የሚማሩ መምህራን ቅዳሜ ለማስተማር እንደሚቸገሩ ተናገሩ

0
671

በአዲስ አበባ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች ላይ የሚያስተምሩ እና የሚማሩ መምህራን በኮቪድ 19 ምክንያት ቅዳሜን እንዲያስተምሩ በመደረጉ የቅዳሜ እና እሁድ (ኤክስቴሽን) የሚማሩ መምህራን ትምህርታቸውን ለመከታተል ሳንካ ስለሆነባቸው ያላቸውን ቅሬታ ለአዲስ አበባ መምሕራን ማህበር አስታወቁ።

በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ላይ የሚገኙ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች በተለያየ የትምህርት መስክ ላይ ተሰማርተው የሚያስተምሩ መምህራን ቅዳሜ ለማስተማር እንደተቸገሩም ለአዲስ ማለዳ ቅሬታቸውን ያቀረቡ ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ መምህር ተናግረዋል።

እንደ መመምህሩ ገለፃ ኮሮና ቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ ከመግባቱ በፊት በሳምንት አምስት ቀን ብቻ እናስተምር ስለነበር የኹለተኛ ዲግሪዬን መማር ጀምሬ ነበር ብለዋል።
አሁን ግን በኮሮና ምክንያት ቅዳሜንም ጨምሮ ማስተማር በመጀመሩ ትምህርቴን ያስተጓጉልብኛል በዚህም የሚመለከተው አካል ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ ያነጋገረቻቸው የአዲስ አበባ መምህራን ማሕበር ፕሬዚዳንት ድንቃለም ቶሎሳ እንደተናገሩት የመምህራኑ ጥያቄ አግባብነት ያለው እንደሆነ ተናግረዋል።

መምህራኑ በቅዳሜ እና እሁድ የሚሰጥ ትምህርት ላይ የሚማሩ እንደሆኑ እና የመጀመሪያ ዲግሪ ፣ የኹለተኛ ዲግሪ የሚማሩ መምህራን እንዳሉ የሦስተኛ አመት እንዲሁም የአራተኛ አመት ተማሪ የሆኑ መምህራን እንዳሉም ተናግረዋል።

በዚህም ሦስት አመት እና ከዛ በላይ የለፋ መምህር ትምህርቱን ሳይጨርስ ማቋረጥ የለበትም የመምህራኑ ጥያቄ አግባብነት ያለዉ ሲሆን እንደ ማህበር በርካታ ስራዎችን እየሰራን ነው ብለዋል።

እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለፃ መምህራኑ ያለባቸውን ችግሮች ለመፍታት ከሚመለከተው አካል ጋር ለመስራት እየሞከርን ነው አንዳንድ አስተማሪዎች ከትምህርት ቤቱ አስተዳደር ጋር በመወያየት ፈረቃ እንዲቀየሩ ያመቻቸንላቸው አሉ ብለዋል።

ተጠሪነታቸው ለአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ እንደሆነ የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ ከአስተማሪዎች የሚነሱትን ቅሬታ በመያዝ ለትምህርት ቢሮ ለማቅረብ በዝግጅት ላይ እንዳሉም ተናግረዋል።

ኮሮና ቫይረስ በመጋቢት 4/ 2012 ወደ አገራችን መግባቱ ይታወሳል። በዚህም ምክንያት የቫይረሱን ሥርጭት ለመቆጣጠር እንዲያስችል በማለት በመንግሥት በኩል የተለያዩ ተቋማት በአፋጣኝ እንዲዘጉ መደረጋቸውም የሚታወስ ሲሆን ከእነዚህም መካከል የትምህርት ተቋማት ተጠቃሾች ናቸው።

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መስከረም 12/2013 ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባው ላይ የሴቶች፣ ወጣቶችና ማኅበራዊ ጉደዮች ቋሚ ኮሚቴ እና የሕግ፣ ፍትህና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የጤና ሚኒስቴር አገራዊ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምላሽ ቀጣይ እርምጃዎችን በተመለከተ ባቀረበው ሪፖርትና ምክረ ሐሳብ ላይ ያቀረቡትን ሪፖርትና የውሳኔ ሐሳብ በዝርዝር ተመልክቶ ማጽደቁ ይታወሳል።

ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን መከላከልን መሰረት በማድረግ ክልከላ የተጣለባቸው ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እንዲፈቀዱ እና ትምህርት ቤቶችም እንዲከፈቱ ሲልም ውሳኔ ማስተላለፉ የሚታወስ ነው።

በዚህም በአዲስ አበባ ከተማ የ2013 የትምህርት ዘመን ከአምስተኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል የገጽ ለገጽ ትምህርት ኅዳር 28/2013 መጀመሩ ይታወቃል።
በዚህም መሰረት የቫይረሱን ሥርጭት ለመቆጣጠር ሲባል በአንድ ክፍል ውስጥ ከ25 ተማሪ በላይ ማስተማር እንደማይቻል መወሰኑ ይታወቃል።
በዚህም ትምህርቱን ተማሪዎች በፈረቃ እንዲማሩ ተደርጓል በሳምንት ሦስት ቀን ሰኞ ፣ ረብዕ ፣ አርብ የመጀመሪየው ፈረቃ ሲሆን ማክሰኞ ፣ ሐሙስ ፣ ቅዳሜ ደግሞ ኹለተኛው ፈረቃ ሁኖ ያገለግላል።

በዚህም ተማሪዎች በሳምንት ሦስት ቀናትን ብቻ ሲማሩ መምህራን ስድስቱንም ቀን ማለትም ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ያስተምራሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 118 ጥር 8 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here