የኢሰመኮ ሪፖርት ክፍተቶች

0
845

በቅርቡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል የነበረውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት በተመለከተ ያወጣውን የምርመራ ሪፖርት ትኩረት በመስጠት መጣጥፋቸውን ያጠናቀሩት ማርሸት መሐመድ ሐምዛ፥ በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየተከሰቱ የሚገኙ መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከትኮሚሽኑ በሚያወጣቸው የምርመራ ሪፖርቶች እና መግለጫዎች ውስጥ በአብዛኛው ገለልተኛ መረጃዎችን እና የምርመራ ግኝቶችን ለማቅረብ መሞከሩ አበረታች ነው ብለዋል። ይሁናን የሚመለከተውን አካል በድፍረት ለመለየት፣ ለማጉላት እና ለመኮነን ሲቆጠብ ሲታይም ተስተውሏል፤ እንዲሁም በተለይ በቅርቡ ይፋ ባደረገው የምርመራ ሪፖርትና መግለጫው ላይ የተስተዋሉ ያሏቸውን ክፍተቶች በመጣጥፋቸው አመላክተዋል።

(በኢትዮጵያ ወንጀል ሕግ ያልተደነገገው በሰብኣዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል)
ሰኔ 22/2012 የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በተለይ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በነበረው ኹከት እና ግጭት በሰዎች ሕይወት እና ንብርት ላይ የደረሰውን ጉዳት አስመልክቶ የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ያደረገውን ምርመራ ሪፖርት በታኅሣሥ መጨረሻ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። ይህ ሪፖርት ከዚህ ቀደም በኮሚሽኑ ከሚወጡት ሪፖርቶች በተሻለ ደረጃ ጠለቅ ያለ ምርመራ የተደረገበት፣ በአንጻራዊነትም ፈጣን ሊባል የሚችል ነው።

የኮሚሽኑ ዋና ኀላፊ ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ድርጅቱን ለመምራት ከተሾሙበት ጊዜ ጀምሮ የኮሚሽኑን አሠራር በማጠናከር በአገራችን በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ ግጭቶችን ተከትሎ የሚፈጸሙ የሰብኣዊ መብቶች ጥሰቶችን በተመለከተ የተለያዩ ፈጣን ሪፖርቶችን እና መግለጫዎችን በማውጣት የመብቶቹን ጥሰቶች ለመከታተል ሲጥሩ ታይተዋል።

በቅርብ ጊዜያት ኮሚሽኑ ያወጣቸው ሪፖርቶች እና መግለጫዎች ትኩረት በአብዛኛው መንግሥት እና ሌሎች አካላት ሰብኣዊ መብቶችን እንዲያከብሩ እና እንዲያስከብሩ የሚያሳስቡ ናቸው። በኦሮሚያ ክልል የሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በነበረው የሰብኣዊ መብቶች ጥሰቶች ላይ ያተኮረው ይህ ሪፖርት ግን ከዚህ በፊት ከነበረው አንድ እርምጃ ወደፊት በመሄድ በአጠቃላይ ሁኔታው በሰብኣዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል ስለመፈጸሙ የሚያመላከቱ ሁኔታዎችን በምርመራው እንደደረሰበት ያትታል።

የሪፖርቱ አጠቃላይ ይዘት
በ56 ገጾች የተጠናቀረው የኮሚሽኑን ሪፖርት ይዘት በአጠቃላይ በሦስት ከፍለን ልንመለክት እንችላለን። እነዚህም ሪፖርቱ የዳሰሳቸው የኦሮሚያ ከልል አካባቢዎች እና ጉዳዮች ወሰን (scope)፣ ሰብኣዊ መብቶችን በመጣስ የተሳተፉ አካላት፣ እና በሰብኣዊ መብቶች ጥሰት የተፈጸመ(ሙ) የወንጀል ዓይነት የለየበት ናቸው።

ሀ. የሪፖርቱ ወሰን
ሪፖርቱ ቀዳሚ ትኩረቱን ያደረገው በምርመራ ሒደት ከእማኞች፣ ከተጎጂዎች፣ ከተጎጂዎች ቤተሰቦች እንዲሁም ከመንግሥታዊ አካላት የሰባሰባቸውን ጥሬ ሀቆች (facts)እና መረጃዎች ማቅረብን ነው። በዚህም ኮሚሽኑ በ40 የኦሮሚያ ከልል አካባቢዎች ያሰባሰበውን መረጃ፣ በሰዎች ሕይወት እና አካል ላይ የደረሱ ጥቃቶችን፤በቡድን በሚንቀሳቀሱ ሰዎች የተፈጸሙ ጥቃቶችን እናየጥቃት አድራጊዎችን ቡድናዊ እንቅስቃሴዎች ዳሷል።እንዲሁም ጥቃቶቹ የተፈጸሙበትን ዓውድ፣ ለጥቃት መፈጸሚያ የዋሉ ቁሶችን፣ በመንግሥት የጸጥታ አካላት የተፈጸሙ ድርጊቶችን፣ በአጠቃላይ በሁኔታው የደረሱ የሰብኣዊ መብቶች ጥሰቶችን እና ጥቃቱን ከመከላከል አንጻር የመንግሥት የጸጥታ አካላት የነበራቸውን ጠንካራ እና ደካማ ጎኖችን በዝርዝር አቅርቧል።

እንደ ኮሚሽኑ የምርመራ ረፖርት በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በ40 ከተሞች በነበረው ኹከትእና ያን ተከትሎ በደረሰው ጥቃት በአጠቃላይ የ123 ሰዎች ሕይወት አልፏል፤ 35 ሰዎች በኹከት ፈጣሪ ቡድኖች፣ 76 ሰዎች ደግሞ በመንግሥት ጸጥታ ኀይሎች በተወሰደ የኀይል እርምጃ የተገደሉ ናቸው። ቀሪዎቹ 12 ሰዎች በጥቃቶቹ በቀጥታ ባይገደሉም በኹከቱ ወቅት በነበሩ የተለያዩ ሌሎች አደጋዎች የሞቱ ናቸው።

እዚህ ጋር ጥያቄ ሊነሳበት የሚችል ጉዳይ ቢኖር የሟቾቹ ቁጥር በኹከቱ ወቅት በመንግሥት ኃላፊዎች ከተጠቀሰው ቢያንስ የ239 ሰዎች ሕይወት መጥፋት ለምን ዝቅ አለ የሚለው ነው። በርግጥ በወቅቱ በተለያዩ የዜና ዘገባዎች እና ሪፖርቶች የተለያዩ አሃዞች ቢጠቀሱም ባብዛኛው ኢሰመኮ ካቀረበው ሪፖርት ከፍ ያለ ቁጥር ሲቀርብ ነበር። ለምሳሌ በወቅቱ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኃላፊ የሆኑት አቶ ሙስጠፋ ታዲርበይፋ እንደገለጹት በኦሮሚያ ክልል ቢያንስ 215 ሲቪል ሰዎች፣ ዘጠኝ የጸጥታ አካላት እና አምስት የሚሊሻ አባላት እንደተገደሉ አሳውቀው ነበር። ከዚህ በተጨማሪም ቢያንስ 10 ሰዎች በአዲስ አበባ ከተማ መገደላቸውን እና ከነዚህም ውስጥ ስምንቱ ሲቪል ሰዎች እንደነበሩ የመንግሥት ኃላፊዎች በወቅቱ አሳውቀዋል።

የኢሰመኮ የምርመራ ሪፖርት በ40 የኦሮሚያ አካባቢዎች ላይ ያተኮረ በመሆኑ ኹከት እና ጥቃት ተፍጽሞባቸዋል የተባሉትን ሁሉንም የክልሉን ቦታዎች እና ተጎጂዎች አለመዳሰሱን ይጠቅሳል። በአዲስ አበባ የሞቱ/የተገደሉ ሰዎች ጉዳይም በሪፖርቱ አልተካተተም።ነገር ግን በሪፖርቱ የተጠቀሰው የምርመራ ዘዴ ለምን 40 ቦታዎች እንደተመረጡ፣ የቀሩት ምን ያህል ቦታዎች እንደሆኑ፣ እንደ አዲስ አበባ ያሉ በቅርብ መርጃ ሊገኝባቸው የሚችሉ ቦታዎች ላይ የተፈጸሙ ግድያዎች/ሞቶች ለምን በምርመራው እንዳልተካተቱ፣ ወዘተ ሪፖርቱ ግልጽ ምላሽ የለውም።

የኮሚሽኑ መርማሪዎች ከሐምሌ 14 እስከ ሐምሌ 30/2012 ድረስ ለኹለት ሳምንታት ያህል በአካል በቦታዎቹ ተገኝተው መረጃ በማሰባሰብ ነው ላለፉት አራት ወራት ሪፖቱን ያጠናቀሩት። ኮሚሽነር ዳንኤል ሪፖርቱ ይፋ ከተደረገ በኋላ ከአባይ ሚዲያ ጋር በነበራቸው ቆይታ ኮሚሽኑ ባለበት የሥራ መደራረብ የተነሳ ሪፖርቱን ማዘጋጀት ከስድስት ወራት በላይ እንደወሰደ ይሞግታሉ።ይህን እንደ ምክንያት ተቀብለን ሪፖርቱ ራሱ በወቅቱ በኦሮሚያ እና አዲስ አበባ የነበረውን የመብት ጥሰት በሙሉ ያልዳሰሰ መሆኑን ስናገናዝብ ሪፖርቱ ሁሉንም በክልሉ ተፈጽመዋል ተብሎ የተዘገበውን የሰዎች ግድያ እና ጉዳት እንዳልዳሰስ፣ ያቀረበውም ሪፖርት በወቅቱ የነበረውን ጥቃት እና የሰብኣዊ መብት ጥሰቶችን በሙሉ ያልመረመረ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል። ነገር ግን ኮሚሽኑ በምርመራ ሪፖርቱ ያልተካተቱ ድርጊቶች መኖራቸውን አጽንዖት ሳይሰጥ ማለፉ እንዲሁም የሪፖርቱ ይዘት ጠቅላላ የሟቾች ቁጥር 123 ብቻ በሚመስል መልኩ ማቅረቡ ሪፖርቱ ግልጽነት እንዳይኖረው ያደርገዋል።

ለ. የመብት ጥሰት ፈጻሚ ቡድኖችን ያደራጀው እና የመራው አካል ማን ነው?
ኹለተኛው የኢሰመኮ ሪፖርት ትኩረት የአርቲስት ሀጫሉን መገደል ተከትሎ ከሰኔ 22/2012 ጀመሮ በነበሩት ሦስት ተከታታይ ቀናት በኦሮሚያ ክልል በተፈጸሙት የሰብኣዊመብቶች ጥሰት የተሳተፉ አካላትን መለየት ነው። ከዚህ አንጻር ሪፖርቱ የሰብኣዊመብቶች ጥሰት ፈጻሚዎችንበኹለት ከፍሎ አስቀምጧል፤ እነዚህም “በቡድን የተደራጁ ወይም በቡድን ሲነቅሳቅሱ የነበሩ ሰዎች” እና የመንግሥት የጸጥታ አካላት ናቸው።“በቡድን የተደራጁ ወይም የሚንቀሳቀሱ” ሲል ሪፖርቱ የሚያመለክታቸው አካላት ጠቅለል ባለ አገላለጽ የተገለጹ፣ ባብዛኛውም የአርቲስት ሀጫሉን ሞት ተከትሎ ሀዘናቸውን ለመግለጽ ከወጡ ሰላማዊ ሰልፍኞች መካከል ተቀላቅለው የነበሩ በኹከት እና ጥቃት በቡድን የተሳተፉወጣቶችን የሚመለከት ሆኖ ነው የቀረበው።

በሪፖርቱ ድምዳሜ ላይ የተደረሰበትን በሰብኣዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል ስለመፈጸሙ ለማረጋገጥ በጥቃቱ የተሳተፉትን የእያንዳንዱን ቡድን ማንነት እና የቡድን አባላቱን ዝርዝር መለየት የግድ ላያስፈልግ ይችላል። ነገር ግን እንደ አንድ የተሟላ የምርመራ ሪፖርት እና የተጠቀሰውን ወንጀል ለመፈጸምከሚረዱ ዓለም ዐቀፍ መሥፈርቶች አኳያ ኮሚሽኑ በሪፖርቱ የተመለከቱት ቡድኖችን ያደራጃቸውን አካል እና ቡድኖቹ ሲመሩ የነበሩበትን ሁኔታ በጥልቀት መመርመር ነበረበት።

ነገር ግን ሪፖርቱ ይህንን ጉዳይ በአትኩሮት ለመመርመር የፈለገ አይመስልም። ከዛ ይልቅ አብዛኛውን ትኩረቱን ያደረገው የተደራጁት ቡድኖች የፈጸሙት ድርጊት በአጠቃላይ ሲታይ “ስልታዊ እና በተቀናጀ መንገድ” መፈጸመ አለመፈጸሙን መመርመር ላይ ነው። ሪፖርቱ ይህንን ያደረገበት ምክንያት ግልጽ ባይሆንም ግዙፉን ጥቃት ያስተባበሩ፣ የመሩ እና ቡድኖቹኑም ያደራጁትን አካላት በጥልቀት መመርመር የሚኖረውን ፖለቲካዊ አንድምታ በማገናዘብም ሊሆን ይችላል። ዞሮ ዞሮ ሪፖርቱ ጥቃቶቹን በዋናነት የመራውን አካል ለመመርመር ባይደፍርም በጥቃቱ ተሳታፊ የሆኑ ግለሰቦች ለድርጊታቸው የሚኖራቸውን የወንጀል ተጠያቂነት አያስቀረውም።

እንደ ሰብኣዊ መብቶች ተቋም እና በሪፖርቱከተረጋገጠው ግዙፍ እና ዓለም ዐቀፍ ወንጀል አንጻር፣ እንዲሁም ወደፊት ተመሳሳይ ድርጊት በመንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ባልሆኑ አካላት እንዳይደገም፣ እንዲህ ያሉ ከባድ ወንጀሎች የመሩ፣ ያስተባበሩ ወይምከጀርባ ያሉ አካላትን ለይቶ በምርመራ ሪፖርት ማመላከት ፋይዳው የጎላ ነው የሚሆነው።

ሐ. ሪፖርቱ ተገቢውን ትኩረት ያልሰጠው በጸጥታ አካላት የኀይል አጠቃቀም
በሦስተኛ ደረጃ የኢሰመኮ ሪፖርት በዋናነት ትኩረት ያደረገው በተለይም የተፈጸሙትን የሰብኣዊ መብት ጥሰት ዓይነቶችን እና ድርጊቶች የሚያስከትሉትን የወንጀል ዓይነት መለየት ነው። የመጀመሪያው በ35 ሲቪል ሰዎች ግድያ፣ እና ሌሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የአካል ማጉደል ጥቃት ድርጊት የተፈጸመውን የወንጀል ዓይነት መለየት ነው። በኮሚሽኑ ግምገማ መሠረትም አጠቃላይ ኹከት የተፈጸመበት ሁኔታ፣ የ35ቱ ሰዎች ግድያ አፈጻጸም፣ ጥቃቶቹ ያነጣጠሩበት የኅብረተሰብ ከፍል፣ የጥቃቶቹ መጠንና እና ስልታዊነት በድምሩ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ከባድ የግፍና ጭካኔ ወንጀሎች (atrocity crimes) መካከል አንዱ የሆነውን በሰብኣዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል (crime against humanity) የተፈጸመ መሆኑን ያመለከታል ሲል ከድምዳሜ ደርሷል።

ሌላኛው ኮሚሽኑ በምርመራ ሪፖርቱ የለየው የሰብኣዊ መብቶች ጥሰት፣ ነገር ግን ከደረሰው መጠነ ሰፊ ጉዳት አንጻር ተገቢው ትኩረት የተሰጠው የማይመስለው፣ በጸጥታ ኀይሎች የተገደሉትን 76 ሰዎች እና የ196 ሰዎች የአካል ጉዳት የተመለከተው ነው። በርግጥ ይህ መጠነ ሰፊ የሰዎች ሞት እና አካል ጉዳት በጸጥታ ኀይሎች የኀይል አጠቃቀም ላይ ጥያቄ የሚያስነሳ ስለመሆኑ በሪፖርቱ በዝርዝር ለማቅረብ እና አስፈላጊው ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ምክረ ሐሳብ ለማቅረብም ተሞክሯል። ነገር ግን የሪፖርቱን አጠቃላይ ይዘት፤ በተለይ በተደራጁ ቡድኖች እና በጸጥታ ኀይል አካላት የደረሰውን የሕይወት መጥፋት መጠን ከግንዛቤ በመውሰድ፤ በጸጥታ ኀይሎች የደረሰው መጠነ ሰፊ የመብት ጥሰት በራሱ ሰፊ እና ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ መከራከር ይቻላል።

ይህ ማለት በጸጥታ ኀይሎች የተፈጸመው የሰብኣዊ መብት ጥሰት በተደራጁ ቡድኖች ከተፈጸመው ድርጊት እና የጭካኔ አፈጻጸም ጋር የሚነጻጸር ነው ማለት አይደለም። ነገር ግን የጸጥታ አካላት ኹከት ለመቆጣጠር የሚወስዱት እርምጃ ተመጣጣኝ እና ሰብኣዊ መብቶችን ያከበረ መሆን አለበት ከሚለው መርህ አንጻር የተወሰደው የመከላከል እርምጃ ያደረሰው ጉዳት በራሱ መጠነ ሰፊ ሆኖ ከተገኘ ሰብኣዊ መብት ኮሚሽን ይህንን ሁኔታ በሪፖርቱ አጉልቶ ማውጣት፣ በአግባቡ መተቸት ነበረበት።ይህም ማለት ሪፖርቱ በሰብኣዊነት ላይ የተፈጸመውን ወንጀል በኦሮሚያ የተፈጸመው ጠቅላላ ድርጊት ማሳያ አድርጎ እንደቀረበው ሁሉ በጸጥታ አካላት የተፈጸመው የመብት ጥሰትም ሌላኛው ከፍተኛ የመብት ጥሰት ሁኔታ ማሳያ መሆኑ ሪፖርቱ አንኳር ነጥብ ማቅረብ ነበረበት።

በኢትዮጵያ ወንጀል ሕግ ያልተደነገገው በሰብኣዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል
ኢሰመኮ በተደራጁ ቡደኖች የተፈጸመውን የሰብኣዊ መብት ጥሰቶች፣ በተለይም በሰብኣዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀልን፣ በተመለከተ የፌዴራል መንግሥት እና የኦሮሚያ ከልላዊ መንግሥት ተገቢውን ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ በወንጀል ድርጊቱ ተጠርጣሪዎችን ለፍርድ እንዲያቀርቡ እንዲሁም ሌሎች የመከላከል እርምጃዎች እንዲወሰዱ ያሳስባል። የሪፖርቱ ተቀዳሚ መክረ ሐሳብ እንዲህ ይላል፤ የአርቲስት ሃጫሉ ግድያን ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በተለያዩ ቡድኖች በሰብኣዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ስለመፈጸሙ ኮሚሸኑ ያገኛቸውን አመላካች ማስረጃዎችን መሰረት በማድረግ፣ የወንጀል ምርመራ ተደርጎ በሰብአዊ መብቶች ጥሰት የተጠረጠሩ ሰዎች ተለይተው ለፍትሐዊ የዳኝነት ሂደት እንዲቀርቡና ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ (አጽንዖት የታከለበት) ይህንን ምክረ ሐሳብ በተመለከተም የፌደራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ እና የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የአጥፊዎችን ተጠያቂነት እንዲያረጋግጡ፣ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ጨፌ ኦሮሚያ በበኩላቸው ምክረ ሐሳቡ በአግባቡ መፈጸሙን ክትትል እንዲያደርጉ ሪፖርቱ አሳስቧል።

ይህም ብቻ ሳይሆን፣ በሰብኣዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል መከሰቱን እና በኢትዮጵያ እየታዩ ካሉ ሌሎች አዝማሚያዎች ጋር ተዳምሮ አጠቃላይ ሁኔታው ‘የግፍ እና ጭካኔ ወንጀሎች (atrocity crimes)፣ በተለይም የዘር ማጥፋት ወንጀል (Genocide)፣ ስጋት መኖሩን የሚያመላክቱ ሁኔታዎች ያሉ በመሆኑ መንግሥት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተሟላ የመከላከያ ስትራቴጂ በመንደፍ ሥራ ላይ እንዲውል እንዲያደርጉ ሪፖርቱ ጥሪ አቅርቧል።

የኮሚሽኑ ሪፖርት በግልጽ እንዳቀረበው በሰብኣዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል በዓለም ዐቀፍ ሕግ ደረጃ እውቅና ከተሰጣቸው ጥቂት ዓለም ዐቀፍ ወንጀሎች አንደኛው ነው። በተለይም ከኹለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ባለው ጊዜ ወንጀሉ በጦርነት መካከልም ይሁን በሌሎች ኹከቶች መካከል ተፈጽሞ ሲገኝ ተጠርጣሪዎች በዓለም ዐቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤቶች ወይም ልዩ ፍርድ ቤቶች ጭምር ተጠያቂ የሚሆኑበት ሥርዓት ተፈጥሯል።

ለአብነትም በቀድሞ ዩጎዝላቪያ ሪፐብሊክ የተፈጸሙ ዓለም ዐቀፍ ወንጀሎችን እንዲሁም የሩዋንዳው የዘር ማጥፋት ወንጀልን ለመዳኘት የተቋቋሙት ዓለም ዐቀፍ ልዩ ፍርድ ቤቶች በሰብኣዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀሎችን የመዳኘት ሥልጣን ተሰጥቷቸው ነበር። በተመሳሳይም፤ ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ፈራሚ ሀገር ባትሆንም፣ የዓለም ዐቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ማቋቋሚያ ስምምነት (Rome Statute) ከሚደነግጋቸው አራት ዓለም ዐቀፍየወንጀል ዓይነቶች መካከል በሰብኣዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል አንደኛው ነው።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያን የወንጀል ሕግ ማዕቀፎችን ስንመለከት በ1996 የወጣው የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ “ዓለም ዐቀፍ ሕጎችን በመጣስ የሚፈጸሙ የወንጀል ዓይነቶች” በሚል ካስቀመጣቸው ወንጀሎች መካከል በሰብኣዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል አልተካተተም። በወንጀል ሕጉ እውቅና የተሰጣቸው ወንጀሎች የዘር ማጥፋት ወንጀል፣ የጦር ወንጀል እና በሰብኣዊነትሥራ በተሰማሩ ድርጅቶች (humanitarian organizations) ላይ የሚፈጸም ወንጀል (በርግጥ ይሄ አንደኛው የጦር ወንጀል ዓይነት ነው) ነው።

በሌላ አነጋገር ከላይ ኮሚሽኑ በሰብኣዊነት ላይ የተፈጸመውን ወንጀል በተመለከተ ያቀረበውን ምክረ ሐሳብ በተግባር ከማዋል አንጻር ወንጀሉን በተመለከተ ምርመራ ለማካሄድ እና ክስ ለማቅረብ የሚያስችል የወንጀል ሕግ ማእቀፍ ኢትዮጵያ የላትም።

ይህ ምናልባትም የኢትዮጵያ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ካሉት ክፍተቶች መካከል ትልቁ ሊባል የሚችል ነው። ሕጉ በሚረቀቅበት ጊዜ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ በግልጽ ተደንግጎ የሚገኝ እና ከፍተኛ ትኩረት ከሚሰጣቸው ወንጀሎች አንዱ የሆነውን በሰብኣዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል በወንጀል ሕጉ ውስጥ ሳይካተት የቀረበት ምክያት ግልጽ አይደለም። በርግጥ በዓለም ዐቀፍ ሕግ እና በሌሎች የዳበረ የሕግ ሥርዓት ባላቸው ሀገራት ተሞክሮ መሠረት አንድ በዓለም ዐቀፍ ሕግ በማያከራክር ሁኔታ ዓለም ዐቀፍ ወንጀል ሆኖ የሚታወቅ ድርጊት ተፈጽሞ ሲገኝ ምንም እንኳን ሀገር ዐቀፍ የሕግ ማእቀፍ ባይበጅለትም ዓለም ዐቀፍ ሕግን መሠረት በማድረግ ተጠርጣሪዎቹ በሀገር ውስጥ የዳኝነት ሥርዓት ሊጠየቁ የሚችሉበት ሁኔታ አለ።

ይህ አካሄድ ግን በኢትዮጵያ የወንጀል ሥርዓት እምብዛም የተለመደ ባለመሆኑ ተጠርጣሪዎችን በዓለም ዐቀፉ ሕግ መሠረት በሀገሪቱ ፍርድ ቤቶች በሰብኣዊነት ላይ በሚፈጸም ወንጀል ተጠያቂ ማድርግ አዳጋች ነው። ከዚህ አንጻር እና በቅርቡ በኢትዮጵያ አሳሳቢ እየሆነ ከመጣው በሰብኣዊነት ላይ ከሚፈጸሙ የወንጀል ድርጊቶች አኳያ፥ ኮሚሽኑ እና ሌሎች መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት ትኩረት ማድርግ ካለባቸው ጉዳዮች አንዱ ኢትዮጵያ ተገቢው የወንጀል ሕግ ማእቀፍ እንዲኖራት ማድረግ መሆን ይኖርበታል ማለት ነው።

ማጠቃለያ
ኮሚሽኑ በቅርቡ በሚያወጣቸው የምርመራ ሪፖርቶች እና መግለጫዎች በሀገሪቱ በቅርብ ጊዜያት ውስጥ እየተከሰቱ የሚገኙ መጠነ ሰፊ የሰብኣዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከት በአብዛኛው ገለልተኛ መረጃዎችን እና የምርመራ ግኝቶችን ለማቅረብ የሚያደርገው ጥረት የሚበረታታ ነው። አሁን ላይ በኢትዮጵያ ካለው ነባራዊ የፖለቲካ ዓውድ አንጻር አንድ አንድ የሰብኣዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ ኮሚሽኑ የሚመለከተውን አካል በድፍረት ለመለየት፣ ለማጉላት እና ለከመኮነን ሲቆጠብ ቢታይም (ለምሳሌ በአሁኑ ሪፖርት በጸጥታ አካላት የደረሰውን መጠነ ሰፊ የሰዎችን ግድያ ማንሳት ይቻላል) ወደፊት በተሻለ ጥልቀት እና ገለልተኛነት ኀላፊነቱን ሊወጣ እንደሚችል ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴዎችን እያሳየ መሆኑን ግን ማየት ይቻላል።

በሌላ በኩል ኮሚሽኑ የሚያወጣቸው ሪፖርቶች እና መግልጫዎች ለሕብረተሰቡ፣ መንገሥታዊ እና መንግሥታዊ ላልሆኑ አካላት፣ ለተመራማሪዎች፣ ወዘተ በተለያየ መልኩ በአስረጂነት እና በግብዓትነት የሚያገለግሉ ስለሆነ የሪፖርቶቹን እና መግለጫዎች አቀራረብ ወጥ፣ ደረጃቸውን የጠበቁ እና ተደራሽ ማድረግ ይጠበቅበታል።
ማርሸት መሐመድ ሐምዛ ጄኔቭ፣ ሲውዘርላድ በሚገኘው Institute of International and Development Studies የዶክትሬት ትምህርታቸውን እና ጥናታቸውን በመከታተል ላይ ሲሆን በኢሜይል አድራሻቸው marishetm@yahoo.comማግኘት ይቻላል።

ቅጽ 2 ቁጥር 118 ጥር 8 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here