትርክት እነደዲኖር ለማድርግ ሰፋፊ ስራ የሚጠይቁ ከመሆኑ ጋርም ተያየዞ ዜጎች ተቀራራቢ አመለካካት እነዲይዙ ያስችላቸዋል የተባሉ ጉዳዮች ዋና ዋና ጉዳዮች መለየታቸውን አንስተዋል።

በፖለቲካ ፓርቲዎች መካካል መሰረታዊ በሚባሉ አገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት እንዲችል ከፖለቲካ ፓርቲዎች ምክር ቤት ጋር በመሆን የውይይት መድረክ ሲደረግ መቆየቱን፣ በሌላ በኩልም የሊሂቃን መድረክም እንደሚዘጋጅ በተለይ ከታሪክ ጋር የተገናኘው ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝ ታውቋዋል።በዚህ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ የታሪክ ባለሙያዎች አንዲሰባሰቡ መደረጉን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ከታሪክ እይታችን ጋር መታረም ስለሚገባቸው ጉዳዮች ተቀራራቢ እሳቤ ለመያዝ የሚያስችል ሥራም እንደሚሰራ ያነሳሉ።
እንደ ኢዜማ ከሆነ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር የሚካሔዱ ውይይቶች መካሄድ እንዳለባቸው እና እንደ ፓርቲም ባለድርሻ መሆናቸውን አንስተው ከምርጫ በፊት በሚለው አካሔድ ግን እንደማይስማሙ ገልጻዋል። ነገር ግን የብሔራዊ ውይይቱ መድረክ ከምርጫ ጎን ለጎን መደረግ አለበት ብለው እንደሚያምኑ እና በብሔራዊ መግባባት ሰበብ ምርጫ እንዲራዘም እና በምርጫ ይደረግ አይደረግ ንትርክ ሌላ ግጭት ውስጥ መግባት እንደማያስፈልግ ለአዲስ ማለዳ ሃሳባቸውን ሰጥተውናል።
የብሔራዊ የውይይት መድረክ ወይም ጉባኤ በራሱ ሂደት እንጂ ውጤት አይደለም። ይልቁንም በዚህ ብሔራዊ የምክክር መድረክ ላይ የሚደረስባቸው ውጤቶች ብሔራዊ መግባባት ተብለው ሊሰየሙ ይችላሉ ይላሉ። ብዙ ውስብስብ ችግሮች ባሉበት አገር በዋናነት ብሔራዊ የምክክር መድረክ የሚያስፈልገው ፤በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የሚደረግ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ። በዚህ ፖለቲካዊ ውይይት ወቅት ግን ሁሉም ጉዳዮች ሳይሆን በጣም ወሳኝ በሆኑ ገዳዮች ላይ ብቻ የሚያተኩር መሆን አለበት ይላሉ በኢንስቲቲዩት ኦፍ ሴኩዩሪቲ ስተዲስ ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ሰሚር የሱፍ (ዶ.ር).

በፖለቲካው መስክ የሚደረግ ብሔራዊ የመግባባት መድረክ ላይ ታዲያ ሁሉንም የፖለቲካ ሊሂቃን ያሳተፈ ከሁሉም አካባቢዎች ያሉ የተላያዩ ሃቦች እና አመለካካቶች የሚካተቱበት ሐቀኛ ውይይት ማድረግ ይጠበቃል።ዋናው ጉዳይ መጻኢ የአገሪቱን እጣ ፈንታ በጋራ ውሳኔ እና መግበባት መወሰን ነው።

ብሔራዊ መግባባት አንድ አገር ያለባትን የቆየ የመልካም አስተዳደር እጦት ለማተካከል እና የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ያለመ ሒደት ነው። ስለዚህ አንደ ኢትዮጵያ ላሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ላሉባት እና ለተጋረጡባት አገር የብሔራዊ ውይይት መድረክ መዘጋጀት ቅንጦት ሳይሆን ግዴታ ነው ይላሉ ብርሃኑ ሌንጅሳ በ July 2018 Inclusive Dialogue, National Reform & Reconciliation in Ethiopia: A Meta-Modeling Approach በሚለው ጽሁፋቸው።
ብሔራዊ መግባበት የመፈጠሩ ትልቁ ፋይዳ ሕዝቦች በአገሪቱ በሚገኙ የመንግሥት ተቋማት ላይ አመኔታ እንዲኖራቸው ማድረግ ነው። ከመንግሥት ተቋማት ውጪም እንደ ፍትህ ሰጪ ያሉ ገለልተኛ ተቋማት ላይ ጭምር ሕዝቦች አመኔታ እንዲኖራው እና የዳበረ የዲሞክራሲ ሥርዓት እንዲፈጠር ያስችላል ይላሉ።

- ይከተሉን -Social Media

በተጨማሪም የአገሪቱን መከላካያ እና የደህንነት ተቋማት ሳይቀር ከፓርቲ ወገንተኝነት ነጻ ማድረግ እና ለሕዝብ ብቻ የወገኑ ተቋማት እንዲሆኑ የማድረግ ፋይዳ አንደሚኖረው ይታመናል በዚህም ሕዝብ የበለጠ አመኔታ አንዲኖረው ያደርጋል፤ ብሔራዊ መግባበት።በዚህ ረገድ እየተሄደ ያለበት ርቀት ቢኖርም እነዚህን ተቋማት ነጻ አድርጎ ሕዝብ አመኔታ እንዲኖረው ማድረግ ገና ብዙ ርቀት እንደሚቀረው መናገር ይቻላል ይላሉ ብርሃኑ።

እነማን ይሳተፉ የሚለውን ጉዳይ በተቻለ መጠን መንግሥት፣የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ተጽእኖ ፈጣሪ ሰዎች በራሳቸው ካለማንም ተጽእኖ በፍትሃዊነት በየደረጃው መካከት እና ሃሳብ መስጠት መቻል አለባቸው።ይህም ማን ይሳፍ የሚለውን ጉዳይ ካለ መንግሥት ጣልቃ ገብነት መመረጥ አለበት ፤ካልሆነ የብሔራዊ መግባባት ጉዳይ ውጤት አልባ ይሆናል ይላሉ።

ከጎረቤት አገራት ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን ልምድ ብንወስድ እንኳን የብሔራዊ ምክክር መድረኩን እራሱ ገዢው ፓርቲ አመንጭቶ እራሱ አንደፈለገ ለመቆጣጠር መሞከሩ መድረኩ ምንም ዓይነት ውጤት እንዳያመጣ አድርጎታል ይላሉ ሰሚር የሱፍ(ደ/ር).

አሁንም በጠቅላይ ሚንስቴር ዐቢይ ዘመን ለማካሔድ እየታሰበ ያለው ምርጫ ችግሮቻችንን ካልፈታ ምንም ፋይዳ የማይኖረው ምናልባትም አገሪቱን ወደ ቀውስ የሚያመራ ሊሆን ይችላል ። ለዚህም በትግራይ፣ በሶማሌ እና አፋር አዋሳኝ አካባቢ ፣በደቡብ በኮንሶ እና አሌ በመተከል አየተነሱ ያሉ ግጭቶች እንዲሁም በምዕራብ ኦሮሚያ ባላታወጀ ኮማንድ ፖስት ተወጥሮ እያለ ምርጫ ምን ውጤት ያመጣል? ሲሉ ይጠይቃሉ ፕ/ር መረራ።

ከዚህ ምርጫ ዲሞክራቲክ ኢትዮጵያ ትወለዳለች ወይ? ወይስ እንደቀድሞው ዓይነት ቴያትር ይቀጥላል? ይሉና ለምርጫ በሚያስፈልጉ ጉዳዮች ላይ ቁጭ ብለን መመካከር ይገባናል ከዚያም ተስማምተን ወደ ምርጫ መሄድ እንደሚሻል ያነሳሉ።

ጠቅላይ ሚንሰተር ዐቢይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ ጀምሮ መንግሥት የተለያዩ መድኮችን በጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት አዳራሽ፣ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ አዳራሽ በማዘጋጀት የብሔራዊ ምክክር መድረክ ለማድረግ ሙከራ አድርጓል። በምርጫ ቦርድ እና በሲቪክ ማህበራት አማካኝነት እየተካሄዱ ያሉ ጥረቶች አሉ።
ነገር ግን አንዳንዱ አካሄድ ራሱ ትክክል እንዳልሆነ ፕ/ር መረራ ያነሳሉ።ለአብነትም በጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት የሚካሄደው የጥያቄ እና መልስ አካሄድ እንጂ ውይይት መባል የማይገባው አንደሆነ ያነሳሉ።ላለፉት ሶስት ዓመታት የተደረጉ መሰል ውይይቶችም መቋጨት አለመቻሉ በራሱ ችግር መኖሩንም ያመላክታሉ። መሰረታዊ የሆነ የደረስንበት ውይይትም የለም ይላሉ።

“የፖለቲካ ፍላጎት እና ቁርጠኝነት ቢኖረን በሶስት ቀናት ልንፈታቸው እና ልንግባባቸው የምንችላቸውን ጉዳዮችን ለሶስት ዓመታት ውስጥ እንኳን የታሰረ ነገር በእጃችን የለም ፤አንድም ጉዳይ አልታሰረም” በማለት ፕ/ር መረራ ይናገራሉ።

ዋናው ጉዳይ በታሪክ አጋጣሚ የምኒልክን ቤተመንግስት የያዙ ሰዎች ከመሰረታዊ ስምምነቶች የመሸሽ ጉዳይ ነው ይላሉ።በዚህ ምክንያት በአሁኑ ወቅት አደጋ ይታየኛል ይህን አደጋ ለመሻገር በተለይ መንግሥት ቁርጠኛ አቋም ማራመድ አለበት ይላሉ።

- ይከተሉን -Social Media

ከምርጫው ጋር በተገናኘ የምርጫው መራዘም ሆነ በተቆረጠለት ቀን መከናወን በራሱ ዋጋ የለውም። ይልቁንም ትርጉም ያለው ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር በተለይ ከመንግሥት ብዙ ርቀት ይጠበቃል ይላሉ።

እንደ መደምደሚያ፣ብሔራዊ መግባባት ላይ የደረሱ አገራት ዛሬ ላይ ጥሩ የዲሞክራሲ እና የልማት ጎዳና ላይ ሲገኙ ብሔራዊ መግባባት ማስፈን የተሳናቸው እንደ ዩጎዝላቪያ ያሉ አገራት ደግሞ ፈራርሰዋል። ይህ ደግሞ ኒውክሌር የታጠቁትን እና እልፍ ሰራዊት ያላቸውን እንደ ቀድሞው ሶቪየት ሕብረት ያሉ አገራት ሁሉ ሊቋቋሙት የማይችሉት ጉዳይ በመሆኑ አገር ሳይፈርስ እና ሳይበጣጠስ ብሔራዊ መግባባት ላይ መድረስ ተገቢ ነው እንላላን።

ቅጽ 2 ቁጥር 118 ጥር 8 2013

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች