የመጀመሪያዋ!

0
379

በአገራችን ‹የመጀመሪያ› የሚለው ቃል ተወዳጅ መሆኑን ጸሐፍት በትችት ይናገራሉ። በጽሑፍ ሥራዎቹ ‹መጽሐፍ አያስከድንም› ብንል የማይበዛበት፤ ገጣሚና ደራሲ በእውቀቱ ስዩም በአንድ ወጉ ላይ ‹ለቤተሰቤ ኹለተኛ ልጅ በመሆን የመጀመሪያ ነኝ› በሚል ሐረግ ለ‹መጀመሪያ› ያለንን አመለካከት ታዝቦ አስታዝቦናል። ግን ቢሆንስ ምን ክፋት አለው? ጀማሪ መሆን ለብዙዎች መንገድ ማሳየትም ነውና፤ እንደዛ ከሆነልን እሰየው ነው’ንጂ!

ታሪክም እንዲሁ ‹መጀመሪያ› እና ‹ብቸኛ› የሚሉትን ቃላት በብዛት ይጠቀማል። በምድራችን ላይ ዛሬ አዲስ ሳይሆኑብን በየዕለቱ የምንጠቀማቸው ነገሮች ሁሉ ጀማሪ ነበራቸውና፤ እነዛ ሰዎች የመጀመሪያ መሆናቸው ተመዝግቧል። ለምሳሌ በአገራችን ክብርት ሳህለወርቅ ዘውዴ የመጀመሪያዋ ፕሬዝዳንት ናቸው። የመጀመሪያዋ ብቻ ሳይሆኑ በአሁኑ ሰዓት በአፍሪካ በሥልጣን ላይ ያሉ ብቸኛዋ ሴት ሆነውም ተመዝግበዋል።

በእርግጥ ባለንበት ጊዜ ሴቶች የመጀመሪያ ልንሆን የምንችልበትና ያልገባንበትን የሙያ ዘርፍ መለየት አዳጋች ነው። የአገራችን ሰዎች ይበልጥ ትኩረት ሰጥተው በሚመለከቷቸውና የኀላፊነት ጥግ አድርገው በሚቆጥሯቸው አገር መሪነት፣ አውሮፕላን አብራሪነት፣ ሕክምና፣ ተመራማሪነት፣ መምህርነትና መሰል ደረጃዎች ላይ አሁን ሴቶች አሉ፤ ስለዚህ ከዚህ በኋላ በሩ ክፍት ሆኗል ማለት ነው።

ጨረቃ ላይ አንድ ጊዜ ከተወጣ ወዲህ ሌላው ሲመላለስባት ቢውል ለሰው አዲስ እንደማይሆነው ሁሉ፤ አንድ ጊዜ እነዚህን ‹አይችሏቸውም› የተባሉ ደረጃዎች ከያዙ ወዲህ እየተተካኩ መመላለስ ነው፤ አለመልቀቅ። ሴት ፕሬዝዳንታችን የሥልጣን ዘመናቸው ካበቃ በሌላ ሴት ፕሬዝዳንት እንዲተኩ፤ የመጀመሪያዋ ተብሎ በዛው እንዲቀር ሳይሆን ለጠቅላላ እውቀት ካልሆነ በቀር ሰው መቁጠር እስኪተው ድረስ መደበኛ ማድረግ ያስፈልጋል።

ይህ በምናየው ሥልጣንና ሹመት ላይ ነው፤ በማይታየውና ሁላችን በያለንበት መስክም በዛው መሰረት መንቀሳቀስ አለብን። ሴቶች! በተለይም ልምዱ፣ እውቀቱ፣ ችሎታውና በራስ መተማመኑ በእጃቸሁ ያለ፤ በተቋማችሁ የመጀመሪያ ሁኑ። በታሪክ ወንዶች ብቻ ሲመሩት የነበረ ተቋም ውስጥ ካላችሁ፤ የመጀመሪያ በመሆን በሩን ክፈቱት። ዓለምን መምራት የሚቻለው መሪውን በመጨበጥ ብቻ አይደለም፤ ጎማውን፣ ፍሬንና ማርሹን፣ በርና መስኮቱን ጭምር በመሆን ነው።

ሴቶች በያለንት መስክ ብቁ ሆነን ስንገኝ፤ ማን ያውቃል በድንገት አንድ ጉባኤ ላይ በብዛት ተገናኝተን አገራችን ላይ የመወሰን ሥልጣን ሊኖረን ይችላል። ልንለውጥ የምንችላቸው ብዙ ጉዳዮችም አሉ። ከዛም አልፎ የመጀመሪያ በመሆን የሚጀመር ጉዞ ለብዙ ሴት ልጆችና ወጣቶች ሕልም ብርሃን እንደማብራት ነው። እህቴ! ባለሽበት የመጀመሪያ መሆን ከግብሽ ይካተት! አለመሆን ምርጫሽ ነው፤ መሆን ግን ለራስሽም ለእህትሸም የምትሰጪው ውድ ስጦታ ነው።
መቅደስ /ቹቹ/
mekdichu1@gmail.com

ቅጽ 2 ቁጥር 118 ጥር 8 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here